ለችግር የተጋለጡ ሕጻናትን ለመደገፍና ለመንከባከብ የሚያስችል ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል

አዲስ አበባ፡- ሕጻናት በተሟላ መንገድ እንዲያድጉና ለችግር ተጋልጠው ሲገኙም ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማድረግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የሕጻናት መብት ስርጸትና ስዕብና ቀረጻ ዴስክ ኃላፊ አቶ በለጠ ዳኘ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ ሕጻናት በተሟላ መንገድ እንዲያድጉና ለችግር ተጋልጠው ሲገኙም ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማድረግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው።

የሕጻናትን ደኅንነት ለማስጠበቅ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፤ መብታቸውን ከማስጠበቅ አንጻርና ለችግር ተጋልጠው ሲገኙም ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማድረግ የተዘጋጁ የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ፣ መልሶ ማቀላቀል፣ የአደራ ቤተሰብና ሌሎችም ፕሮግራሞች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

“ሕጻናት የተለያየ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት አላቸው፤ ጥቃት ሲደርስባቸውም የሚያገግሙበት ማዕከል ያስፈልጋቸዋል” የሚሉት ዴስክ ኃላፊው፤ ለዚህም እራሱን የቻለ ሥርዓት ተዘርግቶ በክልሎች ደረጃም ተግባራዊ እንዲደረግ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የሕጻናት ፓርላማ ከቀበሌ አንስቶ እስከ ሀገር አቀፍ ደረጃ በማቋቋም የሕጻናት ተሳትፎ እንዲያድግ የማድረጉ ሥራ ትኩረት እንደተሰጠው በመጥቀስ፤ ጥቃት ሲደርስባቸውም እንደ ሕግ፣ ጤና፣ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። ከፍርድ ቤት ጋር በተያያዘ ለሕጻናት ተስማሚ የሆኑ ችሎቶችን የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሕጻናትን ከመደገፍ አንጻር በተከናወኑ በርካታ ተግባራትና በተገኙ የግንዛቤ መሻሻሎች የሕጻናት ተሳትፎ የጎለበተበት ሂደት መኖሩንም ገልፀዋል። የውጭ ሀገር ጉዲፈቻን በማስቀረት በሀገር ውስጥ የመተካትና ከሕጻናት ስብዕና ቀረጻ ጋር በተያያዘ የሕጻናት የቀን ማቆያዎች መስፋፋት የተገኙ እምርታዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ለሕጻናት ማሳደጊያ ተቋማት ከሚያደርገው የቁሳቁስ ድጋፎች በተጨማሪ ከሌሎች አካላትም ድጋፎችን እንዲያገኙ የማስተሳሰር ሥራ እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ነገር ግን የሚፈለገው ሕጻናት በወላጆቻቸው እቅፍ ውስጥ እንዲያድጉ ሲሆን የሕጻናት ማሳደጊያ የመጨረሻው አማራጭ መሆኑን አቶ በለጠ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሕጻናትን ቁጥር በእውን ማወቅ ባይቻልም በርካታ ሕጻናት በችግር ውስጥ እንደሚኖሩ አንስተው፤ ከዚህ ቀደም በተሠራ ጥናት ለችግር የተጋለጡ ሕፃናት ቁጥር ከአምስት ሚሊዮን በላይ እንደሆነ አስታውቀዋል።

አክለውም መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተለያዩ ጥናቶች ቢከናወኑም ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ጥናቶቹ ተቀባይነት አይኖራቸውም፤ የሕፃናቶቹን ቁጥር በእውን በማወቅ ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ እንደሀገር ብሔራዊ ጥናት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የሕጻናት ጉዳይ የሁሉም ነው፤ ከቤተሰብ ጀምሮ ማኅበረሰቦች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የሃይማኖት ተቋማትና ሌሎችም ኃላፊነት እንዳለባቸው የገለጹት አቶ በለጠ፤ ሕጻናት ለጉዳት እንዳይጋለጡና መብታቸው እንዲከበር የመጠበቅና የመከላከል ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You