
ቢሾፍቱ:- የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት ለሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት መንግሥት አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አስታወቁ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ኢንዱስትሪንና የታንክና ብረት ለበስ ተሽከርካሪ ማምረቻ ወርክሾፕን ትናንት ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንደገለጹት፣ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል ምቹ መሠረተ ልማት አለው። ነገር ግን የሀገር ውስጥ ባለሀብቱና የመንግሥት ተቋማት ያለውን መሠረተ ልማት እየተጠቀሙ አለመሆኑን ገልጸዋል።
መንግሥት የሀገር ውስጥ ምርትን በስፋት ማምረትና መጠቀም አለብን የሚል እቅድ ይዞ እየሠራ ነው ያሉት አቶ ተመስገን፣ ለዘርፉ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል። በኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ያሉ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ በስፋት ለመተካት በውስጥ አቅም እያመረተ መሆኑ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ የነዳጅ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትን ለማቆም መንግሥት እየሠራ ነው። ድርጅቱ ከወቅቱ ጋር ለመሄድ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችንና ማሽኖችን መሥራት ይኖርበታል ብለዋል።
ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት ለሚያደርገው ተግባር አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ አቶ ተመስገን ገልጸዋል።
በድርጅቱ ብዙ የፈጠራ ሥራዎችን አይተናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ ማሽኖችን ወደ ምርት ለመቀየር የሚሠሩ ሥራዎችን አድንቀዋል። በማምረቻ ፋብሪካው ውስጥ የግብርና ምርቶችን ማቀነባበሪያ ማሽኖችን እየተሠሩ ነው። ይህም አርሶ አደሮች ያሉባቸውን ችግሮች የሚቀርፍ ነው፣ እንደ ሀገር ትልቅ ተስፋ መኖሩን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ተቋሙ ከነበረበት ችግርና እዳ እንዲወጣ ብዙ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸው፤ በቀጣይ ተቋሙ የሚያመርታቸውን ምርቶች በስፋት መጠቀም የመንግሥትና የግል ድርጅቶች ድርሻ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ትልቅ የሀገር ሀብት ነው ያሉት አቶ ተመስገን፣ መሥራት የሚችል አቅም፣ እውቀትና ማሽን እንዳለው በመግለጽ፤ አቅሙን ይበልጥ ለማሳደግ ተገቢው ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም
ሞገስ ጸጋዬ