እንደ ንብ አብረን እንደ አንበሳ ተከባብረን!

ጣሊያናዊውሴቺ (Cecchi) የተባለው ተጓዥ ኢትዮጵያን አይቶ “የሰዎችን ሕብረ ቀለም ከኢትዮጵያ ውጪ አይቼ አላውቅም ሲል ጽፏል፤ ኢትዮጵያን ለመግለፅ “መካነ ሕዝብ “ የሚለውን ሀረግ ተጠቅሟል። የ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንግሊዛዊ አሳሽ ሔነሪ ብላንክ በበኩሉ “ የኢትዮጵያ መልካ ምድር መሰል የለውም፤ “እውቅ ሰዓሊ በሸራ ላይ የከተባቸው የምናብ ውላጆች ይመስላሉ “ሲል በማስታወሻው አስፍሯል።

አዎ! ኢትዮጵያ የሰው ልጅም የተፈጥሮም ሕብር የተገለጡባት የገፀ ምድር ጌጥ ናት። ከምድር ጠለሉ ዳሎል እስከ የአፍሪካው ጣሪያ ራስ ደጀን፣ ከውብ ሰንሰላታማ ተራሮች እስከ እልቁቢስ ደልዳላ ምድር፣ ከቆላ እስከ ደጋ፣ ከክረምት እስከ በጋ የተፈጥሮ አየሩ በልኩ ሆኖ የሚያድርባት ውብ ሀገር ናት። ኢትዮጵያ ተራራ ሜዳውን፣ ደጋ ሸለቆውን እያቋረጡ የሚተሙ ወንዞች፣ የእህል ቡቃያን የሚያወዛ ስምሙ አየርና አፈር ሁሉንም በእጇ በደጇ ያቀፈች ምድር ናት።

ታዲያ ስለምን ሁሉ ኖሮን ብዙ ያጣን ሆንን? ጥሬ እቃ የሞላባት ሀገር እቃን በገፍ ስታስገባ እንዴት ትኑር? አባይ ምንጩን አልፎ ሱዳን ላይ ያበቀለውን ፍራፍሬና ሽንኩርት ስለምን ከሱዳን እንጠብቃለን? በአዋሽ፣ በገናሌ፣ በአኮቦ፣ በባሮ ምድሯን በቡቃያ መሙላት አቅቶን በምግብ ለዓለም መትረፍ ለምን አቃተን?።

የአልባሳቱ ሰበዝና ጥበብ በእጃችን እያለ እንዴት የባህር ማዶ ልባሽ ማራገፊያ ሆነን እንኖራለን? ወንዝና ፏፏቴን አቋርጠን ወደ ወንዝ አልባው በርሃ እየተሰደድን የሰው ሀገር ሲሳይ የምንሆነውስ እስከ መቼ ይሆን? ፖለቲካና ርዕዮት በረከትን ሳይሆን የግጭት መርገምትን ሲጭኑብን እስከመቼ ይቀጥላል ?።

በተለያዩ መዛግብት ተከትበው የተቀመጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ቀደምት የኢትዮጵያ የተጋድሎ ታሪክ ለወራሪ የማይመች ፅኑ ተፈጥሮ ኖሯት የቆየች ሀገር ነች። ከእነዚህ መካከል የአድዋ ድሏ ደግሞ የቀኝ ግዛትን ከዓለም ጫንቃ ላይ አሽቀንጥሮ ለመጣል ጥልቅ መነቃቃት የፈጠረ ነው።

እነዚህና መሰል የወል ታሪኮቻችን ለሀገራዊ አንድነታችን ሆነ እስካሁን ለዘለቀው ሀገረ መንግስታችን ከፍያሉ አቅሞች ናቸው። ትልቁ ጥያቄ ግን በአግባቡ ተረድተን በትውልዶች መካከል ሊኖረው የሚችለውን ሞገስ ተለብሶ እንዲጓዝ የቱን ያህል ሰርተንባቸዋል የሚለው ነው።

ከዚህ ይልቅ የተዛቡ ትርክቶች በዜጎች መካከል ልዩነት እንዲፈጠር ምክንያት ከመሆናቸውም ባሻገር በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለግጭት መነሻ እየሆኑ ይገኛሉ። ከዛም አልፈው ነገ ላይ ተስፋ ያደረግናቸውን ብሩህ ቀናት በቀላሉ አምጠን እንዳንገላገላቸው ፈተና እየሆኑብን ነው።

መሰል ትርክቶች በውይይት መታረም አለባቸው። ትናንት ላይ የብሄር ጥያቄ እንዴት ተነሳ? በወቅቱ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ምን ነበር? የቀዝቃዛው ጦርነት ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? በዛሬዋ ኢትዮጵያ ላይ ምን ፈጠሩ በሚሉና በመሰል ጉዳዮች ላይ ቁጭ ብሎ መወያየት፣ መነጋገር፣ መምከር ያስፈልጋል። ከዛም ስህተት ተሰርቶ ከሆነ ታርሞ መኬድ አለበት።

ታሪክ ቀድሞ የተፈፀመውን ለማረምና መልካሙን ስራ ለትውልድ ለማስቀጠል የሚያግዝ እንጂ የግጭት መንስኤ መሆን የለበትም። የተፃፈ ታሪክ ሁሉ እውነት አይደለም። በተዛባም ሆነ በትክክለኛ መንገድ የተፃፉ ታሪኮች አሉን። ገና ሊፃፉ፣ ሊመዘገቡ፣ ሊዘከሩ፣ አንድነታችንን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ብዙ ትርክቶች አሉን። ከሁሉም ብዙ መማር እንችላለን ።

አሁን እንደ አድዋ ጊዜው ከውጭ የመጣብን ጠላት የለምና እርስ በእርሳችን መገዳደል የለብንም። መገዳደልን በትውልድ ቅብብል መቀባበል ማብቃት አለበት። ቂም በቀልን እያስተላለፍን ከምንኖር ኢትዮጵያን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማስቀጠል የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው።

የመከፋፈልና የመለያየት ትርክቶች ለሀገር አንድነትና እድገት እንደማይጠቅሙ በመገንዘብ ሕብረ-ብሄራዊ አንድነትን ማጠናከር የሚያስችሉ የጋራ ትርክቶች ላይ መስራት ያስፈልጋል። ከፋፋይ ትርክቶች ሀገርን አያሳድጉም። ከዚህ አይነቱ ትርክት ወጥተን ሀገርን አንድ በሚያደርግ፣ አንድነትን በሚያዳብረው፣ ሰላማዊ ሀገር መፍጠር ወደ ሚያስችል ትርክት ፊታችንን ማዞር ይጠበቅብናል።

የሕዝቦችን ችግር በኃይል እንፈታለን በሚል የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ ኃይሎች ሕብረተሰቡ ለሚያነሳው የሰላም ጥያቄ ተገዢ ሆነው መንግስት ላቀረበው የሰላም ጥሪ በጎ ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል። ችግሮች በውይይትና በውይይት ብቻ እንደሚፈቱ ሁላችንም ልናምን ይገባል። ለተግባራዊነቱም ሁሉም እኩል መጣር አለበት።

ሰላም በአንድ ወገን ብቻ ስለተፈለገ የሚመጣ አይደለም። ሰላምን በሰለጠነ መንገድ ወንበር ስቦ በሀሳብ የበላይነት የሚገኝ ነው። የጠመንጃ ቃታ በመሳብ የሚገኝ ሰላም የለም፤ ኖሮም አያውቅ። በዚህ መንገድ ሰላምን ለማምጣት የሚደረግ የትኛውም አይነት ጥረት ትርፉ ኪሳራ ነው። የኪሳራው አይነት ደግሞ በማይተካ የሰው ሕይወትን ላይ የቆመ ነው።

ሰላም ቃሉ በራሱ ሰላም፣ እረፍት የሚሰጥ ነው። ሰላምን መሻት ደግሞ የፍጥረታት ሁሉ ግብ ነው። ይህም ሆኖ ግን ሰላም በመፈለግ ብቻ አትመጣም፤ በተግባር መተርጎም ቁርጠኛ መሆን ትፈልጋለች። ዓለም ከመቼውም ጊዜ በላይ በግጭትና ጦርነት እርፍት ያጣችበት ወቅት ላይ ነን። ሰላም ማጣት ደግሞ “አፍንጫ ሲመታ አይን ያለቅሳል “አይነት የማይነጣጠሉ የሕልውና ጉዳዮች ከነመልካቸው ይመጣሉ።

ሰላም ለዜጎች ደህንነት፣ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንዳሻቸው ለመንቀሳቀስ ወይም በመንቀሳቀስ ሰርቶ ለማደር መሰረታዊ ጉዳይ ከመሆኑም በላይ ለሀገር ምጣኔ ሀብትም ማኮብኮቢያው ነው። ሁሉም ነገር ከሰላም ቅድሚያ ሊመጡ አይችሉም። ለዚህም ነው ሰላምና ሰላም ላይ ጊዜና ገንዘባቸውን ያፈሰሱ ቃላቸውን የጠበቁ የፖለቲካ መሪዎች የሰላም አየር የሚማግበት አውድን የፈጠሩት።ሰላም የበለጸገች ዴሞክራሲያዊ ሀገር ለመመስረት ቅድመ ሁኔታ ቢሆንም በጠመንጃ ብቻ የፖለቲካ ፍላጎትን ለማስፈፀም የሚታትሩ ኃይሎች ሀገርን ፈተና ውስጥ ጨምረዋት ታይቷል።

በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ ከሰላም ውጭ ቀዳሚ አጀንዳ የላትም። ሰላም ለምናስበው ልማት፣ ብልፅግናና አብሮነት እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው። ሰላም በሌለበት ሁኔታ ትልልቅ ነገር ማለም ማቀድ ያስቸግራል። ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም፣ በዴሞክራሲና በምርጫ ካልሆነ ጠመንጃ ይዞ ወደ ስልጣን መምጣት ፍፁም አይቻልም። ሰላም ሁሌም በውድ ዋጋ የሚገኝ ነው። ችግሮችን በውይይት ብቻ መፍታትን ይጠይቃል።

ሰላም መሻት ብቻ ሳይሆን ተግባር ትፈልጋለች። ከዚህ ሀገራዊ ሰላምን ለማጽናት አንጻር ሁሉም ስለሰላም በተጨባጭ የሚታይ እርምጃ መጀመር አለበት። የሰላም ውይይቶች ሂደትን የሚሹ እንደመሆናቸው ለስኬታማነታቸው የሚመለከታቸው ሁሉ ከእልህና ከማን አለብኝነት መንገድ ወጥተው ስለ፤ ሰላም በሆደ ሰፊነት ሊንቀሳቀሱ ይገባል። በሰላም እጦት የሚደርሰውን ኪሳራ ከራሳችን ካለፍንበት ታሪኮች መማር ተገቢ ነው።

በተለይም መሳሪያ አንስተው እየተዋጉ ያሉ አካላት የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ሙሉ እምነታቸው መወያየት መሆን አለበት። ውይይት ሀገርን ከውድመትና ከጥፋት የዜጎችን ሕይወት ከሞት ማዳኛ መንገድ መሆኑን አሁን ላይ በአግባቡ ማጤን ያስደልጋል። በመወያየት ችግር ይፈታል፣ በመወያየት ሀገር ታድጋለች፣ በመወያየት ሰላም ይገኛል፣ በመወያየት ነፃነት ይረጋገጣል። በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ ሀሳብን መግለፅ፣ አላማን ማስረዳት፣ ችግሮችን ማቅረብ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው።

በሀገራችን እየተካሄዱ ባሉት ግጭቶችና ጦርነቶች ተጎጂ እየሆኑ ያሉት ንፁሀን ዜጎች ናቸው። መንግስት ካለበት የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ሀላፊነት አኳያ ያለውን ሀገራዊ አቅሞች አስተባብሮ ስለ ሰላም መስራት አለበት። ለዚህም፣ ሆደ ሰፊ መሆን ይጠበቅበታል

መላው ሕዝባችንም ከነጠላና ቡድናዊ ትርክቶች በመውጣት አሰባሳቢና የጋራ ትርክቶችን መፍጠር ይጠበቅብናል። እንደ ንብ አብረን እንደ አንበሳ ተከባብረን በጋራ ከፍ ልንል ይገባል !።

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You