የሸማቹን ሸክም የሚያቀሉ ወሳኝ ርምጃዎች የተወሰዱበት መጋቢት ወር

የመጋቢት ወር የሸማቾች ቀን የተከበረበት ብቻ ሳይሆን፣ ለሸማቹ ብስራት የተበሰረበት ወር ነው ማለት እችላለሁ። በዚህ ወር ሸማቹን የተመለከቱ ሶስት አበይት ተግባራት የተከናወኑበት ልዩ ወር ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። መንግሥት የሸማቹን ጀርባ ያጎበጡ ሸክሞችን የሚያቀሉ ርምጃዎችን መውሰድ መጀመሩ የሸማቾችን ተስፋ እያለመለመ ይገኛል። የችርቻሮ ንግድን ለውጭ ኩባንያዎች ለመክፈት መወሰኑ በችርቻሮ ገበያው ላይ ማርሽ ቀያሪ ነው።

ሸማቹ ዋጋ አወዳድሮ፣ ጥራት አማርጦ እንዲሸምት ከማስቻሉ ባሻገር አቅርቦቱን ፍጹም ያሻሽለዋል ተብሎ ይጠበቃል። በአፈታትና በአቦሰጥ የሚመራውን የችርቻሮ ንግድም ያዘምነዋል ተብሎ ይጠበቃል። ሌላው ሰሞኑን በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀው ደንብ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የሕብረተሰብ ክፍል ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የሚያደርግ ነው። ይህ በተለይ በመሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ ተጥሎ የነበረውን የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚያቀል ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አምራቹን ከሸማቹ በቀጥታ ያለ ደላላ ጣልቃ ገብነት ለማገናኘት የሚያስችሉ የመሸጫ መደብሮችን በመስጠቱ የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ ሊረጋጋ ችሏል። ቲማቲም ባለፈው ዓመት በዚህ ሰዓት በኪሎ ከ80 ብር በላይ የነበር ሲሆን አሁን ላይ ከ12 እስከ 35 የገባ ሲሆን፣ ሽንኩርት ደግሞ ባለፈው ዓመት በዚህ ሰዓት ከ120 ብር በላይ የነበር ሲሆን አሁን ግን እንደየአካባቢው ከ40 እስከ 60 ብር ይገኛል። ይህ ደላላ ከግብይት ሥርዓቱ ተወግዶ አምራችና ሸማች በቀጥታ ሲገናኝ እንዲሁ ሁለቱም ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያሳያል።

በእህልና ጥራጥሬም አምራቹን ከሸማቹ በቀጥታ መገናኘት ከተቻለ ዋጋውን ማረጋጋትና መቀነስ ይቻላል። የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ባካሄደው ጥናት ምርት ሸማቹ ጋ የሚደርሰው 58 በመቶ ተጨምሮበት ነው። የሚገርመው ይህ ጭምሬ ከአምራቹ ሳይሆን ከደላላውና ከነጋዴው ኪስ ነው የሚገባው። የግብይት ሰንሰለቱ አምራቹንም ሆነ ሸማቹን ተጠቃሚ እያደረገ አይደለም። ለዚህ ነው የሕገ ወጥ ደላላና የስግብግብ ነጋዴ ሲሳይ ነው እየተባለ የሚተቸው።

መንግሥት አሁንም ደላላውን ከግብይት ሰንሰለቱ የሚያስወጣ ሕግ ሥራ ላይ ሊያውል ይገባል። በዚያ ሰሞን የግብይት ሰንሰለቱ ላይ እንቅፋት በመፍጠር የዋጋ ንረት እንዲባባስ ያደረጉ 790 ደላላዎች ላይ አስተዳደራዊ ርምጃ መወሰዱን፤ በእህልና ጥራጥሬ፣ በአትክልትና ፍራፍሬና በቁም እንስሳት ግብይት ውስጥ የነበሩ ደላላዎችን ፈቃድ በመሰረዝ ከግብይት ሂደቱ እንዲወጡ መደረጉን፤ በቀጣይ የደላላን ጣልቃ ገብነት በዘላቂነት እልባት ለመስጠት የሚያስችል መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገልጾ ነበር። እኛም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን መመሪያውን ከምን አደረስኸው ስንል እንጠይቃለን። የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አርቅቆ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ ከተሻሻለ በኋላ ሰሞኑን በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወደ አጸደቀው የአከራይ ተከራይ አዋጅ እንለፍ።

የአከራይ ተከራይ አዋጁ ደግሞ ጨዋታ ቀያሪና የተከራዩን ሸክም የሚያቀልና መብቱን የሚያስከብር ነው። የነፃ ገበያ ሀዋሪያና ደቀ መዝሙር በሆኑት እንግሊዝና አሜሪካ ሳይቀር ነፃ ገበያ ስድ አይለቀቅም። ፈር ሲለቅ መንግሥታት ጣልቃ በመግባት ፈር ያሲዙታል። በዩናይትድ ኪንግደም ለንደንን ጨምሮ በዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች፣ በአውሮፓ በርካታ ሀገራት፣ በላቲን አሜሪካ እንዲሁ በርካታ ሀገራት የአከራይ ተከራይ ሕግ አላቸው። አከራይ ከመሬት ተነስቶ ዋጋ አይጨምር፣ ተከራይ አያስለቅቅም። ከዚህ አልፈው የኪራይ ተመንና የዋጋ ጣራ አላቸው።

በመንግሥት በተለምዶ የኪቤአድና የቀበሌ ቤቶች ኪራይ ዋጋ በተወሰነ ደረጃ የዋጋ ተመን ያላቸው ሲሆኑ፣ ዋጋቸውም ከግል ቤቶች ርካሽ ነው ማለት ይቻላል። በአንጻሩ የግለሰብ ቤቶች ኪራይ ግን ስድ የተለቀቀና ተከራዩን የሚያማርር ነው። በሰበብ አስባቡ ዋጋ በየጊዜው የሚጨመርበት፣ የተከራዩን መብት የማያከብር ነው። አከራይ እንዳሻው ኪራይ የሚጨምርበት፣ ከቤት የሚያስለቅቅበት፣ ከሁሉም በላይ ደላላ ጣልቃ እየገባ ዋጋ የሚተምንበት ተከራዩን ያማረረ ነበር። ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየጎነቆለ ያለ ቁልፍ ችግር ነበር ማለት ይቻላል። አሁን ግን ምንም እንኳ የዘገየ ቢሆን ይሄን አንገብጋቢ ችግር የሚቀርፍ አዋጅ ጸድቋል።

መንግሥት ጣልቃ ገብቶ የመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋ መናርን ለማስተካከል፣ የቤት ኪራይ ውል በሕግ እንዲመራ ለማድረግ የሚያስችለውንና በአከራይና ተከራይ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን አዋጅ፣ ባለፈው መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀደቀ። አዋጁ ‹‹የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ ዓላማው ግልጽና ተገማች የሆነ የመኖሪያ ቤት ኪራይ አስተዳደር፣ እንዲሁም የአከራይና

ተከራይን መብት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የሚያስተናግድ ሥርዓት ለመዘርጋት ያለመ ነው። በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕጎች ከሚታወቁ ሰብዓዊ መብቶች መካከል አንዱ መኖሪያ ቤት የማግኘት መብት ሲሆን፣ መንግሥት የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ለማሻሻል የተለያየ ጥረት ቢያደረግም ከፍላጎቱ ጋር መጣጣም እንዳልቻለ የሪፖርተር ዘገባ ያመለክታል።

በቤት ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት በመጠቀምም ምክንያታዊ ያልሆነ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪዎች በሀገሪቱ ከተሞች እየተስተዋሉ መምጣታቸውን፣ በዚህም ሳቢያ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች መቸገራቸውንና ተረጋግተው ኑሯቸውን እንዳይመሩ ማድረጉን፣ በተጨማሪም የመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋ መናር በከተሞች የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት እያባባሱ ከሚገኙ ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ መሆኑ፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የመንግሥትን አስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ሆኗል። የኪራይ ዋጋ ጭማሪን በተመለከተም በተቆጣጣሪው አካል ከሰኔ 30 ቀን ጀምሮ ለአንድ ዓመት የፀና የዋጋ ጭማሪ እንደሚደረግ ተገልጿል።

አዋጁ ከመታተሙ በፊት ከፀደቀበት ዕለት ጀምሮ የፀና እንደሚሆን የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) አብራርተው፣ አንድ የውል ዘመን ከሁለት ዓመት ሊያንስ እንደማይችል ገልጸዋል። የቤት ኪራይ ውልና ዋጋ እንደ ክልሎች ነባራዊ ሁኔታ መወሰን እንዳለበት የተደነገገ ሲሆን፣ ይህንንም የሚቆጣጠር በክልል ደረጃ የሚሰየም አካል እንዲኖር መደረጉን ሚኒስትሩ አስረድተዋል። በዚህ መሀል በሁለቱ ወገኖች መካከል አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ጉዳዩን ተቆጣጣሪው አካል እንደሚመለከተውና ወደ ፍርድ ቤት እንደማይሄድ ገልጸው፣ ይህም የሆነው በመደበኛ የሕግ ሂደት ላይ ጫና እንዳይፈጠር በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል።

አዋጁ ስለቤት ኪራይ ሲያብራራ፣ ለመኖሪያ ቤት የሚያገለግል ከአንድ ክፍል ቤት ጀምሮ መሆኑን፣ ለአጭር ጊዜ የኪራይ አገልግሎት የሚሰጡ ማለትም ሆቴል፣ ሪዞርት፣ እንዲሁም አልጋ ቤቶችን እንደሚያካትት ሚኒስትሩ አስረድተዋል። አዲስ የተገነባ ወይም ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከራይ ቤት የኪራይ ዋጋ በአከራይና በተከራይ ስምምነት የተዋዋይ ውል እንዲፀና ይደረጋል ሲሉ ጌዲዮን (ዶ/ር) ገልጸዋል። ተከራዩ ውሉን ማቋረጥ ቢፈልግ ከሁለት ወራት በፊት ቀድሞ ማሳወቅ እንደሚኖርበት በአዋጁ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ቤቱን ተከራይቶ ሲኖር የኪራይ ክፍያውን ለመጀመሪያ ጊዜ ለ15 ቀናት ካሳለፈና ለሁለተኛ ጊዜ ለሰባት ቀናት ካሳለፈ፣ አከራዩ ውሉን ማቋረጥ እንደሚችል ተደንግጓል። ተከራይ ሊጠየቅ የሚችለው ቅድመ ክፍያም ከሁለት ወራት የቤቱ ኪራይ ዋጋ ሊበልጥ አይችልም።

አከራዩ ቤቱን ለመሸጥ ሲፈልግ ለተከራዩ የማሳወቅ ግዴታ ባይኖርበትም፣ ቤቱን የሚገዛው ግን ውሉ እንዲቀጥል ካልፈለገ ለተከራዩ የስድስት ወራት ጊዜ መስጠት እንደሚኖርበት፣ ለአዲስ ተከራይ ሲያከራይም ከዚህ በፊት ከነበረው የኪራይ ዋጋ በላይ አድርጎ ማከራየት እንደማይችል ተደንግጓል። ነገር ግን ቤቱ የሚተላለፈው በስጦታ ከሆነ የውል ዘመኑ እስኪጠናቀቅ ድረስ ውሉ ቀጣይነት ይኖረዋል። በሌላ በኩል ቀደም ሲል ሲከራይ የነበረ የመኖሪያ ቤት ወይም ግንባታው የተጠናቀቀ አዲስ ቤት ያለ አገልግሎት ከስድስት ወራት በላይ እንዲቀመጥ ከተደረገ፣ ቢከራይ አከራዩ ሊከፍል ይችል የነበረውን የኪራይ ገቢ ግብር ተሠልቶ እንዲከፍል ይደረጋል።

የቤት ኪራይ ክፍያን በተመለከተም በባንክ ወይም በሌላ ሕጋዊ የኤሌክትሮኒክ ዘዴ ብቻ እንዲፈጸም በአዋጁ ተደንግጓል። አዋጁ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት የነበሩ የአከራይ ተከራይ ውሎችን የሚያስቀር አለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ አዋጁ ሲወጣ የነበረ ውል እስከ ቀጣዩ ሦስት ወራት ድረስ እንዲመዘገብ ይጠበቃል። ይህን አዋጅ የጣሰ አከራይና ተከራይ የወንጀል ቅጣት እንደማይጣልበት፣ ነገር ግን አስተዳደራዊ ቅጣት እንደሚጣልበት ተገልጿል።

አዋጁ የአከራዩንና የተከራዩን መብት በማጣጣም የሚያስከብር ስለመሆኑ ጠቁመው፣ በሁለቱ መካከል አለመግባባት ካለ በተቆጣጣሪው አካል በሚደረግ አስተዳደራዊ ፍትሕ የሚቀረፍ መሆኑን ሚኒስትር ጌዲዮን (ዶ/ር) አስረድተዋል። አዋጁ የመኖሪያ ቤት ችግር በስፋት በሚስተዋልባቸው ከተሞች ተግባራዊ የሚደረግ ስለመሆኑና ዝርዝር አፈጻጸሙ ግን ለከተማ መስተዳድሮችና ለክልሎች እንደሚሰጥ አመላክተዋል።

መንግሥት የመኖሪያ ቤት ፍላጎትን ለማሟላት ስላልቻለ ቁጥጥሩ ላይ ትኩረት አድርጓል የሚባለው አግባብ አይደለም ያሉት፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ በቤት ግንባታ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ገልጸዋል። አዋጁ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞችና የከተማ ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት ያጋጠማቸውን የኑሮ ጫና ለመቀነስ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ዜጎች ከሚያገኙት ገቢ ከ25 እስከ 30 በመቶ በላይ ለቤት ኪራይ ማዋል የለባቸውም ያሉት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ፣ አንድ ተከራይ ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ ሳይደረግበት በተከራየው ቤት ውስጥ ለሁለት ዓመታት ያህል ተረጋግቶ መኖር እንዲችል አዋጁ መብት እንደሚሰጠው አስረድተዋል። የቀረበው አዋጅ የመኖሪያ ቤቶችን ኪራይ ብቻ የሚመለከት እንደሆነ፣ የንግድ ቤቶችን የኪራይ ዋጋና ውልን በተመለከተ በሂደት እንደሚታይ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

አዋጁ ከመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋና የኪራይ ውል ጋር የተገናኙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ሥርዓት የሚያበጅ ከመሆኑ ባሻገር፣ መንግሥት ከቤት ኪራይ ገቢ ሊያገኝ የሚገባው የኪራይ ግብር በአግባቡ እንዲከፈል በማድረግ የከተሞችን ገቢ ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል። ለምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር ዕይታ ወደ ቋሚ ኮሚቴ ሳይመራ ድምፅ እንዲሰጥበት የተደረገ ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎ ረቂቅ አዋጁ በሦስት ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።

ሆኖም አዋጁ ዋና የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት አባባሽ የሆነውን የንግድ ሱቅና ሕንጻ ኪራይ አለማካተቱ ሙሉኡ እንዳይሆን አድርጎታልና መንግሥት እንደገና ሊያጤነው ይገባል ስንል በአክብሮት እናሳስባለን። በተረፈ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት በዘላቂነት እንዲፈታ በማዕቀፍ ማየት ይገባል። ሰላምን ማረጋገጥ፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ብልሹ አሠራርንና ሙስናን ማስወገድ፣ ጠንካራ የፊስካል ፖሊሲን በመከተል የፋይናንስ ሥርዓቱን ማረጋጋት፣ አምራቹንና ሸማቹን ይበልጥ በቀጥታ ማገናኘት እና የሕግ የበላይነትን በተለይ በግብይት ሥርዓቱ ማስፈን ይጠይቃል። በተረፈ ለዚህ ሁሉ ችግር ከዳረጉን ክፍተቶች አንዱ ነፃ ገበያን አዛብተንና አዛንፈን ስለ ምንረዳ ነውና ስለ ነፃ ገበያ ምንነትና አንድምታ ነጥቦችን እናነሳሳ።

በ”The Ethiopian Economic View”ድረ ገጻቸው ቢዝነስ ፣ ኢኮኖሚክስና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመጻፍ ፤ ማህበራዊ ሚዲያውን በተለይ ፌስቡክን ለበጎ አላማ በማዋል የሚታወቁት የኢኮኖሚክስ ባለሙያው አቶ ዋሲሁን በላይ ፤ እንደ ኢትዮጵያ ከሞላ ጎደል Progressive Capitalism (ማለትም በመንግሥት ፤ የግል ሴክተሩ እና የምርምር ተቋማት በመቀናጀት ስትራቴጂክ የሆነ አቅም በመፍጠር አቅርቦት እና ፍላጎትን ማቀራረብ ላይ ያነጣጠረ) ሥርዓት ለመተግበር በምትሞክር ሀገር ውስጥ ነፃ ገበያ ስለሆነ ማስገደድ አንችልም የሚሉ መግለጫዎች ፤ ነፃ ገበያ በመሆኑ መብታችን ነው ተባልን የሚሉ ሸማቾች እና ነፃ ገበያ በመሆኑ ዋጋ ተማኝ ነን የሚሉ አምራቾች/ሻጮች ፤ መስማት በጣም እንግዳ ነገር ነው ይላሉ።

ነፃ ገበያ ማለት በጥቂት የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ወይም ያለ መንግሥት ጣልቃ ገብነት ገበያውን አቅርቦት እና ፍላጎትን ተከትሎ እንዲመራ መፍቀድ ማለት ነው (ነፃ ገበያ የዋጋ ጉዳይ ብቻ አይደለም)። ነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ዋና ተዋናይ የሆኑት ሸማቾች እና አምራቾች/ሻጮች ሌላው ተዋናይ መንግሥት ተቀንሶ ገበያው ላይ የመወሰን መብት እንዲወስዱ የተሰጠ የውክልና አካሄድ ነው። በዜጎች መካከል ያለው የሀብት ክፍፍል ሲዛነፍም ሆነ ፍታሃዊነትን ለመጠበቅ ሲባል ገበያን ለብዙሃን ምቹነት ሲባል በመንግሥት መጎብኘቱ አይቀርም።

ምክንያቱም ነፃ ገበያን ይዞ ብቅ ካለው አዳም ስሚዝ (1723-1790) ጀምሮ ላለፉት 250 ዓመታት ነፃ ገበያ በወረቀት እንጂ በተግባር አሟልቶ መተግበር የቻለ አንድም ሀገር የለም። በዓለም የኢኮኖሚ ታሪክ ውስጥ ነፃ ገበያ ሥርዓት ምናባዊ ነው ተብሎ የሚተችበት ምክንያት ሙሉ ለሙሉ መተግበር አለመቻሉ ነው። ምክንያቱም መንግሥታት በጥቂቱም ቢሆን ገበያውን ማየት አለመቻላቸው የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ጣልቃ መግባታቸው ወደው ሳይሆን ተገደው ነው።

ሀገራት በተለይ ፖለቲከኞች ነፃ ገበያ ላይ ገደብ ለማስቀመጥ የሚደፍሩበት መሠረታዊ ምክንያት የሚመነጨው ለፖለቲካል ኢኮኖሚው ደህንነት ፤ ፍታሃዊነትን ለመጠበቅ እና የሕዝብ የጋራ መጠቀሚያ ሀብቶችን ለመፍጠር ሲባል ነው። ገበያ ቸል በተባለ ቁጥር የጥቁር ገበያ መፈርጠም ፤ የብቸኛ አምራች እና አቅራቢነት /ሞኖፓል/ ባህሪ መፈጠር እንዲሁም ወደ ኢኮኖሚው ሥርዓት መግባትን ከባድ የማድረግ ልምምድ ስለሚፈጠር ነው ሲሉ ያብራራሉ አቶ ዋሲሁን ።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)

አዲስ ዘመን መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You