ኢትዮጵያ በማዕድን ሀብት የታደለች ታድላለች። የማዕድን ሀብቶቹም በሀገሪቷ በሁሉም አካባቢዎች የተለያዩ ማዕድናት በስፋት እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የወርቅ፣ የፖታሽ፣ የታንታለም፣ የሊትየም፣ የከበሩ ማዕድናት፣ የክሮማይት፣ የፎስፌት፣ የኒኬል፣ የጨው፣ የኢንዱስትሪ፣ የኮንስትራክሽን፣ የጂኦተርማል ኃይል፣ ለኢነርጂ ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት እና እጅግ አስፈላጊ የሚባሉ የማዕድን አይነቶች በሀገሪቱ እንደሚገኙ ከተለያዩ መረጃዎች መረዳት ይቻላል።
ሀገሪቱ እነዚህ ሁሉ የማዕድን ሀብት ይኑራት እንጂ ማዕድናቱን በጥናት በመለየትና በማልማት ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ በኩል ብዙም አልሠራችበትም። የማዕድን ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፡-እስካሁንም ሀገሪቱ ያላት የማዕድን ሀብት በዓይነትም ሆነ ክምችት መጠን በትክክል አይታወቅም፤ እነዚህ የማዕድን ሀብቶች ለማወቅ ጥናቶች በየጊዜው እየተካሄዱ ናቸው።
እስካሁን በተደረገው የአሰሳ ጥናት የአንዳንድ ማዕድናት የክምችት መጠን ተለይቶ ታውቋል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ወርቅ ሲሆን፣ በቅርቡ የማዕድን ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መሠረት በሀገሪቱ ከ517 ቶን በላይ የወርቅ ክምችት መኖሩ ተረጋግጧል። ከአንድ ቢሊዮን ቶን በላይ የሚገመት የብረትና ብረት ነክ የማዕድናት ክምችትም አላት። የድንጋይ ከሰልን ብንመለክትም ከግማሽ ቢሊዮን ቶን በላይ የድንጋይ ከሰል ክምችት በሀገሪቱ ይገኛል።
ከዓለም ግዙፉ ያልለማ የፖታሽ ክምችት ካላቸው ሀገራት አንዷ መሆኗንም መረጃዎች ያመለክታሉ። በደናክል ተፋሰስ ውስጥ ከ26 ቢሊዮን ቶን በላይ የፖታሽ ሃብት ያላት ሲሆን፤ 540 ሚሊዮን ቶን የሚገመት የፖታሽ ክምችት አላት። የጂኦተርማል አቅሟም እስከ 10ሺ ሜጋ ዋት ይደርሳል ተብሎ ይገመታል።
በሀገሪቱ ይህን የመሰለ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት እና የመልማት አቅም ያላት ቢሆንም፣ ለማዕድን ዘርፉ ትኩረት ሳይሰጥ በመቆየቱ ምክንያት ሀብቶቹን አልምቶ መጠቀም አልተቻለም። አሁን ላይ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ሀገሪቷ ያላትን የማዕድን ሀብት ክምችት አሰሳ በማድረግ የማዕድን ሀብቶቹ ለምተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።
የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ኢትዮጵያ የማዕድን ሀብቷን በማልማት የመጠቀም ሰፊ ዕድል እንዳላት ይገልጻሉ። ለእዚህ የመጀመሪያው ሥራ መሆን ያለበት የማዕድን ሀብትን ለይቶ ማወቅ መሆኑን ያመለክታሉ። የማዕድን ሀብቱ በየትኛው አካባቢ እንደሚገኝ፣ በምን ያህል መጠን ሊለማ እንደሚችል ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊሠራበት ይገባል ሲሉ ተናግረው፣ በመቀጠልም የማዕድን ሀብቱ የሚለማበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ይህ ማድረግ ያስችል ዘንድ ባለፉት ዓመታት የማዕድን ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማት ምሰሶዎች ተብለው ከተለዩ አምስት ዘርፎች አንዱ እንዲሆን ተደርጓል ሲሉም ጠቅሰው፣ ዘርፉ ለኢኮኖሚ ልማት አስተዋፅዖ የሚያበረክትና ለሀብት ፈጠራ ወሳኝ ተብሎ መለየቱንም አመልክተዋል።
የማዕድን ሀብቱ እንደ ሌሎች ዘርፎች እምቅ ሀብቶች ሀብት አመንጪ እንዲሆን በተለየ መልኩ የፖሊሲ ትኩረት ማግኘቱንም ሚኒስትር ዴኤታው ይገልጻሉ። ማዕድናት ከመድኃኒት ጀምሮ የተለያዩ ቁሳቁስ የሚመረትባቸው ግብዓቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በቂ ትኩረት ተሰጥቷቸው ቢሠራባቸው የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ ከመሆን ባሻገር፣ ለግብርና፣ ለማኒፋክቸሪንግ እና ለሌሎች ዘርፎች ግብዓት በመሆን ለሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት በብዙ መልኩ ሊጠቅሙ እንደሚችሉም አስታውቀዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳስታወቁት፤ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት መነሻ በማድረግ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። እስካሁን በማዕድን ዘርፉ ከተሠሩ ሥራዎች በሀገሪቱ ያሉ የማዕድናት መረጃዎች በማጥራት፣ በአነስተኛ፣ በመካከለኛ እና በከፍተኛ ደረጃ ዘርፉን ለማልማት ዝግጅቶች እየተደረጉ ናቸው። በአስር ዓመቱ እና በአምስት ዓመቱ የልማት እቅድ ላይ በተመለከተው መሠረት ዘርፉ ለአገር የሚያበረክተውን ሚና በሚለይ መልኩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚውሉ ማዕድናትን ድንጋይና አሸዋን ጨምሮ፣ ወርቅ፣ ኒኬል፣ ኮፐር፣ ማንጋኒዝ፣ ፖታሽ ፣የጌጣጌጥ ማዕድናት፣ ኢንዱስትሪ ማዕድናት፣ ታንታለም፣ ብረት እና ብረት ነክ ማዕድናት፣ በዘመኑ በጣም ተፈላጊ የሆኑ ማዕድናት እና የሌሎች ማዕድናት በተፈጥሮ ያላት ሀገር ናት። ለኃይል ማመንጨት በእጅጉ የሚፈለገው የድንጋይ ከሰል ክምችትም በስፋት ያላት ሲሆን፤ የድንጋይ ከሰሉን በማልማትም ለሲሚንቶ እና ለብረት ኢንዱስትሪዎች የኃይል ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
በዓለም ላይ ሰፊ የጂኦተርማል ሀብት አላቸው ከሚባሉት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ተጠቃሽ መሆኗን አመልክተው፣ ኢትዮጵያን አቋርጦ የሚያልፈው ስምጥ ሸለቆ ያበረከተው አንድ አዲስ የተለየ ፀጋ የጂኦተርማል ኃይል ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
በጂኦተርማል ኃይል ልማት 11 የሚጠጉ ኩባንያዎች ገብተው እየሠሩ ይገኛሉ ሲሉም ጠቅሰው፣ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ሦስት የሚሆኑት ኩባንያዎች ወደ ልማት ተሸጋግረው የኃይል አቅርቦቱን ለማከናወን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በመነጋገር ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
ከእነዚህ በተጨማሪም በሀገሪቱ የኢነርጂ ማዕድን የሚባሉት የተፈጥሮ ጋዝ እና ነዳጅ ሀብቶች እንዳሉም ይገልጻሉ። እነዚህን ሀብቶች በማልማት ረገድም በፍለጋ ሥራ ላይ የተሠማሩ እና ፍለጋቸውን እያጠናቀቁ ያሉ ኩባንያዎችም መኖራቸውን አስታውቀዋል፤ በወርቅ ማዕድን ልማትም የተሠማሩ በርካታ ባሕላዊና ከፍተኛ የወርቅ አምራች ኩባንያዎች እንዳሉ አመላክተዋል ።
‹‹የማዕድን ፍለጋ ሥራ ረጅም ዓመታት ይወስዳል›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ባለፉት 15 ዓመታት በተደረጉት የአሰሳና የፍለጋ ሥራዎች ከ517 ቶን በላይ የወርቅ ሀብት ክምችት መኖሩ ተረጋግጧል ብለዋል። የወርቅ ሃብቶቹም በሚቀጥሉት 20 እና 25 ዓመታት እንደሚለሙ ጠቅሰው፤ ሀብቶቹ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች አንደሚገኙ አስታውቀዋል።
የወርቅ ማዕድን ልማት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ልማት አዲስ ዕድል ይዞ የሚመጣ ነው ሲሉ የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በባሕላዊ መንገድ ሲመረት የኖረው የወርቅ ምርት አሁን በተለያዩ ማሽኖች እገዛ ወደ ማምረት እየተገባ መሆኑን አስታውቀዋል፤ ይህን ተከትሎም ምርቱን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ መቻሉንም ይገልጻሉ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የወርቅ ልማቱን በኩባንያ ደረጃ ለማካሄድ አንድ ኩባንያ በግንባታ ሂደት ላይ መሆኑ ይታወቃል። በክልሉ ኩርሙክ አካባቢ እየተገነባ ከሚገኘው ከዚህ የወርቅ ማውጫ ፋብሪካ በተጨማሪ፣ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት አራት የወርቅ ማውጫ ፋብሪካዎች እንደሚገነቡም ይጠቅሳሉ። እነዚህ ፋብሪካዎችም በወለጋ፣ በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ እና ትግራይ ክልሎች ይገነባሉ ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፤ የማዕድን ሀብት የመጀመሪያ ሥራ የሚባለው የማዕድን ፍለጋ ነው። የማዕድን ፍለጋ ሥራው ከሦስት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት ሊቆይ ይቻላል። ይህም ከማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት አንጻር የሚታይ ዓለም አቀፍ አሠራርን የተከተለ ነው።
በሀገሪቱ የማዕድን ልማት ሥራው እስካሁን በተበጣጠሰ መልኩም እየተሠራ ቆይቷል። ከለውጡ በፊት የማዕድን ሀብቶችን የመለየት ሥራ በተለያዩ ኩባንያዎች ሲሠራ ነበር። አሁን ላይ ኩባንያዎቹ የፍለጋ ሥራቸውን ጨርሰው ወደ ልማት እየተሸጋገሩ ይገኛሉ።
በአሁኑ ወቅትም በፌዴራልና በክልል መንግሥት ቅንጅት የፍለጋ ጊዜያቸውን ጨርሰው ወደ ልማት ምዕራፍ የተሸጋገሩ የወርቅ ኩባንያዎችን ወደ ልማት ለማስገባት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።
አቶ ሚሊዮን እንዳብራሩት፤ በማዕድን ዘርፉ በ2016 በጀት ዓመት ባለፉት ስምንት ወራት የተለያዩ ማዕድናት ለውጭ ገበያ ተልከዋል፤ ወርቅ ከሁለት ሺህ 673 ኪሎ ግራም በላይ፣ ታንታለም ከ66 ቶን በላይ፣ ሊቲየም ኦር ከ11 ሺህ 176 ቶን በላይ ለውጭ ገበያ ቀርበዋል። በተጨማሪም ከ99 ሺህ 021 በላይ ቶን የጌጣጌጥ እንዲሁም 29 ሺህ 281 ቶን በላይ የኢንዱስትሪ ማዕድናት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ተችሏል።
በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስምንት ወራት ከማዕድን ዘርፍ 252 ነጥብ 15 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉንም ጠቅሰው፤ ገቢው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ ያሳየ መሆኑንም ጠቁመዋል።
‹‹አሁን ላይ በማዕድናት ፍለጋ ሥራ ላይ በስፋት እየተሠራ ነው›› መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል፤ ዘርፉ በጥንቃቄ መመራት እንዳለበት ተናግረው፣ ኩባንያዎችም ሆኑ ኢንቨስትመንቱ ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ አካላት ሲመለመሉ በዘርፉ ላይ ያላቸውን ልምድ እንዲታይ እየተደረገ መሆኑን ይገልጻሉ።
‹‹ይህ እንዲሆን ያስፈለገበት ምክንያት የማዕድኑ ዘርፍ እንደ ሌላው ዘርፍ የተወሰነ ሥራ ብቻ ተሠርቶበት ወደ ልማት የሚገባበት ዘርፍ ስላልሆነ የፍለጋ ሥራው ከሦስት ዓመት እስከ አስር ዓመት ከፍ ሲልም እስከ 15 ዓመት ከፍተኛ ፋይናንስ መደቦ መሥራትን የሚጠይቅ ስለሆነ ነው›› ሲሉ አብራርተዋል። ‹‹ይሄ ደግሞ በአጭር ጊዜ ፈጥኖ ሊደርስበት የማይችልበት ሁኔታ ስለሚኖር ኢንቨስትመንቱ ላይ መሠማራት የሚፈልጉት ባለሀብቶች ያላቸው የመነሻ ፋይናንስ፣ ቴክኒካል እና የሰው ኃይል አቅም ጭምር የመለየትና ሥራ ይሠራል›› ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳብራሩት፤ በሀገሪቱ እስካሁን ድረስ በዓለም ላይ ቁጥር አንድ ከሚባሉት መካከል አንዱ የሆነ ኩባንያ ጀምሮ ትላልቅ ኩባንያዎች በማዕድን በፍለጋ ላይ ተሠማርተው ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ የፍለጋ ሥራቸውን አጠናቅቀው ወደ ምርት ተሸጋግረዋል። እስካሁን የተሠራው ሥራ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤ እነዚህ ኩባንያዎች ወደ ውጤታማነት ማሸጋገር ይገባል።
ሀገሪቷ ከማዕድን ዘርፍ ባላት አቅም ልክ ተጠቃሚ እንድትሆን ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ የማዕድን ዘርፍ ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር እንደሚያስችልም ያመላክታሉ። በማዕድን ዘርፍ እስከ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዜጎች በቀጥታ በዘርፉ ላይ ተሠማርተው እንደሚገኙ አስታውቀዋል። በተዘዋዋሪ ደግሞ ከ7 ሚሊዮን በላይ የሆኑ ዜጎች ከዘርፉ ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ አመላክተዋል።
እንደ አቶ ሚሊዮን ማብራሪያ፤ የዘርፉ ተግዳሮት የሆነውን ሕገወጥነት ለመከላከል ከፌዴራል እስከ ክልል ያለው ተቋማት ተቀናጅቶ እንዲሠሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚመራ ሀገራዊ የማዕድን ካውንስል ተቋቁሞ ወደ ተግባር ገብቶ እየሠራ ይገኛል። ካውንስሉ የክልል ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ሚኒስትሮችም የተካተቱበት ስለሆነ ከክልልና ከፌዴራል ያሉ አካላት በቅንጅት ሥራዎችን የሚሠሩበት ነው።
የማዕድን ካውንስሉ ቅንጅታዊ አሠራሮችን መከተል በማዕድን ዘርፍ ውጤት ያመጣል ተብሎ ይታሰባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዘርፉ ተንሰራፍቶ ያለውን የኮንትሮባንድ ንግድና ሕገወጥነት ለመከላከልም የክልልና የፌዴራል የፀጥታ መዋቅሩ ከፖለቲካ አመራሩ ጋር ተቀናጅቶ የሚሠራበትን ዕድል ይፈጥራል ሲሉ አብራርተዋል።
ዘርፉን ለመምራት እንዲቻል የተለያዩ ሥራዎች በቅንጅት መሠራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፣ በዚህ ረገድ የሚሠሩ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ መንግሥት ተገቢውን እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ጠቁመዋል። እነዚህ ተጠናክረው ወደ ውጤት እየተቀየሩ ሲመጡ ለዘርፉ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ይሄዳል ተብሎ ይታሰባል ሲሉ ያስረዳሉ።
‹‹ሕገወጥ እና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ የሀገርን ጥቅም ብቻ አይደለም የሚያሳጡት፤ ለሀገራዊ ሠላምና መረጋጋት ጭምር ከፍተኛ ጠንቅ ናቸው›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የማዕድን ካውንስሉ መቋቋም ሀብት እንዳይመዘበር፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር እንዳይካሄድ እና ሠላምና ደኅንነት እንዲኖር ያደርጋል ይላሉ።
ከዚህ በተጨማሪም በሚቀጥሉት ዓመታት ወርቅ ለማውጣት ለሚገነቡት ፋብሪካዎች የሚፈልጉት መሠረት ልማት እና ከውጭ የሚገቡ ትላልቅ ማሽኖች ለማስመጣት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም አስታውቀዋል። ይህም በተለያዩ ተቋማት ላይ ሲያጋጥሙ የቆዩ ውጣ ውረዶችን በማስቀረት ሥራዎች በተቀናጀ መልኩ እንዲፈጸሙ ያስችላል ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ለዚህም ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ በአብነት ይጠቅሳሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ የሀገሪቱ ግዙፍ ፋብሪካ ነው። ይህ ፋብሪካ እውን እንዲሆን ፋብሪካው ሲገነባ ጀምሮ ተቀናጅቶ ለመሥራት ጥረት ተደርጓል። አሁን ፋብሪካው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የሥራ ዕድልና አጠቃላይ ኢኮኖሚ ሊያንቀሳቅስ የሚችል አንድ ትልቅ አቅም ፈጥሯል። በቀጣይ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገነቡ ፋብሪካዎችን የመሠረተ ልማት ችግር እንዳያጋጥም ቅንጅታዊ አሠራር በመዘርጋት ከወዲሁ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን አስገንዘበዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም