“ድርጅቱ በቅንጅት ባለመሥራቱ ከአንድ ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አጥቷል” -የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ

“ችግሩ በሁለቱ ድርጅቶች መገፋፋት የመጣ አይደለም”- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከባለድርሻ አካላት ጋር በዋናነትም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በቅንጅት ባለመሥራቱ ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማጣቱን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ። ድርጅቱ በበኩሉ ችግሩ በሁለቱ ተቋማት መገፋፋት የመጣ አለመሆኑን ገልጿል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2014/15 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ፕሮጀክት አፈጻጻም የክዋኔ ኦዲት ሪፖርትን በትላትናው እለት ገምግሟል።

በወቅቱ የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ የሺእመቤት ደምሴ እንደገለጹት፤ ድርጅቱ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችንና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት መሠረተ ልማት ዝርጋታና የኃይል ደራሽነትን ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችል ወጥ የሆነ ሥርዓት እንዳልዘረጋ በሪፖርቱ ተቀምጧል።

ኃይል ሲቋረጥ በድርጅቱ እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መካከል ኃላፊነት ወስዶ ችግሮችን በጋራ ለመቅረፍ በእቅድ ላይ የተመሠረተ ሥራ አልተሠራም ያሉት ሰብሳቢዋ፤ በዚህም ከአገልግሎቱ ጋር በቅንጅት ባለመሥራቱ እና የኤሌክትሪክ ኃይል ለሀገር ውስጥ እና ለጎረቤት ሀገሮች ባለመሸጡ በአማካኝ አንድ ቢሊዮን 271 ሚሊዮን 244 ሺህ 977 ብር ድርጅቱ ማጣቱን በ2013 ዓመታዊ ሪፖርት የተገለጸ መሆኑ በኦዲት ሪፖርቱ ተመላክቷል ሲሉ ተናግረዋል ።

 

ሰብሳቢዋ፤ እነዚህ ተቋማት እንደ ሀገር ትልቅ ኃላፊነት የተሰጣቸውና እንደ አንድ የሚታዩ መሆናቸውን ገልጸው፤ ሆኖም በሁለቱ ተቋማት መገፋፋት ምክንያት ሀገሪቱ ማግኘት ያለባትን ገቢ ማጣቷን ተናግረዋል። ለዚህም ድርጅቶቹ ምንም አይነት የሕግ ማዕቀፍ በሌለው መንገድ መሥራታቸው ምክንያት ነው ብለዋል ።

በቀጣይ በሕግ የታሠረ በስምምነት ሰነድ የተደገፈ ቅንጅታዊ አሠራር በአስቸኳይ በመመሥረት ወደ ሥራ መግባት ይኖርባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በተለያዩ ጊዜያት በመገናኘት የእቅድም ሆነ የኦፕሬሽን ሥራዎችን በቅንጅት ተወያይቶ ይሠራል ።

ነገር ግን ቋሚነት ያለው የተፈረመ ሰነድ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የለም ሲሉ ገልጸው፤ ይህም እንደ ክፍተት የሚወሰድ ይሆናል ብለዋል ።

ከዚህ በፊት የነበረው ችግር አሁን ላይ እየተቀረፈ ይገኛል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ችግሩ በሁለቱ ተቋማት መገፋፋት የመጣ አይደለም ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው አስረድተዋል።

በተጨማሪም ድርጅቱ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር እንዲሁም ከክልሎች ጋር በጥሩ ግንኙነት እየተሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በቀጣይ በጀት ዓመት ያሉትን ክፍተቶች በማስተካከልና የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት የቅንጅት ሥራውን ለማጠናከር ጥረት ይደረጋል ሲሉ ገልጸዋል ።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን  ሚያዝያ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You