የአረንጓዴ ዐሻራው መርሀ ግብር የስኬት ጉዞ ሌላው ማሳያ

ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ከ32 ቢሊየን በላይ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች ተተክለዋል፡፡ በችግኝ ተከላው መንግሥትና ሕዝቡ ከፍተኛ የተቀናጀ ጥረት ያደረጉ ሲሆን፣ እንደ ችግኝ ተከላው ሁሉ በእንክብካቤውም ተመሳሳይ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

የግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም የሥነ ሕይወታዊ አፈርና ውሃ ጥበቃና የጥምር ደን እርሻ ዴስክ መረጃን ዋቢ ያደረገ ዘገባ እንዳመለከተው፤ ኅብረተሰቡ እንደ ተከላው ሁሉ ለችግኞቹ በኃላፊነት ስሜት እንክብካቤ እያደረገ ነው፤ ሚኒስቴሩ በአምስተኛው ዙር በተተከሉ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኞች ላይ የመጀመሪያ ዙር የጽድቀት ምዘና መደረጉንም ጠቅሶ፤ በዚህም የችግኞቹ የጽድቀት ምጣኔ 90 ነጥብ አራት በመቶ መድረሱን አመልክቷል፡፡

ሚኒስቴሩ እንዳለው፤ የችግኞች የጽድቀት ምዝና በዓመት ሁለቴ የሚካሄድ ሲሆን፣ አሁን የተመዘገበው የ90 ነጥብ አራት በመቶ መጠን ከእዚህ በፊቱ የተሻለ ውጤት የታየበት ነው፡፡ የጽድቀት መጠኑ ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ መጥቷል፤ ቀደም ሲል የጽድቀት መጠኑ 80 በመቶ ነበር፡፡ የዘንድሮ ከፍ ማለቱ ሥራው በእኔነት ስሜት መሠራቱን እንደሚያመለክትም ነው ሚኒስቴሩ ያብራራው፡፡

በመርሀ ግብሩ የተተከሉ የአቮካዶና አንዳንድ የፍራፍሬ ችግኞች ማፍራት ጀምረዋል፤ ምርት መስጠት መጀመር ብቻም ሳይሆን ምርታቸው ለሀገር ውስጥ እንዲሁም ለውጭ ገበያ እየቀረበም ነው፡፡ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብሩ ችግኞች በአየር ንብረት ላይም እንዲሁ አዎንታዊ ተጽእኖ ማሳደር መጀመራቸውን የደን ዘርፍ ባለሙያዎች እያረጋገጡ ይገኛሉ፡፡

የችግኞች የጽድቀት መጠን እየጨመረ መምጣትና ከችግኞቹ መካከል አንዳንዶቹ የታለመላቸውን ግብ ማሳካት መጀመራቸው ኅብረተሰቡ ለችግኞቹ የሚያደርገው እንክብካቤ በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን ይጠቁማል። መንግሥት ኅብረተሰቡ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብሩን በባለቤትነት ስሜት እንዲመራው ያከናወነው ተግባር ውጤታማ መሆኑንም ያመለክታል፡፡

በችግኞች ጽድቀት መጠን ላይ የታየው ከፍተኛ ለውጥ ትርጉሙ ብዙና በመርሀ ግብሩ ላይ እምርታ እንዲመዘገብ ማድረግ የሚያስችል ነው፤ የጽድቀት መጠኑ በእዚህ መልኩ እየተሻሻለ የሚመጣ ከሆነ፣ በመርሃ ግብሩ የተያዙትን አላማዎች አስቀድሞ በሚገባ ማሳካት ይቻላል፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ የተመናመነውን የሀገሪቱን የደን ሀብት በቅርብ ጊዜ መተካት እንደሚቻል ያመላክታል፡፡

ተገቢ ችግኞች በተገቢው ሥፍራ በተገቢው ወቅት መተከላቸው፣ ከእንስሳትና ሰው ንክኪ መጠበቃቸው፣ የዝናቡ ሁኔታ ጥሩ መሆንና የመሳሰሉት ለጽድቀት መጠኑ መጨመር አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደቻሉ ይገመታል።

አሁን ለታየው የችግኞች የመጽደቅ መጠን መጨመር የኅብረተሰቡ እንክብካቤ ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል። ኅብረተሰቡ በችግኝ ተከላው ያሳየው ርብርብ በእንክብካቤውም ተጠናክሮ መቀጠሉንም ያመለክታል፡፡

ችግኞችን ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ በመጠበቅ ብቻ በጽድቀት መጠን ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ይታመናል፡፡ ይህን ማድረግ የሚችለው ደግሞ ኅብረተሰቡ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ይህንን በማድረጉም ነው በጽድቀት መጠኑ ላይ ለውጥ ማምጣት ተችሏል፡፡

ከዚህ ውጭ በበጋው ወቅት የሚጥል ዝናብ ለጽድቀት መጠኑ መጨመር ከፍተኛ ሚና ሊጫወት ይችላል፤ የተተከሉት ችግኞች ለመተከል የደረሱ መሆን አለመሆናቸው፣ የተተከሉበት ቦታም ለችግኞቹ ምቹ መሆን አለመሆኑም በጽድቀት መጠን ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ፡፡ ለጽድቀት መጠኑ ከፍተኛ መሆን የኅብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ቢገለጽም፣ የተጠቀሱት ጉዳዮችም የበኩላቸውን ሚና አበርክተዋል ብሎ መውሰድ ይቻላል።

ለችግኞች የጽድቀት መጠን መጨመር ኅብረተሰቡ አሁንም ሚናውን መወጣቱን መቀጠል የሚኖርበት መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ ችግኞች በሚተከሉባቸው ሥፍራዎች መረጣ፣ በአግባቡ በመተከላቸውና ለተከላ ብቁ በመሆናቸው ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ሁለተኛው ዙር የጽድቀት መጠን ምዘና ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ በዚህ ግምገማ ከእስከ አሁኑም በላይ የተሻለ የጽድቀት መጠን እንዲመዘገብ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ በጀት ዓመት ባለፉት ወራትና አሁንም ሲጥል የነበረውና እየጣለ ያለው ዝናብ ለችግኞች የጽድቀት መጠን መጨመር ሁነኛ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፤ በዚህ ላይ እየጎለበተ የመጣውና ከፍተኛ የጽድቀት መጠን እንዲመዘገብ ያስቻለው የኅብረተሰቡ የችግኞች እንክብካቤው ል ምድ የጽድቀት መጠኑን ሊያሳደገው ይችላል።

ከዚህ ሁሉ መረዳት የሚቻለው በችግኞች የጽድቀት መጠን ላይ ይህን ከፍተኛ እምርታ በማምጣት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብሩ የተያዙ ግቦችን ማሳካት እንደሚቻል ነው፡፡ አስቀድሞ የተተከሉትን በዚህ መልኩ በመንከባከብ ለውጤት ማብቃት ከተቻለ፣ በቀጣይ የሚተከሉትንም እንዲሁ በጥንቃቄ በመትከልና በመንከባከብ በአረንጓዴ ዐሻራው ይበልጥ ውጤታማ መሆን ይቻላል፡፡

ለእዚህ ሁሉ ደግሞ የጽድቀት መጠን እንዲጨምር ከዚህ አልፎም አንዳንድ የፍራፍሬ ተክሎች ወደ ምርት እንዲሸጋገሩ ያስቻሉ ሥራዎች ተሞክሮ ተቀምሮ ለቀጣይ የመርሃ ግብሩ ሥራዎች ውጤታማነት ሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረግ ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የችግኞች የጽድቀት መጠን መጨመሩ የአረንጓዴ ዐሻራው መርሀ ግብር የስኬት ጉዞ ሌላው ማሳያ ተደርጎ መወሰድ የሚኖርበት ሲሆን፣ በቀጣይም ይሄ ስኬት እንዲመዘገብ ኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከእነ ግለቱ መቀጠል ይኖርበታል!

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You