አትሌቶች በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚደርስባቸው ጉዳት ከተለመደው ልምምድና ውድድር የሚቀርበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ከጉዳታቸው አገግመው ወደቀድሞ ብቃታቸው ለመመለስም ብዙ ፈተናዎችን ማለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሴት አትሌቶች ደግሞ ከዚህ ባለፈ ከውድድር ሊያርቃቸው የሚችል ሌላም ፈተና አለባቸው። ይህም ከወሊድ ጋር በተያያዘ ምክንያት ለረጅም ጊዜ ከስፖርቱ የሚርቁበት እድል ነው፡፡
ሴት አትሌቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ አስቸጋሪውን ተፈጥሯዊ ሂደት አልፈው ወደ ቀደመ አቋማቸው በመመለስ በውድድሮች ድል መንሳት አስቸጋሪ መሆኑን መረዳት አያዳግትም፡፡ ነገር ግን በርካታ ብርቱ ሴት አትሌቶችን ያፈራችው ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ አልፈው ወደ ውጤታማነት መመለስ እንደሚቻል በተደጋጋሚ አሳይተው ለሌሎችም ምሳሌ የሆኑባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም፡፡
ከእነዚህ አትሌቶች መካከል አንዷ ደጊቱ አዝመራው ናት፡፡ በረጅም ርቀት ሩጫዎች የምትታወቀው አትሌት ደጊቱ እአአ በ2019 በሞሮኮ በተደረገው የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ በግማሽ ማራቶን ሃገሯን ወክላ በመሳተፍ የብር ሜዳሊያ ባለቤት ነበረች፡፡ በዚያው ዓመት በተደረገው የአምስተርዳም ማራቶን ስታሸንፍ፣ በራክ ግማሽ ማራቶን ደግሞ 4ኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠናቀቀችው፡፡ በቀጣዩ ዓመት የቫሌንሺያ ማራቶንን በ4ኛነት ስታጠናቅቅ፤ እአአ በ2021 ደግሞ በለንደን ማራቶን 2ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡
እመጫቷ አትሌት ደጊቱ ከዚያ በኋላ ያሉትን ጊዜያት በእርግዝና እና ወሊድ ምክንያት ከውድድር መድረኮች ርቃ ቆይታለች፡፡ ከወሊድ መልስ በተያዘው የውድድር ዓመት ግን ወደ ውድድር የተመለሰች ሲሆን፤ ከሳምንታት በፊት በቱኒዚያ በተደረገው የአፍሪካ ሃገር አቋራጭ ቻምፒዮና ሃገሯን ወክላ ተሳትፋለች፡፡ በባርሴሎና ማራቶን ደግሞ አስደናቂ ድልን አስመዝግባለች፡፡
የባርሴሎናውን ውድድር ተከትሎም በርካታ የዓለም መገናኛ ብዙኃን የዘገባ ሽፋናቸውን ያደረጉት የአትሌቷን ጥንካሬ ነበር፡፡ ይህ ጥንካሬ ወደስፔን ከማምራቷ አስቀድሞ ባደረገችው ከፍተኛ ዝግጅት የተገኘ መሆኑን የምታስታውሰው አትሌቷ፤ ከወሊድ በኋላ ጥሩ ሰዓት አስመዝግባ በማሸነፏ ደስተኛ መሆኗን ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራት ቆይታ ገልጻለች።
ከእርግዝናዋ ጋር በተያያዘ ከ3 ወር አንስቶ መደበኛ ልምምዷን ብታቆምም ረጅም የእግር መንገድ የመሄድ ልምድ ማዳበሯ ልጇን በምጥ እንድትገላገል ረድቷታል፡፡ ከወሊድ በኋላ ወደ ስፖርቱ ለመመለስ 4 ወር የፈጀባት ሲሆን፤ እስከ 6 ወር እያጠባችም በጂምናዚየም ጥንካሬዋን ልትመልስ ከዚያም ወደ ልምምድ ልትገባ ችላለች፡፡
በባንኮክ ግማሽ ማራቶን ወደ ውድድር በመመለስም 5ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች፡፡ በጃንሜዳ ኢንተርናሽናል የሃገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከተወዳደረች በኋላም በታንዛኒያ የነሐስ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አስገኝታለች፡፡ ከታንዛኒያ መልስ ከሁለት ሳምንት፣ ከወለደች ደግሞ ከ1 ዓመት ከ4 ወር በኋላም ወደ አቋሟ በመመለስ በከባዱ የአትሌቲክስ ውድድር ማራቶን (ባርሴሎና) ከ2ሰዓት ከ20 ደቂቃ በታች በመሮጥ አሸናፊ ልትሆን ችላለች፡፡
ይህንንም ተከትሎ ‹‹ከተሠራ ሁሉም እንደሚቻል ተምሬበታለሁ፡፡ በእርግጥ ሕጻን ልጅን ትቶ ለውድድር ወደሌላ ሃገር መጓዝ ከባድ ነው፤ ነገር ግን ሩጫ ሥራችን በመሆኑ መጠንከር የግድ ነው። አትሌቶች ከወሊድ በኋላ እንደቀድሞ የምንመለስ አይመስለንም ነገር ግን ከልጅ ደስታ በቶሎ ተላቀን ጠንክረን ብንሠራ ወደነበርንበት የማንመለስበት መንገድ የለም፡፡ እኔን መሰል ሴቶች በሕይወታችን ማድረግ ያለብንን በጊዜው ማድረግ አለብን ምክንያቱም ጥንካሬያችን ይመለሳል›› ስትልም መልዕክቷን ታስተላልፋለች፡፡
ደጊቱ ከወሊድ በኋላ በቶሎ ውጤታማ ከመሆኗ ባለፈ ብዙ አትሌቶች የማይደፍሩትን በአጭር ጊዜ ውስጥ ረጃጅም ርቀቶችን በመሮጥ (ሁለት የሃገር አቋራጭ፣ ግማሽ ማራቶን እና ማራቶን) ጥንካሬዋን አስመስክራለች፡፡ ይህም በሥራ ላይ የተመሠረተ እንደመሆኑ ስጋት ላይ የማይጥልና፤ ራስን ነፃ ማድረግ አስፈላጊ ለመሆኑም ማሳያ ናት፡፡ አትሌቷ አሁን ወደ ቀድሞ አቋሟ የተመለሰች ቢሆንም በምትታወቅበት ማራቶን ግን በበለጠ ጥንካሬና ብቃት ላይ መገኘት እንዳለባት እምነቷ ነው፡፡ በመሆኑም ጠንክራ በመሥራት ለሚቀጥለው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ለመወከልም ታልማለች፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም