ሃይማኖት፣ እንደ ማኅበረሰብም፣ እንደ ግለሰብም ከፍ ያለ የመተሳሰብ፣ መደጋገፍና የአብሮነት እሴቶችን የሚያጎናጽፍ መንፈሳዊ ኃይል አለው፡፡ ይሄ መንፈሳዊ ኃይል ደግሞ በግለሰቦች አልያም በማኅበረሰቦች መካከል የሚኖርን የእርስ በእርስ መስተጋብር ቀናና ሠላማዊ የሚያደርግ ነው፡፡
ይሄው ሃይማኖታዊ ልዕልናም ነው በተለይም በሃይማኖታዊ በዓላት ወቅት በሰው ልጆች መካከል ከፍ ያለ የመተሳሰብና መደጋገፍ እሴትን እንዲገለጥ የሚያደርገው፡፡ ያሳለፍነው ወርሐ መጋቢትም፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በዚህ መልኩ የሚገለጡ አያሌ ተግባራት የታዩበት፤ በተለይም በእስልምናም ሆነ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በጋራ የጾሙበት ወር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍ ያለ መንፈሳዊ ተግባራት ሲከናወኑበት ቆይተዋል፡፡
የየሃይማኖቶቹ አስተምህሮቶች በሚፈቅዱትና በሚያዝዙት መጠንም አማኙ ሲተጋ፤ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅርና ክብርም ሲገልጥ ቆይቷል፡፡ ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ደግሞ፣ ትናንት መቋጫውን ባደረገው የታላቁ ሮመዳን ወር በእለተ ኢድ አልፈጥር፣ በሕዝበ ሙስሊሙም ሆነ በሌላው ኢትዮጵያዊ ዘንድ የነበረው መንፈስ ልዩ ነበር፡፡
ሕዝበ ሙስሊሙ በጋራ ኢድን ሰግዶ በጋራ በዓሉን ከማሳለፍ ባለፈ፤ አንዱ ከሌላው ሲያደርግ የነበረው የመተሳሰብና አብሮነት ሁነት የኢትዮጵያውያንን የመተሳሰብ ልዕልና የገለጠ ሆኗል፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙ ብቻም ሳይሆን፣ የሌሎች እምነቶች ተከታዮች ጭምር በየጉርብትናው የነበረው ማኅበራዊ መስተጋብር፣ ለበዓሉ ድምቀትም፤ ለኢትዮጵያውያን የአብሮነት እሴትም ዘላቂነት ከፍ ብሎ የሚናገር ተግባር ነበር፡፡
ዜጎቿ በየሃይማኖታዊ በዓላት ወቅት ያላቸው ይሄን መሰሉ የመልካምነት ተግባር ደግሞ 99 በመቶ ሕዝቧ አማኝ (ሃይማኖተኛ) ነው ለሚባልላት ኢትዮጵያ ቀጣይ የአብሮነት መንገዷን በመልካም እንዲገለጥ የሚያስችል ነው፡፡
ሊዘነጋ የማይገባው ጉዳይ ግን፤ ሃይማኖት እና ሃይማኖተኛ በመልካም ምግባር ሊተሳሰሩ የሚገባቸው በሃይማኖታዊ ወራት አልያም በዓላት ወቅት ብቻ ነውን? የሚለው ዐቢይ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ላይ የሚታዩ የሠላም መደፍረሶች፤ መፈናቀልና የኑሮ ጫናዎች እየተፈጠሩ ያሉት በእኛው ሃይማኖተኛ ነን በምንል፤ በእኛው ፆምና ኃይማኖታዊ በዓላትን እየጠበቅን መልካም በምንሆን ሃይማኖተኞች ነው፡፡
ይሁን እንጂ አንድ ሃይማኖተኛ፣ ሃይማኖታዊ አስተምሕሮው የሚያዝዘው ቀን እና ወር መርጦ፣ ጊዜ ለይቶ መልካም አልያም ክፉ እንዲሆን አይደለም፡፡ ይልቁንም በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ የሰው ልጆች እርስ በእርሳቸው እንዲዋደዱ፣ እንዲረዳዱ፣ እንዲተሳሰቡ፣ አንዳቸው ለአንዳቸው አለኝታ እንዲሆኑ፣ በሠላምና በፍቅር አብረው እንዲኖሩ ነው፡፡
አንድ አማኝ ደግሞ፣ በትክክል የእምነቱን መንገድ የሚከተል፤ ትዕዛዙንም ለመፈጸም ራሱን ያስገዛ ከሆነ፣ እነዚህን ነገሮች ገንዘቡ ሊያደርግ የተገባ ነው፡፡ ከሰው ልጆች ጋር ፍቅርና ኅብረትን ሊያጸና እንጂ ፀብና መለያየትን ሊያነግስ አይገባውም፡፡ ለሰው ልጆች መልካም ነገርን ከማሰብና ከማድረግ የዘለለ፣ በሰው ልጆች ላይ ክፋትንና ጥቃትን ለማድረስ ማሰብም ሆነ መንቀሳቀስ አይገባውም፡፡
አንድ ሃይማኖተኛ፣ ለሰው ልጆች ሠላምና አብሮነት ብቻ ሳይሆን፤ ለሰው ልጆች ሠላማዊና ምቹ የኑሮ ከባቢ እንዲፈጠር አብዝቶ ይተጋል፡፡ የሰው ልጆች ሠላማዊ ኑሮን፣ የተመቻቸ ከባቢን ማግኘት የሚችሉት ደግሞ፣ የሚኖሩባት ሀገር ሠላሟ የተጠበቀ፣ ልማቷም የተሳለጠ መሆን ሲችል ነው፡፡
በመሆኑም የትኛውም ሃይማኖተኛ፣ በፈጣሪው አምሳል ለተፈጠረ የሰው ልጅ መልካም ነገርን ሲያስብ፤ የሚኖርበትን ከባቢ ሠላማዊም፣ ምቹም በማድረግ ሂደት ውስጥ ድርሻዬ ምንድን ነው ብሎ ራሱን መጠየቅ፤ በዛው ልክም ለዚህ መልካምነት መትጋት ይጠበቅበታል፡፡
በዚህ ረገድ ባለፈው ወር በፆም እና ትናንትንም በኢድ አልፈጥር ዕለት የታዩ የመልካምነት፣ የመተሳሰብ፣ የመደጋገፍ፣ የመረዳዳትና የአብሮነት ሁነቶች፤ በጊዜ እና በሁኔታ ሳይታጠሩ በቀጣይነት መገለጥ ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህ መገለጦች ደግሞ ለሰው ልጆች ካለን መልካም እሳቤ ጋር የተቆራኙ ሊሆን ያስፈልጋል፡፡
ምክንያቱም መልካም ተግባር የሚመነጨው ከልብ ሀሳብ ነው፡፡ የልባችን ሀሳብ ሠላም ሲሆን፣ ስለ ሠላም እንተጋለን፤ የልባችን ሀሳብ ፍቅር ሲሆን፣ ስለ ፍቅር እንተጋለን፤ የልባችን ሀሳብ የዜጎች እና የሀገር መበልጸግ ሲሆን፣ ስለ ሀገርና ሕዝብ ብልጽግና እንተጋለን፡፡ በመሆኑም በሃይማኖታዊ በዓላት ወቅት የታዩና የሚታዩ መልካም ተግባራት፤ ከበዓላት ዓውድ ባሻገር ባለው ዘላቂ የሰው ልጆች ሠላም፤ የሀገርም ልማት ላይ እንዲገለጡ ሁሌም አብረውን የሚኖሩና የሚገለጡ ሀብቶቻችን ልናደርጋቸው ይገባል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2016 ዓ.ም