የተባበሩት መንግሥታት(ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ፍልስጤም የተመድ ሙሉ አባል ለመሆን ያቀረበችውን ማመልከቻ ለሚመለከተው ኮሚቴ መርቷል። የፀጥታው ምክር ቤት ፍልስጤም ያቀረበችውን ማመልከቻ በዚህ ወር እንደሚመክርበት ተገልጿል።
የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት የፍልስጤም አስተዳደር ያቀረበውን የተመድ ሙሉ አባል የመሆን ማመልከቻ አዲስ አባል ለሚቀበለው የተመድ ኮሚቴ መመራቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
ማልታ የምክር ቤቱ የሚያዝያ ወር ፕሬዚዳንት ስትሆን የማልታ የተመድ አምባሳደር ቫኔሳ ፍራዚየር ኮሚቴው ማመልከቻውን ለማየት ትናንት ከሰዓት እንዲሰበሰብ ሀሳብ ማቅረባቸውን እና በዚህ ወር ውይይት እንደሚያደርግበት ገልጸዋል።
በተመድ የፍልስጤም ተወካይ ርያድ መንሱር የፀጥታ ምክር ቤት የሙሉ አባልነት ጥያቄያችንን በመቀበል ዓለምአቀፉ መግባባት የተደረሰበትን የ’ቱ ስቴት ሶሉሽንን’ ለመፈጸም ቁርጠኛ ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል። ፍልስጤም ከ12 ዓመታት በፊት በመተድ የታዛቢነት ቦታ ተሰጥቷታል።
የፍልስጤም አስተዳደር በ2011 ያቀረበውን ሙሉ የተመድ አባልነት ጥያቄ በድጋሚ እንዲያየው ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አቅርቧል።
15 አባላት ያሉት ምክር ቤቱ ማመልከቻው አባል ለመሆን የሚያስፈልገውን መስፈርት ማሟላቱን ይገመግማል። ከግምገማው በኋላ በቂ ሆኖ ከተገኘ ለውሳኔ በምክር ቤቱ ይቀርባል።
የአባልነት ጥያቄው የሚፀድቀው ቢያንስ ዘጠኝ አባላት ሲደግፉት እና ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸው ሩሲያ፣ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ካልተቃወሙት ብቻ ነው። በተመድ የእስራኤል አምባሳደር ጊላድ ኢርዳን ፍልስጤም ለእስራኤል የደኅንነት ስጋት ነች ሲሉ ተናግረዋል።
አምባሳደሩ ለእስራኤል የሀገርነት እውቅና መስጠት የተመድን ቻርተር የሚጥስ እና በድርድር ዘላቂ መፍትሔ እንዳይመጣ የሚያደርግ ነው ሲሉ ተቃውመዋል።
የዓረብ ሀገራት ከእስራኤል ጎን የፍልስጤም ሀገር ማቋቋም የሚያስችለው ‘የቱ ስቴት ሶሉሽን’ ተግባራዊ ካልሆነ በመካከለኛው ምሥራቅ ዘላቂ ሠላም አይመጣም የሚል አቋም ያራምዳሉ።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2016 ዓ.ም