ለአንድ ማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ዕድገት የአስተሳሰብ ለውጥ ወሳኝ ነው። ባልተለወጠ ማኅበረሰባዊ ማንነት የተለወጠ ሀገር መፍጠር የሚታሰብ አይደለምና። መፍጠር ይቻላል ብሎ ማሰብም ያልተገባ ዋጋ በመክፈል በትናንቶች ላይ ከመዳከር ባለፈ ሊያመጣ የሚችለው አንዳች ነገር አይኖርም። በዚህ መልኩ ያደገ ሀገርና ሕዝብም የለም።
ዛሬ ላይ በዕድገት /ስልጣኔያቸው አንቱ የተባሉ ሀገራት እና ሕዝቦች ዛሬ ላይ ሆነው ለተገኙበት መሆን የደረሱት ትናንቶቻቸውን መሻገር ያስቻሉ አዳዲስ የለውጥ አስተሳሰቦችን መፍጠር እና እሱን ተቀብሎ የሚተገብር ትውልድ ማፍራት በመቻላቸው ነው። ይህንን የሚሸከም ሀገራዊ /ማኅበረሰባዊ ሥርዓት መፍጠራቸውም ዕድገታቸው ቀጣይ እንዲሆን አስችሎታል።
እኛ ኢትዮጵያውያን የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪክ፤ በተለያዩ ወቅቶች የተፈጠሩ ስልጣኔዎች ባለቤት የመሆናችን እውነታ የአደባባይ ምስጢር ቢሆንም፤ እንደ ማኅበረሰብ የአስተሳሰብ ለውጥ ሊያመጡ የሚያስችሉ የታሪክ ምዕራፎችን መክፈት ባለመቻላችን ፤በትናንቶች እና ትናንቶች በሚያስከፍሉት ዋጋ ውስጥ ለመኖር ተገደናል።
እንደ አንድ ትልቅ ማኅበረሰብ በተለያዩ ወቅቶች ወደ ቀደመው የስልጣኔ ትርክታችን እና ብሔራዊ ክብራችን መመለስ የሚያስችሉ ሕዝባዊ መነቃቃቶች ውስጥ ብናልፍ፤ መነቃቃቶቻችን ባልተለወጡ ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰቦቻችን ተሰናክለው ፤ መነቃቃቶቹ ሊፈጥሩ የሚችሉትን የስልጣኔ ጉዞ መጓዝ ሳይቻለን ቀርተናል። በዚህም ዛሬ ላይ ላለንበት ድህነት፣ ኋላቀርነት እና ጠባቂነት ተዳርገናል።
ይህ ብሔራዊ ክብራችንን እየተፈታተነ ያለ አሁናዊ ማንነታችን ፤በቀደመው ታሪካችን ሙሉ ሆነን አንገታችንን አቅንተን እንዳንጓዝ ተግዳሮት ሆኖብናል። ራሳችንን በአባቶቻችን የደመቁ የተጋድሎ እና የስልጣኔ ታሪኮች ውስጥ ደብቀን ዘመናትን እንድንቆጥር አድርገውናል።
በርግጥ እንደሀገር በየዘመኑ ወደ ስልጣን የመጡ መሪዎቻችን ሀገርን ወደ ቀደመ ሙሉ ክብሯ መመለስ የሚያስችሉ ጥረቶችን አድርገዋል። ሁሉም በብዙ ቁጭት ዘመናቸውን በሚመጥን የለውጥ እሳቤ ውስጥ ተመላልሰዋል። አንዳንዶችም የለውጥ እሳቤያቸው በፈጠረው ተቃውሞ ብዙ ዋጋ ለመክፈል ተገድደዋል።
ሕዝባችንም ቢሆን፤ የትናንት የትልቅነት ታሪኮቹ ጥለውለት ያለፉትን ዐሻራ እያየ እና ትርክቶቻቸውን እየሰማ፤ዛሬ ላይ ካለበት እሱን ከማይመጥን ማኅበረሰባዊ ማንነት ለመውጣት የተቻለውን ያህል ጥሯል። በየወቅቱ ለተፈጠሩ የለውጥ መነሳሳቶች ያለውን አጋርነት ብዙ ዋጋ በመክፈልም በተጨባጭ አሳይቷል።
ይህም ሆኖ ግን የመለወጥ መሻታችን ሁለንተናዊ የአስተሳሰብ ለውጥን መሠረት ያደረገ ባለመሆኑ፤ በመሪዎቹም ሆነ በመላው ሕዝባችን ስለ ለውጥ የተከፈሉ ዋጋዎች የሚጠበቀውን ያህል ትርጉም ያለው ሀገራዊ ለውጥ ማምጣት ሳይችሉ ቀርተዋል። ትውልዶችንም በየዘመኑ ያልተገባ ዋጋ ሲያስከፍሉ ቆይተዋል።
ይህንን ሀገራዊ እውነታ ኃላፊነት እንደሚሰማው እና የራሱ እና የመጪ ትውልዶች ዕጣ ፈንታ እንደሚያሳስበው ትውልድ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ይህንን ማድረግ ከሁሉም በላይ የቀደሙ ስህተቶችን ላለመድገም ማስተማመኛና አሁን ለጀመርነው የለውጥ ጉዞ ስኬት ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው።
ይህ እንደ ማኅበረሰብ አብሮን ዘመናትን የተሻገረው ለለውጥ እሳቤዎች ያለን ባይተዋርነት፣ከትናንት እና ትናንቶች ከፈጠሩት ማንነቶች ጋር ተዛምዶ የመጓዝ ረጅም የታሪክ ጉዞ አሁን ላይ መቋጫ ሊበጅለት ይገባል። ይህን ማድረግ ቀን ሊቆጠርለት የማይገባ የህልውና ጉዳይ ነው። ከዚህ በላይ ዋጋ ሊያስከፍለንም አይገባም።
እንደ ሀገር በትናንት ያልተለወጡ ማኅበረሰባዊ ማንነቶቻችን ከዚህ በላይ መጓዝ የምንችልበት አማራጭ የለንም፤ ያደሩም ሆኑ አሁናዊ ችግሮቻችን የዚህ እውነታ መገለጫ ናቸው። ችግሩን በመሻገር ሂደት ውስጥ ከሁሉም በላይ አሁን ያለው ትውልድ ኃላፊነት ከፍ ያለ ነው። ራሱ ተለውጦ ሀገር የመለወጥ ታሪካዊ ኃላፊነትም በእጁ ነው። ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት የሰከነ ስብዕና መፍጠር ብሎም የለውጥ እሳቤዎች ለሚጠይቁት መስዋእትነት ራሱን ማዘጋጀት ይጠበቅበታል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2016 ዓ.ም