ዜጎች ለብሔራዊ ምክክሩ መሳካት በህብረት ሊቆሙ ይገባል

ኢትዮጵያ ችግሮችን በራስ የመፍታት የቆየ እሴት ያላቸው ሕዝቦች የሚኖሩባት ሀገር ነች። ይህ ሀገር በቀል ባህል ለዘመናት ከማህበረሰቡ ጋር የኖረ ነው። ሀገሪቱን ይሄ ብቻ አይደለም ልዩ የሚያደርጋቸው። በአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት የሚገኙ ሕዝቦቿ እንደባህላቸው ልዩነት የችግር አፈታታቸውም በዚያው ልክ የሚለያይ ነው፡፡ ሁሉም ግን በአንድ ነገር ይመሳሰላሉ። እርሱም ሰላም የሁሉም መሠረት፤ የአንድነታቸው ምሰሶ መሆኑን ነው።

ሰላም ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ ነው። በሁሉም ዘርፍ አስፈላጊ የሆነውን ማህበራዊ እሴት እውን ለማድረግ ደግሞ የእያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል ኃላፊነት ከፍ ያለ ሊሆን ይገባል። እያንዳንዱ ዜጋም ለሰላም መስፈን የነቃ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል።

ሰላም የማህበረሰቡን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚጠቅመውን ያክል ሁሉ በሰላም በማደፍረስ የራሳቸውን ጥቅም የሚያስጠብቁ በርካቶች ናቸው፡፡ ከብጥብጥና ሁከት የሚያተርፉ የሴራ ፖለቲካና አሻጥር ቀማሪዎች በርካቶች ናቸው። ለአብነት ብንመለከት የሊቢያን ሰላም በማደፍረስ የጦር መሳሪያ በመሸጥ ኢኮኖሚያቸውን የሚደጉሙ ሀገራት መኖራቸው ይነገራል፡፡ ይህ ዓይነቱ የሰላም መደፍረስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዩክሬን እና ሩሲያ፣ በኢራቅ፣ በፍልስጤም እንዲሁም በእስራኤል እና ጋዛ በሚስተዋሉ ሀገራቱ ወደለየለት የጦርነት ቀጠና ተለውጠዋል፡፡ ዜጎችም በማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዜያት በነበሩ በእርስ በርስ ጦርነቶች በርካታ ዜጎቿን ለማጣት ተገዳለች። የኢኮኖሚ ውድቀትና የንብረት ውድመትም አጋጥሟታል፡፡ ከነዚህ ታሪኮቻችን መረዳት የምንችለው ግጭትን በቀላሉ ማስቀረት እየቻልን በቸልተኝነት ካለፍን ሰላማችን ደፍርሶ ነጋችንን ከማበላሸት ውጭ አንዳች ነገር መፈየድ እንደማንችል ነው። በተለይ ዛሬን የቆየውን ማህበራዊ እሴቶቻችንን ተጠቅመን በራሳችን አቅምና ብልሃት የእርስ በእርስ ግጭቶቻችንን ማቆም ካልቻልን ነገ ለቁጭት መዳረጋችን አይቀርም።

አሁን አሁን በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታየው የወንድማማቾች ግጭት የሚያሳየን የሰላም መደፍረስ መኖሩን ነው። እነዚህን አለመግባባቶች ለመፍታት እና በኢትዮጵያ ውስጥ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ በለውጡ ማግስት በመንግስት ገለልተኝ የሆነ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል። የኮሚሽኑ መቋቋም እንደ ሀገር ያሉብንን ችግሮች በምክክር መፍታት እንድንችል እንደ ትልቅ መልካም አጋጣሚ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ይህ ርምጃ አዲስ ሀገራዊ የፖለቲካ ባህል መፍጠር እንደሚያስችልም ይታመናል፡፡

በሀገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ አጀንዳዎች ላይ ሀገራዊ ምክሮችን በማካሄድ፣ ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብ እና ለተግባራዊነቱም የመከታተያ ሥርዓት በመዘርጋት ለሀገራዊ መግባባት ምቹ ሁኔታ መፍጠር የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ተልዕኮ ተደርጎ ተቀምጧል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ውጤቶችን በአግባቡ መረዳት፣ የተገኙ ውጤቶች ተግባራዊ የሚሆኑበትን ዝርዝር ዕቅድ ማዘጋጀትና ስልቶችን መንደፍ እንዲሁም ለትግበራው ምዕራፍ ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት አተገባበሩን መከታተል በምክክር ኮሚሽኑ ትኩረት የሚሰጣቸው አንኳር ጉዳዮች ናቸው፡፡ ሀገራዊ ምክክሩ ትልቅ የሽግግር ፍኖተ ካርታ አካል ሆኖ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በፍትህ ማሻሻያ ሂደቶች የሚታጀብ ነው፤ በራሱ ፍጻሜ ሳይሆኑ የተቀናጀና አሳታፊ የለውጥ ሂደት ጅምር ነው፡፡

ኮሚሽኑ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሃከል መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በመለየት እና ውይይቶች የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመለየት ምክክር እንዲደረግባቸው ያመቻቻል፡፡ የሚካሄዱት ሀገራዊ ምክክሮች፤ አካታች፣ ብቃት ባለውና ገለልተኛ በሆነ አካል የሚመሩ፣ የአለመግባባት መንስዔዎችን በትክክል በሚዳስስ አጀንዳ ላይ የሚያተኩሩ፣ ግልፅ በሆነ የአሠራር ሥርዓት የሚመሩ እና የምክክሮቹን ውጤቶች ለማስፈፀም የሚያስችል ዕቅድ ያላቸው እንዲሆኑ በማድረግ ውጤታማ የሆኑ ሀገራዊ የምክክር ሂደት ተግባራዊ ያደርጋል፡፡

በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እንዲሁም በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል፣ መተማመን የሰፈነበትና አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር በሚያስችል አግባብ ውይይቶቹ እንዲካሄዱ ሥርዓት ይዘረጋል። ከምክክሮቹ የተገኙ የመፍትሔ ምክረ ሃሳቦች በሥራ ላይ እንዲውሉ ድጋፍ በማድረግ በዜጎች መካከል እንዲሁም በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመን የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲገነባ ለማስቻል ይሠራል፡፡

ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ባህል ለማዳበር እና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምቹ መደላድል መፍጠር፤ ወቅታዊ ችግሮች ዘላቂ በሆነ መንገድ ተፈተው አስተማማኝ ሰላም የሚረጋገጥበትን የፖለቲካ እና የማኅበራዊ መደላድል ማመቻቸት፤ ለሀገራዊ መግባባት እና ጠንካራ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ጽኑ መሠረት መጣል የምክክር ኮሚሽኑ ተጨማሪ አላማ ነው፡፡

የምክክር ኮሚሽኑ ይህንን አላማ ብቻውን ከግብ ለማድረስ አይችልም፡፡ ለስኬታማነቱ መንግስት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ምሁራንና መላው ሕዝብ በጋራ ሊንቀሳቀሱ ይገባል። በያገባኛል መንፈስ፤ የሰላማችን ባለቤቶች ለመሆን በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቅ ባቸዋል።

ከልዩነቶች ሁሉ በላይ ገዝፎ በሁሉም ልብ ተመሳሳይ ስፍራ ይዞ ለሚገኘው የጋራ ሰላማችን በአንድነት ልንቆም ይገባል፡፡ የተለየ የፖለቲካ አቋምም ሆነ የተለየ አስተሳሰብ ያላቸው ዜጎች ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው አንድነት በሚፈልጉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በአንድነት ሲሰሩ አይተናል። ይህንን አቅማችንን ሰላማችንን ለማረጋገጥና ችግሮቻችንን በውይይት ለመፍታት ልንጠቀምበት ይገባል።

ለዚህ ሁነኛ ምሳሌ ሆኖ ሊነሳ የሚችለው የሕዳሴ ግድብ ነው፡፡ ከዓመታት በፊት የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ወደ ትግበራ ሲገባና ሀገሪቱ ግድቡን የምትገነባው በራሷ አቅም እና ወጪ መሆኑ ሲታወቅ፤ ከትንሽ እስከ ትልቅ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ለግድቡ ግንባታ በአንድነት ቆሟል፡፡ ግንባታውም እስካሁንም እየተከናወነ ይገኛል።

እስካሁን በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ልዩነቶች ቢኖሩንም ለግድቡ ድጋፍ ማድረጋችንን አላቆምንም። ምክንያቱም የግድቡ ጉዳይ ከልዩነታችን በላይ ከመሆኑም በተጨማሪ ለትውልድ የምናስተላልፈው ትልቅ ቅርስና ታሪክ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ አንድነትም ፍሬ አፍርቶ ውጤቱን ለማየት ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እየደረስን እንገኛለን፡፡

በመሆኑም ለሕዳሴው ግድብ በአንድነት እንደቆምን ሁሉ ለሰላም መስፈን አስፈላጊ ለሆነው ምክክርም በአንድነት መቆም ይኖርብናል፡፡ ልዩነቶችን በመነጋገር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሁሉም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅበታል፡፡

ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑም ባስቀመጠው አላማ መሠረት የሚካሄዱት ሀገራዊ ምክክሮች፤ አካታች፣ ብቃት ባለውና ገለልተኛ በሆነ አካል የሚመሩ፣ የአለመግባባት መንስዔዎችን በትክክል በሚዳስስ አጀንዳ ላይ የሚያተኩሩ፣ ግልፅ በሆነ የአሠራር ሥርዓት የሚመሩ እና የምክክሮቹን ውጤቶች ለማስፈፀም የሚያስችል ዕቅድ ያላቸው እንዲሆኑ በማድረግ ውጤታማ ሀገራዊ ምክክር ማድረግ ይኖርብናል፡፡

ቲሻ ልዑል

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You