የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ጥምረትለኃይል አቅርቦትና ተደራሽነት

ዓለማችን ካፈራቻቸው ስመጥር የምጣኔ ሃብትና ምሁራን መካከል የሚመደቡት፣ ዴቪድ ሰቴርን፣ ፖል ቡሩክና ስቴቨን ቡሩንስ‹‹The Impact of Electricity on Economic Development: A Macroeconomic Perspective›› የሚል የኤሌክትሪክ ኃይል አቅም አቅርቦትና ተደራሽነት ከአንድ አገር ከሁለንተናዊ እድገት ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው በሚያትት የጋራ ጥናታዊ ፅሁፋቸው ይበልጣል ይታወቃሉ። በጥናታቸው፣ ‹‹እድገት ሲታሰብ በተለይም የኃይል ዘርፉ ልማት ከሌሎች ስራዎች ቀድሞ በመገኘት ለማክሮ ኢኮኖሚ እድገትን ወሳኝ ሚና መጫወት እንዳለበት›› ያሰምሩበታል።

በዚህ እሳቤ ልክና መነፅር ኢትዮጵያን ከተመለከትና ከመዘናት የኃይል ዘርፉ ልማትና የአገሪቱ ጉዞ እኩል መገዝ እንዳልሆነላቸው በቀላሉ መረዳት አንቸገርም። በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪው፣ በአገልግሎት ዘርፉ እንዲሁም የእያንዳንዱ ግሰለሰብ ቤት የኃይል ፍላጎትና ፍጆቻ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።

በአገሪቱ በአሁን ወቅትም አስተማማኝ፣ ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሁም የማህበራዊና የኢኮኖሚ ልማት ፍላጎት በበቂ ሁኔታ የሚደግፍ የኃይል አቅርቦት አይስተዋልም። የመነጨውን ኃይል ውጤታማ በሆነ መልኩ ተደራሽ ከማድረግ አንፃር ጉልህ ድክመት ስለመኖሩ የሚያከራክር አይደለም።

የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችም በበቂ ሁኔታ ያልተዳረሱ፤ የኃይል ፍላጎቱን በበቂ ሁኔታ መሸከም የማይችሉና በየወቅቱ አስፈላጊው ጥገና ያልተደረገላቸው ናቸው። የኃይል ብክለቱም ልዩ ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው። በዓለም አቀፉ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጥናት መሰረት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ከሚመረተው ኃይል ውስጥ ከ20 በመቶው በላይ የሚሆነው ይባክናል። ኢትዮጵያ በዓመት እስከ 350 እስከ 400 ሜጋ ዋት እንደሚባክን ይታመናል። ይህም ብክነቱን ጣና በለስ ግልገል ጊቤ 2 የኃይል ማመንጫ ከሚያመርተው ጋር የሚቀራረብ ነው እንደ ማለት ነው።

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገት ለማጎልበት በተለይም አገሪቱን ለኢንቨስትመንት ከሚመቹት ተርታ ለማሳለፍ ሙስናን ጨምሮ ሌሎችም መሰናክሎች ከማስወገድ ባሻገር ለኃይል መሰረተ ልማትና ተደራሽነቱ እንዲሁም ብክነቱን ለመከላከል ከፍተኛ ትኩረት መሰጠት የግድ ይላል።

በአሁን ወቅትም መንግስት የኃይል አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ ሁለንተናዊ ልማቱ የሚጠይቀውን የኃይል ፍላጎት ለማርካት የተለያዩ የኃይድሮ ፓወር ልማት ፕሮጀክቶችን በአገሪቱ ዋና ዋና ወንዞችና ተፋሰሶች ላይ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

ከእነዚህ መካከልም በአሁን ወቅትም በፍፃሜ ዋዜማ ላይ የሚገኘውና ከአፍሪካ ቀዳሚ የኃይድሮ ኤሌክትሪከ ኃይል ማመንጫዎች አንዱ የሆነው የሕዳሴ ግድብ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። 1 ሺ 870 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጨው የጊቤ ሶስት ፕሮጀክትም ሌላኛው ማሳያ ነው።

ይሁንና ኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና እድገት የሚጠይቀውን ፍላጎት ለማሟላት በተለይም የኃይል አማራጭን ማስፋት ብሎም ውጤታማ በሆነ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ እርምጃዋን ወደ ሩጫ መቀየር የግድ ይላል። በተለይም የአየር ንብረት ላይ ተፅእኖ የማያሳድሩና ከብክለት ነፃ የሆኑ የኃይል አማራጮቾችን ማስፋት እጅጉን ወሳኝ ነው።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውሃ ሃብት ያላት አገር ናት። የተለያዩ ጥናቶችም የአገሪቱ የኃይድሮ ፓወር አቅም 45 ሺ ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል መሆኑን ያሳያሉ። የአገሪቱ ኃይል በአብዛኛው የሚመንጨው ከውሃ ነው። ይሕ ደግሞ አቅርቦቱን ከተፈጥሮ ዘላቂነትና አስተማማኝነት ጋር ያስተሳስረዋል። ከአየር ንብረት ሰላማዊነት ጋር ሕልውናው እንዲጣበቅ ያደርገዋል። እንዴት ከተባለም የአየር ንብረት ለውጥ በተለይ የዝናብ እጥረት፣ የግድቦችን የውሃ መጠን ሲቀንስ ብሎም ሲያደርቅ እንደነበር ማስታወስ በቂ ምላሽ ይሆናል። ከመሰል የአየር ንብረት ተፅእኖ ቅጣት ለማምለጥ ታዲያ ፊትን ወደ ታዳሽ ኃይል ማዞር የግድ ይላል።

የአገሪቱ የኢነርጂ ምርት ከካርቦን ልቀት ነጻ በሆኑ በታዳሽ ኢነርጂ ምንጮች ላይ እንዲመሠረትና በቁጠባ ጥቅም ላይ እንዲውል የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ተግባራዊ እየተደረገ ባለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ ውስጥ ዋነኛ ስትራቴጂ ሆኖ ተቀምጧል።

ኢትዮጵያ ታዳሽ የኃይል አማራጮች ሃብታም ናት። በመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ምከንያት ከፍተኛ የፀሃይ ኃይል ማምረት የሚያስችል አቅም አላት። ከነፋስ እና ለእንፋሎት ወይንም ጄኦተርማል ኃይል ያላት እምቅ አቅም እጅግ በጣም ከፍተኛ ስለመሆኑ የተለያዩ ጥናቶች ይመሰክራሉ።

እምቅ የታዳሽ ኃይል ምንጮች ባለቤት እንደመሆኗ መጠን ከዚህ ሀብቷ የራሷን የኢነርጂ ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ቀጠናዊ የኃይል ትስስሩን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የውጭ ምንዛሪ ምንጭን ለማሳደግ እንዲሁም የኃይል ዘርፉ በአካባቢው ጂኦፖለቲካዊ መረጋጋት የሚኖረውን ሚና ከፍተኛ እንዲሆን ይታመናል።

የአሁን ወቅትም የኢኮኖሚ ልማት ግቦችን ለማሳካት የኃይል አማራጭን የማስፋትና ያላትን እምቅ አቅም በአግባቡ ለመጠቀም እየተጋች ትገኛለች። የኤሌክትሪክ አቅርቦት እጥረትን ለመፍታትም ከፍተኛ መዋለ ንዋይ ፈሰስ በማድረግ ከተለያዩ የኃይል አማራጮች ማለትም የውሃ፣ ንፋስ፣ እንፋሎትና የፀሐይ ኃይል አማራጮችን እየተመለከተች ትገኛለች።

በአስር ዓመቱ የልማት እቅድም ማለትም በ2030 ዓ.ም የአገሪቱ የኃይል አቅርቦት ፍላጎት እስከ 17 ሺ ሜጋ ዋት በላይ እንደሚደርስ ይጠበቃል። ይሕ ፍላጎት በመንግስት ተሳትፎና ሕዝብን ማእከል ባደረገ መልኩ በራስ አቅም በሚሰበሰብ ገንዘብ የተለያዩ የኃይል መሰረተ ልማቶች ግንባታ ብቻ ምላሽ ያገኛል ተብሎ አይጠበቅም። ይሕ መንገድም ብዙ ርቀት የሚያስኬድ አይደለም።

በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት የኃይል ዘርፉን የማልማት ተግባር መንግስት ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ መቆየቱን መታዘብ እንችላለን። የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገት የሚፈልገውን ኃይል ጥማት በማርካትና በማልማት ሂደት በተለይ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ አለ ከማለት የለም ለማለት የማያስደፍር ነው።

ይሁንና የኃይል ምንጭ ስብጥሩን በማስፋት፤ የማስተላለፊያና ማሰራጫ መሰረተ ልማትን በማጠናከርና የአሰራር ስርዓቱን በማዘመን የዘርፉን የአገልግሎት ጥራትና አስተማማኝነትን ለማረጋገጥ የግሉ ዘርፉ ተሳትፎ እጅጉን ወሳኝ መሆኑ የሚያከራክር አይደለም።

መረጃዎች የሚያመላክቱት፣ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ መካከል በኃይል መሰረተ ልማት ላይ ያለው ትብብርና አጋርነት እጅጉን ደካማ መሆኑ ነው። ይሕ ውስንነትም በተለይም ባለፉት ዓመታት የኃይል አቅርቦቱን በማጎልበት ብሎም ተደራሽነቱን ውጤታማ በሆነ መልኩ ከማሳለጥ አንፃር የሚፈለገው ለውጥ እንዳይመጣ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል።

በመሆኑም በኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት እና አቅርቦት ጋር ከሚሰሩ የሶስተኛ ወገን ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት መስራት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በጋራ መተግበር የግድ ይላል። ይሕም ዘላቂ፣ አስተማማኝና ጥራቱን የጠበቀ የመሰረተ ልማት ለመዘርጋትም ሆነ ያሉትን ለማጎልበት እጅጉን ወሳኝ መሆኑ አጠያያቂ አይሆንም። የለውጡ መንግስትም ይሕ እሳቤ ጠንቅቆ እንደገባው የሚያስመሰክሩ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል።

በተለይም በ2010 ዓም የመንግስትና ግል አጋርነት የሕግ ማዕቀፍ ይፋ መሆኑም የሚታወስ ነው። ውሳኔውም የግል ባለሃብቶች በኃይል ማመንጨትና ማከፋፈል ዘርፍ እንዲሳተፉ ሰፊ እድል ከፍቷል። ይሕ ማእቀፍም የመንግስትና የግል አጋርነት ስምምነት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማገዝ የሚችሉና በግል ባለሀብቶች ፋይናንስ የሚደረጉ ፕሮጀክቶችን ለማበረታታትና ለመደገፍ የሚያስችል አመቺ ከባቢ እንዲኖር ማድረግ ግልጽነትን፣ ፍትሀዊነትን፣ ቅልጥፍናንና ዘላቂነትን ማበረታታት ታሳቢ ያደረገ ነው።

መረጃዎች እንደሚያመላክቱትም፣ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገቱ የሚፈልገውን የኃይል አቅርቦት ለማሟላት የመንግስትና ግሉ ዘርፍ የትብብር የኢንቨስመንቱ ተሳትፎ ለውጦች እየታየበት ይገኛል። በአሁን ወቅትም ከሃያ የበለጡ በመንግስትና ግሉ ዘርፍ ትብብር የሚተገበሩ ፐሮጀክቶች ተግባራዊ በመሆን ላይ ናቸው። የኮርቤቴ ከርስ ምድር እንፋሎት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ለዚህ ማሳያ ነው።

የአሁን ወቅትም የኢኮኖሚ ልማት ግቦችን ለማሳካት የኃይል አማራጭን የማስፋትና ያላትን እምቅ አቅም በአግባቡ ለመጠቀም በሚደረግ ጥረት በተለይ የታዳሽ ኃይል አማራጭ ወሳኝ መሆኑን በማመን መንግስት በዘርፉ ለሚሰማሩ በርካታ ማበረታቻዎችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። ይሕን ማበረታቻ የተቃደሱ ድርጅቶችና ፕሮጀክቶች እንዳሉም ይታወቃል።

የአንዳንዶቹም ቦታ መረጣና የአዋጭነት ጥናት ተጠናቋል። ስራ የጀመሩ ብሎም ለመጀመር በሚያስችል ተክለ ቁመና ላይ የሚገኙም አሉ። የመንግስትና ግሉ ዘርፍ የትብብር ቦርድ ለተዋናዮቹ ፈቃዱን ሰጥቷል። ለውጦች ካላተደረጉ በስተቀር ቦርዱ ዘጠኝ አባላት ያሉት ሲሆን ሰባት ያህል ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ሁለቱ ደግሞ ከግል ዘርፉ የተወጣጡ መሆናቸውንም ይታወቃል።

በአጠቃላይ በአሁን ወቅት በተለይም የኃይል ዘርፉ ልማት ከሌሎች ስራዎች ቀድሞ በመገኘት ለማክሮ ኢኮኖሚ እድገትን ወሳኝ ሚና እንዲጫወት የተጀመሩ ጥረቶች ይበል የሚያስብሉ ናቸው። ይሑንና በተለይ የግሉን ዘርፍ ከማሳተፍ አንፃር ተጨማሪ ጥረቶችን ማድረግ እንደሚገባ በግልፅ ይታያል።

በመጪዎቹ ዓመታት ከአገሪቱ ሁለንተናዊ ልማትና እድገት ጋር ተያይዞ ትልቅ መፍጠር የሚያስችሉ እድሎች እንዳሉ እርግጥ ነው። እነዚህ እድሎችም እጅጉን አጓጊና ዘርፈ ብዙ በረከቶችን ይዘው የሚመጡ ናቸው። ይሁንና ከበረከታቸው ለማቋደስ ሰፊ ስራን ይጠይቃሉ።

የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት የሚፈልገውን የኃይል አቅርቦት ከማሟላትና በአግባቡ ተደራሽ ከማድረግ አንፃር ከወዲሁ በልዩ ትኩረት የቤት ስራዎችን መስራት ተገቢ ነው። ከሁሉ በላይ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የአገሪቱን የኃይል ጥም የማርካት ግዙፍ አቅም ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር ማድረስና በዲፕሎማሲው መስክ የተገኘውን ድል ይበልጥ በማስቀጠል ቀጠናው ላይ ያለንን አቅም ይበልጥ ማሳየት እጅግ ወሳኝ ነው።

በተለይ በቅርቡ የሚጠናቀቅና ቀጣይ ዓመታት እውን የሚሆኑ ከፍተኛ አቅም ያላቸው የኃይል አማራጮች እንደ አገር ይዘውት የሚመጡትን ዘርፈ ብዙ እድል ከመጠቀም አንፃር በሰፋፊ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ግድቦችን ከደለልና መጤ አረም ዝርያዎች ከመጠበቅ አንስቶ፣ በዘርፉ ላይ ቱሪዝምና ግብርናን ጨምሮ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ኢንቨስተሮችን ለማስተናገድ ከወዲሁ እጅን ሰብስቦ ጠንካራ ተቋማትን አደራጅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል።

ኢንቨስትመንት በማስፋት፣ የኢኮኖሚ መዋዠቆችን ለመከላከል እንዲሁም የኑሮ ውድነት ፈር ለማስያዝ የኃይል አማራጮች ማስፋት፣ የተጀመሩትን በፍጥነት ማጠናቀቅ እንዲሁም የግሉን ዘርፍ ፊት አውራሪ እያደረጉ መዝለቅ ይበልጡን ሊታሰብበት ይገባል።

እንደየደረጃው ከውጭና የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ጋር ተቀራርቦ መስራትና ተሳትፏቸውን ማጎልበት የግድ ይላል። ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ መጎልበትም አነቃቂና አዳዲስ ማበረታቻዎችን ተግባራዊ ማድረግ ፈፅሞ መዘንጋት አይኖርበትም።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You