የወጣትነት አቅምን አሟጦ በመጠቀም የተገኘ ስኬት

ወጣትነት ብርታት፣ ጥንካሬ፣ ድፍረትና እምቅ አቅም አለው። ሞራልና ልበሙሉነትም በመስጠት በኩልም ይታወቃል። ይህን ዕምቅ አቅም አጭቆ የያዘን ወጣትነት ስንቶች በአግባቡ ተጠቅመውበት ይሆን?… መልሱን ለናንተው እያልኩ ይህን ለዛሬ ስለ አንድ ብርቱ ወጣት የስኬት መንገድ እንጨዋወት።

‹‹ወጣት የነብር ጣት›› እንዲሉ ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች በእዚህ እድሜያቸው ከላይ ታች ብለው ሕይወታቸውን ለመለወጥና ለማሻሻል ሲማሩ፣ ዕውቀት ሲሸምቱ፣ ሙያዎችን ሲቀስሙና ሲለምዱ ከአንዱ ሥራ ወደ አንዱ፣ ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው ሲሉ ይስተዋላሉ። በዚህም ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ሃብት ንብረት አፍርተው ለሌሎች ሲተርፉ ይታያሉ።

የዕለቱ የስኬት እንግዳችንም ገና ከአፍላ የወጣትነት ዕድሜው ጀምሮ ‹‹ሕይወት ትግል ናት፤ ታገላት›› ከሚለው አባባልም ባለፈ በተግባር የመኖር ዕጣ ፈንታ ገጥሞታል። በመሆኑም ከዝቅታው ዝቅ ብሎ ለከፍታው እየተንደረደረ የወጣትነት ዕምቅ አቅሙን አሟጦ ተጠቅሟል። በአፍላነት ዕድሜው የገጠሙት ፈተናዎች ብርቱና ጠንካራ ሰው ሆኖ እንዲሠራ እንዳደረጉት ይናገራል።

በሕይወት ከባድ ትግል ውስጥ የገባው ገና በለጋነት ዕድሜው ወላጅ እናቱን በሞት በተነጠቀበት ወቅት ነው። በወቅቱ በልቶ ጠጥቶ ለማደር፣ መሠረታዊ ፍላጎቱን ለማሟላት ሥራ ማግኘት አማራጭ የሌለው ምርጫው ነበርና ራሱን ለሥራ አሳልፎ በመስጠት ያገኘውን ሁሉ መሥራቱን ተያያዘው።

ሥራን ገና በለጋነት ዕድሜው የጀመረው እንግዳችን የትውልድ አካባቢው ኢሉባቦር መቱ ቢሆንም፣ የትምህርት ጊዜውን ጨምሮ አብዛኛውን የልጅነት ዕድሜውን ያሳለፈው በደሴ ከተማ ነው። ነፍስ ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ ደሴ ከተማ ላይ ብዙ ቢቆይም፣ እንጀራ ፍለጋ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውሯል፤ ክፉና ደግ የለየባትን ደሴ ከተማን ጨምሮ ወልቂጤ፣ ድሬዳዋ፣ ባሕርዳርና አዲስ አበባ ከተማ ድረስ ማንም ሳይኖረው ተዘዋውሮ በመሥራት ራሱን ኑሮን ለማሸነፍ ተፍጨርጭሯል።

የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን በደሴ ከተማ በወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ባጠናቀቀ ማግስት የእንጨት ሥራ ሙያን ተዋውቋል። ይህ ብርቱ ሰው የዕለቱ እንግዳችን ወጣት ዐቢይ ወልደሐና ነው። የሶሊና ሾፒንግ ሴንተር መሥራችና ባለቤትም ነው። የእንጨት ሥራ ሙያን ለመልመድና ለመሥራት የወሰነው እንዲህ እንደዛሬው ታዋቂ እንጨት ቤት እከፍታለሁ በሚል ሃሳብ አልነበረም።

ለመኖር ባደረገው ብርቱ ጥረት በእንጨት ቤቶች ዙሪያ ያገኘውን ሥራ ሁሉ ሲሠራ ቆይቷል። ሌላ ሥራ የለም የተባለ ያህል የእንጨት ሥራውን የሙጥኝ ብሎ ከአንዱ ቤት ሌላኛው ቤት፤ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ እየተዘዋወረ በእንጨት ሥራው ላይ ቆይቷል።

ዛሬ በተለይም በሶፋ ምርቶቹ ስመጥር ከሆኑ ሶፋ ቤቶች መካከል አንዱ የሆነው ሶሊና ሾፒንግ ሴንተርን ማቋቋም የቻለው ወጣት ዐቢይ፤ ትናንት በወጣትነት ሙቅ ልቡ ለሙያው ብዙ ዋጋ ከፍሏል። የገጠሙትን መሰናክሎች ሁሉ ግን በትዕግስት አልፏል። ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሰ በሠራባቸው 19 ሶፋ ቤቶች በአንዳቸውም ትችላለህ አልተባለም። ‹‹አትችልም›› ተብሎ ተባረረ እንጂ፤ በእዚህ ሁሉ የተነሳ ግን ተስፋ አልቆረጠም፤ ተዘዋውሮ በሠራባቸው አካባቢዎች ሁሉ ሙያውን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ድካሙ፣ ልፋቱ፣ ትጋቱና መውተርተሩም ሌባ የማይሰርቀውን የእጅ ሙያ አስታጠቀው።

ከዕለት ዕለት በሙያው ይበልጥ እየተሳበና ሙያውን እያፈቀረ የሄደው ዐቢይ፤ በሥራው ተቀባይነትን ከማግኘት ባለፈ የእንጨት ሥራ በተለይም የሶፋ ሥራ የነብሱ ጥሪ መሆኑን ማረጋገጥ እየቻለ መጣ። በተለያዩ አካባቢዎችና ቤቶች ተዟዙሮ ቢሠራም፣ ሥራ ብሎ የሚፈልገው ያንኑ የእንጨት ሥራ እንደነበር ያስታውሳል። በተዘዋወረባቸው የተለያዩ ክልሎችና አካባቢዎች በአጫጭር የጊዜ ቆይታ 19 ቤት ተቀጥሮ ሠርቷል።

ተስፋ ያልቆረጠው ወጣቱ ዐቢይ፤ አዲስ አበባ ሲመጣም ሌላ ሥራ አልተመኘም። እንጨት ቤቶችን እያሰሰ እንዲያሠሩት ተማጽኗል። በከተማዋ በሚገኙ ሶፋ ቤቶች በተለይም ፒያሳ አካባቢ የመሥራት አጋጣሚ ሲያገኝ እንደተለመደው ‹‹አትችልም›› ተብሏል።

እሱ ግን ‹‹ትዕግስት ፍሬዋ ጣፋጭ ነው›› እንዲሉ ሁሉንም በትዕግስትና በብዙ ጥረት አልፎ መቻሉን አስመስክሯል። ‹‹አትችልም›› ተብሎ ከተባረረበት ሶፋ ቤት መቻሉን በተግባር አረጋግጦ በድጋሚ ተቀጥሮ የመሥራት ዕድሉን ያገኘበት አጋጣሚም ነበር። ይህን አጋጣሚ ሲያስታውስ ‹‹ወቅቱ በሕይወት ጉዞዬ ማርሽ ቀያሪ ክስተት የተፈጠረበት ነበር›› በማለት ነው።

በወቅቱ የተለያዩ የሙያ ጓደኞችን ያፈራው ወጣት ዐቢይ፤ እሱን ጨምሮ አራት ጓደኛሞች ሆነው የሶፋ ሥራ ለመሥራት የተቀጠሩት ከዚህ ቀደም ተቀጥሮ ሲሠራ አትችልም ተብሎ የተሰናበተበት ሶፋ ቤት ነበር። ያም ቢሆን በራስ መተማመን ያዳበረ በመሆኑ ስጋት አልገባውም፤ መቻሉን ለማስመስከር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ከጥቂት ቆይታ በኋላ ጓደኞቹ ጥለው ሲሄዱ መቻሉን ያስመሰከረው ዐቢይ ግን፤ ቆይታውን አራዝሞ የተሰጠለትን ሙያ ዳር ለማድረስ ራዕይ ሰንቆ መሥራቱን ቀጠለ። ለራዕዩ መሳካትም በወቅቱ ሁለተኛ ዕድል ሰጥቶ ሲያሠራው የነበረው ሰው ትልቅ ድርሻ እንዳለው አጫውቶናል።

አሠሪው የሰጠውን ምክር መነሻ በማድረግ አንድ ሶፋ ሠርቶ ከሚያገኘው ገንዘብ ላይ የተወሰነውን በመቆጠብ ራዕዩን ለማሳካት ከፍተኛ ጉጉት ያሳየው ወጣት ዐቢይ፣ በሁለትና በሦስት መቶ ብር ቁጠባውን አጠናክሮ በመቀጠል ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ስምንት ሺ ብር መቆጠብ ቻለ፤ ተከራይቶ በሚኖርበት ግቢ ውስጥ በ15 ቀናት ውስጥ አንድ ሶፋ ሠርቶ 9500 ብር ሸጠ። እንዲህ እንዲህ እያለ ሥራውን ማሳደግ የቻለው ዐቢይ፤ ተቀጥሮ ከሚሠራበት ሶፋ ቤት ወጥቶ የግል ሥራውን ‹‹ሀ›› ብሎ በመጀመር ዛሬ በተለይም በሶፋ ምርቱ ዕውቅናን ማትረፍ ችሏል።

በ2002 ዓ.ም ፒያሳ አካባቢ 450 ብር በተከራየው ቤት ሶፋ ማምረት ሲጀምር ዛሬ ላይ ለመድረሱ እርግጠኛ ነበር። በወቅቱ ሁለት ሠራተኞችን ቀጥሮ ሥራውን ሌት ተቀን ሳይል በከፍተኛ ተነሳሽነት ሲሠራ ቆይቷል። ‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል›› እንዲሉ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ሰፋ ያለ ቦታ ተከራይቶ ሥራውን በማስፋት የሠራተኞቹን ቁጥርም ከሁለት ወደ ሦስት፣ አራት አምስት እያለ ዛሬ ሶሊና ሆም ሾፒንግን በማቋቋም ከ380 ለሚልቁ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።

በአሁኑ ወቅት ሙሉ የቤት ዕቃዎችን እያመረተ የሚገኘው ሶሊና ሆም ሾፒንግ፣ በዋናነት የሚታወቀው በሶፋ ምርቶቹ ነው። ከሶፋ በተጨማሪም ወንበሮች፣ የምግብ ጠረጴዛዎች፣ አልጋዎች፣ ቁምሳጥኖችና የቴሌቪዥን ማስቀመጫዎችን ያመርታል። ሌሎች ሲኒ፣ ብርጭቆ፣ ሹካ፣ ማንኪያ፣ መመገቢያ ሳህኖችን ጨምሮ የተለያዩ ደረጃቸውን የጠበቁ የቤት ዕቃዎችን እንዲሁም ኤሌክትሮኒክስ የሆኑ የቤት ውስጥ መገልገያዎችን ደግሞ ከአውሮፓ በማስመጣት ለገበያ ያቀርባል።

ሶሊና ሆም ሾፒንግ የተቋቋመበትን ዓላማ እያሳካ የመጣ ድርጅት ስለመሆኑ ያነሳው ዐቢይ፤ ድርጅቱ መጠነኛ በሆነ ትርፍ ብዙ ማምረትና በስፋት ገበያ ውስጥ መግባት የሚል ዓላማ ይዞ የተነሳ ስለመሆኑ ሲያስረዳ፤ ብዙ ሰዎች ሶፋ ይፈልጋሉ ነገር ግን ዋጋው ከአቅማቸው በላይ ሲሆን ይስተዋላል ይላል። ስለዚህ ሁሉም ሰው በአቅሙ መግዛት እንዲችል ተመጣጣኝ በሆነ ትርፍ ብዙ እያመረተ ገበያ ውስጥ በመግባት አብዛኛው ማኅበረሰብ ጋር መድረስ እንደቻለ ተናግሯል።

ሶፋ ለመሥራት አብዛኛው ጥሬ ዕቃ በሀገር ውስጥ የሚገኝ እንደመሆኑ ጨርቁን ጨምሮ ጥቃቅን የሆኑ ማስጌጫዎች ብቻ ከውጭ የሚመጡ መሆናቸውን የገለጸው ዐቢይ፤ ሶፋን ጨምሮ ቁምሳጥን፣ አልጋና ሌሎችም የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን ከውጭ አጓጉዞ ማምጣት በጣም አሳፋሪ እንደሆነ ነው የጠቀሰው። ሀገር ውስጥ በተሻለ ጥራትና ውበት በተመጣጣኝ ዋጋ መሥራት እየተቻለ ከውጭ ማስመጣቱ ተገቢ አይደለም የሚል ጽኑ ዕምነትም አለው። ሥራው ማንም ሰው ፍላጎት ካለው ሥልጠና ወስዶ መሥራት የሚችለው ቀላል ሥራ እንደሆነም አስረድቷል።

አሁን ላይ መንግሥት እየወሰደ ያለው እርምጃ አበረታች ነው። የሚለው ዐቢይ፤ በተለይም የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማበረታታት ተኪ ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች ነው ብሏል። ሀገር ውስጥ የማይገኙ በጣም ጥቃቅን የሆኑ ግብዓቶችን ብቻ ከውጭ በማምጣት ሁሉንም በሀገር ውስጥ ማምረት እንደሚቻል ያስረዳው ዐቢይ፤ ለዚህም መንግሥት የያዘው አቋም ተጠናክሮ ሊቀጥልና የሀገር ውስጥ አምራቾች ሊበረታቱ ይገባል ባይ ነው።

አንድ ሰው ሶፋ፣ አልጋና ቁምሳጥን ሲገዛ ለረጅም ጊዜ ሊጠቀምበት ነው የሚለው ዐቢይ፤ በሀገር ውስጥ የሚመረቱት ምርቶችም ጠንካራና ብዙ ጊዜ የሚያገለግሉ እንደሆኑ ጠቅሶ፤ በሶሊና ሆም ሾፒንግ የሚመረቱ ምርቶችም እጅግ ጠንካራ፣ ጥራትን ከውበት ያጣመሩ ከመሆናቸው ባሻገር ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው እንደሆኑም ተናግሯል። እሱ እንደሚለው በሶሊና ሆም ሾፒንግ የሚመረት የሶፋ ዋጋ ትንሹ 40 ሺ ብር ሲሆን፤ ትልቁ 170 ሺ ብር ነው።

ቃሊቲ ላይ በሦስት ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ምርቶቹን እያመረተ ያለው ሶሊና ሆም ሾፒንግ ለድርጅቱ ማስፋፊያ መናገሻ አካባቢ ከመንግሥት ባገኘው ተጨማሪ 10 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ግንባታ ጀምሯል። ይህም በቀጣይ ሥራውን እያስፋፋ በመሄድ በተለይም ጥራት ያላቸውንና ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶቹን ከሀገር ውስጥ ባለፈ ለአፍሪካ ሀገራት ኤክስፖርት ለማድረግ ያለመውን ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችለው መሆኑን ተናግሯል። ፋብሪካው ከአንድ ዓመት በኋላ ግንባታው ተጠናቅቆ ወደ ምርት ሲገባ ከፈርኒቸር ምርቶቹ በተጨማሪ ስፖንጅን ጨምሮ የተለያዩ ግብዓችን በማምረት ለገበያ ያቀርባል። ይህም ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነ አመላክቷል።

ሙያውን በተመለከተ ማንም ፍላጎት ያለው ሰው መሥራት የሚችለው ሥራ እንደሆነ ዕምነት ያለው ወጣት ዐቢይ፤ ‹‹ማንም የማይችል ሰው የለም። እኔ አትችልም ተብዬ 19 ጊዜ እንደተባረርኩት ሰዎች ከሥራው እንዲርቁ አልፈልግም። ሙያው የሌለው ማንኛውም ሰው ጥሩ ሥነ-ምግባር፣ የሥራ ፍቅርና ፍላጎት ካለው መማር ማወቅና መሥራት ይችላል›› በማለት ሥራውን ፈልጎ ወደ ሶሊና ሶፋ ለሚመጣ ማንኛውም ሰው ሙያዊ ሥልጠና ከመስጠት ጀምሮ ቀጥሮ ለማሠራት በራቸው ክፍት እንደሆነ ገልጿል።

በእንጨት ሥራ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ብዙ የደከመው ወጣት ዐቢይ፤ በትዕግስትና በበዛ ጥንካሬው አለመቻልን በመቻል ድል ነስቶ ዛሬ ስመ ጥር የቤት መገልገያ እቃዎች/ ፈርኒቸሮች/ ማምረቻ ባለቤት መሆን ችሏል። ያም ቢሆን ዐቢይ ዛሬም እረፍት የለውም። ለሥራው ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ በየጊዜው አዳዲስ ዲዛይኖችን በመፍጠር በተለይም የሶፋ ሥራን በተለየ መንገድ ለመሥራት ሲጠበብ ይታያል።

አዳዲስ ፈጠራዎች ያስደስቱኛል የሚለው ዐቢይ፤ ዓመታት ሲያስብ የነበረውን በዓይነቱ ልዩ የሆነ ትልቅ የሶፋ ቤት ከሙያ አጋሮቹ ጋር ሠርቷል። ይህ ትልቁ የሶፋ ቤትም በአፍሪካ ድንቃድንቅ ተመዝግቦ የዕውቅና ሰርተፊኬት አግኝቷል።

በትልቅ ሶፋ ቅርጽ የተሠራው ትልቁ የሶፋ ቤት ሶፋን ጨምሮ በውስጡ አንድ ቤት ማሟላት የሚገባቸውን ቁሳቁስ በሙሉ ጥንቅቅ አድርጎ ይዟል። የውሃና የኤሌክትሪክ መስመሮችም እንዲሁ ተዘርግተውለታል። ሶፋ ቤቱ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስጦታ የተበረከተ ሲሆን፤ ከተማ አስተዳደሩም ትልቁ የሶፋ ቤት የሚቀመጥበትን ቦታ ፈቅዷል። ቦታው ፒያሳ ቸርቸር አካባቢ ሲሆን ድርጅቱ ቦታውን አፅድቶ ሙሉ መስታወት በመስታወት የሆነ ቤት ሠርቶ ትልቁን የሶፋ ቤት ለሕዝብ ዕይታ ክፍት ለማድረግ እየተዘጋጀ ይገኛል። በቅርቡ ለሕዝብ ዕይታ ክፍት የሚሆነው ትልቁ የሶፋ ቤት መስታወት ቤቱን ጨምሮ አምስት ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበትና 150 ሠራተኞች የተሳተፉበት ድንቅ ሥራ ነው።

ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም ለአካባቢው ማኅበረሰብ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል። ድርጅቱ በሚገኝበት ጎተራ መስቀል ፍላወር አካባቢ ለመኖሪያ ምቹ ያልሆኑና የፈራረሱ የአራት አባወራዎችን ቤቶች አድሶና የቤት ዕቃ አሟልቶ አስረክቧል።

ከዚህ ባለፈም በበዓላት ወቅት ለአቅመ ደካሞች ማዕድ በማጋራት ድጋፍ ያደርጋል። መንግሥት ለሚያደርገው ማንኛውም ጥሪም እንዲሁ ምላሽ በመስጠት የአጋርነቱን እያረጋገጠ መሆኑን ገልጿል። በዚህ ተሳትፎውም ከከተማ አስተዳደሩ ዕውቅናን በማግኘት የዋንጫ ተሸላሚ መሆኑንም ነው ያመለከተው።

ፍሬሕይወት አወቀ

 አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You