የብርዕ፣ የአገዳና የጥራጥሬ ሰብሎችን ምርታማነት ለማሳደግ የምርምር ሥራ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡በብርዕ፣ በአገዳና በጥራጥሬ ሰብሎች ላይ አዳዲስ ዝርያዎችን በማፍለቅ ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግና ምርታማነትን ለማሳደግ የምርምር ሥራዎች በተጠናከረ ሁኔታ እየተሠሩ ነው ሲል የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ፈቶ ኢስሞ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በብርዕ፣ በአገዳና በጥራጥሬ ሰብሎች ላይ አዳዲስ ዝርያዎችን በማፍለቅ ለሀገር አርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግና ምርታማነት ለማሳደግ ከዚህ በፊት ከነበረው የምርምር ሥራ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው፡፡

ተቋሙ በብርዕ፣ በአገዳና በጥራጥሬ በአምስት ሰብሎች ማለትም በስንዴ፤ በገብስ፣ በጤፍ፣ በማሽላና በቆሎ ላይ የዝርያ የማሻሻል ሥራ በመሥራት የአርሶ አደሩን ፍላጎት 95 በመቶ ለማሟላት ከሌሎች ሰብሎች የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ የምርምር ሥራ እየተሠራ ነው፤ እየተሠራ ያለውም አዳዲስ ቴክኖሎጂን የማፍለቅ ሥራ የሀገርን ምርትና ምርታማነትን በእጥፍ የሚያሳደግ ነው ብለዋል፡፡

የብዕር፣ የአገዳና የጥራጥሬ ሰብሎችን የማሻሻል ሥራ ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ምርምር ውጤታማ በማድረግ የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር አጠቃቀም ፍላጎትን በበቂ ሁኔታ ለመሸፈንና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሀገሪቱን የግብርና ዘርፍ ለማዘመን፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ በሕዝብ እድገት ልክ ግብርናውን ለማሳለጥ የግብርና የምርምር ሥራና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማፍለቅ ሥራ በተጠናከረ መንገድ መሥራት አስፈላጊ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ምርትና ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ በብዕር፣ በአገዳና በጥራጥሬ ሰብሎች ላይ የተለያዩና ለየት ያሉ ምርምሮች እየተሠሩ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከግብርና ዘርፍ ለማሳደግ ከዚህ በፊት የሀገሪቱን የአየር ንብረት ግምት ውስጥ የሚያስገቡና የአየር ፀባዩን የሚላመዱ የሰብል ማሻሻያ ሥራዎች ይሠሩ እንደነበር የገለጹት ፈቶ (ዶ/ር) በአሁን ሰዓት እየተሠሩ ያሉ ምርምሮች የአየር ንብረቱን መላመድ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ምርት የሚያሰገኙ ናቸው ብለዋል፡፡

በተቋሙ እየተሠሩ ያሉት የተለያዩ የስብል የምርምር ሥራዎች እንደ ሀገር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ባለው ሥራ ላይ ትልቅ ውጤት እያስገኙ ነው፤ እየተሠሩ ያሉ ምርምሮችም አትክልቶችንና ፍራፍሬዎች እንዳይበላሹ ከሚያደርግ የምርምር ሥራ ወደ ሰብል ዘረመል ማሻሻል ተሸጋግሯል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በሽታን፣ ድርቅን መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን በምርምር በማግኘት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረግ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት በመሆኑ ሀገሪቱ በስንዴ ምርት ራሷን ችላለች ብለዋል፡፡

“የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለግብርናው ግብዓት ለማድረግ የሚሠራው ሥራ እያደገና እየዘመነ መጥቷል፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማፍለቅ ሥራ ከዚህ በፊት አስር ሄክታር መሬት ላይ ብቻ ነበር ዘር የሚዘራው፤ አሁን ወደ ኩታገጠም ከፍ እንዲል ሆኗል” ያሉት ዳሬክተሩ የቴክኖሎጂ ግኝትን አርሶ አደሩ በሚፈልገው ልክ አባዝቶ ተደራሽ ለማድረግ የመሬት እጥረት እንዳለም ጠቁመዋል፡፡

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You