4ኛው ዙር የአዲስ አበባ ብስክሌት ክለቦች ቻምፒዮና እሁድ ይካሄዳል

በየዓመቱ የሚካሄደው የአዲስ አበባ ክለቦች፣ የታዳጊዎች፣ የግል ተወዳዳሪዎችና የቀድሞ ብስክሌተኞች ቻምፒዮና እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ውድድሩ ሶስተኛ ሳምንቱን የያዘ ሲሆን በሰሚት፣ በአዲሱ ገበያና በቴዎድሮስ አደባባይ ለስምንት ሳምንታት ተካሂዶ ይጠናቀቃል፡፡

በዘንድሮው ቻምፒዮና በዋናነት አራት ክለቦች እየተፎካከሩ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ጋራድ፣ አዲስ አበባ ፖሊስና የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ናቸው፡፡ የግል ተወዳዳሪዎች፣ ታዳጊ ፕሮጀክቶችና የቀድሞ ብስክሌተኞች በውድድሩ ድምቀትን መፍጠር ችለዋል። በቻምፒዮናው በርካታ ስፖርተኞች እየተካፈሉ ሲሆን በታዳጊ ፕሮጀክቶች ደረጃ 35 ብስክሌተኞች፣ 39 የግል ተወዳዳሪና አዋቂ ማውንቴን ብስክሌተኞች፣ 16 በማውንቴን ሴቶችና 20 የሚደርሱ የቀድሞ ብስክሌተኞ እንዲሁም 25 የክለብ ተወዳዳሪዎች ጠንካራ ፉክክር እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ውድድሩ መካሄድ የጀመረው መጋቢት 1/2016 ዓ.ም ሲሆን ሶስተኛ ሳምንቱን አስቆጥሯል፡፡ ሚያዝያ 20/2106 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅም የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡ በዚህም መሰረት ቀሪ የአምስት ሳምንታት ውድድሮች በጉጉት የሚጠበቁ ሆነዋል፡፡ ባለፍው እሁድ በተካሄዱ የሶስተኛ ሳምንት ውድድሮች በሁሉም የፉክክር አይነቶች በከፍተኛ ፉክክሮች ታጅበው ተጠናቀዋል፡፡

በኮርስ ብስክሌት በክለቦች መካከል በ28 ዙሮች በተደረገው ፉክክር ፍራኦል ወልደኪዳን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በቀዳሚነት አጠናቀል፡፡ ፉአድ ሻሚል ደግሞ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ሁለተኛ ሆኖ ውድድሩን ሲፈፅም፣ ሰለሞን ዓለሙ በተመሳሳይ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ሶስተኛ በመሆን ውድድሩን ጨርሳል፡፡ በዕለቱ ፉክክርም ብስክለተኞቹ በሰዓት 41.37 ኪሎ ሜትር በመጋለብ ውድድራቸውን እንደጨረሱ ታውቀል፡፡

በአዋቂዎች መካከል 21 ብስክሌተኞችን ባፋለመው ውድድር እሱባለው አማረ 1ኛ፣ የአብስራ ካሳሁን ሁለተኛ እና ዳግም ታሪኩ 3ኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡ በቀድሞ ብስክሌተኞች መካከል የተካሄደውን ውድድር ችኖ ሮልሰ 1ኛ፣ ወልደወሰን አገሬ 2ኛና አንተነህ ተሾመ 3ኛ በመሆን ጨርሷል።

ውድድሩ በተለያዩ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች እየተካሄደ ሲሆን እንደየ ፉክክር አይነቱ የሚሸፍነው ርቀትም የተለያየ ነው፡፡ የመጀመርያው ውድድር ሰሚት የተባበሩት አካባቢ ነበር የተካሄደው፡፡ የሁለተኛ እና ሶስተኛ ሳምንት ውድድር ደግሞ አዲሱ ገብያ አካባቢ ከሚገኘው ጺዮን ሆቴል እስከ ጉለሌ እጽዋት ማእከል ባለው መንግድ ላይ ተካሂዳል፡፡

ብስክሌት ጋላቢዎቹ አንድ ቦታ ብቻ እንዳይለምዱና የመወዳደርያ ስፍራን ምቹ ለማድረግ የተለያዩ የማዘውተርያ ስፍራዎች ማግኘት እንደሚኖርባቸው ታስቦ በተለያዩ ቦታዎች ውድድራቸውን እያከናወኑ እንደሆነም ፌዴሬሽኑ ጠቁሟል፡፡ አዲሱ ገብያ አካባቢ ከፍታና ቀዝቃዛ፣ ዳገታማና ቁልቁለታማ በመሆኑ ለውድድር ተመራጭ አድርጎታል፡፡ ሌላው ውድድሩ የሚካሄድበት ስፍራ ቴዎድሮስ አደባባይ እንዲሁ ቁልቁለትና ዳገት ያለው እንደሆነና ለስፖርተኞቹ የተለያዩ መሰናክሎችን ማለፋቸው በቀጣይ ከተማ አስተዳደሩንና ሀገራቸውን ወክለው ሲሳተፉ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እገዛ ያደርጋል ተብሎ ታምኖበታል፡፡

በዚህም መሰረት ታዳጊዎች እስከ 16 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ግልብያን ያደርጋሉ፡፡ የቀድሞ ብስክሌተኞች እስከ 20 ኪሎ ሜትር ይጋልባሉ፡፡ አዋቂ የማውን ብስክሌት ጋላቢዎች እስከ 30 ኪሎ ሜትር የሚነዱ ሲሆን ክለቦች ደግሞ 95 ኪሎ ሜትር ሚጋልቡ ይሆናል፡፡

የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሲሳይ ተረፈ፣ ክለቦች በዓመቱ መጀመሪያ የአቋም መለኪያ ውድድር በማድረግ አቋማቸውን ከፈተሹ በኋላ ይህ ቻምፒዮና ትልቁ ውድድራቸው መሆኑን ተናግረዋል። ተዳዳሪዎቹ በተለያዩ ውድድሮችና ካታጎሪዎች ከተማ አስተዳደሩን ወክለው የመሳተፍ እድል እንዳለቸውም ጠቅሰዋል፡፡ ሁሉም ተወዳዳሪዎች በደንብ ዝግጅት አድርገው እየተሳተፉ በመሆኑ ደማቅና ጥሩ ፉክክር እየተደረገበት እንደሆም አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በውድድሩ ጥሩ ውጤትና አፈጻጸም ያላቸው ስፖርተኞች በብሔራዊ ፌዴሬሽን ደረጃ ሀገርን ወክለው እንዲሳተፉ ምልመላ ተደርጎ የሚላክበት ሁኔታም እንዳለም የፅህፈት ቤት ሀላፊው ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም ተወዳዳሪዎች በከታማው ውድድር ተገድበው የሚቀሩ ብቻ ሳይሆን ሀገርን የመወክል እድል ሊያገኙ ይችላሉ። ቻምፒዮናው ስፖርቱ እንዲስፋፋ ሰልጣኞች ውድድር በማግኘት ጠንካራ ተፎካካሪና ውጤታማ እንዲሆኑ በር ይከፍታል፡፡ ፌዴሬሽኑም ስፖርተኞች በጥሩ ስነምግባር ተወዳድረው ውጤታማ እንዲሆኑ እገዛዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ለዚህም ከክለቦች፣ ተወዳዳሪ ስፖርተኞች፣ አሰልጣኞችና ዳኞች ጋር በውድድር ድንብ ዙሪያ ውይይቶችን በማድረግ ከሚገኙ ሃሳቦች ተነስቶ በማጽደቅ ወደ ውድድር ተገብቷል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You