የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን በአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ከተማ ማደስና ቅርስ እንክብካቤ ዙሪያ እየተሠሩ ባሉ ሥራዎች ላይ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ በመግለጫው የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ቀደም ሲል በአዲስ አበባ የቅርስ መስፈርት ያላሟሉ ሁሉ ቅርስ ተብለው ተመዝግበው እንደነበር ገልጸው ነበር፡፡
ዓለም አቀፍ የቅርስ ምዝገባን መነሻ በማድረግ በአዲስ መልክ በተዘጋጀው መመሪያ መሠረት አንድ ሕንፃ የተገነባበት ዘመን፣ ውጫዊ እና ውስጣዊ ዲዛይኑ፣ ኪነ-ሕንፃው፣ ታሪካዊ ዳራው፣ እና ሌሎች መስፈርቶችን አሟልቶ ሲገኝ በቅርስነት እንደሚመዘገብና ጥበቃና እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው አብራርተዋል፡፡ የዝግጅት ክፍላችንም ይህንን ጉዳይ በዛሬው አምዳችን ላይ ለመዳሰስ ወዷል።
የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ዳይሬክተር እንደሚሉት፤ የመሥሪያ ቤቱ አንደኛው ተግባር በሀገሪቱ የሚገኙ ቋሚ፣ ተንቀሳቃሽ ሆነ የማይዳሰሱ ቅርሶችን የመመዘገብ ሥራ ነው። እነዚህን ኃላፊነቶች የሚያከናውነው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 209/1992 መሠረት በመቋቋሙና በዚህ አዋጅ መሠረት ቅርስን የመመዝገብ ጥበቃና እንክብካቤ የማድረግ፣ በቅርሶች ላይ ምርምር እንዲሁም የማልማት ተግባርና ተልዕኮ ስለተሰጠው ነው። ሌላው አዋጅ ቁጥር 839/2006 ደግሞ ቅርሶችን በብሔራዊና በክልል ደረጃ የመመደብ ኃላፊነቶች ተሰጥተውታል።
‹‹ቅርሶችን የምንመዘግበው በአዋጁ መሠረት በተሰጠን ተግባርና ኃላፊነት በመመሪያ ቁጥር 9/2006 መሠረት ነው›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ በመመሪያው በወጣው መስፈርት አማካኝነት እስከ ዛሬ ድረስ ቅርሶችን ሲመዘግብ መቆየቱን ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪ ‹‹ቅርስ ምንድነው?›› የሚለውን ጉዳይ ለማስገንዘብ በመመሪያው መሠረት ለክልሎች ሥልጠና እንደሚሰጥ ያስረዳሉ። ይህንን ተከተሎም ክልሎች በየራሳቸው ምዝገባ እንደሚያደርጉ ይናገራሉ።
ረዳት ፕሮፌሰሩ ቀደም ሲል ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው የመመሪያ ቁጥር 9/2006 በ2015 ዓ.ም እንዲሻሻል መደረጉን ይገልፃሉ። ለመሻሻሉ ምክንያት የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱን በድጋሚ በማዋቀር ሂደት ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ለማውጣት መሆኑን ይገልፃሉ። ማንኛውም ቅርስ እሴት ሊኖረው እንደሚገባ በመግለጽም በምዝገባ ሂደት ላይ ያንን የእሴት መስፈርት እንዲጠበቅ፣ አስፈላጊው ምርምርና እንክብካቤ ለማድረግ መሆኑን ያስረዳሉ።
‹‹አዲስ አበባ ላይ ብዙ ቅርሶች አሉ›› የሚሉት የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ዳይሬክተር፤ ሀውልቶች፣ ታሪካዊ አደባባዮች፣ ከእምነት ተቋማት ጋር የሚያያዙ ቅርሶች፣ በየተቋማቱ አገልግሎት የሚሰጡ ቅርሶች መኖራቸውን ይናገራሉ። በቅርቡ ግን በስፋት በማህበረሰቡ ዘንድ አወዛጋቢ ጉዳዮች የተነሱበት የሥነ ሕንፃ ቅርስ የሚባለው መሆኑን ይናገራሉ።
የተሻሻለው መመሪያ የከተማ ሥነ ሕንፃን በጥቅሉ እንደሚያስቀምጥ የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰሩ ይሁን እንጂ በዝርዝር በመከፋፈል እንደማያስቀምጥ ያስረዳሉ። በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች የዓለም ክፍሎች አጨቃጫቂ የሆነው ጉዳይ ‹‹ከተሞች የልማት ማዕከል ስለሆኑና በየጊዜው እየለሙ ስለሚሄዱ ከተማ ላይ ያለ የሥነ ሕንፃ መስፈርት ማውጣት ነው›› የሚለው ዋነኛው ጉዳይ መሆኑን ያነሳሉ። በመሆኑም ቀደም ሲል በወጣው መመሪያ ላይ ‹‹ቅርስ ማለት የሰው ልጅ በፈጠራ፣ በሳይንስ፣ በባህል ያካበተው፣ የሠራውና ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፍ ያለበት ነው›› የሚል ቢሆንም በጥቅሉ ከሥነ ሕንፃ ቅርስ ጋር ተያይዞ በዝርዝር ጉዳዩን የማይገልፅና የሚያወዛግብ መሆኑን ይናገራሉ።
በዚህ ምክንያት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ይህንን ጉዳይ መመልከት መጀመሩን ይገልፃሉ። በዚህም ‹‹የከተማ ሥነ ሕንፃ ቅርስ ማለት ምንድን ነው›› የሚለውን ዝርዝር መስፈርት በማውጣት መመራት እንደሚያስፈልግ ድምዳሜ ላይ መደረሱን ይናገራሉ። ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያትም ከልማት ሥራዎች ጋር ተያይዞ ተደጋጋሚ አጨቃጫቂ ጉዳዮች በመነሳታቸው መሆኑን ያስረዳሉ። አንዳንዶቹ ጉዳዮች ፍርድ ቤት ድረስ የደረሱ በመሆናቸውና ምክንያት መሰል ችግሮች ወደፊትም እንዳይከሰቱ እልባት መስጠት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነ ይገልፃሉ። ከዚህ በኋላም ቅርሶች የከተማ ሥነ ሕንፃ ቅርሶች በጥቅል ሳይሆን በተመዘነ መስፈርት እንዲመዘገቡ የሚያደርግ አሠራር መዘርጋቱን ይናገራሉ።
የከተማ ሥነ ሕንፃ ቅርስ አመዘጋገብ ዝርዝር መስፈርት ስናዘጋጅ የሶስት ሀገራትን ተሞክሮ ወስደናል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ የሲዊዘርላንድ፣ ጃፓንና የካናዳን የአመዘጋገብ ሂደትና መስፈርቶችን እንደ መነሻ እንደተጠቀሙ ይናገራሉ። ዓለም አቀፍ የቅርስ አመዘጋገብ መስፈርቶችን በቀጥታ፣ ከሌሎች ሀገራት የተወሰዱትን ደግሞ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሃቅ ጋር ለማጣጣምና ለመውሰድ እንደተሞከረ ይናገራሉ።
ከዚህ መነሻ የከተማ ሥነ ሕንፃ የሚባሉትን ለመለየት ከ100 የሚመዘን መስፈርት መኖሩን የሚገልፁት ዳይሬክተሩ፤ ይህም በአምስት እንደሚከፈል ይናገራሉ። የመጀመሪያው ሥነ ሕንፃው ሲሆን፤ አንድን ከተማ ከተማ የሚያሰኘው፣ ውበት የሚሰጠውና ታሪክን መናገር የሚችለው እራሱ ሕንፃው (በሥነ ሕንፃ ውበት፣ ዘይቤው፣ አገነባቡ፣ እድሜው፣ አርክቴክቱ፣ ዲዛይኑ፣ ውጫዊ ገፅታው፣ ውስጣዊ ገፅታው) የሚናገረው ነገር መሆኑን ያስረዳሉ። በመሆኑም የመጀመሪያው መስፈርት ሥነ ሕንፃው ላይ እንደሚያተኩር እና በአጠቃላይም 30 ነጥቦችን እንደሚይዝ ያስረዳሉ።
ሁለተኛው ክፍል የሕንፃው ታሪክ መሆኑን የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ታሪክ ሲባል ሶስት ጉዳዮችን የያዘ መሆኑን ይገልፃሉ። የመጀመሪያው ከግለሰብ ጋር የሚያያዝ ታሪክ (በሀገሪቱ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ተፅእኖ ፈጣሪ፣ ጉልህ ድርሻ ያበረከተ) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሁነት መሆኑን ነው ያስረዱት። ‹‹በሥነ ሕንፃው ውስጥ ቀደም ባሉ ጊዜያት ምን ተካሂዶበታል›› የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ መሆኑን ያስረዳሉ። በሶስተኛነት በታሪክ ንዑስ መስፈርት ውስጥ የሚቀመጠው ጉዳይ ዳራው መሆኑን ያስረዳሉ። ይህ መስፈርትም ሥነ ሕንፃው በቀጥታ ከየትኛው የታሪክ ክፍል ጋር እንደሚገናኝ የሚያስረዳ መሆኑ መታወቅ እንዳለበት ይገልፃሉ።
ይህ የሥነ ሕንፃ ታሪኩን የሚያብራራው ክፍል በጥቅሉ 30 ነጥቦችን የያዘ ሲሆን፤ አንድ መቶ ነጥብ ከሚይዙት አምስቱ መስፈርቶች ውስጥ ሶስተኛው ጉዳይ ሥነ ሕንፃው ያለበት ከባቢያዊ ሁኔታ እንደሆነ የሚያስረዱት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ቀደም ሲል የነበሩት ታሪኩ፣ ሥነ ሕንፃው እሴቱን ጠብቆ እንደቀጠለ የሚረጋገጥበት መስፈርት መሆኑን ይናገራሉ። ሌላው ሥነ ሕንፃው ለመልከዓ ከተማው የሚያሳየው ነገር መኖሩ፣ የገዘፈና እንደ ምልክት (landmark) የሚጠቀስ መሆኑና ይህም በአጠቃላይ አስር ነጥቦችን የያዘ መሆኑን ይገልጻሉ።
በተጨማሪም ሕንፃው የሚሰጠው አገልግሎት፣ ለማህበረሰቡ የሚሰጠው ግልጋሎቶች፣ ለሌሎች ግልጋሎቶች መዋል መቻሉ እንዲሁም በጥገና ወቅት የሚኖረው ወጪና ሌሎች ከዚህ ጋር የሚዛመዱ ጉዳዮች መስፈርቶች መሆናቸውን ይናገራሉ። ይህም በጥቅል ተደምሮ 20 ነጥቦችን እንደሚይዝ ይገልፃሉ።
ረዳት ፕሮፌሰሩ በሥነ ሕንፃ ቅርስ ምዝገባ ሂደት በመጨረሻ መስፈርትነት የሚቀመጠው በቅርስ ቋንቋ ኢንተግሪቲ እየተባለ የሚቀመጠው መሆኑን ይናገራሉ፤ ይህም ማለት ሥነ ሕንፃው አሁን ያለበት ሁኔታና እሴትነቱ ምን ላይ እንደሆነ፣ ቀደም ባሉት ጥገናዎች የነበረውን እሴት ጠብቆ ስለመቆየቱ የሚረጋገጥበት እና አሁንም ድረስ ያለበት ሁኔታን የሚታይበት መስፈርት መሆኑን ይናገራሉ። በዚህ መስፈርትም አስር ነጥቦች እንደሚሰጡና በአጠቃላይ ከመቶ ድምር የሕንፃው በቅርስ የመመዝገብና ያለመመዝገብ ውሳኔ የሚረጋገጥበት እንደሆነ ይናገራሉ።
በተሻሻለው መመሪያ ቁጥር 9/2015 መሠረት ‹‹አንድ ሕንፃ የከተማ ሥነ ሕንፃ ቅርስ ነው›› የሚባለው ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ማግኘት ሲችል እንደሆነ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ይናገራሉ። ይህም ለሁለት እንደሚከፈልና ደረጃ (ሀ) እና ደረጃ (ለ) ተብለው እንደሚቀመጡ ይናገራሉ። ደረጃ (ሀ) ላይ የሚቀመጡት ሥነ ሕንፃዎች ከ65-100 ውጤት የሚያመጡት ሲሆኑ ምንም ቅያሬ የማይደረግባቸው፣ የውጭ ገፅታቸው እንዳለ የሚጠበቁ መሆኑን ያስረዳሉ። በደረጃ (ለ) ውስጥ የሚመደቡት ደግሞ ከ50 እስከ 64 ውጤት የሚያገኙት እንደሆነ ይናገራሉ። እነዚህም እንደሚጠበቁ ነገር ግን እንደየሁኔታቸው ማሻሻያ ሊደረግባቸው እንደሚችል ያስረዳሉ። በተለይ በእርጅናና በልዩ ልዩ ምክንያት ማሻሻል ሲፈለግ በፈጠራ ውጤቶች ጥገና እንደሚደረግባቸው ይናገራሉ።
‹‹ከ49 እና ከዚያ በታች የምዘና ውጤት ያመጣ ሥነ ሕንፃ እንደ ቅርስ አይቆጠርም›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፤ በመሠረታዊነት አብዛኛዎቹ የዓለማችን ሀገራት ይህንን አካሄድ እንደሚከተሉ ይናገራሉ። ኢትዮጵያም በሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ መስፈርቶችን በማስቀመጥ ልየታና ምዝገባ እንደሚደረግ ያስረዳሉ።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተጨማሪነት አጨቃጫቂ የሆኑ ሥነ ሕንፃዎች ላይ ውሳኔ የሚሰጥ የባለሙያዎች ቡድን እንዲቋቋም ማድረጉን ይናገራሉ። ሥነ ሕንፃዎቹ በቅርስነት እንዲመዘገቡ አሊያም እንዳይመዘገቡ ከላይ የተዘረዘሩትን መስፈርቶች ተጠቅመው የሚመዝኑ ሶስት ባለሙያዎች መኖራቸውንም ይናገራሉ። ባለሙያዎቹ ምዘናውን ሰርተው ሲያመጡ መረጃው ተቀባይነት ካገኘ ወዲያው ውሳኔ እንደሚሰጥበትም ይገልፃሉ። አወዛጋቢ ነገር የሚያስነሳ ከሆነ ደግሞ በቅርስ ምዝገባ ጉዳይ በሚደረጉ ስብሰባዎችና በማኔጅመንት ምክክር ውሳኔ እንደሚሰጥበት ይገልፃሉ።
ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ የሥነ ሕንፃ ቅርስ ምዝገባ ሂደትን ለማፋጠን ከወረቀት ሥራ በመውጣት በቴክኖሎጂ ለመታገዝ እየተሠራ መሆኑንም ይናገራሉ። ይህም ቅርሶች ሲመዘገቡ በዲጂታላይዜሽን መስፈርቶቹን ሕንፃዎቹንና አጠቃላይ መረጃዎችን በመመዝገብ ለማስቀመጥ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
የኮሪደር ልማቱን አስመልክቶ በሚነሱ ሕንፃዎች አማካኝነት የአራዳ ፒያሳ እና የፍልውሃ አካባቢን መውሰድ እንደሚቻል የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ 147 ቤቶች በቅርስነት ተመዝግበው እንደነበር ያነሳሉ። በመሆኑም ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ለእነዚህ ቅርስ ተብለው ለተለያዩ ሥነ ሕንፃዎች ቅድሚያ ሰጥቶ መገምገሙን ይገልፃሉ። ያም ሆኖ ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ኪነጥበብ ቢሮ ከፍተኛ ባለሙያዎችና አመራሮች ጋር በመሆን የመስክ ጉብኝት መደረጉን ይገልፃሉ። በዚህም ዋና ዋና የሚባሉትን ቅርሶች የመጠበቅና የማልማት ሥራ እንዲሠራ መወሰኑን ይናገራሉ። ቀሪዎቹ በመመሪያው መሠረት መስፈርቱን የማያሟሉት፣ ቀድሞ የነበራቸውን እሴት የቀየሩት፣ ወደ ንግድ የተቀየሩትን፣ ከስም ጋር ብቻ የተያያዙና ከሥነ ሕንፃ ውበትና ጥራት ጋር ያሉት ላይ ደግሞ ውሳኔ እንደተሰጠባቸው አስረድተዋል።
በመጨረሻም የከተማ ሥነ ሕንፃን በሚመለከት ከባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ተግባርና ኃላፊነት በመነሳት ቅርሶችን ለመመዝገብ፣ ውሳኔ የሚሹትን እልባት ለመስጠት የሀገር ውስጥንና ዓለም አቀፍ መስፈርቶች ተመስርቶ የመጠበቅ የማልማትና የመንከባከብ ሥራዎችን እየሠሩ እንደሚገኙ ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ተናግረዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6 ቀን 2016 ዓ.ም