ረመዳን እና መንፈሳዊ ትሩፋቶቹ

መቼም የረመዳን ወር ጨረቃዋ ስትወጣ፣ የረመዳን ወር ውብ ድባብ አየሩን ሲሞላ ሕዝቡ እዝነትን ይላበሳል። የደረቀው ልብ ወደ መርጠቡ ያዘነብላል፣ አስቸጋሪው ፀባይ ይለሰልሳል፤ ይህ እውነታ አንዳች መለኮታዊ ምስጢር ስላለው አፈንግጦ የከረመው ሁላ ተጣጥቦ ከዕዙ መስመር ይሰለፋል። አጃኢብ!! በሚያስብል ዕርጋታና ፀፀት ተቀንብቦ ከአላህ/ሱ.ወ/ ዘንድ የርህራሄ ክንፍ ዝቅ እንዲል ተማፅኖው ይጎላል፤ እጆቹን ዘርግቶ ልመናው ያይላል። የእምነቱ አባቶቹም ምናልባት የተዘናጋ ሕዝብ ካለ ከፅድቅ ገበያው በጊዜ ነቅቶ ፅድቅን እንዲገበይ የበረከትና የጥሞና ልምምድ መጀመሪያ ጥሪ ያቀርባሉ።

በረመዳን ወር ውስጥ ለሰው ልጆች ዘላለማዊ ጠላት የሆነው ሸይጣን የሚታሰርበት፣ የጀሃነብ በሮች የሚከረቸሙበት፣ የጀነት/የገነት/ በሮች ወለል ብለው የሚከፈቱበት፣ ልቦች የሚራሩበት፣ ቀልቦች የሚሰክኑበት፣ ነፍሶች የሚለመልሙበት፣ ደግነትና ቅንነት ከፍታው የሚልቅበት ሰዎች ካላቸው አስቤዛ ቆንጥረው ለድሃ በመስጠት በረከትንና ምሕረትን የሚከጅሉበት፣ የመስጠት ፀጋን ጣዕም የሚያጣጥሙበት ቅዱስ ወር ነው።

ይህ ቅዱስ ወር የፈጣሪ ተዓምር ማሳያ በመሆኑ ወላጅ-አልባና አካል ጉዳተኛ ሕጻናትን እንዲሁም ሕጻናቱን ለማሳደግ አቅም ያጡ ወላጆቻቸውን፣ አዛውንቶችን ከመመገብና ከመንከባከብ ባለፈ ሕይወታቸው በዘላቂነት እንዲሻሻል መሠረት ለመጣል የታደሉ የሚነሳሱበት፣ ቸር ቸሩን የድጋፍ አስተዋፅዖ ለማድረግ የሚተጉበት ገርና አግሪ የበረካ ወር እንደሆነ ብዙኃኑ ይመሰክራሉ። የእምነቱ ተከታዮች በረመዳን የፆም ወር ከሥጋ ፍላጎታቸው ተገተው ወደ አላህ/ሱወ/ የሚቀርቡበት፣ አንገታቸውን ዝቅ የሚያደርጉበት፣ በደላቸውን፣ ወንጀላቸውን እንዲያብስላቸው፣ ምሕረትን እንዲሰጣቸው አበክረው የሚጠይቁበት ብዙ ጥጋብ የማይፈቀድበት፣ ብዙ እንቅልፍና ዝንጋዔ የሚከለከልበት የጥሞና፣ የጸሎት/የዱዓ/ጊዜ ነው።

ምዕመኑ በፆሙ ወቅት በየመስጊዱ በመስገድ፣ ቁርዓን በመቅራትና ሌሎች ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን በመፈጸም አላህ እንዲራራላቸው የሚማፀኑበት፤ አላህም ፍጡሩን በእዝነት የሚመለከትበት፣ ምሕረቱን የሚልክበት፣ የአማኞች እምነት የሚፀናበት፣ ሕዝበ-ሙስሊሙ ቀልቡ የሚረጋጋበት፣ ደግነትና ርህራሄን የሚያበዛበት፣ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ፀባዩ የሚታነፅበት፣ ታዛዥነትና መተናነጽ የሚያዘወትበት ነው።

ጎረቤቶቹን በትኩረት የሚያይበትና ጠንካራ ፍቅር የሚያደራጅበት፣ የሃይማኖት አባቶች የሚሰጡት ትምህርት፣ የታላላቆቹን ምክርና ግሳጼ አበክሮ የሚያስተውልበት፣ ሠላምንና በረከትን አጥብቆ የሚሻበት፣ ከተለያዩ የማኅበረሰብ_ክፍሎች ጋር አስደናቂ የፍቅርና የመግባባት መስተጋብሮችን የሚመሠርትበት የትሕትና ወር ነው።

የረመዳን ገጽታው፣ የአጿጿም ሥርዓቱና ሕግጋቱም እንደሚገልጹት ጿሚዎች በጎ በጎውን ብቻ እንዲተገብሩ ያዛል። ሃይማኖታዊ አስተምህሮቱም ደግ ደጉን ብቻ ይሰብካል፣ በከፍተኛ ጥንቃቄ አስረግጦ ያስረዳል።

የረመዳን የፆም ወር መጠናቀቁን አብሳሪና የእስልምና እምነት ተከታዮች በጉጉት የሚጠብቁት ታላቁ የኢድ አልፈጥር በዓል ነው፤ ይህ በዓል በመላው እስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ ዋና ዋና በዓላት መካከል አንዱ ነው ። መልካም ተግባራትን መፈጸምና በደስታ ማክበር የኢድ አልፈጥር ልዩ መገለጫዎች ናቸው” በእርግጥ ኢድ አልፈጥርና ሌሎችም የእስልምና ዕምነት በዓላት አከባበር የሚወሰነው ከጨረቃ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ነው እንጂ በሰዎች ስሌት ወይም በቀን መቁጠሪያ አጀንዳ /calendar/ መሠረት አይደለም። ታዲያ በዓሉ ተከብሮ የሚውልበትን ቀን ቀድሞ እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል በበዓሉ አከባበር ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ዋና ዋና ነገሮችን ብዙዎቹ ቀድመው ማዘጋጀትን ይመርጣሉ።

የኢድ አልፈጥር በዓል አከባበር ከዋዜማው ጀምሮ የእምነቱ ተከታዮች አላህን በማመስገን/ተክቢራ/እና ፀሎት በማድረግ ሥነ ሥርዓቱ እንደሚከናወን የሚታወቅ ሲሆን የበዓሉ ቀን በሃይማኖታዊ ንፁሕ አልባሳት ደምቀው እና አምረው ወደ መስገጃ አደባባይ እና ወደ መስጂዶች በረድፍ ሲያመሩ ሲታዩ የጎላ ውበት፣ አስደማሚ አንድነት ይንፀባረቃል። ሶላታቸውን በጋራ ሰግደው እና በአንድ አይነት መንፈሳዊ ቋንቋ አላህን አመስግነው፣ እርስ በእርሳቸው የመልካም ምኞት መግለጫ ተለዋውጠው፣ ከልብ የመነጨ ፈገግታ ተመጋግበው፣ አብረን ወደ ቤት እንግባ፣ አብረን እንዋል እያሉ ሲገባበዙ፣ በአክብሮት ሲጠራሩ ማዳመጥ፣ በተግባር መመልከት የተለመደ ነው። ሲለያዩም በታላቅ ትሕትና ነው።

አማኞቹ የሶላት ስግደት ወደሚካሄድባቸው ስፍራዎች በሚያቀኑበትና ሰግደው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ያለው ሥነ_ሥርዓት ራሱን የቻለ ውብ ትዕይንት ነው። ከስግደት መልስ ደግሞ እርስ በእርስ በመጠያየቅና በመደጋጋፍ፣ በመተዛዘንና ያለውን በመረዳዳት በዓሉን በደስታ ማክበር የእምነቱ ድንጋጌ ነው። በዓሉን በተለየ ድባብ የሚታይ የአብሮነት ፍቅርና የጋራ የደስታ በዓል ነውና መልካም እሴቶችና ሠናይ ተግባራቱ የኢድ አልፈጥር ልዩ መገለጫዎች ስለሆኑ በበዓሉ ምክንያት የተቸገሩ ወገኖችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ አዛውንቶችን ያለውን አካፍሎ መሰደቅ /መመጽወት/ እንዲሁም በአካል መጎብኘት /መዘየር/ የተለመደ የምዕመኑ ተግባር መሆኑ ይታወቃል።

ይሄ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት የተሞላው መርሐ ግብር በሌላ እምነት ተከታይ ጓደኞች፣ የሥራ ባልደረቦች፣ ጎረቤቶች ዘንድም የማይረሳ የወዳጅነት ትዝታው ከልብ አይጠፋም ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ በቅርበት እንደሚያውቀው የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ወዳጆች፣ ጎረቤቶች ተጠርተው እና ተጋብዘው፣ በጥልቅና ነፃ የፍቅር መንፈስ ተሳስቀውና ተጫውተው “ኢድ ሙባረክ” እየተባባሉ ቀጣዩን ዓመት በሠላም፣ በጤና ሳይለያዩ ቆይተው እንዲያከብሩ መልካም ምኞታቸውን እየተገላለፁ፣ ከልብ እየተመራረቁ በፍፁም ኢትዮጵያዊ ለዛ እያወጉ በዓሉን እንደሚያከብሩ መናገር “ለቀባሪ ማርዳት” እንደሚባለው ቢሆንም እውነታውን በጥቂቱ ለማስታወስ መሞከር ተገቢ ነው።

በኃረዲን ከድር

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You