የወተት ሃብት ኢንቨስትመንቱ አርዓያነት ያለው ተሞክሮ

ኢትዮጵያ ምንም እንኳን አብዛኛው ዜጋዋ በግብርና ሥራ ላይ የሚተዳደር እና ኢኮኖሚዋም በግብርና ላይ የተመሠረተ ቢሆንም፣ የአመራረት ሂደቱ ኋላቀር፣ በአነስተኛ መሬት ላይ የሚካሄድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዘርፉ ለሃገር እድገት የሚገባውን ያህል ሳያደርግ መቆየቱ ይጠቀሳል፡፡ ለግብርና ልማት ምቹ የአየር ሁኔታና ሥነ-ምህዳር ያላት ሃገር ብትሆንም የዘርፉ አመራረት ከአነስተኛ አቅም ወጥቶ በግዙፍ ኢንቨስትመንት ሳይደገፍ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

እርግጥ በተለይም የለውጡ መንግሥት መምጣቱን ተከትሎ የእያንዳንዱን አርሶ አደርና አርብቶ አደር ምርትና ምርታማነት ሊያሳድጉ የሚችሉ እንዲሁም የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፉን አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም የአሠራር ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ ይህም በተጨባጭም የአርሶ አደሩን ሕይወት የሚለውጡ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እያስገኘ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ጥቂት የማይባሉ ባለሃብቶችንም እየሳበ ይገኛል፡፡ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ እድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ተቋቁመው ሃገራቸውንና ሕዝባቸውን በኢኮኖሚ ለማሳደግ ቆርጠው የተነሱ ባለሃብቶችም በዘርፉ እየተፈጠሩ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህ ባለሃብቶች መካከል አቶ አድማሱ አርፍጮ አንዱ ናቸው፡፡ ግለሰቡ ትውልዳቸውም ሆነ እድገታቸው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከንባታ ዞን ዳምቦያ ወረዳ በምትገኘውና ሄጎ በምትባለው የገጠር ቀበሌ ነው፡፡ እድገታቸው እንደ አብዛኛው የአርሶ አደር ልጅ አነስተኛ ገቢ ካለው ቤተሰብ ውስጥ ሲሆን፣ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በአካባቢያቸው ለወጣቶች የሚሆን የሥራ ዕድልም ሆነ የልማት እንቅስቃሴ ባለመኖሩ ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን ከችግር ለማውጣት ሲሉ ለስደት መዳረጋቸውን አቶ አድማሱ ይናገራሉ፡፡

‹‹ማንም ሰው ቢሆን ተመችቶት ከሃገሩ አይወጣም፤ እንደአጋጣሚ ሆኖ ወቅቱ ጥሩ ስለነበር ተሳካልኝ እንጂ እስከሞት የሚደርስ አደጋ ሰለባ ልሆን የምችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነበር›› ሲሉ የስደት ሕይወታቸውን አስታውሰው፤ በተለይም ደቡብ አፍሪካ ለመድረስ ሲሉ ያለፉባቸውን ፈታኝ ሁኔታዎች ከባድ እንደነበሩ ይጠቅሳሉ፡፡ ለ20 ዓመታት በቆዩባት ደቡብ አፍሪካ እንደማንኛውም ስደተኛ ከዝቅተኛ ሥራ ጀምሮ ሥራ ሳይመርጡ በመሥራታቸው በጥቂት ዓመታት ጥሪት ቋጥረው የግላቸውን የንግድ ሥራ መጀመራቸውን ያመለክታሉ፡፡

ሥራ ወዳድና አዲስ ነገር ለመቀበል ሁሌም ዝግጁ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ አድማሱ፣ በሂደት ባፈሩት ሀብት በዚያው በስደት ሃገር በሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍና በንግድ ሥራ ከፍተኛ ደረጃ ከደረሱ ኢትዮጵያውያን አንዱ መሆን ችለዋል፡፡ ሆኖም የሚሠሩት ለባዕድ ሃገር መሆኑና ይህች ሃገር ደግሞ በኢኮኖሚ ደረጃ የላቀች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአንፃሩ ደግሞ ሳይማር ያስተማራቸው ሕዝብ በድህነት እየማቀቀ መሆኑን ሲያስቡ ቁጭት ያድርባቸው እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹ሃገርና ሕዝብ የእኔን ድጋፍ በጠየቀ ቁጥር ያቅሜን ከማድረግ ወደኋላ ቀርቼ አላውቅም፤ ዓባይ ግድብ እንኳን ሲጀመር በደቡብ አፍሪካ የሚኖረውን ኢትዮጵያውያንን አስተባብሬ 25 ሚሊዮን ብር አሰባስቤ ድጋፍ እንዲደረግ ሠርቻለሁ›› ይላሉ፡፡ ይሁንና ይህ ብቻውን እርካታ አልሰጣቸውምና ወደ ሀገራቸው በመምጣት ከተወለዱበት ቀዬ ዘልቀው ዛሬም በድህነትና በመሠረተ ልማት እጦት እየተሰቃየ ያለውን ማኅበረሰብ አማከሩ፡፡ የማኅበረሰቡ የመጀመሪያ ጥያቄ በአካባቢያቸው በአያያዝ ጉድለት የተጎዳውን የእርሻ መሬት የሚመልስ ሥራ እንዲሠሩ ነበር፡፡ ቀድሞውንም ችግኝ መትከልና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ የልጅነት ሕልማቸው ነበርና በእዚህ ላይ አላንገራገሩም፡፡ ከኅብረተሰቡ ባገኙት 10 ሄክታር መሬት እንዲሁም አምስት ሄክታር መሬት ለአርሶ አደር ካሣ ከፍለው በድምሩ በ15 ሄክታር ልማቱን ጀመሩ፡፡

በቅድሚያም ከፍተኛ በጀት በመመደብና ባለሙያዎችን በመቅጠር የተራቆተውንና የተጎዳውን መሬት ማገገም የሚያስችሉ ተግባራትን አከናወኑ፤ በመቀጠልም ከደቡብ አፍሪካ ድረስ የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን ችግኞች በማስመጣት ተከሉ፡፡ የደን ልማቱ ሥራ እየጎመራ ሲመጣ ደግሞ ጎን ለጎን ሕዝቡን የሚጠቅሙ ተጨማሪ የልማት ሥራ መሥራት አለብኝ ብለው አሰቡ፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሳሉም አካባቢው ለወተት ሃብት ልማት ምቹ መሆኑን ተገነዘቡ፡፡ የዓለም የወተት ቀን ሲከበር በተመለከቱት መሠረት የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ከብቶች ለልማቱ ወሳኝ መሆናቸውን ተረዱ፡፡ በሌላ በኩል ባለሙት ጫካ ውስጥ ያለው የግጦሽ ሣር ጋር ተዳምሮ እሳቸውም በወተት ሃብት ልማት ቢሠማሩ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመኑ፡፡

ጊዜ ሳያጠፉም አስር ሚሊዮን ብር በመመደብና የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸውን ጊደሮች በመሰብሰብ የከንዓን ጥምር ግብርና ኢንቨስትመንትን መሠረቱ፡፡ ከአካባቢው ያገኟቸውን ጊደሮች ከእስራኤል ምርጥ ኮርማዎች ጋር በማዳቀል የከብቶቻቸውን መጠን ከፍ አደረጉ፡፡ አሁን ላይ 65 የሚደርሱ ከብቶች በጥምር ግብርና ኢንቨስትመንቱ ያሉ ሲሆን፣ በተጓዳኝም 300 ዶሮዎችን እያረቡ ይገኛሉ፡፡ በ100 ዘመናዊ ቀፎችም የንብ ማነብ ሥራ ጀምረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በጥምር ግብርና ኢንቨስትመንቱ በቀን 300 ሊትር ወተት ይታለባል፤ ወተቱንም በአካባቢው የሚገኙ አቅመ ደካማ ሴቶች ተደራጅተው በቅናሽ ዋጋ ወስደው ለገበያ እንዲውሉ አድርገዋል፡፡ ባለሃብቱ በተጓዳኝም ማኅበረሰቡም ሆነ ወረዳው የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ኮርማዎች ዘረ-መል በነፃ በመስጠት የአካባቢው የወተት ሃብት ምርታማነት እንዲጎለብት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ከኢንቨስትመንቱ ባሻገር ለዘመናት በጨለማ ይኖር ለነበረው የመንደራቸው ሕዝብ በራሳቸው ወጪ ትራንስፎርመር አስተክለው የመብራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም ክረምት በመጣ ቁጥር ፍዳውን ያይ የነበረው የሄጎ ቀበሌ ነዋሪ በኢንቨስተሩ ቀናነት አምስት ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ተሠርቶለት እፎይ ብሏል፡፡ በአጠቃላይ የኢንቨስትመንት ሥራዎች 60 በላይ ዜጎች ቋሚ እንዲሁም ከ250 ለማያንሱ ሰዎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል፡፡

‹‹ትልቁ ዓላማዬ የአካባቢውን ማኅበረሰብ መጥቀም ነው›› የሚሉት ኢንቨስተር አድማሱ፣ በተለይም የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚ ማሳደግ በሚያስችሉ የልማት ሥራዎች ላይ መዋለ ንዋያቸውን በማውጣትና ምርቶቻቸውንም ወደ ውጭ በመላክ ለሃገርም የውጭ ምንዛሪ ግኝት ምንጭ ለመሆን ራዕይ ሰንቀው እየሠሩ መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡ አቶ አድማሱ ‹‹ወደ ኢንቨስትመንቱ ስንገባ 10 ሚሊዮን ብር ነው የነበረን፤ አሁን ኢንቨስትመንቱ ወደ 100 ሚሊዮን ከፍ ብሏል›› ይላሉ፡፡ ይህንንም ካፒታል በእጥፍ በማሳደግ ለግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ እድገት ወሳኝ ሚና ለመጫወት አቅደው እየሠሩ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹የተሻሻለ ከብት ዝርያ ልማቱ በአካባቢው በሙሉ በደንብ ሲስፋፋ ማሽን በመትከል አሁን የምንሰጠውን ወተት መልሰን ከማኅበረሰቡ በመሰብሰብና በማቀነባበር ምርቶቻችንን እስከ ውጭ ድረስ የመላክ እቅድ ይዘናል›› ሲሉም ያብራራሉ፡፡ ይህም ለበርካታ የአካባቢው ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል የሚል ትልም አላቸው፡፡

ይህ ራዕያቸው እንዲሳካ ግን በተለይ እንደ መብራት፣ ውሃና መንገድ ያሉ መሠረተ ልማቶች በመንግሥት በኩል እንዲሟሉም ጠይቀዋል፡፡ ‹‹የመብራትና የውሃ ችግር ሥራችንን ለማስፋፋት ፈተና ሆኖብናል፤ በድርጅታችን ሙሉ ወጪ ያስገነባውም የውስጥ ለውስጥ መንገድ በዋናው መንገድ ሥራ ሰበብ እየፈረሰና መልሶም እየተጠገነ ባለመሆኑ መስተጓጎል ፈጥሮብናል›› ሲሉም ኢንቨስተር አድማሱ ያብራራሉ፡፡ ያም ቢሆን ግን ለገጠማቸው ተግዳሮት እጅ ሳይሰጡ የሚችሉትን በራሳቸው አቅም እያሟሉ የኢንቨስትመንት ሥራቸውን ማስፋፋታቸውን እንደሚቀጥሉም ነው የሚያመለክቱት፡፡

ልክ እንደእሳቸው ሁሉ ከተለያዩ ሃገራት መጥተው ሃገራቸው ላይ መዋለ ንዋያቸውን አፍስሰው ልማት የጀመሩ ጥቂት የማይባሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን አንዳንድ ቦታዎች ላይ በሚስተዋለው አለመረጋጋትና በቢሮክራሲ የታጠረ የመንግሥት አሠራር ተስፋ ቆርጠው ወደመጡበት ሃገር መመላሰቸውንም አይሸሽጉም፡፡ ‹‹በሃገር ተስፋ አይቆረጥም፤ ደግሞም አሁን ያለው ችግር መፈታቱ፤ ሃገርም ሠላም መሆኗ አይቀርም፤ ያን ጊዜ ደግሞ አሁን ያለው ምቹ ዕድል እንደልብ ላይገኝ ስለሚችል ሸሽተው የሄዱ ባለሃብቶች ወደፊት እንዳይቆጫቸው ተመልሰው ሕዝባቸውና ሃገራቸውን ሊያገለግሉ ይገባል›› ሲሉም ምክረ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

ከሌሎች ኢንቨስትመንቶች ይልቅ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ መሠማራት የተለያዩ ተግዳሮቶች ያጋጥማሉ ሲሉም ጠቅሰው፤ ፈተናውን ሁሉ ተቋቁሞ ሕዝቡን ማገልገል የግድ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ምክንያቱም የተወለድነው ከዚያ ማኅበረሰብ በመሆኑ የዚህን ሕዝብ ችግር መካፈል አለብን፡፡ ደግሞም የእኛ ተንደላቆ መኖር ብቻውን በቂ አይደለም›› ይላሉ፡፡

በመሆኑም እያንዳንዱ ዲያስፖራ ሌላ ሃገር ሲኖር ያገኘውን ልምድ በመቀመር ሕዝቡን የሚጠቅሙ ልማቶች ላይ መሳተፍ እንዳለበትም ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹ችግሮችን በማየት ሀገር ጥሎ መሄድ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ችግሮችን ተቀብሎ ነገሮች ይቀየራሉ ብሎ ተስፋ ሰንቆ መንግሥትንም እየደገፉ መሥራት አለበት›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡

‹‹አሁን ላይ እኔ ትርፍ አልጠብቀም፤ ዛሬም ድረስ ኢንቨስት እያደረኩ ነው ያለሁት፡፡ ሥራው ዋጋ ቢያስከፍለኝም ነገ ውጤት እንደሚያመጣ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ኅብረተሰቤን ማገልገል በራሱ ትልቅ ነገር እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ ሌሎችም የእሳቸውን ተሞክሮ እንዲቀስሙ ይመክራሉ፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ከሌሎች ሃገራት የተሻለ ምቹ የአየር ንብረትና ሥነምሕዳር እንዳለ ጠቅሰው፣ ዜጎች በግብርና ኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ቢሠማሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አመልክተዋል፡፡

የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ተክሌ ኃይለማርያም(ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ባለሃብቱ ለ20 ዓመታት በውጭ ሃገር ያገኙትን ሃብት በሀገራቸው ሥራ ላይ በማዋል ከፍተኛ አደጋ ውስጥ የነበረውን የአካባቢውን የተፈጥሮ ሃብት በመታደግ ረገድ ያከናወኑት ሥራ ለግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ወሳኝ ሚና አበርክቷል፤ እያበረከተም ይገኛል፡፡ በዚህ ሥራቸው ተመናምኖ የነበረው ደን አሁን ተመልሷል፤ የአካባቢው ልምላሜና እርጥበትም አንሰራርቷል፡፡ አካባቢው የእንሳሳት ሃብት በስፋት የሚገኝበት እንደመሆኑ ለከብት መኖ የሚውሉ የሣር ዝርያዎች በስፋት በመብቀላቸው ኅብረተሰቡ ለመኖ ግዢ ያወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ማስቀረት አስችሏል፡፡

በጥምር ግብርና ኢንቨስትመንቱ በየቀኑ የሚታለበው ወተት ደካማና ደጋፊ የሌላቸው የአካባቢው እናቶች በቅናሽ ዋጋ የሚያገኙበት ሥርዓት በመበጀቱ ሲያሻቸው አትርፈው ለመሸጥ፤ አሊያም ቂቤና አይብ በማድረግ ለቤተሰባቸውና ለተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ ማድረጉ በርካቶች ከድህነት እንዲወጡ የበኩሉን አስተዋፅዖ እያበረከተ መሆኑን ተክሌ (ዶ/ር) ያመለክታሉ፡፡

‹‹ድርጅቱ ከሁሉም በላይ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን ኮርማዎች ዘረ፟መል በነፃ የሚያሰራጭ መሆኑ ለከንባታ ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን እንደሃገርም በቀንድ ከብት ሃብት የላቀ ተጠቃሚ እንድንሆን ያደርጋል›› ይላሉ፡፡ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በአካባቢው ያለውን የመሠረተ ልማት ችግር በመፍታት ድጋፍ እንዲያደርጉ እሳቸውም ጠይቀዋል፡፡

ማሕሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2016 ዓ.ም

Recommended For You