ከተመሠረተች ከ135 ዓመት በላይ የሆናት አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች መናኸሪያ፤ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የአፍሪካ መዲና እና የተለያዩ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መገኛ ነች። ከ90 በላይ ኤምባሲዎችን በማቀፍም በዓለም ላይ ካሉት ጥቂት የዲፕሎማቲክ ማዕከል ከሆኑ ከተሞች ውስጥ ግንባር ቀደሟ ነች።
ይህም ሆኖ ግን በመሀል ከተማዋ ከተሠሩ ዘመናትን የተሻገሩት ቤቶች /መንደሮች/ የሚያድሳቸው ጠፍቶ በእርጅና ምክንያት ጎብጠው፤ ግድግዳዎቻቸው ፈራርሶ፤ ጣራዎቻቸው ወይቦ የከተማዋን ውበት ሆነ የነዋሪዎቹን ሕይወት አስቸጋሪ አድርገውታል።
በእነዚህ ቤቶች ውስጥ በበጋም ሆነ በክረምት መኖር ስቃይ ነው። ቤቶች ከተማዋ ስትቆረቆር ጀምሮ የነበሩ በመሆናቸው የሚያፈርሳቸው አካል ባይኖር በራሳቸው እየፈረሱ ስለመሆናቸው የሚኖሩባት የሚመሰክሩት የአደባባይ እውነት ነው።
አብዛኞቹ ቤቶች ባለአንድ ክፍል በመሆናቸው ለነዋሪዎቹ መኝታም ምግብ ማብሰያም ናቸው። እናትና አባትን ጨምሮ ልጆችም ይህችኑ አንድ ክፍል ይጋራሉ፤ ይህም በራሱ በልጆች አስተዳደግ ላይ የሚኖረው አሉታዊ የሥነልቦና ተጽእኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
በእነዚህ ቤቶች ገበና መደበቅ የሚባል ነገር የለም። ሰዎች የግሌ የሚሉት ነገር የለም። ምግቡም መኝታውም ሌላም ሌላም ነገሩ በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ስለሚከወን ሁሉም ነገር የአደባባይ ሚስጢር ነው። ባልና ሚስት እንኳን የግል ነጻነት የላቸውም።
ሰፈሮቹ ችምችም ብለው በተሠሩ ቤቶች የታጨቀ፤ ከዘመኑ ጋር ያልዘመኑ፤ ከ135 ዓመታት በፊት ከነበሩበት በከፋ ሁንታ ያሉ እና በአሁኑ ወቅት ያለውን የአኗኗር ሁኔታ የማይመጥኑ ናቸው። አብዛኞቹ ቤቶች አንድ መጸዳጃ ቤትን ለሰላሳ፤ ለአርባ የሚጠቀሙ ብዙዎችም መጸዳጃ ቤት የሌላቸውና በየጥጋጥጉ ለመጠቀም የተገደዱ ዜጎች የሚኖሩባቸው ናቸው።
እነዚህ አካባቢዎች የአዲስ አበባን የኋሊት ጉዞ የሚያሳዩ፤ ከተማዋ ተመልካች የሌላት ስለመሆኑ ተጨባጭ መገለጫዎችም ናቸው። ጎዳና ተዳዳሪነት፤ ሴተኛ አዳሪነት፤ ማጅራት መቺነትና የመሳሰሉት ኢ ሞራላዊ እና ወንጀል ነክ ድርጊቶች የሚፈጸምባቸው፤ የቁማር፤ የጫት፤ የሺሻ እና የአረቄ ቤቶች መገኛም ናቸው።
በእነዚህ አካባቢዎች መሸት ሲል በቀላሉ ወጥቶ መግባት አይታሰብም። እነ ዶሮ ማነቂያ፤ እሪ በከንቱና ውቤ በረሃ የመሳሰሉ ሰፈሮች መጠሪያቸው የሚናገረውም ይህንኑ ነው። ፒያሳም ቢሆን ስሙ የደመቀ ቢሆንም በገቢር ያለው እውነታ ግን ስሙን የሚመጥን ገጽታ የተላበሰ አይደለም። አካባቢዎቹ ምንም ዓይነት ዘመናዊነት የማይታይባቸው ኋላቀር አካባቢዎች ከመሆናቸውም በላይ በስመ አራዳ ለዘመናት ድህነት ተጭኗቸው የቆዩ ናቸው።
ስምና ግብር በተራራቀበት በእነዚህ አካባቢዎች ሰዎች በአንዲት ክፍል ውስጥ ቆጥና ምድር ሰርተው፤ መጸዳጃ ቤት ተጋርተው፤ በአንዲት ክፍል አስር፤ አስራ አምስት ሆነው ተደራርበውና ተነባብረው የሚኖሩባቸው የድህነት ጥግ የሚታይባቸው የከተማችን አካል ናቸው።
ይህ አልበቃ ብሎ አካባቢዎቹ በመሠረተ ልማት እጥረት የተጎዱ ናቸው። ለስሙ መሃል አካባቢ ይባል እንጂ የአሌክትሪክ ዝርጋታው እጅግ ኋላቀር ከመሆኑ በላይ እጅግ የተወሳሰበና ለአደጋም የተጋለጠ ነው። በዚህ ላይ ዝናብና የንፋስ ሽውታ ሲያገኘው በቀላሉ የሚበጠስ፤ መብራት በየአጋጣሚው የሚጠፋበት አካባቢ ነው።
የውሃ ማስተለላፊያ መስመሮችና የቆሻሻ ማስወገጃ ትቦዎች የተቀበሩበት ሁኔታ ኋላቀርና የጤና ችግርም የሚያስከትል ነው። አብዛኞቹ ውሃ መስመሮች ከትቦዎች ጋር መሳ ለመሳ የተቀበሩ በመሆናቸው ከመጸዳጃ ቤት የሚወጣው ፍሳሽ ከሚጠጣው ውሃ ጋር እየተደባለቀ ለከፋ የጤና ችግር ሲዳርግ የቆየበት አካባቢ ነው።
አብዛኞቹ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች የተቀበሩት ከከተማዋ ምስረታ ጋር በተያያዘ በመሆኑ ከማርጀታቸውም ባሻገር አሁን ያለውን የሰው ቁጥር የማስተናገድ አቅም የላቸውም። በዚህም ላይ በየጊዜው በሚሰሩ ግንባታዎች አማካኝነት ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎቹ ለብልሸት ስለተዳረጉ በአግባቡ ፍሳሽን የማስወገድ አቅም ተስኗቸዋል። በዚህም ምክንያት አካባቢዎቹ በየጊዜው በሚፈነዱ መጸዳጃ ቤቶች የሚጥለቀለቁና አፍንጫ በሚሰነፍጥ ጠረናቸውም የሚታወቁ ናቸው።
እነዚህ አካባቢዎች ከችግር የተነሳ ሰዎች በግድ ይኑሩባቸው እንጂ በምንም ዓይነት መልኩ ለኑሮ የሚመረጡ አይደሉም። አካባቢዎቹ ከነግሳንግሳቸው አስታዋሽ አጥተው እና የከተማዋ ድህነት ቋሚ ዘካሪ ሆነው ዘመናትን ተሻግረው ዛሬ ላይ ደርሰዋል።
ዛሬ ግን አስተዋይ ዓይኖች ተመልክተዋቸው፤ ቅን ልቦች ዘክረዋቸው የአሮጌው አራዳ ሰፈሮች ስማቸውን የሚመጥን ዘመናዊነት ሊላበሱ ከጫፍ ደርሰዋል። ይህ አካባቢ እንደሌሎቹ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ቀን ሊወጣለት ጥቂት ቀናት ቀርተውታል። እንደ ካሳንቺስ በለውጥ ሊታበስ፤ እንደ እንጦጦ በውበት ሊያሸበርቅ፤ እንደ አንድነት ፓርክ መንፈስን ሊያድስ የንስር ዓይኖች ተመልክተውታል፤ ብርቱ ክንዶች ዳሰውታል።
አሁን ላይ ሙሽራዋ አዲስ አበባ በአዳዲስ ፕሮጀክቶች ብቅ ብላለች። አዲስ አበባ የዓለም የዲፕሎማሲ መዲና፣ የአፍሪካ ዋና ከተማ፣ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ እንቅስቃሴ መናኸሪያ እንደ መሆኗ ይህን የሚመጥን ልማት እየተከወነላት ይገኛል።
“የኮሊደር ልማት” በሚል ስያሜ የተጀመረው ልማት በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የተሠሩ ‹‹የሚያማምሩ የልማት ሥራዎችን ማገጣጠም›› ወጥ የሆነ ገጽታ እንዲላበሱ ማስቻል ነው። እንደ ፒያሳ የመሳሰሉ በእርጅና ምክንያት ጎብጠው እየፈረሱ ያሉ የከተማዋን አካባቢዎች መልሶ ማልማት ነው።
ባለፈው ዓመት ግንቦት ጨረታው ወጥቶ የተጠናው የኮሪደር ልማቱ ወደ ትግበራ ከተገባም ቀናት ተቆጥረዋል። ልማቱ ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ፣ ከአራት ኪሎ እስከ ቦሌ ድልድይ፣ ከቦሌ ድልድይ በመገናኛ ወደ ሲኤምሲ፣ ከቦሌ ተርሚናል ወደ ጎሮ፣ ከሜክሲኮ ወደ ወሎ ሠፈር፣ እንዲሁም ከእንግሊዝ ኤምባሲ ወደ አራት ኪሎ የሚወስዱ ኮሪደሮችን የሚመለከት ነው። ሥራውም በስድስት ወራት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
እነዚህ ሥራዎች ሲከናወኑም ከተለያዩ ቦታዎች ለሚነሱ ግለሰቦች ምትክ ቦታ እንደሚሰጥ ፤ ቀደም ሲል በቀበሌ ቤት ውስጥ ለሚኖሩ ነዋሪዎች ከቦታው በመነሳታቸው ምክንያት ለችግር እንዳይጋለጡ ምትክ የቀበሌ ቤት ወይም ኮንዶሚኒየም እንደ ምርጫቸው እንደሚሰጣቸው፤ በተመሳሳይም የግል ይዞታ የነበራቸው ነዋሪዎች ምትክ ቦታና ካሳ እንደሚያገኙ መስተዳድሩ አስታውቋል። ይህም ተግባራዊ እየሆነ ነው።
በአጠቃላይ በአምስት አቅጣጫዎች እየተከናወነ ያለው ኮሪደር ልማት ከተማዋን ከመሠረቱ የሚቀይር ነው። ከሁሉም በላይ ሥራውን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማጠናቀቅ የሚደረገው ርብርብ አግራሞትን የሚፈጥር ሆኗል። ከዚህ በመነሳትም የኮሪደር ልማቱ በታሰበለት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ መገመት አያዳግትም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ውብና በኢትዮጵያ ልክ የሆነች ዋና ከተማን ለመፍጠር ያለመ ነው ሲሉ መደመጣቸውም አሁን ላይ እየሆነ ካለው ተጨባጭ እውነታ አንጻር ብዙም ለእሰጣ ገባ የሚጋብዝ አይደለም።
ይህም ሆኖ ግን አንዳንዶቻችን ባለማወቅ ሌሎች አውቀው ይህንን ለከተማዋ ትንሳኤ ሊሆን የሚችልን ልማት በአደባባይ ባልተገባ መንገድና ባልተገራ ቋንቋ ሲቃወሙ ይሰማል። በተለይም በሆነው ባልሆነው በተቃውሞ ቋንቋ እና መንፈስ አደባባይ ለመሙላት የሚሮጡ ግለሰቦች እና ቡድኖች ልማቱን መቃወም ከጀመሩ አረፋፍደዋል።
እነዚህ ተቃውሟቸውን ቅርስ ፈረሰ በሚል የጀመሩት ተቃውሞ ሰሚ ሲያጣ፤ ልማቱን በራሱ ወደ ማጥላላት፤ የልማቱን ባለ ራዕዮች ወደ ማጥላላት ሄደዋል። ሰሚ አላገኙም እንጂ ከዚህም አልፈው ተነስ ፤ ታጠቅ ወደሚል የጥፋት ዜማ ከገቡ ሰነባብተዋል።
እርግጥ ነው በአዲስ አበባ ከመቶ ዓመት በላይ ያስቆጠሩና የቱሪዝም መስህብ ሊሆኑ የሚችሉ ቅርሶች ባለቤት ነች። ነገር ግን ያረጀ እና ያፈጀ ቤት ሁሉ ቅርስ ነው ማለት አንድም የቅርስን ትርጉም አለማወቅ አሊያም ደግሞ ድህነትን ታቅፎ የመኖር አባዜ/እርግማን ነው።
ለመልሶ ግንባታ /እድሳት የተመረጡ አካባቢዎች ከዚህ በላይ ጎብጠው ሊቆሙ የሚችሉ አይደሉም፤ ነዋሪዎቻቸውም ከዚህ በላይ በዚህ አስቸጋሪ ሕይወት ውስጥ መቀጠል የሚችል ሰብዓዊ ስብዕና ሊኖራቸው አይችልም። አሁን ባለችው ኢትዮጵያም ከዚህ በላይ በሕይወት ሊፈተኑ አይገባም።
ይህ አካባቢ አይፍረስ፤ ሰዎች በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ይኑሩ ብሎ መፍረድ ከጭካኔ በላይ ነው። አንዳንዶችም ይህን ፍረደ ገምድል ውሳኔ የሚሰጡት በአማረ ቪላ ውስጥ ሆነው ነው። አለፍ ሲልም በውጭ ሀገራት ዘመናዊ አውቶሞቢል እያሽከረከሩና በቅንጡ ቤት ውስጥ እየኖሩ ነው።
ችግሩን በሩቅ ሳይሆን አብሮ በመኖር ጭምር የሚያውቀው የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቼ በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ አይኖሩም በማለት አዲስ አበባንም ለማደስ፤ የዜጎቹንም ሕይወት ለመቀየር ቆርጦ የተነሳበት መንገድ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው። እኛ ነዋሪዎቿም በብዙ አድናቆት የቸርነው ነው።
እኛ ብቻ ሳንሆን በልማቱ ተነስተው ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሄዱ ነዋሪዎች ‹‹ቀን ወጣልን›› ሲሉ ተደምጠዋል። ብዙዎቹ ነዋሪዎች የቀድሞው ኑሯቸውን ከጨለማ ጋር አመሳስለው በምሬት ሲናገሩ መስማት፤ ያሳለፉትን የስቃይ ኑሮ ለመስማት ፈቃደኝ ለሆነ ሰው የልብ ስብራት የሚፈጥር ነው።
በአንዲት ክፍል ለዘመናት ተጨቁነው የኖሩት እነዚህ ምስኪን ዜጎች ዛሬ ገበናቸው ተከቷል። የጋራ መኖሪያ ቤትም ሆነ ተገጣጣሚ ቤቶችን የመረጡ ዜጎች እንደ ሰው ለመተኛት፤ በዘመናዊ ሻወር ለመታጠብ፤ በሁለት በሶስት ክፍል ውስጥ ለመምነሽነሽ ፤ በንጹህ መጻዳጃ ለመጠቀም በቅተዋል።
የኮሪደር ልማቱ ሰፊ አካባቢን የሚሸፍን በመሆኑ ልማቱ ገና የሚቀጥል ነው። የተጀመረው ልማትን በፍትሃዊነት ለዜጎች የማዳረስ ጥረት እስከ መጨረሻው ሊቀጥል፤ በልማቱ የሚነሱ ዜጎች ያልተገባ እንግልት እንዳያጋጥማቸው ሥራዎች በጠንካራ ዲሲፕሊን ሊመሩ ይገባል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እንዳሉት ሌብነትና ኢፍትሃዊነት ካለ ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ዋጋ ቢስ ስለሚሆን ፤ ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ሌብነትንና ኢፍትሃዊነትን መዋጋት ፕሮጀክቱን የሚያስተባብሩ ኃላፊዎች ዋነኛ ትኩረት ሊሆን ይገባል።
አሊሴሮ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም