ደስታ ሮቦት መጪው ትውልድ የተሻለ የቴክኖሎጂ እሳቤ እንዲያዳብር የምታስችል ናት

አዲስ አበባ፡- “ደስታ” የሚል ስያሜ የተሰጣት ሮቦት በተለይ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ቋንቋዎች የተቃኘች መሆኗ መጪው ትውልድ የተሻለ የቴክኖሎጂ እሳቤ እንዲያዳብር የምታስችል ናት ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት “ደስታ” የሚል ስያሜ የተሰጣት ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም ትናንት ለዕይታ አቅርቧል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በዕለቱ እንደገለጹት፤ ደስታ ሮቦት በሀገር ወስጥ መቃኘቷ መጪው ትውልድ የተሻለ የቴክኖሎጂ እሳቤ እንዲያዳብር የምታስችል ናት፡፡
ሮቦቷ ሀገሪቷ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ እየሠራች ያለችው ሥራ በተግባር የተገለጸባት ናት ያሉት ዶክተር እዮብ፤ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዓለም የደረሰበት ለመድረስ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን ማሳደግ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ኢዮብ (ዶ/ር)፤ ቴክኖሎጂ ጥሩም መጥፎም ጎኖች አሉት ያሉ ሲሆን፤ ሰው ሠራሽ አስተውሎት አዲስ እንደመሆኑ ጉዳቱና ጥቅሙ በማመዛዘን በከፍተኛ ጥንካሬ መምራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ረገድ ሀገሪቱ ቴክኖሎጂ ይዞት የሚመጣው ዕድል በመጠቀም የሚያስከትለው ጉዳት የሚያስቀር የፖሊሲ እሳቤ እየተከተለች ትገኛለች ነው ያሉት፡፡

እንደ ኢዮብ (ዶ/ር)ገለጻ፤ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ለማሳደግ ትኩረት ከሰጠባቸው ዘርፎች መካከል ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አንዱ ነው፡፡ ይህም በተለያዩ ዘርፎች ተጨማሪ አቅም እየፈጠረ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሰው ልጅ የማሰብ አቅም በከፍተኛ ደረጃ የሚጨምር ነው ያሉት እዮብ (ዶ/ር)፤ እንደ ከዚህ በፊት ቴክኖሎጂዎች ዘመን ካለፈባቸው በኋላ መላመድ ሳይሆን ቀድሞ መጠቀም በሚል እሳቤ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የኮሙኒዩኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ዘውዴ በበኩላቸው፤ በተለይ ሮቦቷ በሀገር ውስጥ ቋንቋ መናገር መቻሏ መጪው ትውልድ ቴክኖሎጂን የበለጠ እንዲላመድ ያስችለዋል ብለዋል።
አቶ ተስፋዬ ፤ ኢንስቲትዩቱ ሀገሪቱ በቴክኖሎጂው ረገድ ዓለም የደረሰችበት ለማድረስ ትኩረት ተደርጓል ያሉ ሲሆን ሮቦቷ በሀገረ ውስጥና በውጭ ሀገር ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መዘጋጀቷን ተናግረዋል።
በኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን እየተሠራ ይገኛል ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ከእነዚህ መካከል የሮቦት ቴክኖሎጂ ዘርፍ አንዱ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ደስታ ሮቦት ከተመልካች ለሚቀርብላት ጥያቄም በሀገር ውስጥና በውጭ ቋንቋዎች ምላሽ የምትሰጥ ሲሆን ኢንስቲትዩቱና ከiCog Labs በጋራ በመሆን በሀገር ውስጥና በውጭ ባለሙያዎች ማዘጋጀታቸውን ተገልጿል።
የአርቲፊሻል ቴክኖሎጂ የደረሰበትን ደረጃ ለማሳየት እንደሚረዳና የነገው ትውልድ ተረካቢ ሕፃናት ለሚሠሩት የፈጠራ ሥራዎች አጋዥ እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን በቅርቡ የሙዚቃ ኮንሰርት ታዘጋጃለች ተብሏል፡፡
በደስታ ሮቦት የፕሮግራሚንግ እና የቋንቋ ሥርዓት ላይ ኢትዮጵያውያን መሳተፋቸውም ተጠቁሟል፡፡
በ5ጂ ኔትዎርክ ቴክኖሎጂ አማካኝነት የተገናኘችው ሮቦቷ ሰው ከሚመስል የፊት ገጽታ ባሻገር የሰዎችን መሠረታዊ እንቅስቃሴዎች ማከናወን እንደምትችል ታውቋል፡፡
ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You