የእርቅ፣ የይቅርታ፣ የፍቅር ተምሳሌት፣ አባት፣ ረቡኒ/አስተማሪ/ የሆኑት የደቡብ አፍሪካ የፀረ አፓርታይድ ትግል መሪና የነፃዋ ደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ/ማዲባ/ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1995 ለንባብ በበቃው” Long Walk to Freedom” በተሰኘው ድንቅ ግለ ታሪክ መፅሐፋቸው፤” ሁሉም ሰው ጥላቻን ተምሮ እንጂ ከእናቱ ማህፀን ይዞት አልተወለደም፡፡ ጥላቻን የተማረ አዕምሮ ደግሞ ፍቅርንና እርቅን መማር አይከብደውም” ብለዋል፡፡
በሩዋንዳ በጥላቻ ታውረው የገዛ ዜጎቻቸውን የጨፈጨፉ፤ ስድስት ሚሊዮን አይሁዶች በግፍ የፈጀው ናዚ ሆነ፤ በሀገራችን የተንሰራፋው ጥላቻም ሆነ በየዕለቱ የምናየውን ሰቆቃ የሚፈጽሙት ከእናታቸው ማሕጸን ይዘውት የተወለዱት ሳይሆን ለዓመታት ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ የተጋቱት ጥላቻ ውጤት ነው። ማናችንም ብንሆን ጥላቻን ተጋትነው እንጂ ከእናታችን ማሕፀን ይዘነው አልተወለድንም ፡፡
ከእናታችን ማሕፀን ይዘነው ያልተወለድነውን ግን በአንድም ሆነ በሌላ መልክ የተማርነውን ጥላቻ፣ ልዩነትና ቂም በቀል፤ ከአዕምሮአችን ለመሰረዝ፣ ለማጥፋት እንደ ኔልሰን ማንዴላ ካሉ ባለግዙፍ ተክለ ሰብዕና ባለፀጋዎች መማር እንችላለን፡፡ አዎ! ከእነ ማሕተመ ጋንዲ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ ተዝቆ የማያልቅ የይቅርታ መዝገብም መማር ይቻላል፡፡ ለዛውም ጥላቻን ከመማር ይልቅ ፍቅርንና ይቅርባይነትን መማር ይቀላል፡፡ ምክንያቱም ፍቅር ይቅር ባይነት አምላካዊ ሲሆን ጥላቻ ደግሞ ሰይጣናዊ ነው ፡፡
የሰው ልጅ አምላኩ በአምሳሉ የፈጠረው ስለሆነ አዕምሮው ለፍቅር፣ ለይቅርታ ይቀርባል፡፡ ያደላል፡፡ ከማዲባ ወይም የቀድሞው የነፃነት ታጋይና መሪ ማንዴላ ይቅርባይነት ያረጋገጥነው ይሄንኑ ነው፡፡ መቼም ስለ ፍቅር፣ ይቅርባይነት በተነሳ ቁጥር ከፈጣሪ ቀጥሎ ስሙ የሚወሳው ማንዴላ ነው፡፡ ከፍ ብዬ በጠቀስሁት መጽሐፉ ስለ ይቅርባይነት ከፍታና ኃያልነት ፤” ይቅርባይነት ነፍስን አርነት ያወጣል፡፡ ፍርሀትን ያስወግዳል፡፡” ሲል እማኝነቱን፣ ምስክርነቱን ገልጿል ፡፡
ወንድሞች ይቅር በመባባል ነፍሳችንን ከባርነት ነፃ እናውጣ፡፡ በይቅርባይነት ቀይዶ አላላውስ ካለን የፍርሃት ቆፈን እንላቀቅ ፡፡ ወገኖቼ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የበደልኋችሁ፤ በዚህ ጋዜጣ በምጽፋቸው መጣጥፎች የተቀየማችሁ ብትኖሩ ከእግራችሁ ስር ወድቄ ይቅር እንድትሉኝ እለምናለሁ፡፡ እንዲሁም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የበደላችሁኝንም ከልብ ይቅር ብያለሁ፡፡ ለመንደርደሪያ ያህል ይሄን ካልሁ፤ ሰሞነኛውን የሩዋንዳ የዘር ፍጅት ወይም ጄኖሳይድ 30ኛ ዓመት ሰበብ በማድረግ ብንማርበት በሚል እስያኤል ዘ ኢትኤል፣ “የሩዋንዳ ቆይታዬና የተማርኩት፤” በሚል ያስነበበንን መጣጥፍ ላጋራችሁ ወደድሁ።
ሩዋንዳ ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ውስጥ አንዷ ናት፤ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሀገር ስትሆን አብዛኛውን መልክዓ ምድሯ ተራራማ ቦታ ሲሆን “የሺህ ኮረብቶች ምድር” በመባል ትታወቃለች፡፡ ከአፍሪካ ታላላቅ ሐይቆች አንዱ በሆነው ከምድር ወገብ በስተደቡብ እና ከኪቩ ሐይቅ በስተምሥራቅ የምትገኝ በመካከለኛው አፍሪካ ያለች ትንሽ ወደብ የለሽ፣ ኮረብታማ አገር ነች። እኔ ከተወለድኩበት ታላቁ የስምጥ ሸለቆ የምዕራብ ጫፍ ላይ የምትገኝ በሰሜን ከዑጋንዳ፣ በምስራቅ ከታንዛኒያ፣ በደቡብ ከብሩንዲ፣ በምዕራብ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ (ኪንሻሳ) እና ከኪቩ ሐይቅ ትዋሰናለች።
አገሪቷ 26,338 ኪሜ² ስፋት ያላት ሲሆን ከሌሎች ሀገሮች አንጻር ስትነጻጸር መቄዶንያ (ሪፐብሊክ) ታክላለች፣ ወይም ደግሞ ከአሜሪካ የሜሪላንድ ግዛት በመጠኑ አነስ ያለች ነች፡፡ እ.ኤ.አ 2016 በተገኘ መረጃ መሠረት 11.5 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሲሆን (የሩዋንዳ የሕዝብ ብዛት ከሰሐራ በስተደቡብ ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ትልቁ ነው፡፡) ዋና ከተማዋ እና ትልቁ ከተማዋ ኪጋሊ የምትባል ሲሆን ወደ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ነዋሪዎች ይገኙበታል፡፡ አብዛኛው ሕዝብ የሚናገረው ቋንቋዎች መካከል ኪንያሩዋንዳ (የሩዋንዳ ኦፊሴላዊ ቋንቋ)፣ እንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ፣ ስዋሂሊ በብዛት ይነገርባታል፡፡
በ1890ዎቹ ጀርመን ሩዋንዳን በቅኝ ግዛት ስር አደረገቻት፡፡ እ.ኤ.አ. በ1916 ፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ፣ ጀርመን በእሷ ቅኝ ግዛት ስር የነበረችውን ሩዋንዳን ቤልጂየም በቅኝ እንድትገዛት ፈቀደችላት። በመቀጠልም ቤልጂየም ለአገዛዝ እንዲመቻት እያንዳንዱን ሰው ሁቱ (84%)፣ ቱትሲ(15%)፣ ትዋ(1%) በማለት በመከፋፈል ለሁሉም ዜጎች የብሔር መታወቂያ ካርዶችን አዘጋጅታ ለሕዝቡ ሰጥታለች።
በመቀጠልም ቤልጂየሞች ቱትሲዎችን ሁሉንም የመንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች እንዲይዙ እና በሁቱዎች ላይ የበላይ ሆነው እንዲገዙ ወሰኑ፤ ይህም በሁለቱ ቡድኖች (ብሔረሰቦች) መካከል ከፍተኛ ውጥረት ፈጠረ። ቱትሲዎች ከሁቱዎች ተለይተው የተመረጡበት ምክንያት ተብሎ የሚታሰበት ቤልጂይማውያኑ ቱትሲዎቹን በረዥሙ እና ከታላቁ የሰውነት ቅርጻቸው የበለጠ “አውሮፓውያን” እንደሚመስሉ ያምኑ ስለነበረ ነው።
ይህ ዘዴ በአውሮፓ ሀገራት በያዙት ሀገራት ላይ ልዩነት በመፍጠር ሕዝቡን በመከፋፈል ለረዥም ጊዜ ለመግዛትና ሀገሪቱን በራሳቸው ሰው ከመምራት ይልቅ፣ በእነዚህ ምስለኔ የሀገሪቱ ዜጎች ማስተዳደሩ መልካም መሆኑን ስለተረዱና አዋጭ መሆኑን ስለተገነዘቡ ነው፡፡ በዚህም የቱትሲ ዘውዳዊ ሥርዓተ መንግሥት በማቋቋም በሁቱዎች ላይ የበላይ ሆነው እንዲያስተዳድሩ አድርጓዋል፡፡
ከጊዜ በኋላ ግን ቱትሲዎች ከቤልጅየም ነፃ ለመውጣት እንቅስቃሴ በመጀመራቸው ቤልጅየሞች በዚህ በመናደድ ሁቱዎችን በቱትሲዎች ላይ እንዲነሱባቸው የጥላቻ ዘመቻ ጀምሩ፡፡ ቱትሲዎች እስከ ኅዳር 1959 የሁቱ አመጽ እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ መንግሥትን መምራት ቀጠሉ። ሁቱዎች በፍጥነት ቱትሲዎችን እና የቤልጂየምን አገዛዝ በመገርሰስ በሺዎች የሚቆጠሩ ቱትሲዎችን ገድለው፤ የቀሩትን ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገሮች እንዲሰደዱ አደረጓቸው።
እ.ኤ.አ. ሐምሌ 1 ቀን 1962 ቤልጂየም ለሩዋንዳ በይፋ ነፃነቷን ሰጠች፤ ይህም አመጹ እንዲቆም አድርጓል። በዚያን ጊዜ ሁቱዎች የመንግሥት ሥልጣን ተቆጣጥረው ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1959 ከነፃነት 3 ዓመታት በፊት ቀደም ብሎ፣ አብላጫው ብሔረሰብ ሁቱ ገዢውን የቱትሲ ንጉሥ አስወገዱ። በሚቀጥሉት በርካታ ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ቱትሲዎች ተገድለዋል። በነበረው የእርስ በእርስ ግጭት ከ150,000 ሺ እስከ 300,000 ሺ የሚጠጉ ቱትሲዎች ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል።
እ.ኤ.አ. ጥቅምት 26 ቀን 1962 የሁቱ ተወላጅ ግሬጎየር ካይባንዳ የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ። ሁቱዎች በሩዋንዳ ላይ ሥልጣን ከመያዛቸው ቱትሲዎችን ማፈናቀላቸውንና መበቀላቸውን ቀጠሉ። እንደ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በ1960ዎቹ አጋማሽ ከመጀመሪያዎቹ ቱትሲዎች ግማሹ ከሩዋንዳ ውጭ ይኖሩ እንደነበር ይገመታል። ከዚህ እንደምንረዳው ከከፍተኛ እልቂት ከተፈጸመበት ጊዜ አስቀድሞ ብዛት ያለው ግድያዎችና ማፈናቀሎች እንደነበረ መረዳት ግድ ይለዋል፡፡
የእነዚህ ግዞተኞች ልጆች የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር (RPF) የተባለውን አማፂ ቡድን አቋቁመው በ1990 የእርስ በርስ ጦርነት ጀመሩ። ጦርነቱ ከበርካታ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውጣ ውረዶች ጋር፣ በኤፕሪል 1994 ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ቱትሲዎች እና ለዘብተኛ ሁቱዎችን የዘር ማጥፋት ዘመቻውን ያባባሰው። ከእነዚህ ሁሉ ታሪክ በፊት ግን በሩዋንዳ ሦስቱም ማኅበረሰቦች በመጋባት፣ በመዋለድና በጋራ በመኖር ባሕላቸውን ጠብቀው ይኖሩ ነበር፡፡ ሀገር ሁሉም ብሔረሰቦች አብረው በጋራ ጠላቶቻቸው በጋራ በመመከትና በደህናው ጊዜ እርስ በእርስ በመጋባት፣ ግጭቶች ሲኖሩ በባሕላዊ ግጭት አፈታት ችግራቸውን በመፍታት በትብብርና ተደጋግፈው ይኖሩ ነበር፡፡
ይህ ሁኔታው ቢለያይም በሌሎች ሀገሮችም ያለ የሚኖር የማኅበረሰብ አኗኗር ዘይቤና ትስስር ነው፡፡ ሰዎች በቡድን ሲኖሩ የተወሰኑት መሪዎች ሌሎቹ ደግሞ ተመሪዎች ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን ማኅበረሰቡ እነዚህ መሪዎች ከየትኛውም የማኅበረሰብ ክፍል ቢመጡ ማኅበረሰቡ ዋና ሀሳቡ በአግባቡ እየመሩ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ እንጂ ሌላ ሀሳብ የላቸውም፡፡ ከዚህ ውጭ ያለው ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ በጣም ጠንካራ ሲሆን በተለይም በሁቱና ቱትሲዎች መካከል ያለው ግንኙነት በጣም ጠንካራ ነው፡፡ አብሮ መጨፈር፣ መብላትና መጠጣት፣ የባሕል ለባሕል ልውውጥ ማድረግ ነበር፣ ክፋትና መጥፎ አስተሳሰብ ሳይዘራ በፊት በፍቅርና በመተጋገዝ አብረው ይኖሩ ነበር፡፡
ነገር ግን በሁለቱ ብሔረሰቦች መካከል በደንብ እንዲከፋፈሉ አንዱን ብሔረሰብ በመጥቀም ሌላውን በማግለል ቅራኔ እንዲሰፋ ያደርጋሉ፡፡ አንድን ብሔረሰብ አባላት ወደ ሥልጣን በማምጣት ሌላው ብሔረሰብ የተገፋ እንዲመስለው በማድረግ ጥላቻንና በቀልን እንዲቆጥሩ ጊዜና ሁኔታ እስኪፈጠር እንዲጠብቁ ያደርጋል፡፡ ይህ ሁኔታ በሩዋንዳ የታየ ሲሆን በተለይም ቤልጅየሞች ቱትሲዎችን ወደ ሥልጣኑና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ሁቱዎች የተገፋ እንዲመስላቸው አድርገዋል፡፡
በሩዋንዳ ባየሁት ሁኔታ በቱትሲዎችና ሁቱዎች መካከል ይህ ነው የሚባል ሰፋ ልዩነት ያላቸው ሕዝቦች አይደሉም፡፡ ለምሳሌ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው የሚጠቀሙት መግባቢያ ቋንቋ አንድ አይነት ነው፡፡ እንግዲህ አስቡት እንደ ኢትዮጵያ ባለሀገር የተለያዩ ቋንቋዎችና ባህሎች ባለበት ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡
በሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ጄቪናል ሀይኮሚን በ1973 በመፈንቅለ መንግሥት ወደሥልጣን ሲመጣ አዲስ አዋጅ አወጣ፤ ይኸውም ሀገሪቱ ላይ ያለው የሥልጣን ቦታዎች ሀገሪቷ ላይ ያለው የብሔር ስብጥር ሚዛን የጠበቀ መሆን እንዳለበትና ተማሪዎችም ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲመደቡ ከፍተኛው ቦታ አብዛኛውን ቁጥር ላላቸው ሁቱዎች ሲሆን ቀሪው ትንሽ ቁጥር ደግሞ ቱትሲዎችና ትዋ ብሔረሰቦች እንዲሆን አደረገ፡፡
ለዚህ ምክንያቱ ሁቱዎች በቁጥር ትልቁ ስለሆኑ ከፍተኛው የመንግሥት ሥልጣን ቦታዎችን መያዝ ያለባቸው እነሱ እንደሆኑ የሚደነግግ አዋጅ ነበር፡፡ በሩዋንዳ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ቡድን ወይም ኢንተርሀሙይ የተባለ ቡድን በማቋቋም በቱትሲ ማኅበረሰብ ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ አደራጅተዋቸው እና በመሣሪያ ድጋፍ አድርገው ለብዙኃን ዜጎች ሞት ምክንያት ዋና ተዋናይ ሆነዋል፡፡
የሩዋንዳው አይነት ድርጊት ሟችን ብቻ ሳይሆን ገዳይንም የጎዳው ስለሆነ ከዚህ ትምህርት ወስደን በቂ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡም ዘርን ያነጣጠሩ ግድያዎችን ሲያይ ዝም ከማለት ብዙ አደጋ ሳይደርስ አፋጣኝ እርምጃዎችንና ጫናዎችን በማድረግ፣ በተለያዩ ጊዜ እንደተፈጠሩት የዘር ፍጅቶች “Never Again” ወይም “በጭራሽ አይደገምም” እያለ ከአይሁዶች እስከ ሩዋንዳ ተመሳሳይ መፈክር ማሰማት ብቻ ሳይሆን በተግባር እንዳይፈጸም ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
ለዚህም በዓለም አቀፍ ያለው የዲፕሎማሲና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መሣሪያዎችንና መርሆችን ማዕከል ያደረጉ እርምጃዎችን በእንደዚህ አይነት መንግሥታት ላይ እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል፤ ነገሮች ከመዘግየታቸውና እልቂት ከመፈጠሩ በፊት አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ እንደዚህ ያሉ እልቂቶችን እንዳይፈጸሙ ማድረግ አለበት፡፡
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2016 ዓ.ም