ከትናንት ስህተቶቻችን ለመማር ዝግጁ እንሁን !

እኛ ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ ደረጃ አንገታችንን ቀና አድርገን የምንሄድባቸው የነፃነት፤ የፍትሕ፣ የአትንኩኝ ባይነት የደመቁ ታሪኮች ባለቤት የመሆናችንን ያህል አንገት የሚያስደፋ፤ የሚያሳቅቁ እና ምንነካቸው የሚያስብሉ ታሪኮችም ባለቤት የመሆናችን እውነታ የአደባባይ ምስጢር ነው።

በተለይም የብዙ ሺ ዓመ ታት የሀገረ መንግሥት ምሥረታ ታሪክ ባለቤት ከመሆናችን ጋር ተያይዞ፤ እንደ ሀገር የሚፈጠሩ የፖለቲካ ልዩነቶቻችን በሠላማዊ መንገድ በውይይት መፍታት ባለመቻላችን በዚህም ያልተገቡ ዋጋዎችን ለመክፈል የተገደድንባቸውን ብዙ ታሪካዊ ክስተቶች አሳልፈናል ።

የሩቁን ትተን የቅርቦቹን የግጭት ታኮዎቻችንን እንኳን ለማየት ብንሞክር፤ ብዙ ተስፋ እና ሀገራዊ ራዕይ ሰንቆ የተንቀሳቀሰው የስልሳዎቹ ትውልድ አንድ አይነት ቋንቋ እየተናገረ፤ በሰከነ መንፈስ፤ በተረጋጋ አዕምሮ ቆም ብሎ መነጋገር ሳይችል በመቅረቱ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ የከፋ የሚባል ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ለማለፍ ተገድዷል።

ያ እንደ ሀገር ብዙ ተስፋ የተጣለበት ትውልድ፤ የተነሳበትን ትልቁን ሀገራዊ ራዕይ፤ ሀገርና ሕዝብን ከኋላቀርነትና ከድህነት ለማሻገር አስቦ እና በብዙ አምጦ የጀመረውን የመለወጥ ትግል ረስቶ በጠላትነት ተፈራርጆ፤ በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት ላልተገባ እልቂት እና ለስደት ተዳርጓል። በዚህም ሀገርና ሕዝብ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል አድርጎታል ።

በቀጣይ የነበሩት ስድስት አስርት ዓመታትም እንደ ሀገር በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት የተገዛው የፖለቲካ አስተሳሰባችን፤ አሸናፊዎችን የፖለቲካ መንበር ላይ ከማስቀመጥ ባለፈ፤ ዘላቂ የሆነ የፖለቲካ መረጋጋት ሊያመጣ አልቻለም። ከዛ ይልቅ ሀገርን እንደ ሀገር ወደብ አልባ የሚያደርግ ታሪካዊ ስህተት እንዲፈጠር አድርጓል ።

ከዚህም ባለፈ፤ እንደ ሀገር ለዘመናት በትውልዶች ቅብብሎሽ በጠንካራ መሠረት ላይ የቆመውን ሀገራዊ አንድነት፤ በተለያዩ የልዩነት ትርክቶች በመሸርሸር፤ ብሔራዊ አንድነታችን ሆነ በአጠቃላይ ሀገረ መንግሥቱ ስጋት ውስጥ የሚገባበትን አደጋዎች ይዞ መጥቷል። የታሪካዊ ጠላቶቻችን የማይቆም ሴራ ሰለባ እንድንሆንም አድርጎናል ።

ከዚህ እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ ካስከፈለን፤ የቅርብ ጊዜ ስህተታችን መማር አለመቻላችን ትናንት ላይ ተመሳሳይ ስህተት በመሥራት ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል የተገደድንበት ታሪካዊ ክስተት ውስጥ እንድንገኝ አድርጎናል። እንደ ቀደመው ጊዜ በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት /በይዋጣልን /መንገድ ሄደን ዛሬዎቻችንን ጭምር የስህተታችን ጥላ ሰለባ እንዲሆኑ አድርገናል።

ይህ በዘመናት መካከል ትውልዶችን ዋጋ እያስከፈለ ያለ የተበላሸ የፖለቲካ አስተሳሰብ፤ አንድ ቦታ መቆም ካልቻለ፤ እንደ ሀገር የሚኖረን ቀጣይ ዕጣ ፈንታችን ከቀደመው ዘመን ከነበርንበት የከፋ እንጂ የተሻለ እንደማይሆን፤ ከተለመደው የግጭት አዙሪት አውጥቶ ሀገር አልባ ሊያደርገን እንደሚችል ለመገመት የሚከብድ አይደለም ።

በተለይም የመልማት መሻታችን፤ ለመሻታችን ያለን ቁርጠኝነት እና አሁን ላይ በተጨባጭ እያስመዘገብነው ያለው ስኬት፤ መልማታችንን እንደ ስጋት ለሚያዩ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ሆነ ለሌሎች ኃይሎች የጥፋት ሴራ ትልቅ አቅም እየሆነ እንደሚገኝ ከየእለት ተግባራቸው እያስተዋልነው ያለ እውነታ ነው።

የቀደሙትን ትውልዶች ራዕይና ሀገራዊ ተስፋ የተናጠቀ ይህ ኋላ ቀርና ዘመኑን የማይዋጅ የፖለቲካ እሳቤያችን፤ በተመሳሳይ መልኩ የዚህን ትውልድ ሀገራዊ ራዕይና ተስፋ እንዳይናጠቅ፤ ትውልዱንም እስካሁን ካስከፈለው ያልተገባ ዋጋ በላይ እንዳያስከፍለው ቆም ብለን ነገዎችን ተስፋ አድርጎ እንደሚጠብቅ ትውልድ በሰከነ መንፈስ ልናስብ ይገባል።

ከየትኛውም አይነት የይዋጣልን፤ የእልህ እና የስሜት መንገድ ወጥተን፤ ችግሮቻችንን በሰከነ መንፈስ ቁጭ ብለን በመነጋገር የምንፈታበትን በእጃችን ያለ አማራጭ ልንጠቀም ይገባል። ለዚህ ዘመኑን ለሚዋጅ የፖለቲካ አስተሳሰብ ተገዥ በመሆን እንደ ሕዝብ ከግጭት አዙሪት የምንወጣበት አስቻይ ሁኔታ ልንፈጥር ያስፈልጋል ።

እንደ ሀገር ወደምንመኘው ብልጽግና ልንጓጓዝ የምንችለው፤ ብዙ አንገት የሚያስደፋ ሀገራዊ ትርክቶች ባለቤት ካደረገን፤ ከአሸናፊ ተሸናፊ የፖለቲካ ትርክት እሳቤ ወጥተን ልዩነቶቻችንን በድርድርና በውይይት መፍታት የሚያስችል ሀገራዊ የፖለቲካ ዓውድ መፍጠር ስንችል ነው። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ከትናንቶች ተምሮ እራሱን ሊያዘጋጅ ይገባል። እንደ ሀገር የተሻሉ ነገዎች የሚኖሩን ይህንን ስናደርግ ብቻ ነው።

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You