በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂና በአዲስ የፈጠራ ሥራ መታገዝ ግድ ሆኗል። ያለ ቴክኖሎጂ ያለሙበት መድረስ ከባድ እየሆነ መጥቷል። ከእነዚህ ዘመን አፈራሽ የቴክኖሎጂ ዘርፎች መካከል አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቀዳሚውን ስፍራ እየያዘ መጥቷል።
ያደጉትም ሆኑ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ቴክኖሎጂው በሚያስፈልጋቸው ዘርፎች እንደየሁኔታው እየተጠቀሙበት ችግሮቻቸውን እየፈቱ ይገኛሉ። ኢትዮጵያም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች። የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብርና፣ የጤና፣ የደህንነት እና መሰል ዘርፎችን አቅም ለማሳደግ እየተሠራ ነው።
ወጣት ሳሙኤል ዘካሪያስ ይባላል። ውልደትና እድገቱ በአሁኑ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን ነው። የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ሳሙኤል ከልጅነቱ ጀምሮ ለቴክኖሎጂና ለፈጠራ ሥራ ልዩ ተሰጥኦ አለው። ከአካባቢው ከሚያገኛቸው የወዳደቁ ነገሮች የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን መሥራት የጀመረው ገና በልጅነቱ ነበር። ወደ ፈጠራ ሥራ እንዲገባ ምክንያት የሆነው ነገሮች እንዴት እንደሚሠሩ ለማወቅ ባለው ከፍተኛ ጉጉት እንደሆነ የሚናገረው ሳሙኤል፤ በአንድ ወቅት በትውልድ አካባቢያቸው በመንገድ ግንባታ ሥራ የተሰመሩ የውጭ ሀገር ዜጎች የሚሰሩትን ሲመለከት ስለቴክኖሎጂ ደጋግሞ በማሰብ ጉዳዩ ውስጡ እንደሰረፀ ይናገራል።
በወቅቱ የውጭ ሀገር ዜጎች የሚሰሩትን “በየቀኑ እየሄድኩ እመለከት ነበር” የሚለው ሳሙኤል፤ ነገር ግን ከባለሙያዎቹ መካከል አንድ ቻይናዊ ማሽኖችን በምን መልኩ እንደሚጠቀሙ ከሌሎች የዕድሜ እኩዮቹ በተለየ መልኩ በትኩረት ስለሚከታተል ለእርሱ ጥሩ አመለካከት እንዳልነበረው እና እንደማይወደው ያስታውሳል።
አንድ ቀን ይህ ቻይናዊ የኮንስትራክሽን ማሽኑን ሞተር ሳያጠፈ አቁሞ ከእንግዶች ጋር እያወራ በነበረበት ወቅት፤ ሳሙኤል ማሽኑን ለማሽከርከር ወጣ። በዚህ ምክንያት ደግም ወደዚያ አካባቢ እንዳይቀርብ በመከልከሉ ‹‹ማሽኑ እራሴ ለምን አልሰራውም።›› በሚል ተነሳሽነት ወደ ፈጠራ ሥራ እንደገባ ያስረዳል።
በመጀመሪያ የፈጠራ ሥራው አነስተኛ አፈር ማንሻ ኤክስካቫተር የሠራው ሳሙኤል፤ በመቀጠልም በጤና፣ በግብርና እና በወታደራዊ ቁሳቁሶች ላይ ትኩረቱን በማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት ችሏል። በዋናነት የፈጠራ ሥራዎቹ ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውሉ መሳሪያዎችን ማምረት ላይ እንደሚያተኩር የሚናገረው ሳሙኤል፤ የእዚህ ምክንያትም ሀገሩ ኢትዮጵያ በማንም የማትዳፈር ኃያል ሀገረ ሆነ መቀጠልን ህልሙ መሆኑን ያስረዳል።
የ11ኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት #ETR S1KM የተባለ ሮኬት የሠራው ሳሙኤል፤ አንድ ኪሎ ሜትር ድረስ የመወነጨፍ አቅም ያለው መሆኑንና፤ ሮኬቱን የሚሸከም መኪና አብረው መሠራቱን ይናገራል። በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት የገንዘብ ድጋፍና ትብብር የተሰራችው ሮኬት በተሳካ መልኩ ሙከራ ተደርጎባት እንደነበር ይናገራል።
ይህንን ሥራ ለመሥራት በተጨማሪነት ምን እንዳነሳሳው ወጣቱ ሲናገር፤ ኢትዮጵያ ከሸማችነት ወደ አምራችነት በምታደርገው ጉዞ ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት ያምናል። በዋነኝነት ደግሞ ኢትዮጵያ ከላት አነስተኛ የውጭ ምንዛሬ አንፃር ለወታደራዊ መሳሪያ ግዥ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት በማለም እንደሆነ ይገልፃል።
ሌላኛው ጉዳይ በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራትና የሥራ ዕድል እንዲያገኝ በማሰብ ወደዚህ ሥራ እንደገባ የሚገልጸው ወጣት ሳሙኤል፤ ገና ከጅምር ባለው ሥራ ለነገ ትልቅ ህልም በማለም ሥራውን አጠናክሮ ስለመቀጠሉ ይናገራል።
ለሀገር ደህንነት ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ ነው የሚለው ወጣቱ፤ ኢትዮጵያ ብዙ ዓይነት የጦር መሳሪያዎችን ከራሺያ፣ ከቱርክ፣ ከቻይና፣ ከአሜሪካ፤ ከእስራኤል በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባ መሆኑን በማስታወስ፤ ስለዚህ ይህንን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት ከፍ ሲልም በረዥም ጊዜ ሂደት የጦር መሳሪያ ወደ ወጭ ለመላክ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን ለማሳደግ፤ እንዲሁም የሀገር ደህንነትን በራስ አቅም ለማስጠበቅ ትልቅ ህልም ይዞ የምርምር ሥራዎቹን እንደሚሰራ ይናገራል።
የመጀመሪያ ፕሮጀክቶቹን የሠራቸው ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ሲሆን፤ የወላይታ ዞን አስተዳደር ድጋፍና ክትትል በማድረግ ለተሠሩ ሥራዎችም የምስክር ወረቀቶች የድጋፍ ደብዳቤ የተሰጠው መሆኑ ይበልጥ እንዳበረታታው ተናግሯል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው የወላይታ ዩኒቨርሲቲ፣ የዞኑና የክልሉ መንግሥት ለሥራው አጋርነት በማሳየት እንደደገፉት እና ይህ ድጋፋቸውም ለውጤታማነቱ ትልቅ ሚና እንደነበርው ያስረዳል።
በቅርቡ ኢትዮጵያ BM 21 የተሰኘ አዲስ ሮኬት የሠራው ወጣት ሳሙኤል፤ ስለዚህ ሥራው ሲናገር፤ ከስድስት እስከ አስር ኪሎ ሜትር ማስወንጨፍ የሚችል የራሱ ማዘዣ ሲስተም ቦርድ ያለው 330 ዲግሪ እየዞረ የተሰጠውን ተልዕኮ መወጣት የሚችል በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚታገዝ አስተማማኝነቱ የማያጠራጥር እንደሆነ ይናገራል።
በቅርቡ በሠራው ሥራ ደግሞ በወላይታ ሶዶ ከተማ የሚገኙ ሞሀበና ቻይና ጋራዥ የተሰኙ የግል ድርጅቶች ከፍተኛ ድጋፍ እንዳደረጉለት ይናገራል። ሃሳብ ያለው ሰው ያንን ወደ ተግባር ለመለወጥ ሲያስብ በሃሳብ፣ በገንዘብ ከጎን የሚቆሙ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች መኖር ወሳኝ ነው የሚለው ሳሙኤል፤ ለእሱም ውጤታማነት የእነዚህ ግለሰቦች ድጋፍ ትልቅ ብርታት እንደሆነው ያስረዳል።
ከሮቦቲክስ፣ ከኮዲንግ እንዲሁም ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ጋር በተገናኘ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ በሚገኘው በኢትዮጵያ መረጃ መረብ ደህንነት፤ በሮቦቲክስና በኢንዱስትሪያል አውቶሜሽን በኤይሮ ስፔስ ዘርፍ ተሳትፎ እያደረገ የሚገኘው ወጣት ሳሙኤል፤ በተቋሙ የተለያዩ ሥራዎች እየሠረ ቆይቷል።
ከተቋሙ ጋር አሁንም በአጋርነት እየሠራ እንደሆነ የሚገልጸው ሳሙኤል፤ የተለያዩ ስልጠናዎችን እየወሰደ እንደሆነ እና እያከናወነ ለሚገኘው የፈጠራ ሥራም የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ድጋፍ እንዳገኘ እንዲሁም ተቋሙ ሁልጊዜም ከጎኑ የማይለይ በመሆኑ ለተቋሙ አመራሮች ያለው ምስጋና የላቀ እንደሆነ ይገልጻል።
ስለሚሰራቸው ወታደራዊ ምርቶቹ አጠቃላይ እውነታ ወጣት ሳሙኤል ሲናገር፤ የወታደራዊ ቁሶቹ ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ጋር የተገናኙ፣ የወደፊት ጥቅማቸው እጅግ የላቀ የሰው ልጅ መወጣት የማይችላቸውን ሥራዎች መሥራት የሚችሉ ዓለም እየሄደበት ባለው የቴክኖሎጂ ልቀት የሚሰሩ በመሆኑ እንደ ሀገር ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ጥቅሟን ማስጠበቅ እንድትችል አቅም የሚሆናት እንደሆነ ይናገራል።
ወጣት ሳሙኤል፤ እነዚህ በራስ አቅም የሚሰሩ ሥራዎች ለሀገር ያላቸው ጠቀሜታ ላቅ ያለ በመሆኑ የመንግሥትም ሆነ የግል ድርጅቶች ቴክኖሎጂን መሠራት አድርገው ለሚነሱ ወጣቶች በሁሉም አቅጣጫ ድጋፍ በማድረግ ሀገሪቱ ከድህነት ለመውጣት የምታደርገው ጥረት ሊደግፉ እንደሚገባ ያስረዳል።
ኢትዮጵያ በራሷ አቅም በምታመርታቸው የጦር መሳሪያ ምርቶች ደህንነቷን መጠበቅ መቻል አለባት የሚለው ወጣት ሳሙኤል፤ ይህ ካልሆነ በዙሪያዋ ብዙ ጠላቶች በመኖራቸው ከምንም ነገር በላይ ደግሞ የሀገር ሉዓላዊነት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ በመሆኑ ዘርፉ የሚመለከተው የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ለፈጠራ ሥራዎቹ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል።
በኢትዮጵያ የተመረተ የሚል ምልክት ያለባቸው የወታደራዊ ምርቶች ለዓለም ገበያ የማቅረብ ራዕይ አለኝ የሚለው ወጣት ሳሙኤል፤ ከዚህ በተጨማሪ በኤሮስፔስ ዘርፉ ላይ የራሱን ድርሻ በመወጣት ለሀገሩ ሁልጊዜ የሚነገር ታሪክ ለማኖር ውጥን እንዳለው ይናገራል።
መንግሥት በየአካባቢው እንደ እርሱ ዓይነት የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸው ወጣቶች ሥራቸውን ማጎልበትና ማሳደግ የሚችሉባቸውን የፈጠራና የቴክኖሎጂ ማዕከላት ቢፈጥሩ የተሻለ ሥራ መሥራት እንደሚቻል እና የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራ በይበልጥ ድጋፍና ክትትል የሚያገኝበት መንገድ ቢኖር መልካም ነው ይላል።
የልጅነት ህልሙን ለመኖርና ሥራውን ለመሥራት ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ከሚያጋጥሙት ተግዳሮቶች አንዱ ከአንዳንድ ግለሰቦች የሚሰጥ አሉታዊ አስተያየት ነው የሚለው ወጣት ሳሙኤል፤ በተለይም “ሚሳኤል እሠራለሁ ብለህ አትልፋ፤ የጦር መሳሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት የማይታሰብ ነው” የሚሉ ሰዎችን አስተያየት ለመስማት ጆሮ እንዳልሰጠ ይናገራል።
“ሁልጊዜ ችግሮች መልካም አጋጣሚ ይዘው ይመጣሉ ብዬ አምናለሁ” የሚለው ሳሙኤል፤ ሰው የራሱን አስተያየት ይሰጣል፤ መርጦ መውሰድ ደግሞ የግለሰቡ ኃላፊነት ነው። የትኛውም አሉታዊ የሰዎች ሃሳብ ደግሞ ትክክለኛ ግብ አስቀምጦ የተነሳን ዓላማ ያለው ሰው ከመንገድ ማስቀረት አይችልም ይላል።
በተደጋጋሚ “ለምን ደቦ የሚተኩስ ማሽን አትሰራም?” የሚል የሰዎች አስተያየት እንደሚደርሰው የሚናገረው ወጣት ሳሙኤል፤ እርሱ ግን “እኔ በሀገር ደህንነት ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ልሥራ ሌላው ደግሞ ደቦ የሚተኩስ ማሽን ይሰራ” የሚል ምላሽ በመስጠት ጉዞውን እንደቀጠለ ገልጾ፤ ሁሉም በተለያየ መልክ የራሱን ሚና መወጣት ከቻለ ሀገርን መለወጥ ከባድ እንዳልሆነ ይናገራል።
ወጣት ሳሙኤል እንደሚያስረዳው፤ የተለያዩ ሀገራት የሰው ሠራሽ አስተውሎትን በተመለከተ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ። በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለመሳብ ጥረት እያደረጉ ነው። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ መንግሥት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ አለበት። ምክንያቱም በሚመጣው ዘመን ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ለቴክኖሎጂ ሥራና ምርምር ትልቅ ትኩረት መስጠት የግድ ነው።
እንደ ቱርክ ባሉ ሀገራት ለወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች የሚሰጠው ድጋፍ ጠንካራ እንደሆነና በዚህም የራሳቸውን የሰው ኃይል ተጠቅመው ውጤታማ እንደሆኑ የሚናገረው ሳሙኤል፤ ኢትዮጵያም ይህንን ልምድ በመውሰድ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች ዘላቂነት ባለው መልኩ የምትደግፍበት አሠራር መዘርጋት እንደሚገባት ያስረዳል።
ኢትዮጵያ አቅም አላት። ብዙ መሥራት ትችላለች የሚለው ሳሙኤል፤ ነገር ግን የሚመለከታቸው አካላት በቴክኖሎጂ ዘርፍ በተገቢው መንቀሳቀስ ባለባቸው ልክ እየተንቀሳቀሱ አለመሆኑን ይናገራል። ይህ መቀረፍ አለበት፤ ምክንያቱም በዚህ ዘርፍ እየሠራ ያለው ወጣት የሚደግፈኝ አካል የለም ብሎ ሥራውን ተስፋ በመቁረጥ ማቆም የለበትም ይላል። በሌላ በኩል የሚደግፍ አካል ባይኖርም የራስን ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ይገልፃል።
በመጨረሻም ወጣት ሳሙኤል ባስተላለፈው መልዕክት፤ ህልም ሁልጊዜ ዋጋ መክፈል ይኖረዋል፤ ፀንቶና ተግቶ በመሥራት የማይሳካ ነገር የለም ብሎ በማመኑ፤ ኢትዮጵያን በተለያየ ዘርፍ የማበልጸግ ግዴታና ኃላፊነት ያለባቸው ወጣቶች እንደመሆናቸው ለዓላማቸው መሳካት ባለመሰልቸት መትጋት አለባቸው ይላል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም