የጎበጠውን የዜጎች ወገብ የሚያቀና አዋጅ

በከተሞች አካባቢ የሚታየው የመኖሪያ ቤቶች ዋጋ (ሽያጭም ሆነ ኪራይ) መናር የዜጎች ፈተና እየሆነ ከመጣ ሰንብቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ምክንያታዊ እና ፍትሐዊ ያልሆኑ የቤት ኪራይ ጭማሪዎች እየተባባሱ መጥተዋል። በቅርቡ በዓለም ዙሪያ የኑሮ ደረጃዎችን የሚከታተለው ነምቤኦ (NUMBEO) የተባለ ድርጅት በ2024 በአፍሪካ ሀገራት ያለውን የመኖሪያ ቤቶች ዋጋ ዝርዝር ሪፖርት በድረ-ገጹ አውጥቶ ነበር።

በዚሁ ድርጅት መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ በመኖሪያ ቤት ዋጋ ውድነት ከአፍሪካ 2ኛ፤ ከዓለም ደግሞ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ዜጎች ለመኖሪያ ቤት የሚያወጡት ዋጋ ከሚያገኙት ገቢ 43 ነጥብ 1 በመቶውን እንደሚሸፍንም ይኸው ድርጅት አስታወቋል። ይህም በሀገራችን የመኖሪያ ቤት ኪራይ መጨመር እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ያመላክታል።

በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ችግሩ ጎልቶ የሚታይ ሲሆን የኑሮ ውድነትን በማባባስ ረገድ ድርብ ፈተናን ፈጥሯል። በዋናነት በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እያስነሳ እና ዜጎችም ተረጋግተው ኑሯቸውን እንዳይመሩ እያደረገ ይገኛል። ተከራይ ለቤት ኪራይ የሚያወጣው ክፍያ ከ30 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይናገራሉ።

አዲስ አበባ ውስጥ ተቀጣሪ ሠራተኞች ከገቢያቸው እስከ 70 በመቶውን፤ አልፎ አልፎምም ሙሉ ገቢያቸውን ለቤት ኪራይ ያወጣሉ። ይህም በመዲናችን አዲስ አበባ የችግሩ ጥልቀትና አሳሳቢነት እስከምን ድረስ እንደሆነ ጠቋሚ ነው። በእርግጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የችግሩን አሳሳቢነት ተገንዝቦ ጊዜያዊ መፍትሔ ለማበጀት ሞክሮም እንደነበር አይዘነጋም።

ከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ጊዜያት መንግሥት ለችግሩ እልባት ለመስጠት የኪራይ ጭማሪ እገዳ ማድረጉ ይታወቃል። ይሁንና አከራዮች ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ከማድረግ አልተቆጠቡም። ደንቡ በአግባቡ ተፈጻሚ መሆን ባለመቻሉ፤ መንግሥት ለችግሩ ጊዜያዊ መፍትሔ ለመስጠት ያደረገው ሙከራ የተሳካ አልነበረም።

ዘርፉ በሕግ የሚመራ አለመሆኑ ችግሩ ስር ሰዶ ከቁጥጥር ውጭ እንዲሆን እንዳደረገው ይታመናል። የአከራይ እና ተከራይን መብት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ማስጓዝ አልቻለም። ስለዚህ ችግሩን ለመቅረፍ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም።

በመሆኑም መንግሥት ጣልቃ ገብቶ የመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋ መናርን ለማስተካከል፣ የቤት ኪራይ ውል በሕግ እንዲመራ ለማድረግ የሚያስችለውንና በአከራይና ተከራይ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን አዋጅ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል። የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ ከአውሮፓ ጀርመን፣ ከኤስያ ቻይና፣ ከአፍሪካ ኬንያ ሕጉን ለማውጣት ልምድ የተወሰደባቸው ሀገራት መሆናቸውም ታውቋል።

የአዋጁ መፅደቅ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንደሚኖረውም መረዳት ይቻላል። በአዋጁ መሠረት ማንኛውም የመኖሪያ ቤት ተከራይ እስከ ሁለት ዓመት የመከራየት መብት ተሰጥቶታል። ይህም የመኖሪያ ቤት አከራዮች ይቋቋማሉ በተባሉ “ተቆጣጣሪ አካላት” በዓመት አንድ ጊዜ በሚሰጡት የኪራይ ተመን ዋጋው የሚመራ ሲሆን፤ ይህም የዘፈቀደ የኪራይ ዋጋ ጭማሪን ያስቀራል ተብሏል።

ከዚህ በፊት አከራዮች በፈለጉት ጊዜ ዋጋ ይጨምሩ ነበር። በአዲሱ አዋጅ መሠረት ግን አከራይ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ ማድረግ የሚችለው ተቆጣጣሪው አካል የሚወስነውን ውሳኔ መሠረት በማድረግ ነው።

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ ምክንያታዊ ያልሆነ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር፣ ሕገ ወጥ የደላላ ጣልቃ ገብነትን በመቀነስ የኑሮ ውድነቱን በተወሰነ ደረጃ ማርገብ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

ስለዚህ መንግሥት አዋጁን ማውጣቱ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን የኑሮ ጫና፤ በተለይ በመኖሪያ ቤት ላይ ያለአግባብ የሚደረገውን የኪራይ ጭማሪ በማስቀረት ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ያስችላል። ስለሆነም የአዋጁ መውጣት ለሕዝብ ትልቅ እፎይታን ይፈጥራል፤ በተወሰነ መልኩም ለኑሮ ጫናው ዘላቂ መፍትሔ ያስገኛል ተብሎም ይጠበቃል።

በቀጣይ ከአዋጁ ተፈፃሚነት ጋር ተያይዞ ከወዲሁ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ። አዋጁ በወረቀት ላይ እንዳይቀር ከወዲሁ ከአተገባበሩ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግን ያስፈልጋል። ብዙዎች ተስፋ ያደረጉበት ይህ አዋጅ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ በአተገባበሩ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ የግድ ይሆናል።

በአጠቃላይ፣ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ መፅደቅ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ወጥነት እና ተገማችነት ያለው፤ እንዲሁም፣ የአከራይ እና የተከራይን መብት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለማስተዳደርና ዘርፉን በሕግ ለመምራት ያስችላል። ነገር ግን ከአዋጁ ተፈፃሚነት ጋር ተያይዞ በትኩረት መሥራት እና ለብልሹ አሠራር ክፍት እንዳይሆን ጥብቅ ክትትል ማድረግም ያስፈልጋል።

ዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You