መልካሚቱ እረኛ – ስለ አንዲቱ ግልገል …

እንደ መነሻ …

ሀድያ ዞን ‹‹እሙጩራ›› ቀበሌ መሬቱ ለምለምና አረንጓዴ ነው። ስፍራው ያሉ ነዋሪዎች እንሰትና ቡና ያመርታሉ። ከአብዛኞቹ ጎተራ በቆሎና ስንዴ ይታፈሳል። መሬቱ የሰጡትን አብቃይ ነውና ጠንካሮቹ አርሶአደሮች ዓመቱን ሙሉ ሥራ አይፈቱም።

ዓለሚቱ ሳሙኤል የብርቱ ገበሬ ልጅ ነች። እሷን ጨምሮ መላው ቤተሰብ መተዳደሪያው የግብርናው ፍሬ ነው። የቤቱ አባወራ ከእርሻው ጎን ጎን ጠንካራ ይሉት ነጋዴ ናቸው። የሰባቱ ልጆቻቸውን ዓለም ለማየት የመጀመሪያ ምርጫቸው ሁሉንም ማስተማር፣ ዕውቀትን ማስጨበጥ ሆኗል። ልጆቻቸውን በወግ አስተምረው ለቁምነገር ማ ድረስ ይሻሉ።

በነ ዓለሚቱ ቤት ከትምህርት ያልዋለ፣ ከቀለም ያልተዛመደ ልጅ የለም። ዛሬን ከገጠር ኑሮ አልፎ ነገን በተሻለ ለመራመድ ሁሉም ትምህርትን የሙጥኝ ብሏል። አባወራው ቤታቸውን አሸንፈው ልጆችን ለማሳደግ በብርታት ኖረዋል። ሰባቱም ልጆች የእናት አባታቸውን ቃል አክብረው በታዛዥነት ዘልቀዋል። መላው ቤተሰብ ተከባብሮ ፣ተዋዶ መኖርን ያውቃል።

በድንገት…

ከቀናት በአንዱ በዚህ ቤተሰብ መሐል የደረሰው ኃዘን የሁለንም ልብ ሰበረ። የአባወራው ድንገቴው ሞት የእማወራዋን አንገት አስደፋ። ነገን አርቀው የሚያዩ ልጆች በተስፋ መቁረጥ ቀናት ገፉ። ይህ ስሜት በጠንካራዋ እናት ሊመለስ አፍታ አልፈጀም። የባላቸውን ትከሻ የተኩት ወይዘሮ ጥርሳቸውን ነከሱ። ልጆቻቸው ከትምህርት እንዳይቀሩ፣ ከመንገድ እንዳይሰናከሉ በአባወራው መንገድ ተጓዙ ።

ጥረታቸው ከእርምጃ በላይ ሆነ። የሰበራቸውን ኃዘን እጁን ይዘው ሰበሩት። ተስፋ መቁረጥን ቀድመው አሸነፉት። ዓለሚቱና ስድስት እህት ወንድሞቿ የአባታቸው ምኞት በጠንካራዋ እናት ብርታት ከግቡ ደረሰ። ሁሉም ያለአንዳች ስንፍና ትምህርታቸውን አጠናቀቁ።

የቤቱ አራተኛ ልጅ ዓለሚቱ የእናቷን ልፋት፣ ድካም አትዘነጋም። ከአባታቸው ሞት በኋላ እማዋራዋ ስለልጆች የከፈሉት ዋጋ ቀላል አለመሆኑን ታውቃለች። ዛሬ ላይ ቆማ ትናንት የሆነውን ስታስብ ዓይኖቿ በዕንባ ይሞላሉ። ከዚህ ስሜት ባሻገር ስለእናቷ ያላት ፍቅርና ክብር ለየት ይላል።

ዓለሚቱ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች ከትውልድ ቀዬዋ ርቃ ሆሳዕና ላይ ከተመች። ሆሳዕና ትልቅ እህቷ አለችና እንግድነት አልተሰማትም። በዚህ ስፍራ ለመነገድ ራስን ለመቻል ያመቻል። ከእህቷ ዘንድ የጀመረችው የሱቅ ንግድ የአባቷ ሙያ ነው። በሥራው ልትቀጥል አልከበዳትም።

ወጣቷ በዚህ ውሎ ራሷን መቻሏ ከሌላ አጋጣሚ ጣላት። ሆሳዕና የእንጀራ ክፍሏ ብቻ አልሆነም። ከብቸኝነት የምርትቅበት፣ ቁምነገርን የምታስብበት ጭምር እንጂ። የትዳር አጋሯን ያገኘችው፣ በዚህ ከተማ ነበር። እሷን ያለው ሰው በቀረባት ግዜ አልገፋችውም። ስለእሱ በጎነት የተነገራት ሁሉ እውነት ሆኖ አገኘችው። ልቧ ከልብ ፈቀደው።

ሶስት ጉልቻ…

ዓለሚቱ ሆሳዕና ላይ የጀመረችው የሱቅ ንግድ ከትዳሯ አገናኝቶ ጎጆ ቀልሳለች። በግብርና የሚኖረው ባለቤቷ ስለሚስቱ ክብር አለው። ሆሳዕና ላይ የጀመረው ሕይወት መልካም ሆኖለታል። ጥንዶቹ ስለነገ ብዙ ያልማሉ። ልጆች ወልዶ ለማሳደግ ፣ወግ አድርሶ ቁምነገር ለማየት ምኞታቸው ነው።

ውሎ አድሮ የባልና ሚስት ጎጆ በልጅ ፍሬ ተባረከ። የመጀመሪያውን ወንድ ልጅ አቅፈው ሳሙ። የሕጻኑ ጌዲዮን ለቅሶና ሳቅ ቤቱን በፍቅር ሞላው። የትዳራቸው መልካምነት በጥንዶቹ መተሳሰብ ተገለጠ። ጌዲዮን ጥቂት ከፍ እንዳለ ሁለተኛው ልጅ ተወለደ። ይኸኔ ደስታቸው በእጥፍ ጨመረ። ትንሹ ዳግም ወንድሙን ከብቸኝነት የሚታደግ ሕጻን ሆኖ የቤቱን በረከት አበዛ።

ሦስተኛው ልጅ…

አሁን ደግሞ ሦስተኛው ልጅ ቤቱን በእንግድነት ተቀላቅሏል። ከዚህ ቀድሞ ሁለት ወንድ ልጆች ያገኘው አባወራ በሦስተኛው ሕጻን መምጣት የልቡ ሞልቷል። የውስጡ ምኞት ሴት ልጅን መታቀፍ ቢሆንም ከፈጣሪ ባገኘው ስጦታ አልተከፋም። ውስጡ ደስታን ሸምቷልና ስለሆነለት በረከት ዝም አላለም። ‹‹ልጅ ተጨመረልኝ፣ ሌላ ተካበልኝ›› ሲል ትንሹን እንግዳ ‹‹ተካበ›› ሲል ሰይሞታል። ተካበ ለእሱ ተጨማሪ ደስታ ነው። የቤቱ ሌላ በረከት ሆኖ ታክሏል።

ተካበ በሁለት ወንድሞቹ መሐል ደስተኛ ሆኖ ማደግ ጀመረ። መልካም ባሕሪ መገለጫው ነው። ከፊቱ ደማቅ ፈገግታ አይጠፋም። ገና ከልጅነቱ ትኩረቱ ልዩ ሆኗል። እንደወንድሞቹ ማንበብ መጻፍን ይፈልጋል። ዕድሜው ሲደርስ ትምህርት ቤት ሊገባ ግድ ሆነ። ትንሹ ተካበ የልቡ ምኞት ሞላ። እንደእኩዮቹ አፀደ ሕፃናት ገብቶ እንደ ምኞቱ መማር ጀመረ።

ተካበ የትምህርት ጅማሬው ማስደነቅ የያዘው ሳይውል ሳያድር ነበር። ከሌሎች ይበልጥ ጎበዝ መሆኑ ምስጉን አደረገው። በየግዜው በአድናቆት በሽልማት፣ ተንበሸበሸ። ቆይታውን አጠናቆ አንደኛ ክፍል ሲገባ ጉብዝናው አልራቀውም። በትምህርቱ ልቆ አንደኛነትን ተቀዳጀ።

ከቀናት በአንዱ…

ትንሹ ተካበ የትምህርት ቤት ውሎው በጨዋታ የተሞላ ነው። ከእኩዮቹ ጋር መዝለል መጫወት ደስ ይለዋል። እንደልጅ ኳስ መጠለዝ፣ በአባሮሽ መዞር ይወዳል። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን ፍላጎቱን የሚገታ ነገር ይሰማው ጀምሯል። ገና ሊራመድ ሲሞክር ጉልበቱን በሚይዘው ስሜት እየተረበሸ ነው። እንዲያም ሆኖ ከሩጫው አይቆምም። እያመመው ይቦርቃል፣ እየተሰማው ይፈነጥዛል።

አንድ ቀን ተካበ ኳስ እየተጫወተ በድንገት ወደቀ። ከወደቀበት ሲነሳ የተለየ ሕመም ተሰማው። ከትምህርት ሲመለስ ለእናቱ የሆነውን ሁሉ ነገራት። እናት እግሩን፣ ጉልበቱን እያሻሸች ችግሩን ልታውቅ ሞከረች። ተካበ ክፉኛ አሞታል። የእናቱ እጅ እንዳይነካው መጮህ፣ መከላከል ያዘ።

ውሎ ሲያድር ሕመሙ ባሰ። ትምህርት ቤት ለመሄድ፣ ቆሞ ለመራመድ ጭንቅ ሆነ። ቤተሰብ አብዝቶ ቢያስብ ቢጨነቅ ልጁን ከወጌሻ ዘንድ ወሰደው። ወጌሻው የጉልበቱን ችግር አስተዋለ፤ ለማሸት አልደፈረም፣ እጁን አላነሳም፣ ለማሰር ፈጥኖ አልወሰነም። እንደነበር መልሶ ለቤተሰቡ አስረከበ።

ትንሹ ተካበ ከሕመሙ አልዳነም። እንደልጅ መሮጥ መራመድ እያማረው ከቤት ዋለ። አንድ ቀን ደግሞ አንድ ጓደኛው አዝሎት ሲጫወት በጀርባው ወደቀ። ይህ አጋጣሚ ለትንሹ ተካበ የከፋ ስቃይ አስከተለ ።

ወራት ተቆጠሩ። እናት አባት ስለ መፍትሔው በየቦታው ሮጡ። ችግራቸውን ያዩ አንዳንዶች በመላ ምት አስጨነቋቸው። የልጁ ሕመም ክፉ መንፈሰ ነው ያሉ፣ በራሳቸው ሀሳብ ብዙ አሏቸው። ዓለሚቱና ባለቤቷ ስለልጃቸው መዳን በየቦታው ዋተቱ። የተገኘ መፍትሔ አልነበረም።

ከአንገቱ ስር …

ውሎ አድሮ በተካበ አንገት ስር አንድ ምልክት ተስተዋለ። እናት በዓይኗ ያየችውን በእጆቿ ዳብሳ ልታውቅ ሞከረች። በቀላሉ የሚለይ ጠንካራ ዕብጠት ነበር። እሱን ተከትሎ የመጣው ቶንሲል ሌላ ስቃይ ሆነበት። ፈጥኖ ከሆስፒታል የደረሰው ሕጻን አስቸኳይ ምርመራ ተደረገለት። ከሐኪሞች የተገኘው ውጤት የደም መርጋት መሆኑን አረጋገጠ።

የቀዩ ደም ሴል መውረዱን ተከትሎ ተካበ ለከፍተኛ ሕክምና ወደ አዲስ አበባ መላክ ነበረበት። ጎበዙ ተማሪ፣ ተስፋ የተጣለበት ለጋ ጅምር ትምህርቱን አቋርጦ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሊላክ ግድ ሆነ። እናት አባት የተጻፈላቸውን ማስረጃ ይዘው ከሆስፒታሉ ደረሱ።

በድንገተኛ ክፍል ሕክምናው ፈጥኖ ተጀመረ። እነሱ እንዳሰቡት ቆይታው በቀላሉ የሚጠናቀቅ አልሆነም። ጊዜው ቀናትን አስከትሎ ወራት ተቆጠሩ። የሆስፒታሉ ተከታታይ ሕክምና ሲጠናቀቅ ባልና ሚስት ልጃቸውን ይዘው መውጣት ግድ ይላቸዋል። አዲስ አበባ ‹‹የእኔ›› የሚሉት ማረፊያ ዘመድ የለም። በማያውቁት ስፍራ እንደልብ ወጥቶ መግባት ይቸግራል።

ምስጢረኛው አባት…

የጥቁር አንበሳ የሕክምና ሂደት ለትንሹ ተካበ ቀላል አልነበረም። በልጅነት አቅሙ መድኃኒቶችን መጠቀም፣ ከአካሉ ወሳኝ ናሙናዎችን መውሰድ ፈታኝ የሚባል ስቃይ አለው። ዓለሚቱ ልጇ ሕመም ላይ መሆኑን እንጂ ምን እንደታመመ ያወቀችው የለም። አባት ከሐኪሞች የተነገረውን ውጤት በምስጢር ይዞ ብቻውን ይብሰለሰላል። የሰማውን ለሚስቱ አጋርቶ ችግሩን የእኩል ማድረግን አላጣውም። ይህ እንዳይሆን ስለሚስቱ ጤና ተጨነቀ። ስለ እርሷ ሠላም አሰበ። ውጤቱን ድንገት ብትሰማ የምትሆነውን አያውቅም። እናም በልጁ ሕመም ብቻውን ታመመ። በያዘው ምስጢር በውስጡ ጋየ።

የሕክምናው ውጤት…

ትንሹ ልጅ ተካበ ሕመሙ የደም ካንሰር መሆኑ ተረጋግጧል። በአባትዬው ውስጠት ያለው ምስጢር የግሉ ብቻ አልሆነም። ከቀናት በኋላ እናት ዓለሚቱ እውነቱን ማወቋ ግድ ሆኗል። በወቅቱ ስለካንሰር የሚገልጹ የሙሉ መረጃ በራሪ ወረቀቶች በእጇ ይደርሷት ነበር። እንዲህ ሲሆን ነጋሪ አላሻትም፣ አሁን ስለ ልጇ ሕመም ድብቅ ምስጢር የለም። ፊቷ ካለው ሐቅ ጋር ልትጋፈጥ ጊዜው ደረሰ።

እናት ስለተካበ ሕመም ባወቀች ግዜ ውስጧ አምኖ ሊቀበል ቸገረው። ካንሰር በሕጻናት ላይ ስለመከሰቱ ለአንድም ግዜ ሰምታ አታውቅም። ለቀናት ራሷን ካረጋጋች በኋላ አባወራው ወደ ቤት ሊመለስ ተወሰነ። ባልና ሚስት ስለአንዱ ልጃቸው ጤና መላውን ቤተሰብ ትተው ከሀገር ከራቁ ሰንብተዋል። በቤታቸው ሁለቱ የተካበ ታላላቆችና ከእሱ ኋላ የተወለዱት ሁለት ሴት ሕጻናት በዘመድ እጅ ናቸው። አሁንም ሕክምናው ተጨማሪ ጊዜን ይፈልጋል።

ዓለሚቱ ተካበን ይዛ አዲስ አበባ ቀርታለች። አሁንም እግሮቹ በወጉ አይራመዱም። ራሱን ችሎ መቆምና መቀመጥ አይችልም። ጤናው ጨርሶ አልተመለሰም። በየግዜው የሚወስደው ሕክምና በእሱ አቅም የሚከብድ ነው። በዕድሜው ሰባተኛ ዓመቱን ደፍኗል። ቁመቱ መለሎና ረጅም በመሆኑ እንደ ልጅ አዝሎ ለመንቀሳቀስ ያዳግታል።

እናት በመጀመሪዎቹ ቀናት የወሰዳቸው ሕክምናዎች አስጨናቂነት ዛሬም ድረስ ውል ይላታል። ለሰዓታት ራሱን ይስት ነበር። ከጀርባ አጥንቱ ላይ የመቅኔ ምርመራ ሲወሰድ ደግሞ በሕይወት አለመኖሩን እስክታምን በተስፋ መቁረጥ ተመላልሳለች። የሀያ ስምንቱ ቀናት ኬሞ ቴራፒ በከባድ ሕመምና ስቃይ የተሞላ ነበር።

አንዳንዴ ዓለሚቱ ስለልጇ ክፉው ብቻ ይሰማታል። ድንገት የሚሞት የሚለያት ሲመስላት አምርራ ታለቅሳለች። አባወራው ግን ሁሌም ራሱን አጠንክሮ እሷን ያበረታል። ዘወትር ውስጡ የሚነግረው ልጁ በሕክምናው ዘልቆ ፈጽሞ እንደሚድን ነው።

ይህ ዕምነቱ ወደ ዓለሚቱ እንዲጋባ በፈጣሪ ያለውን መተማመን ይነግራታል። እናት ዓለሚቱ አሁን ባለቤቷን ወደ ቤቱ ሸኝታለች። ከእሱ የወሰደችው ጥንካሬ ግን ዛሬም ከእሷ ጋር ነው። ሕክምናው አሁንም ቀጥሏል። ባልና ሚስት አዲስ አበባ ላይ ሁነኛ ዘመድ የላቸውም። ይህ እውነት ለብዙ ችግሮች ይዳርጋል።

የታበሰ ዕንባ…

አሁን በእነሱ አቅም የሆስፒታሉን ሕክምና በተመላላሽ መቀጠል የሚቻል አይደለም። ይህ የገባቸው ልበ መልካሞች ዓለሚቱ ልጁን ይዛ ወደምታርፍበት የማቲዎስ ወንዱ ካንስር ሶሳይቲ አመላከቷት። በዚህ ቅጥር በርካቶች ከፍቷቸው መጥተው ዕንባቸውን አብሰው ተመልሰዋል። የታመሙ ድነው ቤታቸው ገብተዋል ።

ዓለሚቱ ልጇን ይዛ በመጣች ግዜ ቤቷ እስኪመስላት በእፎይታ ተንፍሳለች። አሁን ስለልጇ ሕክምና፣ አስፈላጊ መድኃኒትና ምግብ እንዳታስብ ጎዶሎዋ ሞልቷል። አራቱን ልጆቿን ትታ ከቤት ከወጣች ወራት ተቆጥረዋልና ብዙ ታስባለች።

እናት ሁሌም ናፍቆትና ትዝታ ይፈትኗታል። ልጆቿ በራቧት፣ በናፈቋት ግዜ በስልክ ታወራቸዋለች። በእጇ ያለው ፎቶግራፋቸው ደግሞ ዘወትር ከእርሷ ጋር ውሎ ያድራል። አንዳንዴ በትዝታ ርቃ በሀሳብ ታወጋቸዋለች። ይኸኔ እንደ እናት የሚታያት ደግ ደጉ ብቻ አይደለም። ከሳቃቸው ይልቅ ለቅሷቸው፣ ከደስታቸው ደግሞ ኃዘናቸው ልቆ ይሰማታል።

ሁለቱ የተካበ ታላቆች ትምህርት ቤት ይውላሉ። የእሱ ታናሽ ስድስት ዓመቷ ነው። ከእሷ ቀጥላ ያለችው ሕጻን ደግሞ በወጉ ጡት ያልጣለች ሁለት ዓመት ያልሞላት ጨቅላ ናት። በተለይ እሷ ከእናቷ ጉያ መውጣት፣ ከዓይኗም መራቅ የማይገባት ነበረች። ይህን ስታስብ ዓለሚቱ አንገቷን ትደፋለች። የልጆቿ ናፍቆት የትዳሯ ድምቀት በዓይኗ ጥግ ይዞራል።

አሁን ሕጻኑ ተካበ ጤንነቱ መልካም ሆኗል። ሕክምናው ባያበቃም። ቀና ብሎ እየሄደ ነው። እግሮቹ እርምጃቸው ተሻሽሏል። ባለቤቷ ከአይኗ ቢርቅም በሀሳብ ሁሌም ከጎኗ ነው። ስለልጇ ልጆቿን ትታ በደጅ ስላለችው ወይዘሮ አክብሮቱ ከፍቅር ጋር ነው።

ስለአንዱ ሌሎቹን…

እናት ዓለሚቱ ስለአንድ ልጇ የከፈለችው ዋጋ ዘጠና ዘጠኙን በጎች በዱር ትቶ አንዲቱን ግልገል ፍለጋ እንደወጣው መልካም እረኛ ይመስላል። እሷ ተካበን አስታማ ለማዳን ከቤት ከቀዬዋ ርቃለች። ለአንድ ልጇ መኖር ስትልም አራት ልጆቿን ትታለች። ዛሬ ስለጤናው መድኃኒቱን አግኝታለችና ነገ ወደ ቀሪዎቹ ልጆቿ እንደምትመለስ ጥርጥር የላትም።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You