ለማዕድን ኢንዱስትሪዎች ጥራትና ምርታማነት

ሀገሪቱ በማዕድን ሀብት ባለጸጋ ናት፤ የወርቅ፣ የጌጣጌጥ፣ የድንጋይ ከሰል፣ የእምነበረድ፣ የብረት፣ የተፈጥሮ ጋዝ፣ የሊቲየም፣ ወዘተ ማዕድናት በስፋት እንደሚገኙባት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይሁንና ባላት የማዕድን ሀብት ልክ ግን ተጠቃሚ አልሆነችም፤ ለዚህም በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል የማዕድን ሀብቶቹ በአይነትም ሆነ በክምችት መጠን በትክክል አለመታወቃቸው፣ የታወቁትን ማዕድናትንም ቢሆን ከባህላዊ መንገድ በዘለለ በዘመናዊ መንገድ ወደ ማልማት በስፋት አለመገባቱ የሚሉት ይገኙበታል።

እነዚህን የማዕድን ሀብቶች ለመለየትና የክምችት መጠናቸውን ለማወቅ በየጊዜው ጥናቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል፤ እየተካሄዱም ናቸው። እንዲያም ሆኖ ግን በጥናት የተለዩት ከአጠቃላይ የማዕድን ሀብቶቹ 20 በመቶው ብቻ መሆናቸውን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።

ይህ እምቅ የማዕድን አቅም ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል ታምኖበት እየተሰራ ነው። መንግሥት የዚህን ዘርፍ ፋይዳ በሚገባ በመገንዘብ በሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያው የአስር ዓመት መሪ እቅድ የምጣኔ ሀብቱ ምሰሶዎች በሚል ከያዛቸው አምስት ዘርፎች መካከል የማዕድን ዘርፉን አንዱ አድርጎት እየሰራ ይገኛል።

በዘርፉ በኢንዱስትሪና በኮንስትራክሽን ዘርፉ ግብዓት ማዕድናት፣ በወርቅ ማዕድንና በመሳሰሉት ላይ የማዕድን ልየታና ክምችት መጠንን ለማወቅ የሚያስችሉ የጥናትና ልማት ስራዎች በስፋት እየተካሄዱ ናቸው። የጥናትና ምርምር ስራዎቹ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር እየተካሄዱ ሲሆን፣ ኩባንያዎች በራሳቸው የሚያካሂዷቸው የጥናት ስራዎችም እንዳሉ ይታወቃል።

በዩኒቨርሲቲዎች እየተካሄዱ ከሚገኙ የጥናትና ምርምር ስራዎች የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ያካሄደው ጥናት ይጠቀሳል። በቅርቡ በዚሁ ጋዜጣ የወጣ ዘገባ እንዳመለከተው፤ ዩኒቨርሲቲው በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በደቡብና በደቡብ ምዕራብ የሃገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ማዕድናት ላይ ዘርፈ ብዙ ምርምሮችን እያካሄደ ይገኛል። ለሃገሪቱ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የጀርባ አጥንት የሆነው የብረት ማዕድን በክልሉ በስፋት መኖሩን አጥንቶ ይፋ አርጓል።

መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ በድንጋይ ከሰል ክምችት በኩልም እንዲሁ እንደ ሀገር ያለው ክምችት ተለይቷል። ለኢንዱስትሪዎቿ ኃይል አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ የሚያስፈልጋትና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም በዓመት ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ስታወጣበት የኖረችው ሀገሪቱ ከግማሽ ቢሊዮን ቶን በላይ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ክምችት እንዳላትም ይገለጻል።

ይህን የማዕድን ክምችት በጥናት መለየት ብቻም ሳይሆን ወደ ማልማትም ተገብቷል። ባለፈው በጀት ዓመት ከውጭ ይመጣ የነበረውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የታቻለበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል። ልማቱም በማህበራት በተደራጁ የማኅበረሰብ ክፍሎችና በኢንዱስትሪዎች እየተካሄደ ይገኛል። በማዕድኑ ምርት ጥራት ላይ የነበረውን የጥራት ችግር ለመፍታትም የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካዎች በተለያዩ አካባቢዎች እየተተከሉ ናቸው።

ሀገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የወርቅ ማዕድን ክምችት እንዳላትም ይታወቃል። በቅርቡ የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ዋቢ ያደረገው ዘገባም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው፤ ሚኒስትር ዴኤታው እንዳስታወቁት፤ በሀገሪቱ ባለፉት 15 ዓመታት በተደረጉ የአሰሳና የፍለጋ ሥራዎች 517 ቶን በላይ የወርቅ ሀብት ክምችት መኖሩ ተረጋግጧል። የወርቅ ሃብቶቹም በሚቀጥሉት 20 እና 25 ዓመታት የሚለማ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኩርሙክ አካባቢ እየተገነባ ከሚገኘው የወርቅ ማውጫ ፋብሪካ በተጨማሪ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት አራት የወርቅ ማውጫ ፋብሪካዎች እንደሚገነቡም አስታውቀዋል፤ ሀብቶቹ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች የሚገኙ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሌሎች መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ በሀገሪቱ ከአንድ ቢሊዮን ቶን በላይ የሚገመት የብረትና ብረት ነክ ማዕድናት ይገኛሉ። አገሪቱ ከዓለም ግዙፉ ያልለማ የፖታሽ ክምችት ካላቸው አገራት አንዷ ናት። የጂኦተርማል አቅሟም እስከ 10ሺ ሜጋ ዋት ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። ለሴራሚክ ኢንዱስትሪ ግብአትነት ሊውሉ የሚችሉ የማእድናት ክምችቶች አሏት።

ይሁንና የቱንም ያህል በማዕድን ሀብት እምቅ አቅም ቢኖራት፣ የማዕድን ውጤቶች የሆኑ የግንባታ ማጠናቀቂያ ምርቶች በብዛት ከውጭ እንደምታስመጣ ይታወቃል፤ ለዚህም ወደ ሀገሪቱ የሚገቡት የሴራሚክ፣ የመስታወትና የመሳሰሉት የኢንዱስትሪ ግብአት ማእድናት ምርቶች ውጤቶች ይጠቀሳሉ።

ሀገሪቱ እነዚህ የማዕድን ሀብቶቿን ለማልማት ጥረት እያደረገች ትገኛለች፤ የማዕድን ልማቱ እንደ ወርቅ፣ ጌጣጌጥ፣ እንዲሁም የግንባታና ኢንዱስትሪ ማዕድናት ላይ እያካሄደች ቢሆንም፣ ልማቱ ግን በአብዛኛው በባህላዊ መንገድ የሚካሄድ ነው። በተለይ እንደ ወርቅ ባሉት ማዕድናት ላይ የሚካሄደው ልማት ሜድሮክ ከሚያካሂደው የወርቅ ልማት በዘለለ ኩባንያ ብዙም የገባበት አይደለም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የወርቅ ልማቱን ኩባንያዎች እየተቀላቀሉት ናቸው። ለዚህም በአብነት ሊጠቀስ የሚችለው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኩርሙክ የወርቅ ማምረቻ እየገነባ ያለው ኩባንያ ነው። ኩባንያው ግንባታውን አጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ ከፍተኛ መጠን ያለው የወርቅ ምርት እንደሚያመርት ይጠበቃል። ይህን ኩባንያ ጨምሮ በተለያየ የዝግጅትና የግንባታ ምዕራፍ ላይ የሚገኙ ኩባንያዎች ግንባታቸውን አጠናቀው ወደ ማምረት ስራ ሲገቡ በባህላዊ መንገድ እየተመረተ ካለው ወርቅ በእጅጉ የሚልቅ ምርት ማግኘት እንደሚቻል እየተጠቆመ ነው።

መንግስት ዘርፉን ለማልማት እያከናወናቸው ከሚገኙት ተግባሮች መካከል በማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በኩል እየተከናወነ ያለው ተግባር ይጠቀሳል። ከማዕድን ኢንዱስትሪዎች ልማት ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ኢንስቲትዩቱ ተጠሪነቱ ለማዕድን ሚኒስቴር ሆኖ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 52 ውሳኔ ተሰጥቶበት የተቋቋመ ነው። ስልጣንና ተግባሩም በደንብ ቁጥር 508/2022 ተወስኗል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብስራት ከበደ እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ ማዕድናትን በጥሬ እቃነት በመጠቀም ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች ግብአት መሆን የሚችሉ ምርቶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን በግንባታ ግብአት፣ በብረት፣ በጌጣጌጥ ማዕድናት፣ በኃይል አመንጪ እና በመሰረታዊ ኬሚካል ላይ በምርምር፣ በስልጠና እና በቴክኖሎጂ መረጣ ለመደገፍ የተቋቋመ ተቋም ነው። ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታቸው ጉልህ የሆኑና ከውጭ የሚገቡ የማዕድን ውጤቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እንዲቻል ለኢንዱስትሪዎች ድጋፍ በመስጠት የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን የልማት እምርታ ለማምጣትና ኢንዱስትሪው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማብቃትም ይሰራል።

ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመበት ስልጣንና ተግባር በመነሳት የተሰጠውን ተልእኮ ለማሳካት በ2016 በጀት ዓመት ስትራቴጂክ ጠቀሜታቸው ጉልህ የሆኑና ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪና የኮንስትራክሽን የኃይል ምንጭና የግብርና ግብአት ማዕድናትን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ጥራትና ምርታማነትን በማሳደግ ከውጭ የሚመጡ የእነዚህ ዘርፎች ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እንዲቻል በጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ እየሰራ ይገኛል።

በተለይ በሲሚንቶ፣ ሴራሚክና መስታወት፤ በብረት፤ በማርብል፣ ግራናይትና ጌጣጌጥ፤ በኢንዱስትሪ ማዕድናት ከሜካል እና ማዳበሪያ፤ በኃይል አመንጪ ማዕድናት /በተለይም ድንጋይ ከሰል/ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

የማዕድን ልማት ኢንስቲትዩት በተለይ ዘንድሮ በማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት አጠቃላይ የማዕድን ዘርፉ የሚመራበት ሮድ ማፕ እየተዘጋጀ ይገኛል ያሉት ዶክተር ብስራት፣ በዚህ መሠረት የድንጋይ ከሰል ረቂቅ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደበት መሆኑንም አስታውቀዋል። የስትራቴጂው ዋና ዓላማ የድንጋይ ከሰልን በጥራት፣ በብዛት በማምረት የሀገር ውስጥ ፍጆታን መሸፈን፣ ከዚያ ባሻገር ደግሞ ኤክስፖርት ማድረግ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ በአራት ክልሎች (በቤኒሻንጉል፣ በኦሮሚያ፣ በደቡቡ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ) በተሰበሰበው ናሙናዎች መሠረት የድንጋይ ከሰል የኮሎሪ መጠንን መለካት መቻሉንም ጠቅሰው፣ በዚህም አሁን ላይ ከውጭ ከሚገባው በላይ ሆነ የኮሎሪ መጠን ያለው የድንጋይ ከሰል መገኘቱንም አስታውቀዋል።

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ በ2016 በጀት ዓመት የማዕድን ሚኒስቴር ከውጭ የሚመጣውን የድንጋይ ከሰል ለማስቀረት እንዲያስችል የስትራቴጂክ ሰነድ በማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በኩል እንዲሰራ ያደረገ ሲሆን፣ ለዚህም ሪቂቅ ሰነዱ ተዘጋጅቷል፤ በዚህም የድንጋይ ከሰል የአመራረት ሂደቱን በማስተካከል እና እሴት በመጨመር እና ሌሎች የሚታዩ ተግዳሮቶችን በመፍታት በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ከውጭ የሚመጣውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያስችል አቅም እንዳለ ታይቷል።

በተጨማሪም በባህላዊ መንገድ የሚመረቱትን የወርቅ እና ጌጣጌጥ ማዕድናት ምርታማነት ለማሻሻልም እንዲሁ የስትራቴጂክ ሰነድ ረቂቅ ሰነዶች መዘጋጀታቸውን ገልጸው፣ በዚህም መሰረት በስትራቴጂክ ሰነዱ የተለዩት ስትራቴጂክ እቅዶች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ተናግረዋል።

ዶክተር ብስራት አንዳብራሩት፤ ኢንስቲትዩቱ የማዕድንን ግብዓት ተጠቅመው የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን የመደገፍ ሥራን ይሰራል፤ የአቅም ግንባታ ስልጠና ይሰጣል። በተለይ ስልጠናው ለክልሎች የማዕድን ቢሮ ኃላፊዎች የሚሰጥ ሲሆን ከአወቃቀራቸው ጀምሮ፣ የጂኦሎጂካል ማዕድን ዘዴ፣ ላይሰንሲንግ እና በመሳሰሉት ዙሪያ የተለያየ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ ይደረጋል። ከዚህ በተጨማሪም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች በቅንጅት ይሰራሉ፤ በዚህም መሰረት ከወሎ፣ ከአዲስ አበባ፣ ቡሌሆራ ዪኒቪርሲቲዎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ሥራዎችን በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።

በቀጣይም በተመረጡ ማዕድናት ላይ ዝርዝር የአዋጭነት ጥናቶችን በማካሄድ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ፕሮፋይሎችን አዘጋጅቶ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች ተደራሽ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ ኢንስቲትዩቱ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ኢንስቲትዩቱ ለማዕድን ኢንዱስትሪዎች የምርት ጥራትና ብዛት እንዲያድግ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የምክር አገልግሎትና የቴክኒክ ድጋፍ ይሰጣል። የማማከርና የቴክኒክ ድጋፍ የማድረግ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። እንዲሁም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን በማላመድና በማስረጽ የቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር የማፋጠን ስራ ከመሰራት አንጻር አንድ ቴክኖሎጂ ተጠናቆ ስራ ላይ እንዲውል የተደረገ ሲሆን፣ ሌሎችም በሂደት ላይ ይገኛሉ።

በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ የዘርፉን ኢንዱስትሪ ምርትና ምርታማነት ሊያሳድጉ የሚችሉ የአቅም ግንባታ ስራዎች መስጠት ዋና ተግባሩ ሲሆን፣ በድንጋይ ከሰል፣ በጌጣጌጥ፣ በሲሚንቶ ቴክኖሎጂ በኢነርጂ አጠቃቀም ዘዴ /ኢነርጂ ማኔጅመነት ሲስተም/ ላይ ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል።

ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታቸው ጉልህ የሆኑ የማዕድን ኢንዱስትሪ ውጤቶች ልማትን ሊያፋጥንና ተወዳዳሪ ሊያደርግ የሚችል የድጋፍ ስርዓት በመዘርጋት ይሰራል። ፕሮጀክቶችን ያዘጋጃል፤ ተግባራዊ ያደርጋል፤ በዘርፉ ለተሰማሩ አልሚዎች ድጋፍ ይሰጣል።

በጋዜጣው ሪፓርተር

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You