የትውልድ አደራ በኢትዮጵያዊነት በትላንት በዛሬና በነገ የሚመነዘር የታሪክ ውርርስ ነው። ውርርሱ ከአንድ ወገን ብቻ የሆነ ሳይሆን ከእርስ በርስ መሰጣጣት፣ ከእርስ በርስ መተሳሰብ፣ ከእርስ በርስ መከባበር፣ ከእርስ በርስ መደማመጥ እና ከብዙሀነት ውስጥ የሚመዘዝ ሀገር ሰሪ፣ ትውልድ መሪ ቡዳኔ ነው። ይሄ ቡዳኔ በኢትዮጵያ ላይ በሶስት ትውልድ በኩል ተንጸባርቆ እናገኘዋለን። የመጀመሪያ የአድዋ ትውልድ ነው። አባቶቻችን የነበሩበት ትላንት ብለን የምንጠራው የአብሮነት ቡዳኔ።
ይሄ ቡዳኔ የዛሬውን ትውልድ ባለክብር ያደረገ፣ የነጻነትን ዘውድ ያስደፋ ከብዙዎች ብርሀንን የተፋ ቡዳኔ ነው። እኔን ከሌላው ሌላውን ከእኔ ያስተሳሰረ ፍቅር የዘነበበት፣ ኢትዮጵያዊነት ያበበበት ነበር። በሀሳባችን በኩል፣ በተግባራችን በኩል እያንዳንዳችን ስለሀገራችን አደራ አለብን። አደራው ሁሉም ለማንም የሚሰጠው የፍቅርና የመተሳሰብ አደራ ነው። ከአባቶቻችን በተቀበልን የእውነት እና የአብሮነት አደራ ወደዛሬ እንደመጣን ወደነገ የምንሄድበትንም በጎ መንገድ መጥረግ ግዴታችን ይሆናል።
የትዝታ ገሳ ለብሰን፣ በወፍ በረር አድዋን ስንቃኘው ..የካቲት 23 1888 የዛሬ መቶ ሀያ ስምንት ዓመት የተከሰተን የጥቁር አንበሶችን የጀግንነት ድል እናገኛለን። አግኝተንም አንቆምም ለምን? እንዴት? የሚሉ መጠይቆችን እንጠይቃለን። ጠይቀንም መዳረሻውን እኔና እናተን ያደረገ መልስ እናገኛለን። ሁለት በታሪክ፣ በባህል፣ በስልጣኔ፣ በአይዶሎጂ የተራራቁ ሀገራት ኢትዮጵያና ጣሊያን አንዱ በራስ ወዳድነት አንዱ ደግሞ ለነጻነቱ በጦርነት አውድማ ተገናኝተዋል።
ከመዲናችን አዲስ አበባ በስተ ሰሜን አቅጣጫ በ1065 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አድዋ ላይ የነጻነት ሰንደቃችንን ሰቀልን። ስለሀገርና ርስት፣ ስለነጻነትና እኩልነት፣ ስለሰውነትና ፍትህ የተከፈለ ይሄ ተቧድኖ በዛኛው ዘመን ለእኛ የተከፈለ የፍቅር ቡዳኔ ነው። ትላንት ብለን ዛሬን ስንቃኝ፣ ዛሬ ብለን ወደነገ ስናገድም አድዋ ፋና ወጊያችን ነው። አድዋ መቼት የለውም..መቼና የት የለውም። ጦርነቱ አድዋ ላይ ተጀምሮ ቢያበቃም የመላው ሕዝብ ጉዳይ ነበር። መቼ የሌለው..ከየት እስከየት የማይከነዳ፣ ሽንጠረጅም እንዥርግ ብቸኛ ታሪካችን ነው ።
ቀጣዩ ቡዳኔአችን የአባይ ግድባችንን ይዘክራል። ከአድዋ ተነስተን ያረፍንበት የትስስብና የውዳዴ የብዙሀነትም አሻራችን ነው። ቁጭት ያበቃበት የተስፋ ብርሀን የፈነጠቀበት የድል አድራጊነት አርማችን ሆኖ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ተሰቅሏል። የዛሬ አስራ ሶስት ዓመት በጉባ ምድር መልህቁን ሲጥል እኛን አምኖ፣ በእኛ ታብዮ እንደሆነ ይታወቃል። እኛም ሳናሳፍረው እንሆ ማብቂያው ላይ አደረስነው።
በአሁኑ ሰዓት አጠቃላይ ሂደቱም 95 ከመቶ የደረሰ ሲሆን ሰባት ወራትን በሚሸፍን ሂደት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚውል ይጠበቃል። የግድቡ የሲቪል ስራ 99% የተጠናቀቀ ሲሆን የኤሌክትሮ ሜካኒካል የተርባይንና ጄኔሬተር ተከላ 78%፣ የግድቡ የውሀ ማስተላለፊያ አሸንዳ ከ85 ከመቶ በላይ መድረሳቸው አጠቃላይ ሂደቱን 95 ከመቶ አድርሰውታል። ግድቡ ሲጠናቀቅ በቀን እስከ 6 ሺህ ሜጋ ዋት፣ በዓመት ደግሞ 15 ሺህ 130 ጊጋ ዋት ኃይል እንደሚያመነጭ የሚታወቅ ሲሆን ይሄ የኃይል አሀዝ እንደሀገር፣ እንደሕዝብ፣ እንደትውልድ የኢኮኖሚ ሀይላችንንና የተሰሚነት ሚናችንን እንደሚጨምረው ሳይታለም የተፈታ ነው።
አፍንጫችን ስር በቅሎ በእልህ አክ እንትፍ ስንልበት፣ ጥርሳችንን ነክሰን ስናጉረመርምበት የነበረው ዘመን፣ 86 ከመቶ ያህሉን እያዋጣን ለባዕድ ሀገራት ጸጋ መሆናችን አብቅቶ በሕዝብ በሚሰጡ እጆች ለወግ ማዕረግ በቅተናል። እርግማንና ወቀሳችን ወደ ውዳሴ ተቀይሮ አባይ ክብራችን ነህ ወደ ማለት ተመልሰናል። ይሄ ታሪካዊ አሻራ በዚህ ትውልድ ላይ ሲደገም መነሻው አብሮነት ነው። አድዋን በፈጠሩ ሕብረብሄራዊ ልቦች አሻራችንን ስናስቀምጥ በምንም ሳይሆን በጋራ በርትተን ነው። ተሳስበንና ተጋግዘን፣ መክረንና ተወያይተን፣ አዋጥተንና ከመቀነታችን ላይ ፈትተን ያቆምነው የብዙሀነት ምስላችን ነው።
በዚህ ረድፍ ስር የሚነሳው ሌላኛው የተስፋችን ሰንደቅ የወደብ ባለቤትነት ጉዟችን ነው። ተፈጥሮና ታሪክ ካወራረሱን፣ ካዋሃዱንና ካቆራኙን ለስልጣኔአችን መሰረት ከሆነ ወደባችን ተቆራርጠን በተፈጥሮአችን ላይ ባይተዋር ሆነን ኖረናል። የሰው የማይነካ የራሱንም የማያስነካው ትውልድ ወደመነሻው ሊሄድ የወደብ አጋሩን ጥያቄን ይዞ ተነስቷል። ይሄኛው የትውልድ አሻራ ለጀመርናቸውና ልንጀምራቸው ላሰብናቸው የስልጣኔ ርምጃዎቻችን መንገድ የሚጠርግ፣ ያለንን ሰጥተን የሌለንን የምንቀበልበት፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ቁርኝትም የምንፈጥርበት ነው።
ሀገራችን በዓለም ላይ ካሉ 44 ወደብ አልባ ሀገራት መሀል አንዷን ነች። በአፍሪካም በ16 ከሚቆጠሩ የባህር በር ከሌላቸው ሀገራት ውስጥ ትመደባለች። ከመቶ ሚሊዮን የዘለለ የሕዝብ ቁጥር ኖሮት ወደብ አልባ የሆነ ሀገር በታሪክ የለም። ሀገራችን ብቻዋን የጠቅላላውን የወደብ አልባ ሀገር 1 ሶስተኛ የምትሸፍን ናት። የሕዝብ ቁጥር ፍሰቱ፣ የፍላጎት መናሩ፣ የኢኮኖሚ ግስጋሴው የባሕር በር ጥያቄው ተገቢ መሆኑን ከማመላከቱም በላይ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያስገድድም ጭምር ነው።
የባህር በር በአጭር ቋንቋ ቢገለጽ ‹የእድገት መሰረት› የሚል ይሆናል። ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዲፕሎማሲያዊም ፋይዳው እንዳለ ሆኖ እያደገ ለመጣው የሕዝብ ፍላጎትና ኢኮኖሚ እንደማስተንፈሻ ቦይነትም የሚያገለግል ነው። የባሕር በር ማጣት በአንድ ሀገር ላይ በኃይል መጥቶ መሄጃ እንደአጣ ጎርፍ ነው። ኢኮኖሚያችን፣ የሕዝብ ቁጥራችን፣ ፍላጎቶቻችን በኃይል መጥተዋል ከሌላው ዓለም ጋር በነጻነት የምንነካካበት የራስ መተላለፊያ ያስፈልገናል።
ከቀይ ባህር ጋር የነበረንን ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ ቁርኝት እንድንበጥስ መንገድ ከጠረጉ ውሎች ውስጥ ዋነኞቹ የ1900፣ የ1902 እና የ1908ቱን የቀኝ ገዢዎች ውልን ማስታወስ እንችላለን። እነዚያ ውሎች በኃይልና በአስገዳጅነት የተፈጸሙ የአንድ ወገን የበላይነት የተንጸባረቀባቸው ውሎች ስለመሆናቸው ብዙዎች ምስክርነታቸውን ከመስጠት ባለፈ በሉአላዊ ሀገር ላይ የተፈጸመ ታሪካዊ ውንብድናም እንደሆነ የሚናገሩ ናቸው።
ያለ ቅኝ ተገዢዎች ፍቃድና ይሁንታ በመፈጸማቸው ውሎቹ በተባበሩት መንግስታት ማቋቋሚያ ቻርተር ላይ ተግባራዊነት እንደማይኖራቸው በግልጽ ሰፍሯል። ዓለም አቀፉ ሕግ ከፍትህና ከሚዛናዊነት አንጻር የሁለት ወገኖችን ፍቃድና ይሁንታ በማጤን መልስ የሚሰጥ እንደሆነ ይታወቃል። ኢትዮጵያና ጣሊያን የተፈራረሙት ውል እንዲሁም ደግሞ ኤርትራን ወክላ ጣሊያን የፈረመችው ስምምነት የወቅቱን የኢትዮጵያ ትክክለኛ ፍላጎት ያላማከለ፣ እንደ እንግሊዝና ፈረንሳይ ባሉ ሀገራት ጣልቃ ገብነት የተፈረመ እንደነበር ማስታወስ አስፈላጊም ጭምር ነው።
ዓለም አቀፉ ሕግ የባህር በር የማግኘትም ሆነ የመጠቀምን ነጻ መብት በሀገራት መካከል ይፈቅዳል። ከዚህ አኳያ ያነሳነው ጥያቄ ስህተት እንዳልሆነ እንገነዘባለን። ሌላ መጥቀስ ካስፈለገ ደግሞ በአንድ ዘመን ላይ ያለ የታሪክና የስልጣኔ ፈር ቀዳጅ የሆነን ይዞታ ነው እየጠየቅን ያለነው። በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የባህር በር ጉዳይ የትውልዱ ቀጣይ የቤት ስራው እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው። ታሪክ መስራት የለመደው ትውልድ በአድዋ ጀምሮ በአባይ ደግሞ በቀይ ባህር ላይ ሊሰልስ አሀዱ ብሏል።
የባህር በር የአንድ ሀገርን 20 ከመቶ የኢኮኖሚ አሀዝ ይይዛል። ላለፉት ሰላሳና ከዛ በላይ ዓመታት እንደሀገር ይሄን እድል ሳንጠቀም ቀርተናል። የባህር በር ማግኘት የሕዝብን ጥያቄ፣ የኢኮኖሚ ግስጋሴውን፣ የደህንነት ጉዳይን፣ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ማሳለጥ ነው። አሁን ባለው ሀገራዊ ንቃት የባህር በር ማግኘት በኢኮኖሚ ግንባታ ላይ የላቀ ዋጋ ያለው ነው። የባህር መተላለፊያ በሁሉም ዘርፍ ላይ አሉታዊና አዎንታዊ ተጽዕኖ ያለው መሆኑ እዚህ ጋ ሊነሳ የሚገባው ሌላው ጉዳይ ነው። የባህር በር ተጠቃሚ የሆኑ ሀገራት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ከማዳበር ባለፈ የደህንነት ዋስትናቸውንም ያረጋገጡ በተጽዕኖ ፈጣሪነትም ከፊት የሚሰለፉ ሀገራት ናቸው።
በተቃራኒው የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በኢኮኖሚና በፖለቲካቸው ላይ ስጋትና ጣልቃ ገብነትን ከመፍጠሩም በላይ የሉአላዊነት ጉዳይን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነገር ነው። ሉአላዊነት ለአንድ ሀገር፣ ለአንድ ሕዝብ፣ ለአንድ መንግስት የምንም ነገር መሰረት ነው። ይሄ ትልቅ ነገር ከወደብ ተጠቃሚ ሀገራት ይልቅ ወደብ በሌላቸው ሀገራት ላይ ስጋቱ ጎልቶ የሚታይ ነው። እኚህን ከመሳሰሉት ምክንያቶች በመነሳት የባህር በር ጥያቄአችን ተገቢና ወቅቱን ያማከለ እንዲሁም ደግሞ የማደግና የመለወጥ መሻታችንን ያማከለ ጉዳይ ነው።
ማጠቃለያ…
ኢትዮጵያ ትላንት ዛሬና ነገ በሚል በሶስት ትውልዶች ላይ ተንጠራርቼ ያስቃኘኋችሁ የጋራ አሻራዎቻችን በኢትዮጵያ አሁናዊ ሁናቴ ላይ ደማቅ ብርሀንን የፈነጠቁ ስለመሆናቸው ተጠራጣሪ አይኖርም። በአድዋ የነጻነት፣ የእኩልነት፣ የፍትሀዊነት እና የሰውነት ሚዛኖች ተብለናል። ይሄ ስም ከእኛ ውጪ በየትም የለም። ይሄ ክብር ከኢትዮጵያዊነት ጉያ ውስጥ ካልሆነ በየትም አልታቀፈም። ዛሬም ድረስ ስለዚህ ስምና ስለዚህ ክብር ፊተኞች ነን።
በአባይ ግድብ በኩል ሌላ ታላቅ ድልን እየተጎናጸፍን እንገኛለን። በአይችሉም ውስጥ ችለን፣ በአይሳካላቸውም ውስጥ አሳክተን፣ በአይሆንላቸውም ውስጥ ተያይዘን ማንነታችንን ያሳየንበት የዚህ ትውልድ የላብ አሻራ ነው። ትውል በጋራ አስቦ በጋራ የሚጽፈው የብዙሀነት ታሪክ እንዳለው ሰነዶች ይናገራሉ። ..ልክ እንደአድዋ ሁሉ የሕዳሴ ግድባችንም የብዙሀነታችን ማሳያ ምልክት ነው።
ሌላው የከፍታዎቻችንን ማማ ካረጋገጡልን ሁነቶች ውስጥ አንዱ የባሕር በር ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ ወደመነሻዋ እየተንደረደረች እንደሆነች በማመን ውስጥ እንድንቆም ካጸኑን ውስጥም ነው። ታሪክና ስልጣኔ፣ ዘመናዊነትና ኢትዮጵያዊነት ያበቡበት ጥንተ ጠዋታችን በከሰዓት እና በአመሻሻችን ላይ መጥቶ ዳግም ታሪክ እንድንሰራ፣ ዳግም እንድንዋሃድ፣ ዳግም እንድንበረታ ኃይል እያበጁልን ነው።
ስንነሳ ከማንም ቀድመን፣ ከማንም በፊት ነበር። በእኛ ፊተኝነት ውስጥ ሀገርና ሕዝብ የሆኑ ብዙ ናቸው። አሁን ላይ ኋላ ቀርተን ኋላ ቀር የሚል ስምን ከመጎናጸፋችን በላይ የድህነትና የአለመርባት ማሳያዎች ሆነናል። ለምን የሚሉ በርካታ ጥያቄዎች ቢኖሩም ወደመነሻችን እየወሰዱን ባሉ የጋራ አሻራዎቻችን ግን ተስፋ ወደማድረግ ተመልሰናል።
አድዋና ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከቀይ ባሕር እሳቤ ጋር ተጣምረው የለውጥና የተሀድሶ ተራማጅ አስተሳሰቦቻችን ወደ ሕዝባዊነት ቀይረው መድረሻዎቻችንን እያመላከቱን ይገኛሉ። በተስፋና በብርታትም እየሞሉን ይገኛሉ። መነሻችን ሰውነት መድረሻችን ኢትዮጵያዊነት ነው። ከዚህ አውድ ሳንወጣ ልዩነቶቻችንን በመሻራ በጋራ ታሪኮቻችን ፊት ነገን መልካም ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ ነን።
እንደ እኔነት ያሉ የተለማመድናቸውን አጉል ልምዶች ያለንን ከመቀማት ባለፈ እንዳልጠቀሙንና ከድህነት እንዳላወጡን ከገባን ሰንብቷል። ያጣነው መውጫ ቀዳዳ ነው። የራቀን ወደብዙሀነት የሚወስድ ፖለቲካና ፖለቲከኛ ነው። የጋራ ታሪኮቻችን ይሄን መንገድ በመክፈት የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ወንድማማችነታችንን እያስመሰከሩልን ይገኛሉ።
በጀመርነው የብዙሀነት መንገድ ተጉዘን ጥንተ ጠዋታችን ላይ መድረስ፣ ብሔርተኝነትን ሽረን ኢትዮጵያዊነትን ማጠንከር፣ በጋራና በአብሮነት ድህነትን ከስሬ መንግሎ መጣል፣ ትውልድ በዘር ሳይሆን በሰውነት፣ በእኔነት ሳይሆን በብዙሀነት፣ በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር ወደነገ እንዲሄድ ማበረታት የእኔ የእናንተ የሁላችን ግዴታ መሆኑን በማሳሰብ ላብቃ።
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2016 ዓ.ም