34ኛውን የአፍሪካ ዋንጫን አዘጋጇ ኮትዲቯ ድራማዊ በሆነ ክስተት ራሷ አስቀርታለች። ብሔራዊ ቡድኑ ዋንጫ ከማንሳቱም በላይ ከካንሰር ሕመም አገግሞ ሀገሩን ለቻምፒዮንነት ያበቃው ሴባስቲያን ሀለር ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር። ለጀርመኑ ክለብ ቦሩሲያ ዶርትመንድ የሚጫወተው ሀለር፣ ለስድስት ወራት ሲሰቃይበት ከነበረው የወንድ የዘር ፍሬ ካንሰር ህመም ታግሎ በማሸነፍ ነበር ሀገሩን ለዚህ ክብር ማብቃት የቻለው።
እንደ ሀለር ከባዱን ፣ ተስፋ አስቆራጩንና አስፈሪውን የካንሰር ህመም በታላቅ ጽናት ታግለው በማሸነፍ ስኬታማ መሆን የቻሉ ጥቂቶች ናቸው። የሴቶች እግር ኳስ ዓለም ዋንጫ ኮከቧ ሊንዳ ካይሴዶ ከጥቂቶቹ አንዷ ናት። የኮሎምቢያ የሴቶች እግር ኳስ ምልክት የሆነችው ሊንዳ ልክ እንደ ሀለር ካንሰርን ታግላ ያሸነፈች የጽናት ምሳሌ ናት።
ሊንዳ ካይሴዶ የተወለደችው በደቡብ አሜሪካዊቷ ኮሎምቢያ ካንደሊሪያ ነው። ቤተሰቦቿም ይህ ነው የሚባል ገቢ አልነበራቸውም። ልጅነቷንም ያሳለፈችው በድህነት ነው። የእግር ኳስ ኮከቧ አሁንም የመጣችበትን አልረሳችም። በቅርቡም ወደ ትውልድ መንደሯ አቅንታ ለበርካቶች ምግብ እና የሚያስፈልጋቸውን ቁሶች ይዛ ሄዳለች። ይህንን በጎ ነገር ስታከናውንም ሚዲያ እንዲኖር አልፈቀደችም።
ወጣቷ የእግር ኳስ ኮከብ ሊንዳ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ሕይወትን የተቀላቀለችው ገና በ14 ዓመቷ ነበር። እአአ በ2019 የኮሎምቢያው ክለብ አሜሪካ ደ ካሊን ተቀላቀለች። በዚሁ ዓመት ኅዳር ወር ላይ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ጥሪ ደረሳት። ሆኖም ይህ ትልቅ እድል ሆዷ ላይ በሚሰማት ህመም ተገታ። በ2020 የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለምን እየረበሻት በነበረበት ወቅት፣ እሷም ህመሟ እየጠና ሄደ። ሊንዳ የህክምና ምርመራ ስታደርግ የእንቁላል ማከማቻ ካንሰር (Ovarian cancer) እንዳለባት ተነገራት።
ከምርመራው ሁለት ሳምንታት በኋላ ዕጢ ለማስወገድ ቀዶ ህክምና ያደረገችው ሊንዳ፤ አንደኛው የእንቁላል ማከማቻ (ኦቫሪ) እንዲወገድ ተደረገ። የሞት ትኬት ተቆርጦላት የነበረችው ሊንዳ፤ ከካንሰር ህመሟ ማገገም ቻለች። ለዚህም ቤተሰቧ እና የኮሎምቢያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ኔልሰን አባዲ ያደረጉላትን ድጋፍ እንደረዳት ትናገራለች።
“አስቸጋሪ ወቅት ነበር። ፈጣሪ ይመስገን፣ በብዙ ትግል ፈተናውን ተቋቁሜ ማለፍ ችያለሁ” የምትለው ሊንዳ በዚያ የፈተና ጊዜ ውስጥ ቤተሰቦቿ ሁሌም ከጎኗ ነበሩ። የአሰልጣኟ አብሮነትም አልተለያትም ነበር። “ አሰልጣኜ በርካታ ጊዜ ይደውልልኝ ነበር። አንድ ቀን ቀዶ ህክምና እየሄድኩ በጣም ከፋኝ። ከዚህ በኋላ በደንብ እግር ኳስ መጫወት እንደማልችል ተሰማኝ። እሱም ዘና በይ፤ አይዞሽ ትመለሻለሽ ሲል አበረታኝ። የተስፋ ስንቅ ሆነኝ። በዚህ መልኩ ከነበርኩበት እጅግ በጣም ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ በአሸናፊነት ወጣሁ። በታላቁ የዓለም ዋንጫ መድረክም ለመጫወት በቃሁ” ስትል በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ በማለፍ ለስኬት እንደበቃች ታስታውሳለች።
ሊንዳ ከቀዶ ህክምናዋ በኋላ ለስድስት ወራት የኬሞቴራፒ (የካንሰር የጨረር ህክምና) አድርጋለች። ህክምናዋን ከጨረሰች ከቀናት በኋላም ከካንሰር ነፃ መሆኗ ተነገራት። ከዚያም ወደምትወደው የእግር ኳስ ሕይወት ለመመለስ እንደቻለች ገልፃለች። በኋላም ዲፖርቲቮ ካሊ ከተሰኘው የእግር ኳስ ክለብ እና በብሔራዊ ቡድኑ መጫወትን ቀጠለች። ሊንዳ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ተሳትፋለች። በ2022 በሚያስደንቅ ሁኔታ በደቡብ አሜሪካ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ሻምፒዮና፣ በኮስታሪካ ከ20 ዓመታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ፣ በሕንድ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ እና ኮፓ አሜሪካ ፌሚኒና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ተጫውታለች ።
በነዚህ ውድድሮች ዓለም ስለ ሊንዳ ድንቅ ችሎታ ለመረዳት ችሏል። በወቅቱ የኮፓ አሜሪካ አዘጋጅ የነበረችው ኮሎምቢያን ለፍጻሜ ስትደርስ የ17 ዓመቷ ሊንዳ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሆና ተመርጣለች። መንፈሰ ጠንካራዋ ሊንዳ በ2023 የሴቶች የዓለም ዋንጫ ሀገሯን ኮሎምቢያን ወክላ በታላቁ መድረክ አንፀባርቃለች። የ19 ዓመቷ ሊንዳ በመድረኩ ግብ ያስቆጠረች ሲሆን፤ በዚህም በዓለም ዋንጫ ውድድር ታሪክ በትንሽ ዕድሜዋ ጎል ያስቆጠረች ሁለተኛዋ ደቡብ አሜሪካዊት ተጫዋች ሆናለች።
ሊንዳ በአሁኑ ወቅት በዓለም ምርጥ ከተባሉት ክለቦች አንዱ ለሆነው ሪያል ማድሪድ እየተጫወተች ትገኛለች። በኮሎምቢያው የዓለም ዋንጫ ቡድን ውስጥ ለስፔን ክለቦች ከሚጫወቱ ሰባት እግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል ተጠቃሽ ሆናለች። በማድሪድ ጥሩ ጊዜን እያሳለፈች ያለችው ሊንዳ፤ “አሁንም በጣም ወጣት ነኝ። አሁንም ብዙ መማር አለብኝ። በዚህ ቡድን ውስጥ በየቀኑ ልምድ አገኛለሁ። ይህ የመጀመሪያዬ የዓለም ዋንጫ ነው። በዚህም መደሰት እፈልጋለሁ። ብዙ ጊዜ አለኝ” ስትል በታዳጊነቷ ትልቅ ፈተና ተጋፍጣ ያለፈችው ኮከብ በቀጣይ ብዙ ሥራ እንደሚጠብቃት ተናግራለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6 ቀን 2016 ዓ.ም