ታላቁ ረመዳን በእስልምና መሰረቶች ሲቃኝ

እስልምና አምስት መሰረቶች እንዳሉት አብደላህ ኢብን ኡመር ኢብኑል ኸጣብ ከነብዩ መሀመድ መስማታቸውን ይናገራሉ:: የእምነቱ መሀል አንጓ ተደርገው ከተወሰዱት ውስጥ ሸሃዳ፣ ስላት፣ ዘካን፣ ሃጅ እና ፆም ይጠቀሳሉ:: ሁሉንም አንድ በዐንድ ለመመልከት ብንሞክር መነሻችን የሚሆነው ሸሀዳ ነው:: በእስልምና አስተምህሮት ወይም ደግሞ ከአምስቱ የእስልምና መሰረቶች አንዱ የሆነው ሸሀዳ ከአላህ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው፣ ከአላህ ሌላ የሚመለክ አምላክ እንደሌለ አጽንኦት የሚሰጥ የአስተምህሮ መሰረት ነው::

ሸሀዳ ዋነኛውና ተቀዳሚው የእስልምና መሰረት ሲሆን ለአንድ ሙስሊም የሙስሊምነት ማረጋገጫ የሚሰጥ የእምነቱ ቀዳማይ መሰረትም ነው:: አላህን እንደፈጣሪ የሚያገኝ፣ የሚሰብክ፣ የሚቀበል አስተምህሮ ነው:: ለዚህ ማረጋገጫ የሚሆነን በቅዱስ ቁርአን (አል-አንቢያ፣ 25 ላይ የተጠቀሰው ‹ከአንተ በፊትም እንሆ ከኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዛኝ በማለት ወደእርሱ የምናወርድለት ቢሆን እንጂ ከመልዕክተኛ አንድንም አላልክም› የሚለውን ጥቅስ በማስታወስ ነው::

ቀጣዩ የእምነት መሰረት ሰላት ነው:: በዚህ አስተምህሮ መሰረት አንድ ሙስሊም በቀን ውስጥ ለአምስት ጊዜ ያህል ጊዜውን የጠበቀ ስግደት ማድረግ አለበት:: ይሄ ሙስሊም ለሆነ ሁሉ ግዴታው ነው:: በሰላት ስግደት ወቅት እንደቅድመ ሁኔታም ከተቀመጡት መሀል ሙስሊም መሆን፣ የአእምሮ ጤነኝነት፣ ራስን መረዳት፣ ንጽህናን መጠበቅ፣ ሀፍረተ ገላን መሸፈን፣ የሰላት ወቅት መግባት፣ ፊትን ወደቂብላ ማዞር እና ለመስገድ ኒያህ ማድረግ ይጠቀሳሉ:: እንደዚሁ ሁሉ በሰላት ወቅት የተከለከሉ እንደመሳቅ፣ ማውራት፣ መብላት፣ መጠጣት፣ በስርዐት አለመልበስ፣ ከመጠን በላይ እንቅስቃሴ ማድረግ እና ውዱዕ ማጥፋት ፊተኛዎቹ ናቸው::

ሶስተኛው ዘካ ወይም ምጽዋት ነው:: እስልምና አማኙ ያለውን እንዲሰጥ፣ እንዲያካፍልና፣ ተባብሮ እንዲበላ የሚያዝ ነው:: ዘካ ወይም ምጽዋት ግዴታ የሚሆንበት ስርዐትም አለ:: ይህም ጥሬ ገንዘብ ያላቸው ባለሃብቶች የገንዘባቸው መጠን 85 ግራም ወርቅ ሊገዙ የሚችሉበት መጠን ላይ ሲደርሱ ሲሆን ከዚህ መጠን በላይ ጥሬ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች በየዓመቱ 2.5% ይከፍላሉ:: ለአብነት ያክል 20 ሺህ ብር ተቀማጭ ያለው ሰው ተቀማጩ ዓመት የሞላው ከሆነ የ 20 ሺህ ብር 2.5%

ማለትም 500 ብር ዘካት ይከፈልበታል ማለት ነው:: ባለ ሸቀጦች ከሆኑ የሸቀጡ ዋጋ በወርቅ ወይም በብር ተተምኖ የግዴታው ገደብ ከደረሰ ይከፍላል:: ይሄ የሚያሳየው እስልምናና ምጽዋት የተያያዙና ያለው ለሌለው ሰጥቶ ተካፍሎ የሚበላበት እንደሆነ ነው::

ሌላኛው የእስልምና መሰረቶች ሆነው ከተቀመጡት ውስጥ ጾም አንዱ ነው:: ጾም በቋንቋ ረገድ መታቀብ የሚለውን አቻ ፍች ይሰጠናል። ወደ ሸሪአዊ ትርጓሜው ስንወስደው ከጀምበር መውጣት ጀምሮ እስከ ፀሃይ መጥለቅ ድረስ ባለው ጊዜ ከምግብ፤ ከመጠጥ፤ ከግብር ስጋ ግንኙነት መታቀብ ማለት እንደሆነ አንረዳለን:: ጾምና ረመዳን ደግሞ አብረው የሚነሱ የእስልምና ድምቀቶች ናቸው::

ኢትዮጵያዊ መተሳሰብና መረዳዳት የታየበት ታላቁ ረመዳን ሕዝበ ሙስሊሙ ከፈጣሪው ጋር የሚገናኝበት፣ የሚታረቅበት እንደሆነ ይታመናል:: የዚህ ቅዱስ ወር ትሩፋት ከሆኑት ውስጥ የጀነት በር መከፈት፣ የጀሀነም በሮች መዘጋት፣ የሰይጣን መታሰር፣ የመልካም ስራ አጅር እጥፍ ድርብ መሆን በዋናነት ይጠቀሳሉ::

የረመዳን ወር ቅዱስ ወር ነው:: ቅድስናውን እንዴት አገኘ ብለን ስንጠይቅ ቁርአን የወረደበት፤ በውስጡ ከሺ ወር በላይ የሆነችውን ልዩ ሌሊት (ለይለተል-ቀድር) መያዙ፤ የመላኢካዎች እስቲግፋር፤ በተጨማሪም ቸልተኞች የሚቀሰቀሱበት፤ ሃጢያተኞች የሚፀፀቱበት፤ የጠመሙት የሚቃኑበት፤ የአላህ (ሱ.ወ) ጸጋና ምህረት ለባሮቹ ከመቸውም በላይ ከፍ የሚልበት ወር ስለሆነ ቅዱስ ወር ተብሏል::

ምህረትና ጽድቅን ከማግኘት ጀምሮ የረመዳን በረከት ብዙ ነው:: “መጀመሪያው እዝነት፤ መካከለኛው ምህረት፤ መጨረሻው ደግሞ ከእሳት ነጻ የሚያወጣበት ሆኖ በሀዲሶች ዘንድ ይወሳል:: በመጀመሪያ አስር ቀናቶች አላህ (ሱ.ወ) ለትክክለኛ ባሮቹ እዝነቱን ያርከፈከፈበት፣ በሁለተኛው አስር ቀናቶች ደግሞ ምህረቱን የለገሰበት፣ በመጨረሻዎቹ አስርት ቀናት ጿሚዎችን ከእሳት ነጻ የሚያወጣበት ሆኖ በእዝነት፣ በምህረት፣ በነጻነት ይፈጸማል::

አራተኛው የእስልምና መሰረት ሀጅ ነው:: ሀጅ እስልምና ከጸናባቸው አበይት መሰረቶች አንዱ ነው:: የተከበረውን የአላህን ቤት ከመጎብኘት ጀምሮ ግደታዊ የሆነውን አምልኮ በውስጡ ለመፈፀም የሚደረግ ሂደት ነው። የሀጅ ጉዞ እውቅና የሚሰጠው ሙስሊም ለሆኑ፣ ለአቅመ አዳም (ሄዋን) ለደረሱ፣ ሙሉ ጤነኛ መሆንና ከባርነት ነፃ መሆን ቀዳሚዎቹ ናቸው:: እንደመስፈርት ከተቀመጡት ውስጥ ኢህራም ማድረግ፤ ጠዋፍ፤ ሰዕይ (መሮጥ)፤ ፀጉርን ማሳጠር (መላጨት)፤ አረፋ ላይ መቆም እና መሰናበቻ ጠዋፍ ዋነኛዎቹ ናቸው:: ከአንድነትና ከአብሮነት አኳያ ሀጂ የጎላ ሚና አለው::

ሁለም ሊባል በሚችል ደረጃ አንድ አይነት ነጭ ለብሶ ያለ ምንም ልዩነት ወደ ቤተ እምነቱ ሲያመራ በልዩ መንፈሳዊ ድባብ ውስጥ ነው:: “አቤት ብያለሁ ጌታዬ ሆይ፣ አቤት ብያለሁ ጌታዬ ሆይ፣ አጋር የለህም አቤት ብያለሁ በእርግጥም ምስጋናም ጸጋም ለአንተው ነው፡ ስልጣንም ለአንተ ነው፣ አጋር የለህም” በሚል መወድስ ራስን በማስተናነስ ውስጥ የአላህን ክብርና አምላክነት በማስተጋባት ጭምር ነው::

ከላይ የዘረዘርናቸው አምስቱ የእስልምና መሰረቶች አማኙን ከፈጣሪ ጋር በማቆራኘት እንደቅድመ ትዕዛዛት የሚወሰዱ የጽድቅና የበጎ አምልኮ መሪዎች ናቸው:: በምክንያትና ውጤት የታገዙት እኚህ መሰረቶች ሰው በምድር ላይ በፈጣሪው ሕግና ትዕዛዝ ተመርቶ ምንዳ እንዲያገኝ በኋላም በሰማይ የተዘጋጀለትን ገነት እንዲወርስ እንደቅድመ ሁኔታ የተቀመጡም ናቸው:: የትኛውም አማኝ ሀይማኖቱ በሚፈቅድለት የስርዐት አውድ ስር መቆሙ ለፈጣሪው ያለውን ተዐማኝነት ከመግለጹ እኩል ለራሱም ዋጋ ይሰጣል::

እስላም ሰላም ነው:: የትኛውም ምድራዊ ቃል ከዚህ ቃል በተሻለ እስልምናን አይገልጸውም:: ሰላም ደግሞ የሁሉም ነገር መሰረት ነው:: የሁሉም ነገር መሰረት በሆነ ቃል ስያሜን ማግኘት ሰላምና እስልምና ምን ያክል የተቆራኙ እንደሆኑ የሚያሳይ ነው:: አላህን ጨምሮ የአላህ መልዕክተኛ ነብዩ መሀመድ ተከታዮቻቸውን ከሚያስተምሩት ትምህርታቸው መሀል የሰላም መንፈስ የገዘፈ ነው::

የርህራሄ፣ የደግነት፣ የመስጠት፣ የመረዳዳት እና የፍቅር ወር የሆነው ታላቁ የረመዳን ወር ሂደቱን ጨርሶ እንሆ በዓለ ኢድ ሆኖ ከተፍ አለ:: ኢድ የሮመዳን ጾም የመጨረሻ የፍቺ እለት ነው:: በአንድ ቃል ኢድ ማለት ደስታ ማለት ነው:: በዚህ ታላቅ በዐል ላይ ወዳጅ ከወዳጁ ይጠያየቃል፣ ያለው ለሌለው ይሰጣል፣ የተራቡ ወገኖች ይጎበኛሉ:: ከምንም በላይ ደግሞ ፈጣሪ ይከብራል::

ኢድ እኔነት የሌለው የብዙሀነት በዐል ነው:: ምንም እንኳን በዐሉ የሙስሊሞች በሆንም ሌሎች እምነቶችም ጋር የሚያከብሩት በዐል ነው:: ጎረቤት ተጠራርቶ፣ ቤተዘመድ ተዘያይሮ በፍቅርና በአንድነት በደስታም የሚያከብሩት የኢትዮጵያዊነት ቀለም ነው:: ረመዳን ኢድን ፈጥሮ በጉርብትና ስንጠያየቅ፣ አብይ ጾም ትንሳኤን ሰጥቶ በወንድምነት ስንተቃቀፍ ከሀይማኖታዊ በዐላቸው ጎን ለጎን ሀበሻዊ ቅርርብም የሚንጸባረቅባቸው ናቸው::

በዓልን በጋራ ማሳለፍ ለእኛ ኢትዮጵያውያን አዲስ ነገር አይደለም:: በረመዳንና በፋሲካ፣ በገናና በአረፋ በጋራ እያፈጠርን፣ በጋራ እያመለክን ቀን የወጣን የፍቅር ፋና ወጊዎች ነን:: ነብዩ መሀመድ ተከታዮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ምድር ሲልኩ በዛ ፍቅር አለ፣ በዛ አንድነትና አብሮነት አለ፣ በዛ ማንንም የማይጎዳ ንጉስ አለ ብለው ነው:: ተከታዮቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላም የወቅቱ ንጉስ በተለየ አቀባበል ተቀብሏቸዋል:: መቀበል ብቻ አይደለም የአረቡ መንግስታት የኢትዮጵያ ንጉስ አሳልፎ እንዲሰጠው በወርቅና በገንዘብ በተለያዩ እጅ መንሻዎች ሲያባብለው እንደነበር ታሪክ ይነግረናል::

ይሄ ጥንተ ፍቅራችን ዳብሮና ጠንክሮ የሀይማኖት መቻቻል የተንጸባረቀባትን ኢትዮጵያ ፈጥሯታል:: ክርስቲያን ወንድሞች የሕዝበ ሙስሊሙን መስገጃ በማጽዳት፣ ሙስሊሙ የክርስቲያኑን ቤተ እምነት በማሰናዳት አብሮነታችንን በእውን ያሳየንበት ማረጋገጫችን ነው:: ለዚህ ምስክር የሚሆኑን ሁለቱ ጎረቤታሞች ቤተ እምነቶች አኗር መስኪድና ራጉኤል ቤተክርስቲያን ናቸው:: እኚህ የተለያዩ ግን ደግሞ አንድ አይነት ቤተ እምነቶች የሀይማኖት መቻቻልን በመስበክ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል:: ሙስሊሙን ከክርስቲያኑ፣ ክርስቲያኑን ከሙስሊሙ ያዋሃዱ፣ ያቆራኙ፣ ያፋቀሩና ያነካኩ ቤተ አምልኮዎች ናቸው::

እንዳለፈው ጊዜ የዘንድሮውን ኢድ ስናከብር ካለን ላይ በመቁረስ፣ ጠያቂ የሌላቸውን በመጠየቅ፣ ስለፍቅር፣ ስለሰላም፣ ስለአብሮነት ዋጋ በመስጠት ነው:: እንደመጣንበት ረጅም ርቀት ተያይዘን የምንሄድበትን የአብሮነት ጎዳና፣ በመቻቻልና በመከባበር አርቆ በማየት ጭምር ነው:: የሰላምን ዋጋ በመረዳት ሰላም ሰባኪና አስታራቂ በሆነ የእርስ በርስ መስተጋብር የበኩላችንን በማድረግም ጭምር ነው:: ታላቁ ረመዳን በእስልምና መሰረቶች ሲቃኝ እምነትን ከሰላም ጋር ያጣመረ ሆኖ ነው የምናገኘው::

አዛን አርማችን ሆኖ..ተንስኦ ሰንደቃችን ሆኖ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ለብዙ ዘመናት እንደጸሀይ አብርተዋል:: ሁለቱ ታላላቅ ሀይማኖቶች ኢትዮጵያን እንደመቀነት ታጥቀው የፍቅርና የመቻቻል ቀስተዳመናን አስምረዋል:: እስላም ሰላም ነው፣ ኢድ ደግሞ ደስታ ነው:: ሰላምና ደስታ የተቀናጁበት ረመዳን ማብቂያውን አድርጎ በልዩ ፌሽታ መጥቷል:: በዐላት ከመብላትና ከመጠጣት እኩል ስለሀገር የሚጸለይባቸው ናቸው:: ሀገራችን አሁን ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ የአባቶች ጸሎት፣ የአማኝ ስክነት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን::

በዚህ ወቅት እንደሀገር የገጠሙን ፈተናዎች ብዙ ናቸው:: የሀይማኖት አባቶች አስታራቂና መካሪ በመሆን፣ ምዕመናኑ ደግሞ የመቻቻልን ዋጋ በመረዳት ለብዙሀነት ዋጋ መስጠት ይኖርበታል:: የልዩነቶቻችንን ቀዳዳ በመድፈን የአብሮነትን ቤት ማጽናት፣ አላሻግር ያሉንን የትርክት ድልድዮች አፍርሰን የአንድነት መሻገሪያ መገንባት የትውልዱ ቀጣይ የቤት ስራው ነው:: የሀይማኖት መቻቻል ለአንድ ሀገር ከፍተኛውን የለውጥ ንቃት የሚፈጥር ነው:: ሀገራችን በብዙሀነት ውስጥ በአንድ አይነት ምስል፣ በአንድ አይነት የበኩር ስም የምትጠራው ሕዝብ ከህዝብ ያለልዩነት በፈጠረው መስተጋብር ነው::

የሀይማኖት መቻቻል ከሕዝብ በጎ እሴቶች ውስጥ አንዱ ነው:: አንዱ ብቻ አይደለም ልማትና እድገት ይመጣባቸዋል ተብለው በቀዳሚነት ከሚታሰቡ አቅጣጫዎች ውስጥም የሚመደብ ነው:: የሰላም እሴቶች የሀይማኖት እኩልነትን ታከው ነፍስ የሚዘሩ ናቸው:: ሀይማኖት የመጀመሪያ ተልዕኮው ፍቅርና ሰላማዊነት ነው:: በፍቅርና በመቻቻል በኩል ካልሆነ ፈጣሪያችንን አንደርስበትም:: ስለሆነም በሰላማዊ መንገድ ከሌሎች ጋር ማበር እምነታችን የሚፈቅደው ዋነኛው ግባችን ነው:: ከመጠያየቅና ከመተጋገዝ ጀምሮ ያሉ እንደሀገር ልንጠብቃቸው የሚገቡ ሀይማኖት ወለድ የሆኑ በርካታ በጎ እሴቶች አሉን::

ሀገራችን በጦርነቱ ዘርፍ ብዙ ጀግናዎችን አፍርታለች:: አሁን ላለው ትውልድ የሚያስፈልገው የጦርነት ጀግና ሳይሆን የሰላም ጀግና ነው:: መለያየትን ተጸይፈው በእርቅና በመቻቻል የሚያምኑ የሀይማኖት አባቶች የሰላም ጀግናዎች ናቸው:: ስለሀገር መዛነፍ ግድ የሚሰጣቸው የሀገር ሽማግሌዎች ጀግናዎቻችን ናቸው:: መለያየትን ሽረው ስለአብሮነት ዋጋ የሚከፍሉ እነሱ የትውልዱ ጀግናዎች ናቸው:: የጦርነት ጀግና ይበቃናል:: ስለሰላም፣ ስለአብሮነት ጀግና የሆነ መንፈሳዊና አለማዊ ሰው የሚያሻን ጊዜ ላይ ነን::

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You