አዲስ አበባ ከተማን ልክ እንደ ስሟ አዲስና ውብ ለነዋሪዎቿ፣ ለእንግዶቿና ለጎብኚዎቿ ምቹ ለማድረግ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል። የግብይት ማዕከላት፣ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎች፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች፤ የከተማዋን ገጽታ በመገንባት፣ የቱሪስቶችን ቆይታ ማራዘም የሚያስችሉ ግዙፍ ፓርኮችና የመናፈሻ ስፍራዎች፣ ትላልቅ የመንገድ መሠረተ ልማቶች፣ ወዘተ. ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል። ከተማዋን እንደ ስሟ ውብ የማድረግ እና የዓለም አቀፍ ዲፐሎማት መቀመጫነቷን ታሳቢ ያደረጉ ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎችም ተሰርተዋል፤ እየተሠሩም ይገኛሉ።
የዓድዋን ገድል የሚመጥን ግዙፍ ሙዚየም በከተማዋ እምብርት ፒያሳ ተገንብቶ በቅርቡ ወደ ሥራ ገብቷል። ሙዚየሙ በርካታ አገልግሎቶችንም መስጠት እንዲችል ተደርጎ የተገነባ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም፣ ትላልቅ ስብሰባዎችን እያስተናገደ ይገኛል፤ ለጎብኚዎችም ክፍት ተደርጓል።
ከተማዋን እንደ ስሟ አዲስና ውብ የማድረጉ ሥራ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል። ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ የኮሪደር ልማት እያካሄደ ይገኛል። በፒያሳ፣ ሠራተኛ ሰፈር ፣ ከፒያሳ አራት ኪሎ ፣ ቀበና መገናኛ ድረስ እየተካሄደ ካለው የኮርደር ልማት ሥራ መረዳት የሚቻለውም ሥራው ግዙፍና ሰፊ መሆኑን ነው።
የኮሪደር ልማቱ በአዲስ የሥራ ባህል 24 ሰዓት እየተሠራ የሚገኝ ሲሆን፣ ለኮሪደር ልማቱ የሚያስፈልጉ ቦታዎችን ዝግጁ ለማድረግ ሲባል ከተማዋን አይመጥኑም የተባሉ እንዲሁም አላስፈላጊ የተባሉ ግንባታዎችን የማፍረስ ሥራዎች ተካሂደዋል፤ ግዙፍ የመንገድና ሌሎች መሠረተ ልማት ግንባታዎች እየተፋጠኑ ይገኛሉ።
በዚህ 40ኪሎ ሜትር ያህል በሚሸፍነው ከፒያሳ እስከ መገናኛ፣ ከአራት ኪሎ ቀበና መገናኛ ፣ ከሜክሲኮ ሳር ቤት ቄራ ጎተራ ወሎ ሰፈር ቦሌ እንዲሁም ከቦሌ መገናኛ እና ከመገናኛ ሰሚት አቅጣጫዎች በኮሪደር ልማቱ ከተማዋን የማደስ ሥራ እየተካሄደ ነው።
ከተማዋን እንደ ስሟ ውብ፣ በአፍሪካ ደረጃ ከሚታወቁ ከሚገኙ ከተሞች መካከል አንዷና ስማርት ከተማ ለማድረግ ባለመው በዚህ የኮሪደር ልማትና የከተማ እድሳት ደረጃውን የጠበቀ የተሽከርካሪና የብስክሌት መንገድ ግንባታም ይካሄዳል፤ መንገድ ማስዋብ ሥራ፣ ምቹ የእግረኛ መሄጃዎች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች እንዲሁም ስማርት የመንገድ መብራት ሥራዎች መሠረተ ልማት ይገኝበታል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የኮሪደር ልማቱን አስመልክቶ በቅርቡ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የቆየች፣ የጥቁር ሕዝብ ታሪክ የሆነውን የዓድዋ ታሪክን የጻፈች ታሪካዊ ሀገር ናት። የአፍሪካ ህብረት መገኛ እና የዲፕሎማቲክ ማዕከልም ናት።
እነዚህን ሁሉ ሀገራችን ላይ በማቆየት ከእነ ኒውዮርክ እና ጄኔቫ፣ በመቀጠል የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን ማስጠበቅ ያስፈልጋል። ይህንን መንከባከብ እና ተወዳዳሪነቷን ማሳደግ ካልተቻለ መነጠቅም ሊመጣ ይችላል ሲሉም አስገንዝበዋል፤ ለእዚህም ከወዲሁ ሩቅ አስቦ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል።
የኮሪደር ልማቱ በተለይ ለቱሪዝም በአጠቃላይ ለምጣኔ ሀብት ልማቱ ያለውን ፋይዳም አብራርተዋል። በመዲናዋ ዓለም-አቀፍ ተቋማት የሚሰሩ የውጭ ዜጎችና ዲፕሎማት በውጭ ምንዛሪ የሚያገኙትን ይዘው ለመዝናኛ፣ ለህክምና እና ለተለያዩ ግብይቶች ወደ ሌላ ሀገር ይሄዳሉ ያሉት ከንቲባዋ፣ ሀገራችን ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለባት ሲሉም ተናግረዋል። እነዚህን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ የኮሪደር ልማት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በኮሪደር ልማቱ የሚካተቱ ሥራዎች በጥናት ተለይተው ወደ ሠራ መገባቱንም ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማቱ የዓድዋ ድል መታሰቢያን ፣ የሀገሪቱን ታሪክ አጉልቶ በሚያሳይ መልኩ የፒያሳን ዙሪያ እና አራት ኪሎን ማገናኘቱንም ሥራው ታሳቢ ማድረጉ ተጠቁሟል። ከአራት ኪሎ ቀበና እስከ መገናኛ ፣ ከአራት ኪሎ እስከ ቦሌ አየር ማረፊያ፤ ከቦሌ አየር ማረፊያ እስከ መገናኛ፤ ከመገናኛ እስከ ሲኤምሲ አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ሴንተር (Addis Africa Convention Center)፣ በተጨማሪም ፋይናንሻል ዲስትሪክት ከሚባለው ከሜክሲኮ አካባቢ ጀምሮ እስከ አፍሪካ ህብረት ሳር ቤት፣ ቄራ፣ ጎተራ ወሎ ሰፈር ድረስ ያሉትን ኮሪደሮች ይሸፍናል።
የኮሪደር ልማቱ ባካተታቸው አካባቢዎች ያረጁ፣ አደጋን ለመከላከል የማያስችሉ፣ ነዋሪዎችን ለበሽታ ተጋላጭ የሚያደርጉ አንዳንድ አካባቢዎችንም የሚያድስ በመሆኑም፣ ኮሪደር ብቻ ሳይሆን የከተማ እድሳትንም ማዕከል ያደረገ ነው። የአራዳው አካባቢም በተመሳሳይ የከተማ እድሳትን ጭምር ማዕከል ያደረገ መሆኑን ከንቲባዋ አመላክተዋል።
ከንቲባዋ እንዳብራሩት፤ እነዚህ አካባቢዎች በኮሪደር ልማቱ የተመረጡበት ዋና ምክንያት መንገድ ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን ማገጣጠም የሚገባቸው መሠረተ ልማቶች በመኖራቸውም ነው። አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና አበባ ለማድረግ ታስበው የተሠሩ መሠረተ ልማቶች እና የቱሪስት መስህቦች አሉ። የሀገሪቱና የከተማዋ አንዱና የስልጣኔ ማሳያ ከሆነው ማዘጋጃ ቤት ሲጀመር ከቸርቸር ጎዳና እስከ መስቀል አደባባይ፣ ወንድማማች፣ አንድነት ፓርክ፣ አብርኸት ቤተመጻሕፍት፣ ሳይንስ ሙዚየም፣ አካባቢ ያሉትን መሠረተ ልማቶች ማገጣጠምና ማገናኘት ያስፈልጋል።
የኮሪደር ልማቱ የመዲናዋን ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች ለማስጎብኘትም ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ሲሆን፣ መስህቦቹን አጠቃላይ የአዲስ አበባን ውበት በሚያጎላ መልኩ ማገናኘትን ታሳቢ ያደረገ ነው። ከዚህም ውጭ ትልቅ ኢንቨስትመንት ተደርጎበት የተገነባው የፑሽኪን አደባባይ ጎተራ መንገድ አካል የሆነው የመዲናዋ የዋሻ መንገድ ፣ አቃቂ ቃሊቲን ከቦሌ እና አዲሱን የቦሌ ተርሚናል ከጎሮ ጋር ከሚያገናኘው መንገድ ጋርም ለማገናኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የመዲናዋን የኤግዚቢሽን ማዕከልነት ለመጨመር በሲኤምሲ እየተገነባ ያለው አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ማእከልንና የጫካ ፕሮጀክት ሥራዎችን ለማገጣጠም የኮሪደር ልማቱ አስፈላጊ መሆኑንም ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል።
እነዚህን በሚገባ ማገጣጠም ሲቻል የከተማዋን የቱሪዝም መስህብነት መጨመር እንደሚቻል ጠቅሰው፣ ለእድገትና እና ሰፊ የሥራ እድሎች የጎላ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።
የከተማዋ ከንቲባ የኮሪደር ልማቱ እየተከናወነ ያለባቸውን አካባቢዎች ለተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም አስጎብኝተዋል። በዚሁ ወቅትም የዚህ ኮሪደር ልማት የውኃ፣ የፍሳሽ፣ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮም፣ የሲሲቲቪ ካሜራ፣ አገልግሎቶችን ባሳለጠ መልኩ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል። የግንባታውን ለውጥ በአንድ ወር ለመመልከት ያስችላል የተባለው የኮሪደር ልማት ግንባታ፣ እግረኛው በነፃነት የሚንሸራሸርበት እና ከወንዞች ዳርቻ ልማት ጋር እንዲናበብ ተደርጎ ዲዛይኑ የተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ከመልሶ ልማቱ ባዶ ቦታዎች ውጭ የኮሪደር ልማቱ የመንገድ ሥራ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።
በመሠረታዊነት የከተማን መስፈርት የሚያሟሉና ለኑሮ ምቹ ከሆኑ መስፈርቶች መካከል መንገዶች፣ ሰፋፊ የተሽከርካሪ ማሳለጫ መሠረተ ልማቶች፣ የፍሳሽና ቆሻሻ ማስወገጃ ልማቶች ተጠጋግቶ ለሚኖር ሕዝብና እንደ ዓለም አቀፍ ሕጎችም ለከተማ ወሳኝ መለኪያዎች መሆናቸውም ተገልጿል።
የኮሪደር ልማቱ ተነሺዎችንም በአግባቡ እያስተናገደ መሆኑ ተጠቁሟል። ከዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም አካባቢ ለተነሱት ለተወሰኑ የግል ቤት ላላቸው ሰዎች ብቻ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊየን የሚሆን ካሳ መከፈሉንና እየተከፈለ መሆኑም ተጠቁሟል። የቅሬታ ጽሕፈት ቤት ተከፍቶም ቅሬታ አቅራቢዎች እየተስተናገዱ መሆናቸውንም ይናገራሉ።
በሌሎች ኮሪደር ልማት ሥራዎችም ከመንገድ ዳር የተነሱትን ጨምሮ ስምንት ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ምትክ ቦታ ቀርቧል። በተለቀቁት ቦታዎች ላይም የንግድ ሥራዎች፣ ሕዝብ የሚገለገልባቸው፣ ትልልቅ የመገናኛ ስፍራዎች ፊልምና ትያትር የሚታይባቸው፣ ሰዎች በቀላሉ በእግራቸው እየተንቀሳቀሱ፣ እየተዝናኑ፣ ሳይክል እየነዱ ማህበራዊ ትስስርን ማጠናከር የሚችሉባቸው አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ ግንባታዎች እንደሚካሄድም አመላክተዋል።
በልማት ሥራው ባሉበት የሚታደሱ ስድስት ያህል ቅርሶች መለየታቸውንም ጠቁመው፣ ማቆየትና መያዝ የሚገቡ ቅርሶች፣ መሠረተ ልማቶች፣ ጥንታዊነታቸውን ይዘው እንዲቆዩ በሚያስችል መልኩ የሚታደሱ መሠረተ ልማቶች እንዳሉም ተናግረዋል። ሲኒማ ኢትዮጵያ፣ ሀገር ፍቅር፣ የእነ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ መኖሪያ ቤት፣ የቀድሞ ማዘጋጃ የመሳሰሉት ባሉበት ይታደሳሉ።
የዓድዋ ድል መታሰቢያን ከ128 ዓመታት በኋላ ታሪኩን በሚመጥን መልኩ መገንባት መቻሉን ጠቅሰው፣ በዚህ የኮሪደር ልማት ሥራም ከተማዋን ውብ በማድረግ ለነዋሪውም ይበልጥ ምቹ የምትሆንበት መሠረተ ልማት በመገንባት በተግባር ለማሳየት በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል። ፕሮጀክቱም በተያዘለት ጊዜ እንደሚጠናቀቅም አረጋግጠዋል።
የኮሪደር ልማቱ ያለበትን ደረጃ በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት መድረክ ተካሂዷል። በዚህም የልማቱ ፋይዳ ተብራርቷል፤ ልማቱ በደረሰበት ደረጃ ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር (ዶ/ር) ዐቢይ አሕመድ የመዲናዋ ኮሪደር ልማቱን ከሚያስፈጽሙ አካላት ጋራ ባደረጉት ግምገማ እንዳስረዱትም መዲናዋ ሻል ካሉ ዋና ከተሞች መካከል አንዷ ከተቻለም ቀዳሚ መሆን አለባት። ኮሪደር ልማቱ ይህን እውን ለማድረግ የሚሠራ ነው። ፒያሳን መውሰድ ቢቻል
እውነተኛ ፒያሳ ሆና የአዲስ አበባ እምብርት ሆና ያማረች፣ የተዋበች፣ ሰዎች ሄደው ለማየት የሚናፍቋት አካባቢ እንድትሆን ያለመ ነው። አሁን በተጀመረው ሥራ ከዓመት በኋላ ትክክለኛዋን ፒያሳ ማግኘት የሚቻል መሆኑን ጠቁመው ይህንንም ያመጣው ዓድዋ ሙዚየም፣ ማዘጋጃ ቤት አስተዳደር፣ ቸርችር ጎዳና፣ የወዳጅነት አደባባዮች አሁን ደግሞ የወንዝ ዳርቻ ልማቱ ሲገናኙ ፒያሳን ከፍ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።
ከተማ ውስጥ የተጀመሩትን በነጥብ ደረጃ የሚጠቀሱ ቦታዎችን በማገናኘት ማንም ሰው ሳይነገረው የከተማውን ውበት እና መተሳሰር ማየት እንዲችል የሚያደርግ ሥራ መሆኑን አስረድተዋል።
ከተማ ማለት መንገድ፣ መብራት፣ ውሃ ትምህርት ቤት፣ ጤና ተቋማት፣ የልጆች መናፈሻ ማንኛውንም የሚፈልገውን ነገር በአቅራቢያ ማግኘት የሚችልበት ሁኔታ ካልተመቻቸ በቀር የተጠጋጉ ቤቶቸ ብቻቸውን ከተማ አለመሆናቸውን ይገልጻሉ። ይህን ለማድረግ ከመንገድ፣ ከእግረኛ መሄጃዎች፣ ከፓርኮችና አረንጓዴ ስፍራዎች፣ ከቀለም ቅቦች፣ ከመብራት አኳያ ደረጃቸውን የጠበቁ መሠረተ ልማቶች የተሟላበት ሥራ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም በቅርቡ ይህንኑ የመዲናዋን የኮሪደር ልማት ጎብኝተዋል። በጉብኝታቸው ወቅት መዲናዋ የምታከናውነውን የመንገድ ኮሪደር ልማት እና ከተማዋን የማደስ ሥራ ተመልከተዋል። ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት ለጎብኚዎች እንደገለጹት ፤ የመንገድ ኮሪደር ልማቱ የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች ዘመናዊ በሆነ መንገድ ለእይታ በሚስቡ መልኩ እንደሚገነቡ አስታውቀዋል። በሸራተን ጀርባ የተሠሩት ዓይነት ስማርት መብራቶችም በግንባታው እንደሚካተቱ አስረድተዋል።
ከንቲባዋ እንዳብራሩት፤ የኢንተርኔት ግንኙነት ማድረግ የሚያስችል፣ ስክሪን ያለው፣ ስማርት መብራት ይገባላቸዋል። ዋና መንገዳችን የአፍሪካ መግቢያ መንገድ የሆነውና ከቦሌ አየር መንገድ ጋራ የሚያገናኘው ትልቁ መንገድም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። በመልሶ ማልማቱም ክፍት የነበሩ ቦታዎች እንዲለሙ እንደሚደረግ ገልጸዋል፤ ሕንጻዎችንም በቀለም፣ በመስታወትና በመብራት ወደ አንድ ደረጃ የማምጣት ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የኮሪደር ልማቱን በጎበኙበት ወቅት ፤ አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስና ውብ አበባ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ በተጨባጭ ወደ መሬት እየወረደ መሆኑ ይታያል ሲሉ ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም የተሠሩ ሥራዎችን ለማገናኘት እየተካሄደ ያለውን ርብርብ በጉብኝቱ መመልከት መቻላቸውንም ተናግረዋል። ለውጡ ገና እንደመጣ ከ2010 ነሐሴ ወር ጀምሮ በሃሳብ ደረጃ የነበሩ ነገሮች ወደ መሬት በወረዱበት ሁኔታ አስደናቂ ሥራ ማየታቸውን ጠቅሰዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሜ በዶ በበኩላቸው አዲስ አበባ ዘርፈ ብዙ ልማት ላይ እንደምትገኝ ጠቅሰው፣ የከተማ አስተዳደሩ የኮሪደር ልማት ሥራም ከከተማው አልፎ ኢትዮጵያን የሚያስጠራ መሆኑን አስታወቀዋል። ልማቶቹም ምክር ቤቱ ዘርፈ-ብዙ ድጋፎችን እንዲያደርግ የሚያስገደዱ መሆናቸውንም ገልጸዋል። እየተሠራ ያለው ሥራ ሊበረታታ የሚገባው እንደሆነ ገልጸው ምክር ቤቱ በሚጠበቅበት ሁሉ ልማቱን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም