የድጋፍ ሰልፎቹ ለለውጥ ኃይሉ ተጨማሪ የዓላማ ጽናትን የሚያላብሱ ናቸው

ካለንበት ድህነትና ኋላቀርነት መውጣትን ታሳቢ ያደረጉ፤ በብዙ ተስፋዎች ትውልዶችን ያነሳሱ የለውጥ ንቅናቄዎች በተለያዩ ወቅቶች ተካሄደዋል። እነዚህ ለውጦች ደግሞ ተስፋ የተደረገላቸውን ያህል ባይሆንም፣ እያንዳንዳቸው በደግም ይሁን በክፉ፤ በልማትም ይሁን በጥፋት የሚታሰቡ ብሔራዊ ትርክቶችን ፈጥረው አልፈዋል።

በተለይም ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት የነበሩ ትውልዶች፤ ለዘመናዊ ትምህርትና ከዚህ ጋር ተያይዞ ለውጭው ዓለም ከነበራቸው ቅርበት የተነሳ፤ ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው የተሻሉ ነገዎችን ለመፍጠር ባላቸው አቅም ሁሉ ተንቀሳቅሰዋል። ብዙ መስዋዕትነት በመክፈልም ለዓላማቸው የነበራቸውን ጽናት አሳይተዋል።

ይህ በትውልዶች ቅብብሎሽ ውስጥ ጎልቶ የሚታየው ለሀገርና ለሕዝብ ነገዎች ተስፋ የሰነቀ የለውጥ ንቅናቄ፤ የትናንት ስህተቶችን በማረም ሀገራዊ ተስፋዎችን ተጨባጭ ማድረግ በሚያስችል አዲስ የፖለቲካ አሳቤና መነቃቃት ከተጀመረ እነሆ ስድስት ዓመታትን አስቆጠረ።

በሕዝባችን የመልማት እና እንደ ሀገር በጸና የአንድነት መሠረት ላይ የመቀጠል ፍላጎት ላይ የተመሠረተው ይህ አዲስ የለውጥ የታሪክ ምዕራፍ ፤ እንደ ቀደሙት የለውጥ ታሪኮቻችን በአስቸጋሪ ፈተናዎች ውስጥ ለማለፍ የተገደደበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ሀገርና ሕዝብም ብዙ ዋጋ እንዲከፍሉ ያስገደዱ ክስተቶችንም አስተናግዷል።

የለውጡ ሕዝባዊነትም ሆነ ርዕይ ገና ከጅምሩ ስጋት የፈጠረባቸው የውስጥና የውጭ ኃይሎች፤ የሕዝባችንን የቆየ አብሮ የመኖር ባህል፤ በአንድነት ተቻችሎ በፍቅር የመኖር እሴት በማደብዘዝ ፤ ከዛም ባለፈ የሀገርን ህልውና ጭምር አደጋ ውስጥ በከተተ መንገድ በተቀናጀ እና በተናበበ መልኩ ተንቀሳቅሰዋል።

በዚህም ለውጡን የሚገዳደሩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና እና ፖለቲካዊ ስብራቶች ተፈጥረዋል። ከሁሉም በላይ በለውጥ ሰሞን ግርግር የተፈጠሩ የሴራ አካሄዶች ባልተለመደ መልኩ ሀገራዊ ፈተና ሆነው አልፈዋል። ጠባሳቸውም ተስፋ ባደረግናቸው ነገዎቻችን ላይ ጥቁር ጥላ አጥለዋል።

“ግርግር ለሌባ ይመቻል” እንደሚባለው፣ በለውጡ ማግስት የተፈጠሩ የውስጥ ችግሮቻችንን እንደ መልካም አጋጣሚ የተመለከቱ ታሪካዊ ጠላቶቻችንና መለወጣችንን እንደ ስጋት የሚመለከቱ ኃይሎች ዓለም አቀፍ መድረኮችን ሳይቀር ፤ ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም ሀገሪቱን ከጀመረችው የለውጥ ጉዞ ለማሰናከል ረጅም ርቀት ተጉዘዋል።

የነዚህ ኃይሎች የሴራ ጉዞ ሀገር እንደ ሀገር አበቃላት ወደሚል የሟርት ትርክት ወስዶን የነበር ሲሆን፤ ይህንን የጥፋት ትርክት የመቀልበሱ ትግል መራራ ከመሆን በዘለለ፤ የብዙ ሀገር ወዳድ ዜጎቻችንን ውድ ሕይወት፤ የቀደመውን ዘመን ስለ ሀገር የመሞት ብሔራዊ ክብርን የጠየቀ ነበር።

በዚህም /በብዙ መስዋዕትነት የሀገርን ህልውና እና የሕዝባችንን የመበተን ስጋት መቀልበስ ተችሏል። በዚህ ሂደት ውስጥ የለውጥ ኃይሉ ችግሮችን በጽናት ተቋቁሞ፤ ለውጡን በከፍተኛ ቁርጠኝነት በመምራት፤ ሀገርን እንደሀገር መታደግ በመቻሉ ከፍ ያለ እውቅና ሊቸረው የሚገባ ነው።

እንደሚታወቀው፤ የአመራሩ ቁርጠኝነት እስከ ጦር ሜዳ የዘለቀው፤ የመጨረሻዋን ደቂቃ በተስፋ መጠበቅን፤ ዓለም አቀፍ ሴራዎችን በአግባቡ ተርድቶ ለዚህ የሚሆን ብርታት ፣ የመንፈስ ጽናት እና የመስዋዕትነት ዝግጁነትን የጠየቀ ነበር ።

በተለይም ሀገር በአስቻጋሪ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ወቅት፤ በኢኮኖሚው ዘርፍ ሀገር እንደ ሀገር የምትቆምበትን ስትራቴጂ በመንደፍ እና በጠንካራ ዲስፕሊን በመተግበር በዓለም ደረጃ እውቅና ያተረፈ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቡ የችግሮች መደራራብ ዜጎችን የከፋ ዋጋ እንዳያስከፍል አስችሏል።

ከለውጡ ማግስት ጀምሮም በሀገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ሃሳብ ለመፍጠር/ችግሮችን በውይይትና በድርድር የመፍታት የፖለቲካ ባሕል ለመፍጠር የሄደበት ረጅም መንገድ የተጠበቀውን ያህል ውጤት ባያስገኝም አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ በመፍጠር ሂደት ውስጥ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ነው።

ይሄን እውነት በመገንዘብም፣ አሁን ላይ የሚደረጉ የዜጎች የድጋፍ ሰልፎችም ለዚህ ተግባር ተገቢውን እውቅና ከመስጠት ባለፈ፤ የለውጥ ኃይሉ እንደ ሀገር የተፈጠሩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስብራቶችን ማከም የሚያስችል ቁርጠኝነት እንዲፈጥር ተጨማሪ አቅም እና የዓላማ ጽናት የሚፈጥሩለት ናቸው።

አዲስ ዘመን  መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You