የዘገየም፤ በነፍስ የደረሰም አዋጅ

በሀገሪቱ በተለያዩ መስኮች በተካሄዱ ልማታዊ ተግባሮች የሚታዩ፣ ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ ተችሏል። በግብርናው፣ በኤሌክትሪክ ኃይልና በቱሪዝም መሠረተ ልማትና በመሳሰሉት እየታየ ያለውና ከሀገርም አልፎ ለውጭም እየተረፈ ያለው ስኬት ለእዚህ ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል።

በመኸርና በበልግ የሚለማው ስንዴ እንዳለ ሆኖ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ ከፍተኛ ምርት ማግኘት እየተቻለ ነው። ይህም ሀገራዊ የስንዴ ፍላጎትን ከማሟላት በዘለለ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ በማውጣት ከውጭ የሚመጣውን ስንዴ በሀገር የስንዴ ምርት ማስቀረት ተችሏል፤ ልማቱ በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር አድናቆትን ያተረፈም ሆኗል።

የዓባይ ግድብ ግንባታ ወደ መጠናቀቅ መቃረብ ትልቅ ስኬት ነው፤ ግድቡ ከሀገሪቱ አልፎ አህጉሪቱን በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ሊያግዝ የሚችል በአሕጉር ደረጃ አንደኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ከተጠቃሾቹ መካከል ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።

ለቱሪዝም ዘርፉ ተጨማሪ መስሕብ እንዲሁም ለቱሪስቶች ቆይታ ማራዘሚያ በመሆን ሊያገለግሉ የሚችሉ የቱሪስት መሠረተ ልማቶች ተገንብተዋል፤ እነዚህና የመሳሰሉት በተለያዩ መስኮች እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች የልማቱ ማሳያ ተደርገው ሊቀርቡ ይቻላሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው በነበሩ ግጭቶች፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትና ይህን ተከተሎ በሀገሪቱ ላይ በተጣሉ ጫናዎች፣ ወዘተ ሳቢያ በምጣኔ ሀብቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖዎች አርፈዋል። ተፅዕኖዎቹ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት እንዲያጡ፣ የግብርናው ዘርፍ እንደ ማዳበሪያ ያሉ ግብዓቶችን በወቅቱ እንዳያገኝ፣ ለሀገሪቱ ምርቶች በቂ የውጭ ገበያ እንዳይገኝ፣ ወዘተ አርገዋል። ችግሮቹ ተደማምረው ተደማምረው በሀገሪቱ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ተጠቃሾቹ ሆነዋል።

ይህ የኑሮ ውድነቱ በምግብ እህሎችና ሸቀጣሸቀጦች፣ ምግቦች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ አየጨመረ መምጣት ሳቢያም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ በሀገሪቱ በየጊዜው ዋጋው የማይጨምር የምርትና ሸቀጥ ዓይነት የለም። መንግሥት ባደረገው ድጋፍና ክትትል የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ቢቻልም፣ በአንዳንድ ምርቶች ላይ ዋጋውን ለማረጋጋት ቢሞከርም፣ ችግሩን በሚፈለገው ልክ ማርገብ ግን አልተቻለም። ይህን ችግር ለመፍታት አንዳንድ የፍጆታ ምርቶችን በድጎማ ጭምር በማቅረብ ለማረጋጋት ቢሞከርም የኑሮ ውድነቱን በሚፈለገው ልክ ማረጋጋት አልተቻለም።

ሸማቹ በዚህ ሁሉ መፈተኑ እንዳለ ሆኖ የቤት ኪራይ ዋጋ በየጊዜው እየጨመረ መምጣትም ሌላው የሀገሪቱ ፈተና ሆኗል። ሠርቶ፣ ደክሞ ገቢው ሁሉ ማለት በሚያስደፍር መልኩ ለቤት ኪራይ የሚሆነው በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደር ማኅበረሰብ እጅግ በርካታ ሆኗል። ችግሩ ዝቅተኛ ገቢ ባለው የኅብረተሰብ ክፍል ላይ የበለጠ የከፋ ቢሆንም፣ መካከለኛ ገቢ ያለውም ጭምር በዚህ ችግር በእጅጉ እየተፈተነ ነው።

አንዳንድ ቤተሰብ ውስጥ የባል ወይም የሚስት ደመወዝ ለቤት ኪራይ እንዲውል እየተፈረደበት መሆኑ ይገለጻል። አንዳንዶች ደግሞ ደሞዛቸውን ለቤት ኪራይ በማዋል ወይም ተጨማሪ ሥራዎችን በመሥራት የሚያገኙትን ገቢ ለቤት ኪራይ በማዋል ችግሩን ለመፍታት እየታገሉ ናቸው።

የቤት ኪራይ ዋጋ ከሠራተኞች ደሞዝ አብዛኛውን እጅ እየወሰደ ስለመሆኑ ሠራተኞቹ በምሬት ሲናገሩ የሚሰማ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ። በሀገሪቱ ማኅበራዊ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች በተፈጠሩ ቁጥር የቤት ኪራይ ዋጋም በዚያው ልክ ሲጨምር ቆይቷል። ተከራዮች በሀገሪቱ የሆነ ችግር ሲፈጠር የቤት ኪራይ ደግሞ እንዴት ሊያደርገን ብለው እንዲያስቡ፣ እንዲሳቀቁ እያደረጋቸው ነው።

በተለይ በአዲስ አበባ ተከራዮች በመሐል ከተማዋና ቅርብ ርቀት ላይ የቤት ኪራይ በእጅጉ እየተወደደባቸው መምጣቱ፣ ቀለል ያለ ኪራይ የሚጠይቅባቸውን ቤቶች ፍለጋ ወደ ከተማዋ ዳርቻ አካባቢ እንዲወጡ እያደረጋቸው ነው። ይሁንና እዚህም ቢሆን ችግሩ እየዳኸ ደርሶ አሳሳቢ መሆኑ አልቀረም። አካባቢው እየተነቃቃ ሲሄድ የኪራይ ዋጋም እየጨመረ መሄዱ ስለማይቀር ከቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪው ብዙም መራቅ ሳይቻል ቆይቷል። በዚህ ላይ የትራንስፖርት ተጨማሪ ወጪ፣ የጉዞው ርዝማኔና እንግልት ሌሎች ፈተናዎች ናቸው።

እየናረ የመጣውን የቤት ኪራይ ዋጋ ሊያቀል ይችላል የተባለ ማናቸውም መንግሥታዊ እርምጃ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ሀገራዊ ምክንያቶችን በመጥቀስ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ ሲጨምሩ የነበሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በቤት ኪራይ ዋጋ ላይ ማድረግን የሚከልከል መመሪያ እያወጣ በመተግበሩ ችግሩን ለመፍታት ምን ያህል እንዳስቻለ ተከራዮች መስክረዋል። እርምጃው በርካቶችን ከአከራዮችና ደላሎች ዝርፊያ አስጥሏል። ከተማ አስተዳደሩ የወጣውን መመሪያ በሚገባ የተጠቀሙ ተከራዮች እፎይታ አግኝተዋል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ በቅርቡ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ጠቅሰው እንዳስታወቁት፤ አንድ ሰው ከአጠቃላይ ገቢው ከ15 እስከ 30 በመቶ የበለጠ ለቤት ኪራይ መክፈል የለበትም፤ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግን በትንሹ ከሰባ በመቶ በላይ ለመኖሪያ ቤት ኪራይ እየተከፈለ ነው። ይህም ጤናን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶች በማዛባት ዜጎችን የተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች እየዳረጉ ይገኛሉ።

በቤት ኪራይ ላይ የሚታየውን መሠረታዊ ችግር ለመፍታት እንደሚሠራ ሲገልጽ የቆየው መንግሥትም ችግሩን ያቀላል ያለውን እርምጃ ወደ መውሰድ ተሸጋግሯል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ካፀደቀው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው።

አዋጁን አስመልክቶ በተሰጠው ማብራሪያ ላይ እንደተመለከተው፤ አዋጁ በሁሉም መኖሪያ ቤቶች ኪራይ ላይ ይተገበራል፤ የቤቶች ዋጋ ተመኑም በመንግሥት የሚወሰን ይሆናል። አዋጁ በመኖሪያ ቤት ኪራይ ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ አለመረጋጋት በመቆጣጠር በቤት አቅርቦት ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት የበኩሉን ሚና ይወጣል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ ከክልሎች ጋር ውይይት እንደተደረገበትም ተመልክቷል። አዋጁ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደሮች፣ በክልል ከተሞችና ክልሎች በሚያስተዳድሯቸው ከተሞች ይተገበራል። መሠረታዊ የቤት አቅርቦት ችግርን ባይፈታም፣ አንድ ሰው ቢያንስ ለሁለት ዓመታት ተገቢውን ኪራይ እየከፈለ ተረጋግቶ መኖር እንዲችል አስተዋፅዖ ያበረክታል።

ይህ አዋጅ በእጅጉ የዘገየ ነው። ዜጎች በኪራይ ቤት ዋጋ ውድነት መኖራቸውን እስኪጠሉ አድርሷቸው ቆይቷል። የችግሩ አሳሳቢነት በየጊዜው ለመንግሥት ሲቀርብም ቆይቷል። የጥያቄውን አሳሳቢነት ያህል ወቅቱን ጠብቆ የመጣ ሊባል የሚችል አይደለም። እንዲያም ሆኖ ግን ኅብረተሰቡን በእጅጉ ይታደጋልና ቢዘገይም በነፍስ የደረሰ እርምጃ ነው።

ችግሩ በእጅጉ ከፍቶ የሚታየው በተከራይ ላይ እንደ መሆኑ በአዋጁ ችግሩን ለመቆጣጠር የሆነ ርቀት መጓዝ ይቻላል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ጥቂት ዓመታት የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር የወሰደው እርምጃ ችግሩን ለመፍታት ብዙ እንደመርዳቱ የዚህ አዋጅ እውን መሆን ደግሞ ተከራዮችን የበለጠ መታደግ እንደሚያስችል ከወዲሁ መናገር ይቻላል።

በሀገሪቱ ከተሞች እየናረ ለመጣው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ ብዙ ምክንያቶች ሊቀመጡ ይችላሉ። አንዱና ዋንኛው የመኖሪያ ቤቶች በበቂ ሁኔታ አለመገንባት ነው። ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ የተጠቀሙ ቤት አከራዮችና ደላሎች ችግሩን ሲያባብሱት ኖረዋል፤ እያባባሱትም ይገኛሉ።

በተለይ ደላሎች ባለቤት አርፎ በተቀመጠበት ሁኔታ ቆስቁሰው ተከራይ በቀላሉ የማይወጣውን ኪራይ እንዲጠይቅ በማድረግ ሆድ አስብሰው በማስወጣት ቤቱን ሌላ ሰው በከፍተኛ ኪራይ በማከራየት ያልዘሩትን ሲያጭዱ ኖረዋል። የቤት መሥሪያ፣ መግዣ ማደሻ ሶልዲ ሳያወጡ ተከራዮችን በመትከል በመንቀል፣ ዋጋ በማናር ተከራዮችን ተረጋግተው ተቀመጥው ካሉበት ቤት በጥቂት ወራት ውስጥ በማስለቀቅና አዲስ ተከራይ በማምጣት የግፍ እንጀራቻውን ያበስላሉ።

የሚገርመው ደግሞ አንዳንድ የቤት ባለቤቶች በቤት ኪራይ ጉዳይ ወኪሎቻቸው እነዚህ ደላሎች ናቸው። ደላሎቹ ተከራዮችን ለስድስት ወር ቢያቆዩዋቸው ነው፤ ስድስት ወር እንዳለፈ ወይ ዋጋ ይጨምራሉ፤ አልያም የቤቱ ባለቤት ቤቱን ሊገባበት ይፈልጋል ብለው ያስለቅቃሉ። ግን ሌላ ተከራይ በውድ ዋጋ ያከራያሉ።

እንደ እኔ እምነት በመሠረቱ በቤት ኪራይ ጉዳይ ከአከራይ ቀጥሎ ቢበዛም ቢያንስም የሚመለከተው ባለድርሻ መንግሥት ነው። ይህንንም የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ምሳሌ አንስቼ ላብራራ። መንግሥት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለዜጎች በዝቅተኛ ዋጋ ነው ያቀረባቸው። እነዚህ በዝቅተኛ ዋጋ ከመንግሥት የተገዙ ቤቶች ዛሬ የሚከራዩበት ዋጋ ሲታይ በቤት አቅርቦቱ ብዙ ዋጋ የከፈለው መንግሥት ሕዝቡን መጠቀም አልቻለበትም። በምትኩ እየተጠቀሙ ያሉት ምንም እሴት ያልጨመረው ደላላና ስግብግብ ባለቤቶች ናቸው። መንግሥት ለዜጎች በቀላል ዋጋ ቤትና ቦታ እያቀረበ ባለበት ሁኔታ የቤት ባለቤቶች መንግሥት ከሕገወጥ ድርጊቱ እንዲያስጥላቸው የሚጮሁ ዜጎችን እያሰቃዩ ኖረዋል።

አሁን የግፉ ፅዋ ሞልቷል፤ አከራይንም ተከራይንም እኩል የሚመለከት አዋጅ ወጥቷል። በዚህም የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ በየጊዜው እየጨመሩ ተከራዮችን ሲያሰቃዩ የኖሩ አከራዮች በሕግና ሕግ ብቻ የሚያከራዩበት ሁኔታ ይዞ መጥቷል፤ ይህ በሚገባ ከተተገበረ ምንም እሴት ሳይጨምሩ ዜጎችን መከራ ሲያሳዩ የኖሩ ደላሎችን ከመኖሪያ ቤቶች ኪራይ ጋር በተያያዘ ከሚፈጽሙት ሕገወጥ ተግባር ሊያስወጣቸው ወይም ሚናቸውን ሊያለዝብ ይችላል።

አከራይና ተከራይ የጎሪጥ የሚተያዩትን ያህል አንዳንድ አከራዮች ከተከራዮች ጋር የሚሞዳሞዱበት ሁኔታም ይታያል። ይህ ግንኙነት የመንግሥትን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳ ይገኛል፤ እነዚህ አካላት ቤቱ በ15 ሺ ብር ተከራይቶ ከሆነ በ8 ሺ ነው ያከራየሁት ብለው መንግሥት ቤቱ በተከራየበት ዋጋ መሠረት ማግኘት ያለበትን ጥቅም ያስቀራሉ። አንዳንድ ቤቶች ከተከራዩ በርካታ ዓመታት ቢያስቆጥሩም ግብር የሚከፍልባቸው በዚህ ዘመን ቤቶቹ በሚከራዩበት ዋጋ ሳይሆን በያኔው ዋጋ መሆኑም ሌላው መንግሥትን ገቢ እንዲያጣ የሚፈጸም ሕገወጥ ተግባር ነው።

አዋጁ ይህ ሕገወጥ ተግባር እንዳይቀጥል ማድረግ የሚያስችል እድልም ይፈጥራል። ከቤት ኪራይ ጋር ተያይዞ መንግሥት እንዲያጣቸው ሲደረጉ የነበሩ ጥቅሞችን ለማስጠበቅም ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። ትግበራው በአግባቡ መፈጸሙ ላይ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ይገባል።

ለቤት ኪራይ ዋጋ እየጨመረ መምጣት በተለይ አንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ዋና ተጠያቂ ተደርገው የሚወሰዱት ደላሎች ናቸው። ይህ አዋጅ በሚገባ እንዲተገበር ከተደረገ የእነዚህ የቀን ጅቦች እጅ ይቆርጣል። ሦስተኛ ወገን ሆኖ የሚመጣው የሚመለከተውም መንግሥት እንጂ ሌላ ወገን ወይም ደላላ አይሆንም። የእነዚህ በመኖሪያ ቤቶች ላይ ምንም እሴት ሳይጨምሩ የመኖሪያ ቤት ዋጋን ሲጨምሩ የኖሩ ሕገወጦች ከእዚህ አካባቢ መውጣት በራሱ የቤት ኪራይ ዋጋውን ሊያረጋጋው ይችላል ።

በዚህ አዋጅ መሠረት መንግሥት ዳኛ ነው። ሁለቱንም ወገኖች ይዳኛል። አዋጁ በተከራዮች ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና ለመቀነስ የወጣ ቢሆንም፣ የአከራዮችን ድምፅ እንደሚሰማ ይጠበቃል። በዚህም የአከራዮችን ስጋትንም ያጤናል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢኮኖሚው ላይ በየጊዜው ጫና ያሳደሩ ችግሮች በቤት ኪራይ ላይም ተፅፅኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ማንም አያጣውም፤ እነዚህ ችግሮች በእዚህ ልክም ይሁን ከዚህ ባነሰ ወይም ከዚህም በከፋ መልኩ በቀጣይም ሊከሰቱ ይችላሉ። የቤት ኪራይ ዋጋ ትመናው ይህን ሁሉ ታሳቢ አርጎ የሚወጣ ከሆነ የአከራዮች ስጋትም ይወገዳል።

አዋጁ በቅርቡ ሥራ ላይ እንደሚውል በአዋጁ ሰፍሯል። አዋጁን ማስፈጸም የሚያስችሉት መመሪያና ደንብ ወጥተው ከሆነ ወደ ትግበራው መገባቱ ለተከራዮች ፈጥኖ መድረስ ያስችላል። እነዚህን ማስፈጸሚያዎች ግን ወጥተዋል ብዬ አላስብም፤ ካልወጡ ፈጥኖ ማውጣት፣ ሲወጡም የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች በሚገባ እንዲወያዩባቸው ማድረግ ይገባል።

አዋጁ የተወሰነውን ችግር ይፈታል። ከዚህ ጎን ለጎን ዘላቂ መፍትሔ ላይ ማተኮርም ይገባል። ዘላቂ መፍትሔው ዜጎች የሚያደርጉት የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንዳለ ሆኖ የመኖሪያ ቤቶችን በመንግሥትም፣ በግሉ ዘርፍም በስፋት መገንባት ነው። ዜጎች መኖሪያ ቤቶችን ሊገነቡባቸው በሚችሉባቸው መንገዶች ላይ በስፋትና በትኩረት መሥራት ይገባል። የሀገሮችን ተሞክሮ መቃኘትና ቀምሮ መተገበርም ያስፈልጋል።

ዘካርያስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You