የባህሪ ለውጥ ለማህበረሰብ ጤና

የባህሪይ ለውጥ ብቃትንና ምርታማነትን ለማሻሻል የአንድን ግለሰብ ድርጊት፣ አመለካከትና ልማድ የመቀየር ሂደት ነው። ይህ የግለሰቡን በሥራ ቦታ ላይ ያለውን ባህሪ የማሻሻል ሂደት ሊጠቁም ይችላል። ነገር ግን የባህሪ ለውጥ በተለያዩ ሁኔታዎች፣ ቦታዎች፣ ዘርፎችና ዓይነቶች የተለያየ ትርጓሜና ገለፃ ሊሰጠው ይችላል። በጤናው ዘርፍ የባህሪ ለውጥ የራሱ መገለጫ ይኖረዋል። አንድ የሚያስማማ ጉዳይ ቢኖር ግን የባህሪ ለውጥ ለግለሰቡ ሁለንተናዊ ደህንነትና ስኬት ቁልፍ ሚና ያለው መሆኑ ነው።

የማህበራዊ ለውጥ የግለሰብን ሁለንተናዊ ጤና ከመጠበቅ ባለፈ የማህበረሰብን ጤናና ደህንነት ከማረጋገጥ አንፃርም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ለዛም ነው የግለሰብንና የማህበረሰብን ጤና ለመጠበቅ በባህሪ ለውጥ ዙሪያ ሰፋፊ ሥራዎች የሚሰሩት። አብዛኛዎቹ በባህሪ ለውጥ ዙሪያ ጠንካራ ሥራ የሠሩ ሀገራትም የግለሰቦችን ብሎም የማህበረሰባቸውን ጤና መጠበቅ ችለዋል።

ኢትዮጵያም በባህሪ ለውጥ ዙሪያ፣ በተለይ በወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጋ የተለያዩ ሥራዎችን ስትሰራ ቆይታለች። ይህንኑ ታሳቢ ያደረጉ ጉባኤዎችን በማካሄድ ለጉዳዩ ጠቃሚ ግብዓቶችን በማሰባሰብ ሥራ ላይ አውላለች። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ሶስተኛውን ሀገር አቀፍ የማህበራዊና ባህሪ ለውጥ ጉባዔ ‹‹የማህበራዊና ባህሪ ለውጥ ለዘላቂ ልማት›› በሚል መሪ ቃል በቅርቡ አካሂዳለች። ጉባኤውም የማህበረሰቡን ጤና በማሻሻል ዜጎች የራሳቸውን ጤና መጠበቅ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክሯል።

በጉባኤው ከሀገር ውስጥና ከውጭ የመጡ ከ400 በላይ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን ልዩ ልዩ ጥናቶችና ተሞክሮዎች ቀርበውበታል። ለእውቀት ሽግግር፣ ለፖሊሲ አውጪዎችና ተግባሪዎች፤ እንዲሁም ለሚዲያ አካላት ጠቃሚ ግብዓትም ተገኝቶበታል። ኢትዮጵያ ለምትከተለው የቅድመ መከላከል የጤና ፖሊሲ ውጤታማነትና ሕክምና የመስጠት ሂደት ትልቅ ድርሻ እንደነበረውም ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ጤና ትምህርትና ፕሮሞሽን ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር እሸቱ ግርማ እንደሚናገሩት መንግሥት እያንዳንዱ ግለሰብ ምን እንደሚበላና ምን እንደሚጠጣ ለመከታተል የጤና ባለሙያ ሊያሰማራ አይችልም። ስለጤናው ማወቅና ራሱን መጠበቅ ያለበት ራሱ ግለሰቡና ማህበረሰቡ ነው። አዋጭ የሚሆነውም ማህበረሰብን በጤና እውቀት ማብቃት ነው። ማህበረሰቡ ስለጤናው መጠየቅና ግንዛቤ መውሰድ ይኖርበታል። ስለጤናው ግንዛቤ ያለው ማህበረሰብ መፍጠርም ይገባል። ለዚህ ደግሞ ማህበረሰባዊ የባህሪ ለውጦች ላይ ያሉ ሥራዎችንና ልምዶችን መቀመር ያስፈልጋል። ማህበረሰቡ በደንብ ከነቃ ጤናውን በራሱ መጠበቅ ይችላል።

ኢትዮጵያ በ1978 ዓ.ም በመጀመሪያ ሕክምና ተቋም አገልግሎት መስጠት ከጀመረች ወዲህ የማህበራዊና የባህሪ ለውጥ ሥራዎችን ስትሰራ ቆይታለች። በዚህም በርካታ ለውጦች መጥተዋል። በተለይ በጤና ኤክስቴንሽን አማካኝነት ቤት ለቤት ማህበረሰቡ ጋር በመቅረብ የተሠሩ ሥራዎች ትልቅ እምርታ አምጥተዋል። ማህበረሰቡን የማንቃት፣ ሴቶችና እናቶችን የማስተማርና ማብቃት ሥራዎችም ተከናውነዋል።

በእያንዳንዱ ጤና ኬላ ሁለት የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች አሉ። የእነርሱ ዋነኛ ሥራም ቤት ለቤት ሄደው ማህበረሰቡን ማብቃት፣ ማስተማር፣ እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ ግንዛቤ መስጠት፣ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎቶችን እንዲወስዱ ማድረግ፣ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከበሽታ እንዲከላከሉ ማስቻል ነው። በዚህም በርካታ ሥራዎች ተከናውነው ለውጦች መጥተዋል። ለምሳሌ ኤች አይ ቪ/ኤድስ መድኃኒት የሌለው በሽታ ነው። በማከም አይደለም ሕዝቡን ከኤች አይ ቪ/ኤድስ መጠበቅ የተቻለው። በማህበራዊና የባህሪ ለውጥ ሥራዎች ነው።

እንደ ኮቪድ ያሉ ወረርሽኞች ሲከሰቱም አብዛኛዎቹ ሥራዎች የተከናወኑት በባህሪ ለውጥ ሥራዎች ነው።

ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት የማህበራዊና የባህሪ ለውጥ ሥራ በአንድ ጊዜ የሚጠናቀቅ አይደለም። ውጤቱም የተለያየ ነው። አንዳንዴ ቶሎ ውጤት የሚያመጡ የማህበራዊና ባህሪ ለውጥ ሥራዎች አሉ። ሌላ ጊዜ ደግሞ ውጤታቸው የሚዘገይ የማህበራዊና ባህሪ ለውጥ ሥራዎች ይኖራሉ። ለምሳሌ አንድ ሰው የስኳር በሽታ ታማሚ እንዳይሆን ሥራው ዛሬ ላይ ካልተሠራ በሽታውን የመቆጣጠር ሥራው ሰላሳና አርባ ዓመታትን ሊፈጅ ይችላል። ወይም ደግሞ ዛሬ የስኳር ህመም መከላከል ሥራ የተሠራላቸው በርካታ ሰዎች የዛሬ ሰላሳና አርባ ዓመት የማህበራዊና ባህሪ ለውጥ ሥራዎች ውጤት ሊሆኑ ይችላሉ።

ከማህበራዊና ባህሪ ለውጥ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተነድፈዋል። ነገር ግን የማህበራዊና ባህሪ ለውጥ ሥራዎች ምንም ዓይነት ጉዳት የማያመጡ አድርጎ የማሰብ የተሳሳተ አመለካከት አለ። ይህን ማረም ያስፈልጋል። እንዲያም ሆኖ የማህበራዊና የባህሪ ለውጥ ሥራዎች በትክክል፣ ሳይንሳዊና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ካልተሠሩ ትልቅ ችግር ሊያመጡ ይችላሉ። ለምሳሌ በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ወረርሽኝ በተስፋፋበት ወቅት ማግለልና መድልኦን ያመጣው የማህበራዊና የባህሪ ለውጥ ሥራዎች በአግባቡ ባለመሠራታቸው ነው።

የማህበራዊና የባህሪ ለውጥ ሥራዎች በአግባቡ ካልተሠሩ ደግሞ ሀገርን ሊጎዱና ማህበረሰብን ሊያጠፉ ይችላሉ። አሁን ደግሞ የማህበራዊ ሚዲያውም እንደልብ መስፋፋትና በራሱ መደበኛው ሚዲያም በቁጥር መብዛት የማህበራዊና ባህሪ ለውጥ በብዙ መልኩ ተጋላጭ ያደርገዋል። ስለዚህ የማህበራዊና ባህሪ ለውጥ ሥራ ደግሞ ቁጥጥር ይፈልጋል። ጥራቱ ላይ እጅግ በርካታ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል። ባለሙያዎችን ማብቃት ላይም ተመሳሳይ ሥራ መሥራት ይገባል። ለዚህም የኢትዮጵያ ጤና ትምህርትና ፕሮሞሽን ባለሙያዎች ማህበር ተከታታይ ስልጠናዎችን ለሙያ ማህበሩ አባላትና ለሌሎችም የሚዲያ ተቋማት እየሰጠ ይገኛል።

በማህበራዊና ባህሪ ለውጥ ዙሪያ በወጣቶች ላይ የሚሰሩ በርካታ አጋር ድርጅቶች አሉ። በተለይ ድርጅቶቹ ወጣቶችን ከተለያዩ ሱሶችና ጤና ጎጂ ድርጊቶች የመጠበቅ ሥራዎችን ይሰራሉ። ያልተገቡና በወጣቶች ላይ የሚታዩ ባህሪዎችን የመከላከል ሥራዎችም እየተከናወኑ ይገኛሉ። ለአብነትም በስነ ተዋልዶ ጤና ላይ ሰፊ የማህበራዊና የባህሪ ለውጥ ሥራዎች በወጣቶች ላይ እየተሠሩ ነው።

የማህበራዊና ባህሪ ለውጥ ሥራ የጤናው ሴክተር ሥራ ብቻ አይደለም። በኢትዮጵያ የተከሰቱና እየተከሰቱ ያሉ ቀውሶች ከባህሪና ከማህበረሰቡ ውቅር ጋር የተያያዙ ናቸው። ስለዚህ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በማህበራዊና ባህሪ ለውጥ ዙሪያ በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። የሙያ ማህበሩም ከጤና ባለፈ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ካላቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል። በይበልጥ ደግሞ በማህበረሰቡ የስነ ልቦና ስሪትና የባህሪ ለውጥ ዙሪያ ምርምሮች መሠራት አለባቸው።

በጤና ሚንስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ጤና ኮሚዩኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ተገኔ ረጋሳ እንደሚገልፁት የማህበራዊና ባህሪ ለውጥ ሥራ ከዚህ ቀደም እምብዛም ትኩረት የሰጠው አካል አልነበረም። ከዚህ በተቃራኒ ግን የማህበራዊና ባህሪ ለውጥ ሥራ እጅግ አስፈላጊና በተለይ በሽታን የመከላከል ሥራን በከፍተኛ ደረጃ የሚያግዝ ነው። ሥራው ጤና ትምህርትና ፕሮሞሽን ውስጥ ራሱን ችሎ ሀገር አቀፍ የጤና፣ ኮሚዩኒኬሽንና የባህሪ ለውጥ ስትራቴጂ ተቀርፆለት እየተሠራበት ይገኛል።

የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ መከላከልን መሠረት ያደረገ መሆኑ ይታወቃል። ህብረተሰቡ በበሽታዎች ከመያዙ በፊት ራሱ ባለቤት ሆኖ ጤናውን እንዲጠብቅና እንዲያሻሽል በማህበራዊና ባህሪ ለውጥ ዙሪያ ሰፋፊ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፤ አሁንም እየተሠሩ ነው። የሚሰጧቸው የጤና አገልግሎቶችም በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ተከፍለው ነው የሚታዩት። የመጀመሪያው በሽታዎችን የመከላከል ነው። ሁለተኛው ጤናን የማበልፀግ፣ ህብረተሰቡን የማስተማርና የማሳወቅ ሥራ ነው። ሶስተኛው አክሞ የማዳን ሥራ ሲሆን፤ አራተኛው ደግሞ የማገገም /ሪሃብሊቴሽን/ ሥራ ነው።

በአራቱም ክፍሎች የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶች ውስጥ የማህበራዊና የባህሪ ለውጥ ኮሚዩኒኬሽን /ተግባቦት/ ሥራዎች ይሰራሉ። በዚሁ መሠረት ባለፉት ዓመታት በተለይም ኢትዮጵያ ባስመዘገበቻቸውና ቀጣይነት ያላቸው የጤና ልማት ግቦችን ለማሳካት በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። ከሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተለያዩ የጤና ፕሮግራሞች እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች አሉ። ከነዚህ ተግዳሮቶች ውስጥ በዋናነት የአየር ንብረት ለውጥ ይጠቀሳል። በተለያዩ አካባቢዎች ያጋጠሙ የፀጥታና የሰላም መደፍረሶችም ከተግዳሮቶች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው። በድርቅና ሌሎች ተፈጥሯዊ ምክንያቶች የተከሰቱ ችግሮችም ነበሩ።

ሥራ አስፈፃሚው እንደሚሉት እነዚህንና የመሳሰሉ ችግሮችን በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በርካታ የማህበራዊና የባህሪ ለውጥ ሥራዎች ተከናውነዋል። የመገናኛ ብዙሃንም በተለይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በማስጨበጥ፣ የባህሪ ለውጥ እንዲያመጣ፣ ራሱን ከበሽታዎች እንዲጠብቅ በማድረግ ረገድ የድርሻቸውን ተወጥተዋል። በእነዚህና መሰል ሥራዎች በተሠሩ ሥራዎችም ወረርሽኙ ብዙም ጉዳት ሳያስከትል መቆጣጠር ተችሏል። በዚህ ውስጥ የኮሚዩኒኬሽንና የባህሪ ለውጥ ሥራዎች ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል።

እነዚህን የጤና ችግሮች በማለፍ እዚህ ደረጃ ላይ ቢደርሰም አሁንም ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች ለአብነትም ወባ፣ ኤች አይ ቪ/ኤድስና ቲቢ እየጨመሩ መጥተዋል። እነዚህ በሽታዎች ከከተሞች ባለፈ ወደ ገጠራማ አካባቢዎችም ጭምር እየተስፋፉ ይገኛሉ። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ በሽታዎችን መከላከልና አክሞ የማዳን ላይ ትኩረት ያደረገ እንደመሆኑ ህብረተሰቡ ተላላፊም ሆነ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ራሱን እንዲጠበቅ፣ የአኗኗር ዘይቤውንና የአመጋገብ ሥርዓቱን እንዲያስተካክል የማስተማር፣ የማሳወቅና የማህበራዊና የባህሪ ለውጥ ሥራዎች በተለያዩ የኮሚዩኒኬሽን መንገዶች እየተሠሩ ይገኛሉ።

በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማህበራዊና ባህሪ ለውጥ ጋር በተያያዘ የተሠሩ ጥናትና ምርምሮች አሉ። እነዚህን ጥናትና ምርምሮች ለማህበራዊና ባህሪ ለውጥ ሥራዎችን እንደ ግብዓት መጠቀም ያስፈልጋል። ጤና ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን ሌሎችም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት በማህበራዊና የባህሪ ለውጥ ዙሪያ በጋራና በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል። ህብረተሰቡም በቂ ግንዛቤ አግኝቶ የባህሪ ለውጥ በማምጣት ራሱን ከበሽታዎች መከላከል ይጠበቅበታል። ይህን ማድረግ ከተቻለ ጤናማ ማህበረሰብ መፍጠር ይቻላል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You