የጥራት መሠረተ ልማት ስኬቶች

ኢትዮጵያ ከምርትና አገልግሎት ጥራት ጋር ተያይዞ ውጤታማ ተግባሮችን ለማከናወንና የሚገጥሟትን ችግሮችም ለመፍታት በዘርፉ መሠረተ ልማት አገልግሎቶቿ ተወዳዳሪ መሆን ይጠበቅባታል። ምርቶቿን በዓለም አቀፍ፣ አሕጉራዊና ክፍለ አሕጉራዊ ደረጃ ለገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ግኝቷን ለማሳደግ የምትሠራ እንደመሆኗ በዚህ የተወዳዳሪነት ጥራት ላይ አበክሮ መሥራት ወሳኝ ነው።

ተወዳዳሪነትን ማረጋገጥ የሚቻለው ደግሞ በዓለም እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቀመጡ መስፈርቶች መሠረት ተመዝኖ የሚጠበቀውን ደረጃ ማግኘት ሲቻል ነው። ሀገሪቱም ይህን ምዘና ለማለፍ በጥራት አገልግሎት ላይ የምታከናወነውን ሥራዋን ማጠናከር ላይ በስፋት ልትሠራ ይገባታል።

ለዚህ ደግሞ አንዱ መሠረት ጣይ ተግባር የብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማትን በአደረጃጀት፣ በአሠራርና በተሻለ የጥራት መሠረተ ልማት መገንባት ነው። ይህም የሀገር ውስጥ አምራቾችና ላኪዎችን በዓለም አቀፍ፣ አሕጉራዊና ክፍለ አሕጉራዊ የገበያ መዳረሻዎች ላይ እንዲሳተፉ ሰፊ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፤ ከጥራት ጋር ተያይዞ እየገጠማቸው ያለውን ፈተና በቀላሉ እንዲያልፉም እድል ይሰጣቸዋል።

በኢትዮጵያ የብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት የሚባሉት ደረጃዎችን የሚያወጣና ያወጣቸውን ደረጃዎች እንዲተገብሩ የቴክኒክ ድጋፍና ሥልጠና የሚሰጠው የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲቲዩት፣ ምርቶች የተቀመጠላቸውን መስፈርት ማሟላት አለሟሟላታቸውን የሚያረጋግጠው የኢትዮጵያ የተስማሚነትና ምዘና ድርጅት፤ መሣሪያዎች በትክክል ስለመሥራታቸው በካሊብሬሽን የሚያረጋግጠው የኢትዮጵያ የሥነ-ልክ ኢንስቲትዩትና ምስክርነት የሚሰጠው የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ናቸው።

በእነዚህ ተቋማት አሁን ባለንበት ሁኔታ የተሻሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በቅርቡ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። በሚኒስቴሩ የብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ማረጋገጫ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በጣም የለማና በእጅጉ ያደገ አቅም ያለው ብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋም ከገነቡ ስድስት የአፍሪካ ሀገራት አንዷ መሆን ችላለች፡፡ ለዚህ ስኬቷ ደግሞ መሠረት የጣሉት የብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማቷ በሚገባ በተደራጀ መልኩ መሥራት በመቻላቸው ነው።

ይህንን ደረጃ ያወጣላቸው ደግሞ “ፓን አፍሪካን ኳሊቲ ኢንፍራስትራክቸር” የተሰኘ ተቋም ሲሆን፤ ድርጅቱ በየዓመቱ የአፍሪካን የጥራት መሠረተ ልማት ደረጃ በአራት ነጥብ ከፋፍሎ ይመዝናል። የውድድሩ ተሳታፊዎች 55ቱም የአፍሪካ ሀገራት ሲሆኑ፤ 10 የሚደርሱ ሀገራትን የጥራት መሠረተ ልማት ተቋም ደረጃ የላቸውም አለያም በጣም ጥቂት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ናቸው ሲል ፈርጇቸዋል። 13ቱን ደግሞ በጣም ውስንነት ያለበት አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው ሲል ያስቀምጣቸዋል።

በከፊል የለሙና ያላቸው ደግሞ 13ቱን ነው። ተቀባይነት ያለው አገልግሎት የሚሰጡና የጥራት መሠረተ ልማታቸው ጥሩ የሆኑ በሚል ያስቀመጣቸው 13 ናቸው። በደንብ የለማ ብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋም በመገንባት የተሟላ አገልግሎት መስጠት የቻሉት ያላቸው ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ ቀሪዎቹ ስድስት የአፍሪካ ሀገራትን ነው።

ኢትዮጵያ፤ ይህንን ደረጃ ያገኘችው በሀገር ውስጥ ባለው እንቅስቃሴዋ ብቻ ተመዝና ሳይሆን በአሕጉራዊና በዓለማቀፋዊ ዕይታ ጭምር ተመዝና ነው፤ የተመዘገበው ውጤት በዘፈቀደ የተገኘ ውጤት አይደለም፤ መንግሥት ላለፉት አራትና አምስት ተከታታይ ዓመታት ባደረገው መጠነ ሰፊ የተቋማት ሪፎርም ሥራ መሆኑም በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።

ሀገሪቱ በዚህ ደረጃ ላይ መቀመጧ እንደ ሀገር ምን ታገኛለች? የሚልና መሰል ጥያቄዎች መነሳታቸው የተጀመረውን የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናዊ ትስስር የበለጠ አጠናክራ እንድትሠራበት ያስችላታል። ሀገሪቱ የግብርና ምርቶቿን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ትታወቃለች። እነዚህን ምርቶች ደግሞ የምታቀርበው በአብዛኛው ለአውሮፓ፣ ለእስያና አሜሪካ ገበያዎች እንደሆነ ይታወቃል።

ወደ ሶማሊያ፣ ጅቡቲና የመሳሰሉት የአፍሪካ ሀገሮችም ምርቶቿን ብትልክም፣ ከአጠቃላይ የአፍሪካ ገበያ ብዙ ተጠቃሚ አይደለችም። እንደ አፍሪካ እንደ ምሥራቅ አፍሪካ የግብርና ምርቶቿን ወደ እነዚህ የአሕጉሪቱ ክፍሎች ሀገሮች በመላክ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን የጥራት መሠረተ ልማቶቿ ተጠናክሮ መውጣት ፋይዳ ከፍተኛ ነው።

ሀገሪቱ ምርቶቿን ለአውሮፓ፣ እስያና አሜሪካ የምታቀርብ በትሆንም፣ ምርቶቹን በስፋትና በጥራት በማቅረብ በኩል አሁንም ጠንክራ መሥራት እንደሚኖርባት ይታመናል፤ የምርት መላኪያ መዳረሻ ሀገሮችን ማስፋት፣ ለእነዚህ የዓለም ክፍሎች የሚላኩ ምርቶችን አይነትም መጨመር በትኩረት መሥራት የበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋል። ምርቶችን ወደ እነዚህ ሀገሮች ለመላክ ደግሞ የምርት ጥራት ጉዳይ ወሳኝ ነው፤ ለእዚህ ደግሞ አሁን በአፍሪካዊው ተቋም መመዘኛ መሠረት የሀገሪቱ የጥራት መሠረተ ልማቶች ያገኙት ደረጃ ጠቀሜታ ከፍተኛ ይሆናል።

የተቋማቱ በዚህ ቁመና ላይ የመገኘት ፋይዳ ከዚህ ሁሉም ሊያልፍ ይችላል። የጥራትን ጉዳይ በአሕጉራዊና ክፍለ አህጉራዊ ደረጃ ለማረጋገጥ ብቁ ሆኖ መገኘት በተለያዩ ክፍለ ዓለሞች/ አውሮፓ፣ እስያ፣ ወዘተ/ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከምርት እና አገልግሎት ጥራት ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ጉዳዮች ትልቅ አቅም ሆኖ ያገልግላል።

እንደሚታወቀው ሀገሪቱ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን መንቀሳቀስ ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። አሁን በአፍሪካዊው ተቋም ተመዝና ከአገልግሎት ጥራት ጋር ተያይዞ ያገኘው ደረጃ የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል የጀመረችውን ጉዞዋን እንደሚያፋጥነው በዘርፉ ተዋንያንም ታምኖበታል።

ከጥራት መሠረተ ልማት አኳያ ሀገሪቱ ዘመኑን የዋጀ አሠራር እንድትከተል ዕድል የሚሰጣትም ይሆናል። የዜጎችን ጤንነት እና የአካባቢን ደህንነት ለመጠበቅም ምቹ ሁኔታን ይፈጥርላታል። በተመሳሳይ እንደ ሀገር ተወዳዳሪ ሆና ተቋማትንም ተወዳዳሪ እንድታደርግ ያግዛታል።

አብዛኞቹ የፍተሻ አገልግሎቶች ወደ ውጭ በመላክ ሲረጋገጡ ቆይተዋል፤ አሁን የተገኘው ውጤት አገልግሎቶቹ በሀገር ውስጥ እንዲካሄዱ መደላደሎችን የሚፈጥር ነው። በራስ አቅም የመሥራት ዕድልንም እንድታገኝ ያደርጋታል፤ የውጪ ምንዛሪን ከማስቀረት አኳያ የማይተካ ሚና ይኖረዋል። በተመሳሳይ ለሀገሪቱ አምራቾች፣ ላኪና አስመጪዎችም ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።

በአጠቃላይ በእዚህ ደረጃ መገኘት ተቋማትንና ሀገርን ተወዳዳሪ በማድረግ ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባት ይረዳል። ከደረጃ በታች የሆኑ ሀገራትን የምርትና አገልግሎት ጥራት የማረጋገጥ ሥራን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብም ይጠቅማል፤ የጥራት አገልግሎት ሰጪ ሀገር እንደሚያደርጋትም ተጠቁሟል፤ በዚህም የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ይቻላል።

በአሕጉራዊው ተቋም በኩል የጥራት መሠረተ ልማቶቻችን ያስመዘገቡት ደረጃ ሀገሪቱን በጥራት መሠረተ ልማት በኩል የለማች ሀገር አሰኝቷታል፤ በዚህ ደረጃ መቀመጥ ጥሩ ነው፤ ኢትዮጵያ የጥራት መሠረተ ልማት ደረጃን ከሚያሟሉና በጣም የለማና በእጅጉ ያደገ አቅም ካላቸውና የብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋም ከገነቡ ስድስት የአፍሪካ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ መሆን መቻሏ አንድ ስኬት ነው።

ከጥራት ተቋማት ስኬት ጋር በተያያዘ የለማ መባል ብቻውን ውጤቱን ይዞ ለመቆየት አያስችልም፤ ሀገሪቱ በወጪ ንግድ ውጤታማ ለመሆን፣ በገቢ ንግድም የጥራት ቁጥጥርን አጠናክሮ ለማካሄድ እንዲቻል የጥራት ተቋማቱ ተጠናክሮ መውጣት ወሳኝ ነው።

ተቋማቱ አሁንም ከዚህም በላይ የላቀ ደረጃ ለመድረስ መሥራት ይጠበቅበታል። ሀገሪቱ በዘርፉ እያካሄደች ያለችው የማስፋፊያ ግንባታም ይህን እውን እንድታደርግ የበኩሉን ሚና የሚጫወት እንደመሆኑ ለግንባታው መጠናቀቅና ወደ ሥራ መግባት ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል። የጥራት ጉዳይ የሁሉም ማኅበረሰብ ጉዳይ ነውና ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል። ሠላም!!

ክብረ መንግሥት

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You