ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ከሀንጋሪ አቻቸው ጋር በሳይንስ፣ በባህል እና በትምህርት አብሮ ለመስራት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1965 ተስማሙ፡፡ንጉሱ በሀንጋሪያኑ ግብዣ ሀንጋሪን ሊጎበኙ ይሄዳሉ፡፡ታዲያ በጉብኝታቸው ወቅት አንድ ፕሮግራም ይታደማሉ፡፡በዕለቱ በመድረክ ይከወን የነበረው ደግሞ “ዱና” እና “ሆንቬድ” የተሰኙ የሀንጋሪ ጥንታዊ የዳንስ ትዕይንቶች ነበሩ፡፡
ንጉሱም ፕሮግራሙን ከመታደም ባለፈ ሀንጋሪያኑ በዚህ ልክ ባህላቸውን በመጠ በቃቸው ተገርመው ለአገሪቱ ባለስልጣናት አድናቆታቸውን በመናገር ጉብኝታቸውን አጠናቀው ይመለሳሉ፡፡
አገር ቤት ከገቡ በኋላ ግን ባዩት ነገር ተመስጠው ስለነበር ወደ ሀንጋሪ ደብዳቤ በመጻፍ የኢትዮጵያ ባህላዊ ጭፈራ እና ዳንስ እንዲጠና እና በመቅረጸ ምስል እና ድምጽ እንዲያዝ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡በወቅቱ የነበሩት የሀንጋሪ ሹማምንቶችም የንጉሱን ሀሳብ በደስታ በመቀበል ኢትዮጵያን ሊያግዙ ተስማሙ፡፡
በስምምነታቸው መሰረት ሀንጋሪ ሁለት ባለ ብሩህ አዕምሮ “ኢትኖግራፈር” ባለሙያ ጆርጅ ማርቲን እና ባለንት ሳሮሲ የተባሉ ግለሰቦች ላከች፡፡የኢትዮጵያን ቃላዊ ጭፈራን እና ሙዚቃን የማሰባሰብ ሂደት ከሀንጋሪያኑ ባሻገር ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችም የጥናቱ አካል ሆነዋል፡፡ በቀድሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጸጋዬ ደባልቄ፣ የቀድሞ የሀገር ፍቅር ቴአትር ዳይሬክተር ኢዩኤል ዮሐንስ ተሳታፊ ነበሩ፡፡
ታዲያ ይህ ቃላዊ ቅርስ ከተሰበሰበ በኋላ ለ55 ዓመታት በሀንጋሪያን እጅ ስር ነበር ።እናም እንዲህ ያሉ ቅርሶችን የማሰባሰብ ስልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተመዛግብት እና ቤተመጽሀፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) ለማስመለስ ከሚመለከ ታቸው የሁለቱ አገራት ባለስልጣናት ጋር በመሆን ሥራ ሰርቷል፡፡
የኢትዮጵያ የመረጃ ሐብቶች በማሰባ ሰብ፣ በማደራጀትና በመንከባከብና በመ ጠበቅ ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ለማገናዘቢያ አገልግሎት እንዲውሉ የማድ ረግ ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔ ራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀ ንሲ፣ይህን በአዋጅ የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር ለመወጣት እንዲሁም በአገር ውስ ጥም ሆነ ከአገር ውጭ ያሉ ቅርሶችን የመጠበቅም ብሎም ለማስመለስ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
በር ካታ ቁጥርም ያላቸው ጥንታዊ መዛግብትና የጽሑፍ ቅርሶች ከጥፋት ተጠብቀው ከትው ልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ የመጠበቅና ለተመራማሪዎችም ተደራሽ የማድረግ ሥራዎችንም አከናውኗል፡፡ በቀረጸ ድምጽ እና ቀረጸ ምስል ክፍሎቹም በተለያዩ መንገ ዶች ከተለያየ ሥፍራ የተሰባሰቡና የተደራጁ በርካታ ቁጥር ያላቸውን የሸክላ ዲስክ፣ ቪ ኤች ኤስ፣ የቴፕ ካሴት፣ ሲዲ፣ ቪሲዲ እና ዲቪዲዎችን በጥንቃቄ በመያዝ ለጥናትና ምርምር ተግባር በማዋል ላይ ይገኛል፡፡
ኤጀንሲው በሀገር ውስጥ ያሉ ቅርሶችን ከመንከባከብና ከመጠበቅ ባሻገር በውጪ የሚገኙ የሀገር ቅርሶች እንዲመለሱ ጥረት የማድረግ፤ ከተመለሱም በኋላ የመጠበቅና ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነትም ተጥሎበታል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ባሳለፍነው አርብ በኤጀንሲው፣ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም፣ በሀንጋሪ ኤምባሲ እና በያሬድ ትምህርት ቤት ትብብር በተዘጋጀ መድረክ ከሀንጋሪ የመጣ የኢትዮ ሀንጋሪያን የባሕላዊ ቅርጽ ፕሮጀክት ልዑክ በርካታ የቃል ሙዚቃእና ባህላዊ ጭፈራ ድምጾችን ለብሔራዊ ቤተ መዛግብት ቤተመጻህፍት ኤጀንሲው፣ በአዲስ
አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር ለሚገኙት ለኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ማዕከል እና ለያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት አስረክቧል፡፡ ከዛሬ 55 ዓመት በፊት በሁለት ሀንጋሪያውያን አጥኚዎች በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች የተቀረጹት እነዚህ መረጃዎች በያሬድ ትምህርት ቤትና በሌሎችም አጥኚዎች በሙዚቃ ላይ ለሚደረጉ ጥናቶች የሚያግዙ እንደሚሆኑ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡
በርክክቡ ስርዓትም ከዛሬ 52 ዓመት በፊት ባለዋሽንቱ እረኛ የተሰኘው ዕውቁ ሙዚቃ ላይ ፍሉት የተጫወቱት ሎረንት ኮቨናንት በድጋሚ በመድረኩ ያቀረቡ ሲሆን የብሔራዊ ቲያትር የባህል ቡድን ባህላዊ ውዝዋዜ አቅርቧል፡፡በተጨማሪም የሀንጋሪያን ፎክ ዳንስ ቡድን እና ኢትዮጵያውያኑ ጸሊቀ የዶርዜ ዳንስ ቡድን ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡
ሀንጋሪያውያን ከዛሬ 55 ዓመት በፊት በአጥኚዎቻቸው አማካኝነት የተቀረጹትን የቃል ሙዚቃ ድምጾች ዲጂታላይዝ በማድ ረግ ለኢትዮጵያ መመለሳቸው መልካም እንደሆነ የሚናገሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የሥርዓተ ትምህርት ተመራማሪ ዶክተር ውቤ…… ናቸው። በሀገር ውስጥ የሚገኙ በርካታ ቅርሶች በተለያዩ አጋ ጣሚዎች እንደ ቃጠሎ ባሉ ሠው ሠራሽ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸው መሆናቸውን ያስታወሳሉ።
በውጪ ሀገራት የሚገኙ ቅርሶች ላይ ሊደርስ ከሚችል አደጋ ተጠብቀው በመልካም ሁኔታ መያዛቸው ለቅርሶቹ ደኅንነት መጠበቅ የሚበጅ መሆኑን እንደ መልካም ጎን መውሰድ ያስፈልጋል። ሌሎች በውጪ ሀገራት ያሉ ቅርሶችን ለማስመለስም ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት እንደሚያሻ ይጠቁማሉ፡፡
“ሀገር በቀል ዕውቀት” ለአንድ ሀገር እድገት ትልቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ ላይ የሚያሰምሩት ዶክተር ውቤ፣ ያለ ፈው ትውልድ ታሪክና ባሕልን ማወቅ፤ የተደረሰበትን ዕውቀት መካፈል ነገን የተሻለ ማድረግ፤ የሚጠቅመውን ይዞ የማይጠቅመውን መማሪያ አድርጎ ለመጓዝ እንደሚያግዝ ይናገራሉ፡፡
እርሳቸው እንዳሉት፣“እኛ ኋላቀር ነን ብለን ስለምንጀምር በአገራችን ያለውን አገር በቀል እውቀት ሁሉ ጭቃ ውስጥ ለውሰነዋል። እንደዛ ማለቱን ትተን ያለንን ሀብት ዛሬ ለሚያስፈልገው ነገር ለዛሬዋ ኢትዮጵያ እንጠቀምበት፡፡” ዶክተር ውቤ አክለው እንዳሉት አገር በቀል እውቀቶች ላይ ምሁራን መስራት ሲችሉ ነው፡፡
ከማንኛውም ግለሰብ በተለየ መልኩ ምሁራዊ ትንታኔ እየሰጡ ባህላዊ ቅርሶችን ሊያጎሉ ይገባል፡፡በተጨማሪም ከቤት ያለፈ፣ ከሰሜት የራቀ እና ግላዊነት ያልተንጸባረቀበት ኢትዮጵያዊነትን የተቀዳጀ እውቀትን ለትውልድ ማውረስ ላይ መስራት አለባቸው፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችን የበርካታ ሀገር በቀል እውቀቶች መገኛ፣ የጥንታዊ ባሕልና ቅርስ ሐብት ባለጸጋ ናት፡፡ የቅዱስ ያሬድ ዝማሬ፣ የገዳ ሥርዓትና ሌሎች ቅርሶቻችንም ከራሳችን አልፎ ለሌላው ዓለም ጭምር ምሳሌ መሆን የሚችሉና የውጪ አጥኚዎችንም የሚጋብዙ ናቸው፤ በርካታ ተመራማሪዎችም ምርምሮችን አካሂደውባቸዋል፡፡ይህ ቢሆንም ግን ባለቤቱ ያቀለለውን… እንዲሉ ለቅርሶቻችን ስፍራ ሰጥተን መጠበቅ፣ በባሕላችንም መኩራት ካልቻልን ሌላው መጥቶ የእኛን ቅርስ ሊጠብቅልን ባሕላችንን ከጥፋት ሊታደግልን አይችልም፡፡
ብዙ ልንኮራባቸው የምንችልባቸው ቅርሶች ያሉን ከመሆናችን ጋር ሲነጻጸር ቅርስ፣ ታሪክና ባሕላችንን ለማወቅ የምናደርገው ጥረት አናሳ ነው የሚሉት ዶክተር ውቤ ቅርስና ታሪካችንን ለማወቅ ልንጥር እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡ ገንዘብ ቢጠፋ ገንዘብ ይተካል ፤ታሪክና ቅርስ ቢጠፋ ግን መተኪያ የለውምና የማንነታችን መገለጫ የሆኑ ቅርሶቻችንን ልንጠብቅና ልንንከባከብም ይገባል የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2011
አብርሃም ተወልደ