ፍትሐዊነትን የሚያረጋግጠው የኢትዮጵያውያን አሻራ

መነሻውን ሰከላ ያደርጋል። መዳረሻውን ደግሞ ከ6 ሺህ 700 ኪሎ ሜትሮችን ረጅም ጉዞ በኋላ ሜዲትራኒያን ባህር ላይ ያደርጋል። ሽንጠ ረጅም ነው። ከትንሿ ምንጭ ሰከላ ተነስቶ ከገባሮቹ ጋር እያበረ አስራ አንድ የሚሆኑ ተፋሰስ ሀገራትን አስተሳስሮ ከጥልቁ ባህር ጋር ይቀላቀላል። 86 ከመቶ ያህሉን የውሃ ድርሻም ከኢትዮጵያ ያገኛል። የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ፤ ዓባይ። ይህ ወንዝ ለአንዳንድ ሀገር ልምላሜም፤ ለቀሪዎቹ ደግሞ የዘመናት ተስፋን ሲሰጥ ዘመናት ተቆጥረዋል። ለምዕተ ዓመታት ያልተቋጨ ንትርክም በዚህ ወንዝ ጉዳይ ተሰምቷል።

ዓባይ ፍትህና ሚዛናዊነት ተንጸባርቆበት ሁሉንም ተፋሰስ ሀገራት ተጠቃሚ ሲያደርግ አልታየም። ሆን ተብሎ በተደረገ አግላይ ስምምነት እንደ ግብጽ ያሉ ምንም ድርሻ የሌላቸውን ሀገራት ተጠቃሚ ሲያደርግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላትን ኢትዮጵያንም አግልሎ የበይ ተመልካች አድርጓት ለዘመናት ቆይቷል።

በግብጽ መንግሥት በኩል እየተስተዋለ ያለው የአንድ ወገንን ተጠቃሚነት የሚያንጸባርቅ አካሄድ ከታሪክ አንጻር ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበትን የ1929 እና የ1959 ስምምነትን እንደመነሻ ወስዶ የሚሞግት ነው። ባለፉት ዓመታት የሶስትዮሽ ድርድሩ በሁለት እግሩ እንዳይቆም እንቅፋት ከፈጠሩ ሁነቶች ውስጥ ይሄ ነፍጥ እና ራስ ወዳድነትን ያነገበ ኢ ፍትሐዊ የታሪክ ስምምነት ተጠቃሽ ነው።

ግብጽ በዓባይ ላይ ያላት የበላይነት እንዴት ተረጋገጠ? እንዴትስ ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበት ስምምነት ተደረገ? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው ዘመነ ቅኝ ግዛትን ነው። በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያና መገባደጃ ላይ አፍሪካውያን በበርካታ የአውሮፓ ሀገራት ቅኝ ግዛት ስር ነበሩ። በዚህም ታላቋ ብሪታንያ የግብጽ ገዢ ሆና ወደ ርስቷ ስትገባ ደካማ ጎኗን በማሰብ ጭምር ነበር።

እንግሊዛውያን የግብጽ ደካማ ጎን የዓባይ ወንዝ መሆኑን ለማወቅ ብዙ አልተቸገሩም። በዚህም መረዳት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የተፋሰስ ሀገራት ያልተሳተፉበትን ሁለት ስምምነቶች አድርገዋል። የመጀመሪያው ስምምነት እ.ኤ.አ ግንቦት 7 ቀን 1929 በግብጽና በቅኝ ገዢዋ በእንግሊዝ መካከል የተደረገ የሁለትዮሽ ስምምነት ነው።

በዚህ ስምምነት ውስጥ ዓባይ በሚለው ታሪክ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ሌሎች የተፋሰስ ሀገራትን ባላማከለ መልኩ የግብጽን የብቻ ተጠቃሚነት የሚያውጅ ነበር። በዚህም ግብጽ 48 ቢሊዮን ኪዩቢክ የሚሆነውን የውሃ መጠን ስትጠቀም የሱዳን የውሃ ድርሻ 4 ቢሊዮን ኪዩብክ ብቻ ነበር።

ይሁን እንጂ በሱዳን ውትወታና የይገባኛል ጥያቄ ግብጽ ለሁለተኛ ጊዜ ስምምነት ማድረጓ ግድ ሆነ። ከሰላሳ ዓመት በኋላ እ.ኤ.አ ህዳር 8 ቀን 1959 ሱዳንን ያማከለ ሌላ ስምምነት በቅኝ ገዢዋ በእንግሊዝ በኩል ለሁለተኛ ጊዜ ተደረገ። ይሄ ሲሆን በዓባይ ወንዝ ላይ ከ86 ከመቶ በላይ ድርሻ ያላትን ኢትዮጵያን ፍፁም ያገለለ ነበር። ይህ ሸፍጥ ለግብጽ የልብ ልብን በመስጠት ከፍትህና ከእውነት እንድትርቅ ከማድረጉም በላይ ራሷን ብቸኛ ተጠቃሚ አድርጋ እንድታምን የሚያደርግ የተዛባ ትርክት እንድትጠለፍ አድርጓታል ።

ስምምነቱ ታሪካዊና ዓለም አቀፋዊ ሕግጋትን የጣሰ ስለመሆኑ እንደማስረጃ የሚቀርበው ሌሎች የተፋሰስ ሀገራትን ባላገናዘበ መልኩ ለግብጽ ከ55 ቢሊዮን ኩዩቢክ በላይ የውሃ ድርሻን መስጠቱ ነው። ሱዳን የተሳተፈችበት የሁለተኛው ዙር ስምምነት የ18 ቢሊዮን ኪዩቢክ የውሃ መጠን የጋራ ሆኖ በታሪክ በአድሎ ይታወሳል። እኚህ ሁሉን አቀፍና የተፋሰስ ሀገራትን ግምት ውስጥ ያላስገቡ ስምምነቶች ዛሬም ድረስ ጥያቄ በመፍጠር አለመግባባትን በማወጅ እክል እየፈጠሩ ይገኛሉ።

እንግሊዝ ግብጽን ይዛ የመጀመሪያውን ዙር ስምምነት ስታደርግ የላይኛውን ተፋሰስ ሀገራት ማለትም ሱዳንን፣ ታንዛኒያን፣ ኡጋንዳን እና ኬንያን በመወከል ግን ደግሞ ሌሎች ሀገራትን ባላሳተፈ መልኩ ነበር። የሁለተኛው ዙር ስምምነትም ተመሳሳይ አዝማሚያ የነበረው በግብጽ ጥቅም ውስጥ የቅኝ ግዛት ፍላጎትን የማስፈጸም አይነት ተልዕኮ የነበረው እንደሆነ ለመረዳት ቀላል ነው። ይሄ ተልዕኮ ነው ዛሬም ድረስ ፍትህንና የጋራ ተጠቃሚነትን ወዲያ ብሎ የሶስትዮሽ ስምምነቱን እያደናቀፈ ያለው።

በዓባይ ወንዝ ላይም ሆነ በቀጣናው ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ኃያልነትና የተሰሚነት ሚና እንዴት ደበዘዘ ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው የቅኝ ግዛት መስፋፋትን ተከትሎ የመጣው የአውሮፓውያን ጣልቃ ገብነትን ነው። በዓባይ ወንዝ ላይ የተደረጉትን ሁለት ኢ ፍትሐዊ ስምምነቶች የዚሁ እውነታ ማሳያ ናቸው። ስምምነቱ እንግሊዝ ግብጽን እንዴት በተደላደለ መንገድ መግዛት እንዳለባት ስታስብ የመጣ ራስን የመጥቀም ወይም ደግሞ ‹‹የእከክልኝ ልከክልህ›› አይነት ስምምነት ነው ።

ይሄ የስምምነት ሸፍጥ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በገዢና በተገዢ ሀገራት መካከል የተደረገ ጥቅምን የማስከበር የሴራ ጥንስስ ነው። እንግሊዝ በግብጽ፣ ግብጽ ደግሞ በዓባይ ላይ የበላይ እንዲሆኑ የተፈራረሙት አግላይ ስምምነት ነው። የዚህ ስምምነት አካል ሆነው ከተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል የመጀመሪያው ከግብጽ መንግሥት ይሁንታ ውጪ የግብጽን ጥቅም የሚጎዳ ማንኛውም ተግባር ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የሚደነግግ ነው ። ሌላኛው የስምምነት አካል ደግሞ ወንዙ ላይ የሚካሄድ የትኛውም የግድብ ግንባታ በግብጽ መንግሥት ቁጥጥር ስር እንዲሆን የሚያስገድድ ነው።

ሁለቱም የስምምነት መርሆዎች አሁን ላለው አስተሳሰብና ትውልድ የማይመጥኑ ከመሆናቸው በላይ በወንዙ ላይ ሰፊ ድርሻ ያላትን ሀገራችንን ያላቀፈ፣ ያላሳተፈ፣ ያስቆጣ ድርጊትም ነው። እንደዛ ባይሆን በገዛ መሬታችን፣ በገዛ ተፈጥሮ ሀብታችን ላይ በምንሰራው ግድብ ‹‹በርቱ፣ ጎብዙ›› ከማለት ባለፈ ማስፈራሪያና ዛቻ ባልደረሰብን ነበር። የሆነው ሆኖ ትውልዱ ዓባይን ገድቦታል። ከዚህ በኋላ የሚያስቆመው ምድራዊ ኃይል እንደማይኖርም ቃል በመግባት የተሰለፈ ነው።

የሦስትዮሽ ስምምነቱን አስመልክቶ ዛሬም ድረስ ላለው አለመግባባት በር ከፋች ሆነው ከፊት የሚመጡት እነዚያ ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችባቸው ስምምነቶች ናቸው። በግብጽ በኩል ድሮን እየጠቀሱ አልሸነፍ ባይነትን ማሳየት በእኛ በኩል ደግሞ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያንጸባርቁ ሃሳቦችን እያነሱ አብሮነትን ማስቀጠል ቢሆንም ስምምነቱን የሚያስታርቅ የጋራ መግባባት ላይ ግን አልተደረሰም። የመጀመሪያውን ጨምሮ ሁለተኛና ሦስተኛ አራተኛውም ዙር የሦስትዮሽ ስምምነትም በዚህ መልኩ ባለመግባባት የተቋጩ ናቸው።

ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበት ስምምነት ለዚህ አዲስ ትውልድ እና ለዚህ አዲስ ዘመን መከራከሪያ ሆኖ መነሳቱ አስቂኝ ቢሆንም ለዘመኑ በቀረበ አስታራቂ ሃሳቦች የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ ስምምነቶች እንደሚቋጭ እምነት አለን። ምክንያቱም ማንም የማይጎዳበት አብሮነትን የሚያጠነክር መነሻና መድረሻ የሃሳብ ስምምነት ስለሆነ ወደፊት የሚያራምደው። ተቃቅፎና ተደጋግፎ ከመልማት ውጪ አላማና ተልዕኮ እንደሌለን ጽኑ በሆነ የብዙሀነት ድምጽ በተደጋጋሚ የገለጽን ቢሆንም መጪው ገናናነታችን ያስፈራት ግብጽ ግን ከእምነታችን ጋር ለመቧደን አሻፈረኝ ስትል አስራ ሦስት ዓመታትን ተሻግራለች።

ያለፈውን ትተን ባሳለፍነው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ተገናኝተው የጋራ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል። በዚህ የጋራ መግለጫ መሰረትም ላለፉት አራትና አምስት ወራት በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሦስትዮሽ ድርድር ሲካሄድ የጋራ ተጠቃሚነት መርህን በማታውቀው ግብጽ በኩል ውጤት ማምጣት አልተቻለም። ለዚህ እንደዋነኛ ምክንያት የሚነሳው ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበትን ስምምነት እንደመከራከሪየ ማቅረቧ ነበር።

በፈረንጆቹ 2015 የጸደቀው የጋራ መርህ አብሮ መልማትን፣ አብሮ ማደግን፣ በፍትህና በእኩልነት መራመድን የሚደነግግ ቢሆንም ይሄ የጋራ መርህ ግን ከኢትዮጵያ በቀር ግብጾች ሲጠቀሙበት አይታይም። ለፈረሙበትና ላመኑበት መርህ ተገዢ መሆን አቅቷቸው ኢትዮጵያ ያልነበረችበትን በተንኮልና ሸር በውንብድናም የሆነውን የዛን ዘመን ስምምነት አስታውሰው የሚቀረሹ ሆነዋል።

ወደግድቡ አሁናዊ ሁኔታ ስንምጣ ፤ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት በተገኘ ወቅታዊ መረጃ መሰረት አጠቃላይ ሂደቱ 95 ከመቶ ያህል ተጠናቆ በመጪዎቹ ጥቂት ወራቶች ውስጥ ፍጻሜውን እንድናይ በሚያደርግ ንቃትና ብርታት ውስጥ ነው። የሲቪል ሥራ ግንባታው 98.9 ከመቶ ከመድረሱም በተጨማሪ ሁለት ተርባይኖቹ 540 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ላይ ይገኛሉ።

አሁናዊ የውሃ መጠኑ 42 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ሲሆን ሲጠናቀቅ ወደ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ የሚደርስ የውሃ መጠን ይኖረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ግድቡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 5150 ሜጋ ዋት የሚደርስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መቻሉ ሌላ ብስራት ሆኖ የሚነሳ ነው። ሕዝባዊ እንቅስቃሴው እንደቀጠለ ነው ከሕዝብ በሕዝብ ለሕዝብ በሆነ መርህ በምንምነት ውስጥ እዚህ ደረጃ ስናደርሰው ብዙዎች በስላቅ አይችሉም፤ አይሆንላቸውም ሲሉን ነበር።

አለመቻልን ተረት አድርገን በራስ ገንዘብ፣ በራስ እውቀት፣ በራስ ጉልበት አንጸባራቂ ድልን አስመዝግበናል። በያዝነው የ2016 በጀት ዓመት በስድስት ወራት ሕዝባዊ ተሳትፎ ብቻ ከ643 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል። የግድቡ መሰረት ከተጣለበት ከመጋቢት 24/ 2003 ዓ.ም እስከ አሳለፍነው ወር ጥር መጀመሪያ ድረስ ከሀገር ውስጥና ከውጪ፣ ከቦንድ ሽያጭ፣ ከልገሳ ከተለያዩ ምንጮች ወደ 19 ቢሊዮን ብር ያህል ተሰብስቧል። ቀጣይ በሚኖረው ሂደትም መሰል ተሳትፎዎችን በማድረግ ፍጻሜውን ለማየት ብርቱ ርብርብ በመደረግ ላይ ነው።

ዓባይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የእውቀት፣ የጉልበት፣ የገንዘብና የጊዜ አሻራ ነው። መቀነትን ፈትቶ ያለንን ከመስጠት ጀምሮ የቻልነውን ሁሉ ያደረግንበት የህብረ ብሄራዊነት አርማችን ነው። ከድህነት ወጥተን፣ ከተረጂነትና ከኋላቀርነት ርቀን በኃይል ምንጭ ራሳችንን ከመቻል አልፈን ኢኮኖሚያችንን የምናሳድግበት አንዱ የተስፋችን መሰረት ነው። አጋምዶና አስተሳስሮ እናንተ ማለት ይሄን ናችሁ የሚል የአብሮነት መንፈስ የዘራብን ታሪካችን ነው።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You