የታጣቂዎች በሰላም እጅ መስጠት ጽንፈኝነት ተጨማሪ የጥፋት አቅም እንዳይኖረው ያደርጋል!

ጽንፈኛ አስተሳሰቦች በአንድ ሀገር ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚፈጥሩት አሉታዊ ተጽእኖ ሀገርን እንደ ሀገር እስከ ማፍረስ እንደሚደርስ አሁናዊ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች የሚያረጋግጡት ተጨባጭ እውነታ ነው። በዚህም ግንባር ቀደም ተጎጂ የሚሆኑት ሰላማዊ የማኅበረሰብ ክፍሎች ስለመሆናቸውም ብዙ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።

አስተሳሰቦቹ በአብዛኛው በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ከሚፈጠሩ የተዛቡና የተሳሳቱ ትርክቶች የሚመነጩ ናቸው። በተለይም ለአንድ ሀገር ቀጣይ እጣ ፈንታ ዋነኛ አቅም የሆነውን ወጣቱን ትውልድ ታሳቢ የሚያደርጉ መሆናቸው የጥፋት አድማሳቸውን ከፍተኛ ያደርገዋል።

ችግሩ ብዝሃነት /ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ/ ባለባቸው ሀገራት ውስጥ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት በአግባቡ መከላከል ካልተቻለ ሊያስከትል የሚችለው ጥፋት የከፋ ነው፤ ዛሬን ብቻ ሳይሆን የሀገራቱን ሕዝቦች ነገዎች ተስፋ ቢስ ሊያደርግ የሚችልም ነው። ሀገራትን በማያባራ የግጭት አዙሪት ውስጥ በመክተት ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉም ያስገድዳል።

በተለይ ባለንበት በአሁኑ ዘመን ቴክኖሎጂ ከመረጃ ስርጭት ጋር በተያያዘ እየፈጠረ ካለው ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮት ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ የተለያዩ ፍላጎቶች አንጻር ፤ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች ከአንድ ማኅበረሰብ ባለፈ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ስጋት የመሆናቸው እውነታ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተጨባጭ የታየ፤ የዓለምን ሰላምና መረጋጋት የፈተነ ነው።

ችግሩ እኛንም እንደ ሀገር ፤ እየፈተነን የሚገኝ ዋነኛ ችግራችን ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታ ካተረፍንባቸው ማኅበረሰባዊ የሞራል እሴቶቻችን ባፈነገጡ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች ምክንያት ሕዝባችን ያልተገባ ብዙ ዋጋ እንዲከፍል ሆኗል።

የፖለቲካ ልዩነቶችን ሆነ ግለሰባዊ እና ቡድናዊ ተጠቃሚነትን ለማስፈን፤ የተፈጠሩ ጽንፈኛ እሳቤዎች ለውጡ በመላው ሕዝባችን ውስጥ ፈጥሮት የነበረውን ተስፋ፤ ተስፋው ፈጥሮት የነበረውን መነቃቃት በማደብዘዝ፤ ብሔራዊ አንድነታችንን ጭምር ስጋት ውስጥ ከትተውት እንደነበር የሚታወስ ነው።

ጽንፈኛ ትርክቶቹ የፈጠሩት የተዛባ ምልከታ ፤ በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን ተስማምቶ እና ተሳስቦ የመኖር ማህበራዊ እሴቶች ተፈታትኗል፤ ከፍ ባለ የለውጥ መነቃቃት የተጀመሩ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሪፎርሞች በሚጠበቀው ፍጥነት እንዳይተጋዙም ጋሬጣ ሆኗል።

ከሁሉም በላይ የለውጡ ኃይል የትናንት ቁርሾዎችን በይቅርታና በመደመር አዲስ የፖለቲካ እሳቤ ለማከም ያደረገው ጥረት እና ለዚህ ተብለው የተወሰዱ ታሪካዊ የፖለቲካ ውሳኔዎች ለለውጡ ተጨማሪ አቅም እንዳይሆኑ ትልቅ ፈተና ሆኗል። ከፍ ያሉ ሀገራዊ መንገጫገጮችንም ፈጥሯል።

በተለይም ጠብመንጃ አንስተው የፖለቲካ ስልጣን በኃይል ለመያዝ የተነሱ ኃይሎች፤ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በመናበብ ለጥፋት ተልዕኳቸው ስኬት፤ ጽንፈኛ አስተሳሰቦችን ዋንኛ የፖለቲካ መሣሪያ አድርገው ተንቀሳቅሰዋል፤ የአስተሳሰባቸው ሰለባ የሆኑ ዜጎችም ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ አድርገዋል።

ታሪክን ከማዛባት ፣ አሁናዊ እውነታዎችን ከማፋለስ እና ነገዎችን ጽልመት በማልበስ ላይ የተመሰረቱት ጽንፈኛ የፖለቲካ እሳቤዎች ብዙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን አሳጥተውናል፤ ላልተገባ ዓላማ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ፤ በገዛ ሕዝባቸው /ወገናቸው የነገ ተስፋ ላይ ጠላት ሆነው እንዲነሱ አድርጓቸዋል።

በተለይም የተለያዩ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች ሰለባ በመሆን በኦሮሚያ ክልል በሸኔ ፣ በአማራ ክልል በፋኖ ስም ጠብመንጃ ያነሱ ዜጎች ፤ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ የሀገሪቱን ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ተፈታትነዋል። የገዛ ወገናቸው /ወንድማቸው ጠላት ሆነው ተሰልፈዋል።

እነዚህ ዜጎች አሁን ላይ ጽንፈኛ ኃይሎች እና አስተሳሰቦች የቱን ያህል እነሱን ጨምሮ የገዛ ወገናቸውን ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን ተረድተው፤ ከነበሩበት የጥፋት መንገድ በመውጣት ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመመለስ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እየተጠቀሙ ነው።

ለዚህም በስፋት እጃቸውን ለመከላከያ ሠራዊት ከመስጠት ባለፈ በቀደመው ተግባራቸው በመጸጸት፤ ሕዝባቸውን በቀጣይ ለመካስ እየደረሱበት ያለው ውሳኔ ተጨባጭ ማሳያ ነው።

ውሳኔያቸው ሀገራዊ ሰላም እና መረጋጋት ለመፍጠር፤ በተለይም ጽንፈኞች እና ጽንፈኛ አስተሳሰቦች በሀገሪቱ እና በትውልዱ ላይ ተጨማሪ የጥፋት አቅም እንዳይኖራቸውና ትውልዱ በመስዋዕትነት ጀምሮት ዛሬ ላይ ብዙ ፈተናዎችን አልፎ በጸና መሠረት ላይ የቆመውን ለውጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር ትልቅ ጉልበት እንደሚሆንም ይታመናል!

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You