የሙአለ ሕፃናት ትምህርትና ሥነ-ዘዴው

ኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርትን ማስኬድ ከጀመረችባቸው የትምህርት ደረጃዎች አንዱ አፀደ-ሕፃናት (ኬጂ) መሆኑ ይታወቃል። በአሁኑ ዘመንም የትምህርት ደረጃው እንደሌሎቹ የትምህርት ደረጃዎች አስፈላጊው ትኩረት ተሰጥቶት ተግባራዊ እየተደረገ ላይ ይገኛል። በመላ ኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረጉ ካሉት ሙአለ-ሕፃናት ተቋማት መካከል በመዲናዋ አዲስ አበባ የሚገኘውና በሞዴልነት ተወስዶ የብዙዎች አይን ማረፊያና የጉብኝት ምእራፍ የሆነው የአፍሪካ አንድነት ቁጥር ሁለት አፀደ ሕፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው።

ሙአለ ሕፃናት (ኬጂ) ወይም የመጀመሪያው የልጅነት ትምህርት በመባል ይታወቃል። ለልጆች ትምህርት እድገትም አስፈላጊ አካል ሆኖ ይጠቀሳል። ልጆችን ለሁለት ዓመት በሙአለ ሕፃናት ፕሮግራም ማስመዝገብና ማስተማር የትምህርት ችሎታቸውን እንዲያዳብሩና የሕይወት ክህሎት ቀስመው ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ይረዳል። በአብዛኛውም የሶስት አመት ልጅ የመዋዕለ ሕፃናት ፕሮግራሞችን በየሳምንቱ ከ5 እስከ 15 ሰአታት እና የአራት ዓመት ሕፃናት ደግሞ ፕሮግራሞቹን ለ15 ሰአታት ይወስዳሉ።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ወደ ሙአለ ሕፃናት (ኬጂ) ፕሮግራም የሚገቡ ልጆች ቁጥሮችን መቁጠር፣ ቁጥሮችን እና ፊደሎችን መለየትና ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደሚችሉና መሰል ክህሎቶችን ማዳበር ይጀምራሉ። በመዋዕለ ሕፃናት ልጆች በራስ መተማመንና ነፃነትን ይገነባሉ። ማህበራዊ ክህሎቶችን ይማራሉ። አዳዲስ ጓደኞችንም ያፈራሉ።

ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት ሁለት ወይም ሶስት ዓመት የሙአለ ሕፃናት መርሀ ግብር የተከታተሉ ተማሪዎች በአስራ ስድስት ዓመታቸው በእንግሊዝኛና በሒሳብ ትምህርቶች ከሌላው የበለጠ ውጤት እንደሚያመጡ ጥናቶቹ ያመላክታሉ። እነዚህም “የተረጋገጡ ውጤቶች″ ናቸው ይላል።

ከመማር-ማስተማር ሥነዘዴ አኳያም ወላጆችና የሙአለ ሕፃናት አስተማሪዎች እንዴት አብረው መስራት እንዳለባቸው በጥናቱ ላይ የሰፈረ ሲሆን፣ ሙአለ ሕፃናት ወይም የሙአለ ሕፃናት ትምህርት በወላጆች ወይም በአሳዳጊዎች፣ ቤተሰቦች እና አስተማሪዎች መካከል አንድነት ተፈጥሮ በጋራ የሚከናወን ነው። የመማር-ማስተማር ስራውም በተሻለ ሁኔታ ይካሄዳል። ትምህርቱ ለልጆች እድገትና አጠቃላይ ሰብእና ግንባታም በጣም አስፈላጊ አካል ሆኖ ይወሰዳል።

በመሆኑም ወላጆች ወይም አሳዳጊ ትክክል የሆነውን ከስህተት፣ ቋንቋውን፣ ባህሉን እና እንደ ደግነትና መከባበር ያሉ እሴቶችን ለልጁ ማሳወቅ ይጠበቅበታል። ቤተሰብ ስለልጁ ፍላጎት እና እንዴት መማር እንደሚፈልግ ማወቅ፤ መምህራንንም መጠየቅ አለበት። መምህራን በሙአለ ሕፃናት ላይ ስለሚሆነው ነገር እና ልጁ በቤት ውስጥ እንዴት መማር እንዳለበት ስለሚረዱ መንገዶች ይናገራሉ።

በሙአለ ሕፃናት ውስጥ አስተማሪዎች ልጆች በጨዋታ መልክ እንዲማሩ ያበረታታሉ። እነዚህም ሥዕል መሳል፣ መዘመር መዘመር፣ ተራራ መውጣት፣ መቆፈር እና ከቤት ውጪ መሮጥ፣ በአሻንጉሊት መጫወት እና መጽሐፍ ማንበብን ያካትታሉ። ጨዋታ ልጆች ከሌሎች ጋር በመተባበር ነገሮችን ሲጋሩ እና ተራ በተራ ሲጫወቱ፣ ሃሳባቸውን እንዲጠቀሙ እና አዲስ ነገሮችን እንዲያገኙ ያበረታታል። ልጆች ቋንቋን ለምሳሌ እንግሊዝኛን እንዴት እንደሚናገሩ እና እንደሚረዱ ጨምሮ ስለ ድምጾች፣ ቃላት እና ቋንቋ ይማራሉ።

የሙአለ ሕፃናት (ቅድመ ሙአለ ሕፃናት፣ ሙአለ ሕፃናት፣ እና አንደኛ ክፍል) ተቋማትና ፕሮግራሞች ከሁሉም አስተዳደግ (ዳራ) የመጡ ወላጆችን የማህበረሰባቸው አካል በማድረግ በደስታ ይቀበላሉ። ወላጆች የሚገናኙበት፤ ታሪኮችን የሚለዋወጡበት እና እርስ በርስ የሚማሩባቸው ቦታዎች ናቸው። አስተማሪዎች ስለልጆችና ባህላቸው ማወቅ ይፈልጋሉ። ይህ ለልጆች ትርጉም ያላቸውን ፕሮግራሞች ያዘጋጁ ዘንድ ይረዳቸዋል። ይህም በባህላዊ ቀናት እና ዝግጅቶች ላይ የተመሰረቱ እንቅስቃሴዎችንና በሌሎች ውስጥ ያለውን ልዩነት ማክበርን ያካትታል።

አስተማሪዎች ሁሉንም ልጆች በእንቅስቃሴዎች ውስጥ እኩል ያሳትፋሉ። ስለዚህ እንግሊዝኛ የማይናገሩ ልጆች እንደሌሎች የመጫወት እና የመማር እድሎችን ያገኛሉ ማለት ነው። አንዳንድ የሙአለ ሕፃናት ፕሮግራሞች ትንሽ ቋንቋን ለምሳሌ እንግሊዝኛ የሚናገሩ ወይም ጭራሽ የማይናገሩ ልጆችን የሚረዱ ሁለት ቋንቋ ተናጋሪ አስተማሪዎች አሏቸው። እንዲሁም ልጆች ከሌሎች ጋር እንዲስማሙ፣ ሌሎችን እንዲቀበሉና የባህል ልዩነቶችን እንዲያከብሩ ያስተምሯቸዋል።

የሙአለ ሕፃናት ፕሮግራሞች ዓይነቶችን በተመለከተም ልጆች የሦስት ዓመት ልጅ ሙአለ ሕፃናትን መርሀ ግብር በረዥም (ሙሉ) ቀን ማቆያ ማእከል ወይም ብቻውን የሚሰራ ሙአለ ሕፃናት መከታተል ይችላሉ። እነዚህ አገልግሎቶች ብዙውን ጊዜ ለአራት ዓመት ልጅ የሙአለ ሕፃናት ፕሮግራም ይሰጣሉ።

እንዲሁም፣ የረጅም (ሙሉ) ቀን የእንክብካቤ ማዕከል የሙሉ ቀን ትምህርት እና እንክብካቤ መስጠት ይችላል። ይህም የሙአለ ሕፃናት ፕሮግራምን ይጨምራል። በአስተማሪ የሚመራው የሙአለ ሕፃናት ፕሮግራም ከተጨማሪ የትምህርትና እንክብካቤ ሰዓታትም ጋር ሊጣመር ይችላል።

ከአውስትራሊያ (Government of Victoria) የተገኘው ሰነድ የሙአለ ሕፃናት ፕሮግራም የሚሰራው በተወሰኑ ቀናትና በተወሰኑ ጊዜያት ብቻ መሆኑን ያሳያል። እራሱን ችሎ ለብቻው የሚሰራ አገልግሎት በዓመት በትምህርት ጊዜ ለ40 ሳምንታት የሚሠራ ሲሆን፤ ከትምህርት ቤቶች ጋር በተመሳሳይ ጊዜ እረፍት ያደርጋል። እነዚህ ቀናት እና ሰዓታት የሚወሰኑት በሙአለ ሕፃናቱ በሚሰጡ አገልግሎቶች ነው ሲልም ነው የፕሮግራም አይነቶችን ከነምንነታቸው ነው ሰነዱ የሚያስረዳው።

ከቅድመ ሙአለ ሕፃናት እስከ 12ኛ ክፍል ሥርዓተ ትምህርትና ዲስትሪክት አቀፍ ፕሮግራሞች የሥርዓተ ትምህርት እና የትምህርት ፕሮግራሞች ቢሮ የሙአለ ሕፃናት መምሪያ መጽሐፍ እንደሚለው የሙአለ ሕፃናት ትምህርት ልጆችን በትምህርት ቤት እና በህይወት ውስጥ ስኬታማ ለመሆን ዝግጁ ያደረጋቸዋል። ሊያድጉና ሊማሩ የሚችሉበት አስተማማኝ ቦታ ነው። ወላጆችና መምህራን ስለልጆቹ የወደፊት ስኬታማነት ወሳኝ የሆነ ወዳጅነት የምጥሩበት ቦታ ነው። የማስተማር ፕሮግራሙ በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ከሚገኙ ልጆች ፍላጎቶች ጋር የሚጣጣምበት ቦታ ነው።

ከዚህ ባለፈ ሙአለ ሕፃናት ልጆች በማንበብ፣ በመፃፍ፣ በሂሳብ፣ በትላልቅ እና በትናንሽ የቡድን ትምህርቶች እና የትምህርት ማእከሎችን በመሳሰሉ፣ በተለያዩ የትምህርት ተሞክሮዎች የሚሳተፉበት ስፍራ ሲሆን፤ የልጆችን የማወቅና የአዲስ ግኝት ጉጉትና ደስታ ያበረታታል። ልጆች እንደ ልዩና ብርቅ ሰው ተቀባይነት የሚያገኙበት ስፍራም ነው። ራስን ማክበርና በራስ መተማመን የሚጠናከርበት ልዩ ቦታም ጭምር ነው።

እንደ የመማሪያ መጽሐፍ መረጃው ከሆነ ሙአለ ሕፃናት የራሱ ግቦችም ያሉት ሲሆን፤ እነዚም በራስ መተማመንን ማሳደግ፣ የመማር ዘይቤዎችን መከተልና፣ እውቀትና ክህሎትን ማዳበር ናቸው። በራስ መተማመንን በማሳደግ ግብ ውስጥ መከበርና ዋጋ መስጠት፤ ስኬትን መለማመድና ስሜትን በተገቢ ሁኔታ መግለፅን ያካትታል። የመማር ዘይቤዎችን መከተል በሚለው ግብ ስር ደግሞ መመርመርና አማራጭ መውሰድ፣ በግል፣ በጥንድ፣ ከብዙ እና ጥቂት ቡድኖች ጋር መስራት እና መጫወት፣ ሃሳብን እና አስተያየትን መግለፅና ችግሮችን በአግባቡ መፍታት ይካተቱበታል።

እውቀትና ክህሎትን ማዳበር በሚለው ግብ ስርም ማዳመጥ፣ ማንበብ፣ ንግግር፣ እና መፃፍ፣ ዕቃዎችን መሰብሰብ፣ በትኩረት ማጤን፣ በስም መለየት፣ እና በአይነት እየለዩ መደርደር፣ መቁጠርና ማነፃፀር፣ ማወዳደር እና ከመጻሕፍትና ከተሞክሮዎች ታሪኮችንና ሃሳቦችን ማጋራት ይካተታሉ። እነዚህ በሌላው ዓለም የሚታዩ ቢሆንም ከሞላ ጎደል በአፍሪካ አንድነት ቁጥር ሁለት ትምህርት ቤትም ይታያሉ።

ለስደተኞች እና ለጥገኝነት ጠያቂ ሕፃናት ቀደም ብሎ ስለሚጀመር ሙአለ ሕፃናት (Early Start Kindergarten) ላይ “ሙአለ ሕፃናት መሄድ ለምን ያስፈልጋል?″ በሚለው ንኡስ ርእስ ስር እንደ ሰፈረው ከሆነ፣ ሙአለ ሕፃናት፤ ልጆችን በትምህርት ቤት እና በህይወት ውስጥ ስኬታማ ለመሆን ዝግጁ ያደረጋቸዋል። በሙአለ ሕፃናት ውስጥ ልጆች ጨዋታን በመጠቀም ቋንቋን፣ ቁጥሮችን እና ቅርጾችን (ፓተርን) ይማራሉ። እንዲሁም ከሌሎች ጋር እንዴት መስማማት፣ መጋራት፣ ማዳመጥ እና ስሜታቸውን እንዴት መቆጣጠር እንደሚችሉ ይረዳሉ። መምህራን ልጆች የማወቅ ጉጉት እንዲኖራቸው፣ ፈጠራን እንዲማሩ እና በልበ ሙሉነት እንዲማሩ ይረዷቸዋል።

ከቅድመ ሙአለ ሕፃናት እስከ 12ኛ ክፍል ሥርዓተ ትምህርት እና ዲስትሪክት አቀፍ ፕሮግራሞች የሥርዓተ ትምህርት እና የትምህርት ፕሮግራሞች ቢሮ የሙአለ ሕፃናት መምሪያ መጽሐፍ″ ከሙአለ ሕፃናት (Kindergarte) መማር ፕሮግራሞች አኳያም የልጆቹንና መምህራኑን ሚና አስፍሯል።

ልጆች በትላልቅ እና በአነስተኛ ቡድን መማር እና በአስተማሪዎች የሚመሩ ተሞክሮዎችን በሚያካትቱ የተለያዩ የመማር ክንውኖች ላይ እንደሚሳተፉ የሕፃናት መምሪያ መጽሐፉ ይጠቁማል። በዚህም በመዋእለ ህፃናት ቀን፣ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለመጠቀም፣ ከሌሎች ልጆች ጋር ለመነጋገርና ለመጫወት፣ በጨዋታ ማእከሎችና በፕሮጀክቶች የተማሩትን ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ እድሎች ይኖሯቸዋል።

የሙአለ ሕፃናት አስተማሪ እያንዳንዱ ልጅ ያገኘ(ች)ውን እውቀትና ክህሎቶች ለመሰነድ እንዲቻል እያንዳንዱን ለውጥና መሻሻል በጥንቃቄ እየተከታተለ(ች) ይመዘግባል/ትመዘግባለች። በተጨማሪ፣ የተማሪዎችን ችግር የመፍታት ችሎታ ለማዳበር፣ አስተማሪዎች ብዙ ቀልጣፋ ተግባራትን እያከናወኑ የመማር ልምምዶች ይሰጧቸዋል።

የወላጆችን የትምህርት ተቋማት ጉብኝት በተመለከተም ‹‹ትምህርት ቤቱንና የልጅዎን መማሪያ ክፍል እንድትጎበኙ እናበረታታለን። የጉብኝት ፕሮግራም እንዲያዘጋጁ ለት/ቤቱ ይደውሉ። ሕንፃው ውስጥ እንደገቡ ወደ ትምህርት ቤቱ ጽህፈት ቤት ብቅ ብለው የጎብኝት ባጅ ማግኘት እንዳለብዎት ያስታውሱ›› በማለት ወላጆች ከልጆቻቸው ትምህርት ቤት መራቅ እንደሌለባቸውና ስለልጆቻቸው ውሎና የወደፊት አቅጣጫ በአግባቡ መከታተል እንዳለባቸው ያሳስባል። ይህ ደግሞ ለሁሉም ሀገርና ለሁሉም ሙአለ ሕፃናት ይሰራል ብለን እናምናለንና በልጆች አስተዳደግ፣ አያያዝና የወደፊቱን የነቃ ትውልድ የመፍጠሩ ከባድ ሥራ የመምህራን ብቻ እንዳልሆነ ያመላክታል። ወላጆችም ከዚሁ አኳያ ሊንቀሳቀሱ ግድ ይሆናል ብለን እናምናለን።

የአፍሪካ አንድነት ቁጥር 2 የቅድመ አንደኛ ደረጃ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አቶ አክሊሉ እሸቱ እንደሚናገሩት፤ የወላጆች ክትትል የሚፈለገውን ያህል አይደለም። ነገር ግን አፍሪካ አንድነት ቁጥር 2 የቅድመ አንደኛ ደረጃ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቅድመ አንደኛ ደረጃ (ከኬጂ 1 እስከ ኬጂ 3)ን ወቅታዊ ይዛታ ስንመለከት የምናገኘው ዘመናዊነትን ሲሆን፣ መገለጫውም የኬጂ 1 ተማሪዎች በተሟላ ሁኔታ ትምህርታቸውን መከታተል መቻላቸውና ትምህርት ቤቱም በሞዴልነት ለሌሎች አርአያ ሆኖ መቅረቡ ነው።

አፍሪካ አንድነት ቁጥር ሁለት የቅድመ አንደኛ ደረጃ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅድመ መደበኛ ትምህርትንም የሚሰጥ ተቋም እንደ መሆኑ መጠን ጥራቱን የጠበቀ፤ ለሌሎች በምሳሌነት ሊቀርብ የሚችል፤ ፅዳቱ የተሟላና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን መስፈርት ባሟላ መልኩ ሕፃናትን (ከኬጂ 1 እስከ ኬጂ 3) እያስተማረ ይገኛል።

ኬጂ 1 እና 2 ተማሪዎች ያማረ ምንጣፍ ላይ እንደፈለጋቸው፣ ተገቢ ባለሙያ ተመድቦላቸው እየተንከባለሉ የሚያነቡ፣ የሚጽፉና የሚጫወቱ መሆናቸው የተነገረንና እኛም የተመለከትን ሲሆን፤ ከምሳ በኋላም ለአንድ ሰዓት ያህል የእንቅልፍ ሰዓታቸውን የሚያሳልፉበት ያማረ መኝታ ክፍል ከተሟላ ፍራሽና ትራስ ጋር መሰናዳቱን ተመልክተናል። ይህም በራሱ ሌሎች ሊወስዱት የሚገባ ተሞክሮ መሆኑ በበርካታ የሥነትምህርት ባለሙያዎች ተመስክሮለታል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ጋር በመሆን የአፍሪካ ከንቲባዎች የሊደርሺፕ ኢኒሼቲቭ (AMALI) ተሳታፊዎችን አፍሪካ አንድነት ቁጥር 2 የቅድመ አንደኛ ደረጃ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ማስጎብኘታቸው ይታወሳል። ሰፊ የሚዲያ ሽፋንም አግኝቶ እንደነበር አይዘነጋም።

የጉብኝቱ አላማም “ጉብኝቱ በዋናነት በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የቀዳማይ ልጅነት ፕሮጀክት አተገባበር ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በማየት ፕሮግራሙን በቀጣይነት ለመደገፍ እንዲቻል ታስቦ የተካሄደ″ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፤ የጉብኝቱ ተሳታፊዎችም″ በትምህርት ቤቱ (አፍሪካ አንድነት ቁጥር 2 የቅድመ አንደኛ ደረጃ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት) ቅጥር ግቢ በመዘዋወር የሕፃናቱን የመማሪያ፣ የመጫወቻ እና የማሸለቢያ ክፍሎች″ መጎብኘታቸው ታውቋል።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You