ግብፅ ሰው ሠራሽ ወንዝ ለመሥራት የደረሰችበት ውሳኔ የቀደመ ጩኸቷን ትርጉም አልባነት ያረጋገጠ ነው

በዓባይ ወንዝ የውሀ አጠቃቀም ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎች/ውዝግቦች ዘመናት ያስቆጠሩ፤ ድንገትም ተገቢውን ምላሽ ካላገኙ ተጨማሪ ዘመናትን ሊቀጥሉ የሚችሉ እንደሚሆን ይታመናል። በተለይም ጥያቄዎቹ የደረሱበትን ዘመን የሚመጥን ምላሽ የማግኘት ዕድል ካላገኙ፤ የፖለቲካ አጀንዳ እየሆኑ በተፋሰሱ ሀገራት እና በሕዝቦቻቸው መካከል ያለመተማመን ምንጭ የመሆናቸው ጉዳይ አይቀሬ ነው።

በተለይም የዓባይ ወንዝ ብዙ ሀገራትን አቋርጦ እንደሚሄዱ፤ በወንዙ የውሀ አጠቃቀም ዙሪያ የተለያዩ ፍላጎቶች መኖራቸው አይቀርም። የተፋፈሱ ሀገራት ሕዝቦች ካሉበት የከፋ ኋላቀርነትና ድህነት አኳያ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በውሃው ላይ ያላቸው ፍላጎት ቀስ በቀስ ወደ አደባባይ መውጣቱ የማይቀር ነው ።

ከመልማት፣ ድህነት እና ኋላቀርነትን አሸንፎ ከመውጣት የሚመነጨው የሀገራቱ በወንዙ ውሃ የመጠቀም ፍላጎት፣ የወንዙን ጠብታ ውሃ ትነካና በሚል ፉከራና ማስፈራሪያ መፍትሔ የሚያገኝ አይሆንም። በተለመደው ድንበር ተሻጋሪ የፖለቲካ ሴራም ጥያቄዎችን ማስቆም አይቻልም። ዘመን የረሳቸውን የቅኝ ግዛት ውሎችን በማገላበጥም የሚሆን ነገር አይኖርም።

የወንዙ ተፋሰስ ሀገራት ሕዝቦች በመጪዎቹ ወቅቶች ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም መልማት የሚያስችላቸውን ዕድል መፍጠር ካልቻሉ፣ እንደ ሀገር ጸንተው ለመቀጠል የሚያስችላቸውን አቅም አጥተው ሕልውናቸው ስጋት ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ መፈጠሩ የማይቀር ነው። ሀገራቱ ከዚህ በላይ ድህነትን እና ኋላቀርነትን የሚያስተናግድ ትከሻ አይኖራቸውም ።

ከዓለም አቀፍ መርሕ ጋር በተያያዘ የመልማት ጥያቄ የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ነው፤ በተለይ በከፋ ድህነት ውስጥ ላሉ የተፋሰሱ ሀገራት ሕዝቦች ጥያቄው እንደሀገር የሕልውና ጉዳይ ነው። ይህንን የሕልውና ጥያቄ ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለማስተናገድ የሚደረግ የትኛውም አይነት ጥረት ትርጉም ያለው ውጤት ያመጣል ብሎ ማሰብ፤ ከዘመኑ ጋር ያለመራመድ፤ ዘመኑን በአግባቡ ያለመዋጀት ችግር ነው ።

ለወንዙ ከ90 ከመቶ የሚሆነውን ውሃ የምታበረክተው ሀገራችን ኢትዮጵያ ሆነች ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት የወንዙን ውሃ በፍትሐዊነት፤ ዓለም አቀፍ ሕጎችን መሠረት ባደረገ መንገድ የመጠቀም የሕግም፤ የሞራልም መብት አላቸው። ይህንን መብታቸውን ተጠቅመው የመልማት መሻታቸውን እውን ለማድረግ የማንንም ይሁንታ መጠበቅ አይኖርባቸውም።

ይህንን ዓለም አቀፋዊ እውነታ ግምት ውስጥ ባላስገባ መንገድ፤ የተፋሰሱን ሀገራት በውሃው የመጠቀም መብት፤ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለመሸራረፍ በግብፅ በኩል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ተጠያቂነት የሌላቸው ከዘመኑ እሳቤ ጋር የተራራቁ ናቸው፤ በተፋሰሱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል ያለውን የወንድማማችነት መንፈስ በማደብዘዝ፤ አለመተማመንን ከመፍጠር ያለፈም ትርጉም የለውም።

የግብፅ መንግሥት “ዓባይ የግብፅ ሕይወት” ነው በሚል የተፋሰሱ ሀገራት በወንዙ የጠብታ ውሃ እንዳይጠቀሙ በየዘመኑ የክልከላ አዋጅ እያወጀ፤ እራሱ የወንዙን ውሃ ባልተገባ መንገድ ኃላፊነት በማይሰማው ሁኔታ ለብክነት በሚዳርጉ የእርሻ ሥራዎች ከማዋል ጀምሮ፤ አሁን ላይ በወንዙ ውሃ ሰው ሠራሽ ወንዝ ወደ መፍጠር እየተጓዘ ነው።

ይህም ኃላፊነት የጎደለው ጉዞ ቀደም ሲል የግብፅ መንግሥት በወንዙ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ከኢትዮጵያም ሆነ ከሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ጋር የነበረው እሰጣ ገባ ትርጉም አልባ እንደነበር፤ ከዚህ ይልቅ ዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ በጉዳዩ ዙሪያ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ የተደረገ ጥረት ስለመሆኑ በተጨባጭ ያመላከተ ነው።

ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው የዓባይ ግድብ ወደ ግብፅ የሚፈሰውን የውሃ መጠን ይቀንሰዋል፤ በዚህም የሕዝቦችን ሕይወት አደጋ ውስጥ ይጨምረዋል በሚል ከግንባታው መጀመር ማግስት አንስቶ ሲያሰማ የነበረው የተጋነነ ጩኸት ምን ያህል ከአሉባልታ ያላለፈ ተጨባጭነት የሌለው እንደሆነ በአደባባይ ያረጋገጠ ነው ።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You