መተባበርንና መቻቻልን የሚያጎለብቱ ተግባሮች ይጠናከሩ!

ዘመናትን የተሻገረ ሀገረ መንግሥት አላት። አያሌ የብርሃንና የጨለማ ጊዜያት ተፈራርቀውባታል። ዛሬ ለመቆሟ ትናንት የተተከሉት ምሰሶዎች ምክንያት ናቸው። ለእዚህም ነው ወጀብ በመጣ ቁጥር መሠረቷ የማይነቃነቀው፤ ይልቁንም የጠበቀው።

ህብርና ኅብረት መገለጫዎቿ ናቸው። ሃይማኖት፣ ባህል፣ ማህበረሰብና ሌሎች እሴቶችን ልክ እንደ ልዩ ልዩ ህብረ ቀለማት አጣምራ ይዛለች። ይህቺ ሀገር ነብዩ መሐመድ እጃቸውን ወደ ምእራብ በመጠቆም ‹‹ሂዱ ወደ ምእራብ፤ በእዚያ አንድ የሀበሻ ንጉስ ታገኛላችሁ….የሚነካችሁ አንዳች ነገር የለም›› ሲሉ ለተከታዮቻቸው ከስጋታቸው ነፃ ሆነው በነፃነትና በመቻቻል እንዲኖሩ የላኳቸው፤ እነርሱም ያለስጋት የመጡባት ሀገር ኢትዮጵያ ነች።

ከእዚያን ጊዜ አንስቶ በህብርና በፍቅር ሕዝቦች የሚኖሩባት ሀገር፣ በጊዜያዊ ውጣ ውረድ ሳትፈተን በአንድነት የሚኖርባት ሆኖ ፀንታለች። ኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊነቷንና ሃይማኖቶቿን እንደ ደካማ ጎን ቆጥረው ሊያፈርሷት የሞከሩ በርካታ ጠላቶቿ በማሱበት ጉድጓድ ሲወድቁና ሀገረ መንግሥቷ ሲቀጥል በተደጋጋሚ ታይቷል። ይህን ጥንካሬ ያገኘችውና ለጠላቶቿ እጅ ሳትሰጥ የቆየችው ለዘመናት ባዳበረችው የመቻቻልና የአብሮነት እሴት ምክንያት ነው።

‹‹ሀገር የጋራ ነው። ሃይማኖት የግል ነው›› በሚለው እሳቤ ማንኛውንም አይነት እምነት በነፃነት የሚያከብር እንዲሁም አንድ በሚያደርጉና የጋራ በሆኑ እሴቶች ላይ ደግሞ ጠንካራ ማህበረሰባዊ ትስስር ያለው ድንቅ ሕዝብ መፍጠር ተችሏል። ይህ ዛሬ መሽቶ ሲነጋ ያየነው ጉዳይ ሳይሆን ከጥንትም የነበረ በጠንካራ የመቻቻል መሠረት ላይ የተገነባ እሴት ነው።

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ለማዳከም ብዙዎች በተናጠልና በትብብር ሠርተዋል። ለዚህ እንደ ደካማ ጎን የተመለከቱት ደግሞ የኢትዮጵያን የብዝሃ ሃይማኖት አጀንዳ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ አካላት አንድ ያልተረዱት ጉዳይ ነበር። ለኢትዮጵያውያን ብዝሃ ሃይማኖት ጥንካሬ እንጂ የደካማ ጎን መገለጫ አለመሆኑን አልተረዱም። በዚህ ምክንያት ሃሳባቸው ዳር ሳይደርስ መና ሆኖ እንዲቀር፤ ለወደፊቱም ይህ እኩይ አላማቸው ቅዥት እንዲሆን አድርጎታል።

በኢትዮጵያ የሃይማኖት መከባበርና መቻቻል መገለጫ ከሆኑት መካከል ወሎ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ አዲስ አበባ እና ሌሎችም እያልን…ብዙ ምሳሌ መጥቀስ እንችላለን። እነዚህን እንደ ምሳሌ አነሳን እንጂ በመላ ሀገሪቱ አንዱ የአንዱን ሃይማኖት አክብሮ፣ በዓላት ሲደርስ መልካም ምኞት ተገላልጦ በጋራ በደስታ የሚያሳልፍ መሆኑ ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው።

ይህ ድንቅ እሴት እንዲቀጥል የማይፈልጉ አካላት በተለያየ ጊዜ እጅግ ዘግናኝ ድርጊቶችን ፈፅመዋል፤ ከንቱ ፕሮፓጋንዳ አሰራጭተዋል። ይህ የጥፋት ድርጊት ግን በማህበረሰቡ አርቆ አሳቢነት እንዲሁም ለዘመናት በገነባው ማህበራዊ ጉልበት ሊከሽፍ ችሏል።

ዛሬም በዓላት በመጡ ቁጥር፣ አጀንዳዎችን እየመዘዙ ማህበረሰቡ ውስጥ እኩይ ሃሳብ ለመጨመርና የመከፋፈል አጀንዳ ለማራመድ የሚቅበዘበዙ አይጠፉም። ሃቁ ግን ዛሬም እንደ ጥንቱ፤ ዛሬም እንደ ትናንቱ ኢትዮጵያውያን ለእነዚህ ትናንሽ አጀንዳዎች ልባቸውን ሳይከፍቱ ማህበራዊ መሠረታቸውን ይበልጥ የሚያጠናክሩ መልካም ጉዳዮች ላይ አተኩረው እያየናቸው ነው።

ለዚህ ጥሩ ምሳሌው የረመዳን ፆም ገብቶ እስኪፈታ ድረስ የሚታየው አብሮነትና መደጋገፍ ነው። ባለፈው አንድ ወራት ኢትዮጵያውያን የሃይማኖቱ ተከታዮችም ይሁኑ ከዚያ ውጪ የሆኑ ዜጎች ፆሙ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅና በዓሉም በድምቀት እንዲከበር ለማድረግ እርስ በእርስ ያሳዩት ፍቅርና መቻቻል በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ አስተማሪ ነው። ከ‹‹መልካም ፆም›› ምኞት መግለጫ ጀምሮ ለሃይማኖቱ ተከታዮች እስከ በተለያዩ ቦታዎች እስከተደረጉት አፍጥሮች ድረስ የታየው መደጋገፍ በአርአያነት ሊጠቀስ የሚገባው ደማቅ ተግባር ነው።

ይህ መቻቻል፣ መከባበር እና ራስን በሌሎች ቦታ አስቀምጦ መመልከት ሀገር በጠንካራ ምሰሶ ላይ ለመቆሟ ምሳሌ ነው። ኢትዮጵያ በዚህ መሰል ኅብረት የተገነባች ሌሎች ማህበራዊ ውጥንቅጦችንም በተመሳሳይ ቀና መንፈስ መፍታት እንደምትችል ያመላክታል።

ኢትዮጵያ ‹‹ተመስገን ረመዳን በሰላም ተከበረ የሚል ክርስቲያን፤ አሏህ አምዲሊላሂ ታቦቱ በሰላም ገባ የሚል ሙስሊም›› ያለባት ነች። የእምነቶች ትክክለኛ መሠረት ሰላም ለመሆኑ ማሳያ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሀገር የትም ፈልጎ ማግኘት ይከብዳል።

ይህንን ፍፁም ሰላም፣ መከባበርና መቻቻል ለመናድ የሚጥሩ ደግሞ አይጠፉም። ለዚያ ነው ለግል ጥቅማቸው፤ ለፖለቲካ ፍላጎቶቻቸውና፣ ለስልጣናቸው ሲሉ ጠንካራውን መሠረት ለመሸርሸር የሚማስኑ የሴራ ቀማሪዎችን በየገዜው የምናየው። ለዚህም ነው ‹‹ማህበረሰቡ መሰል ድርጊቶችን በስከነ መንፈስና በጥንቃቄ ሊመለከተው ይገባል›› የሚል መልእክት ለማስተላለፍ የምንወድደው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የትኛውንም አይነት የፖለቲካ ፍላጎት፣ ርዕዮተ ዓለም የሚያቀነቅኑ ፖለቲከኞች ሃይማኖትን ሕዝብን ለመከፋፈያ አጀንዳነት እንዳያውሉ በፅናት መቆምና መታገል ይኖርበታል። ሃይማኖት ሰላም ነው። ሃይማኖትን ተገን የሚያደርጉትን መገሰፅ ደግሞ የሰላም እርምጃ ሀሁ ሊሆን ይገባል። ለዚህ እርምጃ ምሳሌ የሚሆን ጉዳይ ለማግኘት ደግሞ ሩቅ መጓዝ አይጠበቅብንም። ጥንታዊ ዶሴዎቻችንን፣ ታሪካችንን ካገላበጥን አያት ቅድመ አያቶቻችን በብልሃት መሰል ሴራዎችን ሲያከሽፉ እንደኖሩ በሚገባ መረዳት እንችላለን። ከሁሉም በላይ ግን ትናንት የነበረን ፍቅር ዛሬም አብሮን ስለመኖሩ የሚያረጋግጡልንን ድርጊቶች ማቆም አይኖርብንም።

ለዚያ ነው መተባበርን እና መቻቻልን የሚያጎለብቱ ተግባሮች ለሁልጊዜም እንዲቀጥሉ ማሳሰብ የምንወድደው። ትንሽ መስለው የሚታዩ ‹‹አይዞህ፣ በርታ፣ ከጎንህ ነኝ›› የሚሉ መልካም ምኞቶች፣ ከጎናችን ለሚኖረው ጎረቤታችን ከማፅናኛም ያለፈ ኅብረትና መተባበርን ምርጫው እንዲያደርግ የሚያስችለውን አቅም ይፈጥራሉ።

በሃይማኖት የማይመስሉን ወዳጆቻችን አብረውን እንዲዘልቁ የእኛ ቀና አመለካከት ልዩ ትርጉም ይኖረዋል። ከሁሉም በላይ ግን በሃይማኖቶች፣ በብሔሮች መካከል ሽንቁር ፈጥረው ስልጣናቸውን ለማስቀጠል የሚተጉ ኃይሎች፣ የፖለቲካ ቡድኖች ምንም አይነት ክፍተት እንዳያገኙ ያደርጋል።

በዚህ መሠረት ዛሬ ኢድ አል ፈጥርን (ረመዳን) ስናከብር ከሌሎች የሃይማኖት ተከታዮች ጋር ይበልጥ በሚያቀራርቡ በጎ ምግባሮች፣ መቻቻሎች፣ የአብሮነት እሴትን በሚያጠናክሩ ድርጊቶች ሊሆን ይገባል። ዛሬ የኢትዮጵያውያንን ታላላቅ መሠረቶች ለመናድ የሚያሰፈስፉ ቡድኖች ምንም ክፍተት እንደማያገኙ የሚያውቁበት ማስረጃ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

በዋናነት ግን ‹‹ኢስላም ሰላም ፣ የሰብአዊነት እና የሰው ልጆች የፍቅር መንገድ መሆኑን የምናሳይበት በዓል ልናደርገው ይገባል›› የሚለው የዛሬው ቁልፍ መልእክታችን ነው። መልካም ኢድ አል

ፈጥር (ረመዳን) ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ይሁን። ሰላም!!

ሰው መሆን

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You