
ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ ተቋሙ አገልግሎቱን እንዲያሻሻል አሳስቧል
አዲስ አበባ፡– የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የሚሰጠው አገልግሎት የተንዛዛና ተገልጋዩን ያላከበረ በመሆኑ መማረራቸውን ተገልጋዮች ገለጹ፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ አገልግሎት አሰጣጡ ያልዘመነና መሻሻል ያለበት መሆኑን በምልከታው ወቅት አስታውቋል፡፡ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው፤ በሪፎርም ሥራ 11 አጀንዳዎችን ቀርጾ እየሠራ መሆኑንና ችግሮችን ከመቅረፍ አኳያም የባለድርሻ አካላት ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ በተቋሙ በመገኘት ድንገተኛ የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሪፖርተሮችም በቦታው በመገኘት የተገልጋዮችን አስተያየት ጠይቀዋል።
በዕለቱ በፓስፖርት እድሳት ክፍል አገልግሎት ለማግኘት ከመቀሌ ከተማ የመጡት አቶ ጣዕመ ኃይሉ ከለሊቱ 11 ሰዓት በተቋሙ ተገኝተው ቢሰለፉም እስከ ረፋዱ 5 ሰዓት ድረስ አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ ይገልጻሉ። አገልግሎት ፈላጊውና አገልግሎት አሰጣጡ የተጣጣመ እንዳልሆነ የሚናገሩት ተገልጋዩ፤ አገልግሎት የሚሰጡት ሠራተኞች ጥቂት በመሆናቸው ለአላስፈላጊ እንግልት እየተዳረግን ነው ይላሉ።
የዚሁ ክፍል ሌላኛው ተገልጋይ የሆኑት አቶ አበበ በበኩላቸው፤ ፓስፖርት ለማደስ ከሁለት ቀን በፊት በቀጠሯቸው ቢገኙም ወረፋ ሳይደርሳቸው ቀርቶ በድጋሚ በዕለቱ ከለሊቱ 10 ሰዓት መምጣታቸውን ይናገራሉ። በርካታ ተገልጋዮች ለሰዓታት ወረፋ ቢጠብቁም አገልግሎት አሰጣጡ አዝጋሚ በመሆኑ አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸውን ይናገራሉ።
በተቋሙ ትክክለኛ መረጃ የሚሰጥ ያለመኖር፣መጸዳጃ ቤቱ ለበሽታ የሚዳርግ መሆኑ፣ጥሩ መቀመጫ እና ማረፊያ ያለመኖሩ በተቋሙ የተመለከቷቸው ችግሮች መሆናቸውን የሚገልጹት አቶ አበበ፤ ከዚህም በላይ ደግሞ በሰልፍ አስከባሪዎች ተገልጋዮች የሚደበደቡበት ሁኔታ በተቋሙ ያለውን የሥነ ምግባር ችግር ምን ላይ እንደደረሰ ማሳያ መሆኑን በምሬት ይናገራሉ።
በአሻራ ክፍል አገልግሎት ለማግኘት እየተጠባበቁ የነበሩት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ተገልጋይ እንደሚሉት ደግሞ፤ በተቋሙ አገልግሎት ፈልጎ የመጣ ሰው ክብሩን ያልጠበቀ መስተንግዶ እየተሰጠው ነው። ተገልጋይ ዜጋ በመሆኑ አላስፈላጊ “መመነጫጨቅ” ሊደርስበት አይገባምም ይላሉ።
አገልግሎት የሚሰጡት ሠራተኞች ባጅ ባለማድረጋቸው መብት ለመጠየቅም አይመችም የሚሉት እኚሁ ተገልጋይ፤ ባለጉዳይ ተራ የሚጠብቅበት ዲጂታል መሳሪያ የማይሠራ በመሆኑ ተቋሙ ተገልጋይን ወረፋ የሚያስጠብቅበት መንገድ ኋላቀር መሆኑን ይናገራሉ።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ በምልከታቸው አገልግሎቱ ከዚህ በፊት ይሰጥ ከነበረበት መንገድ አሁን መሻሻሎች መኖራቸውንና ተቋሙን ለማዘመን ጥረቶች መደረጋቸውን ገልጸው፤ አሁንም አገልግሎት አሰጣጡ ያልዘመነና መሻሻል ያለበት ነው ይላሉ።
አሁን ተቋሙ ያለበት ቦታ በጣም የቆየ በመሆኑ ቴክኖሎጂ በተገቢው ጥቅም ላይ ለማዋል አስቸጋሪ በመሆኑ ተገልጋዩን የሚመጥን ሰፊ ቦታ ተፈልጎ አገልግሎት መስጠት እንዳለበትም የገለጹት ወይዘሮ እጸገነት፤ ተቋሙ እጅግ በርካታ አገልግሎት ፈላጊ ያለበት እንደመሆኑ ተገልጋዮችን በአግባቡ የሚያስተናግድበት የቦታ ጥበት ችግር እንዳለበት መመልከታቸውንም ይገልጻሉ።
በተቋሙ ከፍተኛ ሰልፍ፣ ግፊያ እና መጨናነቅ መኖሩን መመልከታቸውን የሚገልጹት ወይዘሮ እጸገነት፤ ይህንን ማስተካከል የሚቻለው በአዲስ አበባ እና በክልሎች በርካታ ቅርንጫፎችን በመክፈት አገልግሎቱን በማስፋት እንደሆነ ይናገራሉ።
ትክክለኛ ፓስፖርት ማግኘት የሚቻለው በአዲስ አበባ ብቻ እንደሆነ ተደርጎ በአንዳንድ አካላት የሚሰራጨውን መረጃም ተጋግዞ ማረም እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ። ደላሎች ተገልጋዮችን መግቢያ በር አካባቢ “ ፓስፖርት ቶሎ ይደርስላችኋል” በማለት ኅብረተሰቡን እንደሚበዘብዙ በምልከታው መረዳታቸውን የሚገልጹት ሰብሳቢዋ፤ ኅብረተሰቡ ከሕገወጥ ደላሎች እራሱን እንዲጠብቅም ይመክራሉ።
ግንዛቤ ለመፍጠር ተቋሙ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና አስፈላጊ ነው ያሉት ሰብሳቢዋ፤ 90ሺ ፓስፖርት ታትሞ ሳይወሰድ መቀመጡንም መመልከታቸውን ገልጸዋል፤ ኅብረተሰቡ በትክክል መረጃ አግኝቶ ፓስፖርቱ የሚወሰድበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበትም ጠቁመዋል። በተቋሙ የሠራተኛ ቁጥር መጨመር እንዳለበትና ችግሮችን ለማረምም ተቋሙን ዲጂታላይዝ በማድረግ ማዘመን አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5 ቀን 2016 ዓ.ም