በቴክኖሎጂ እና በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ ያተኮረው ጉብኝት

አዲስ አበባ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፈረንሳይ ፣ ፓሪስ ያደረጉት የኢንዱስትሪ ጉብኝት በቴክኖሎጂ እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ ያተኮረ እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

ጽሕፈት ቤቱ በማህበራዊ ድረ ገጹ ትናንት በአስተላለፈው መልዕክት እንዳለው፤ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከልዑካን ቡድናቸው ጋር በመሆን ‘ስቴሽን ኤፍ’ የተባለውን በዓለም ትልቁን የግል የቴክኖሎጂ የስታርት አፕ የቢዝነስ መፍጠሪያ ማዕከልን ጎብኝተዋል። የኢትዮጵያ ስታርት አፕ ከባቢ ገና በጅምር ደረጃ ያለ ቢሆንም የቴክኖሎጂ እውቀት ጠገብ በሆኑ ወጣቶች የተሞላ እንዲሁም ጠንካራ አቅም እያሳየ በማደግ ላይ ባለ የዲጂታል ትስስር እየተመራ የሚገኝ ነው ሲል ገልጿል።

መንግሥት እንደ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ያሉ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ፈጠራን ለመደገፍ ርምጃዎች በመውሰድ ላይ ይገኛል ያለው ጽሕፈት ቤቱ፤ ይህም ለስታርት አፕ ከባቢ በተለይም በፋይናንስ ቴክኖሎጂ፣ በግብርና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በኢ-ኮሜርስ ግብይት አስቻይ ሁኔታን ለመፍጠር ያለመ ነው ብሏል።

በተጨማሪም የ‘ስታርት አፕ’ አዋጅ የተሰኘ ሁሉን አቀፍ አዋጅ በማውጣት ለስታርት አፕ እንቅስቃሴዎች የሕግ እና ተቋማዊ ማሕቀፎችን በማበጀት ውስን የሆነውን የገንዘብ አቅርቦት የሚያሰፋ፣ የቁጥጥር ተግዳሮቶችን እና መሰል ፈተናዎችን ለማለፍ የሚያስችል ሁኔታ ፈጥሯል ሲል አስገንዝቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር በ5G እና 6G ቴክኖሎጂ፣ በሳይበር ደኅንነት፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና የኦፕቲካል ትስስር ማዕከል የሆነውን የኖኪያ-ፈረንሳይ ዋና መሥሪያ ቤትንም መጎብኘታቸውን ጽሕፈት ቤቱ አመልክቶ፤ ጉብኝቱ የfiber sensing አቅርቦት፣ የኃይል ቁጠባ ብልሃት እና የ5G ላብራቶሪዎች ምልከታን ያካተተ ሲሆን፤ ይህም በዘርፉ ፈጠራ፣ መሠረተ ልማት ግንባታ እና ዘርፍ ዘለል ትብብሮች ላይ ለኢትዮጵያ ዋጋ ያላቸው ትምህርቶች የተገኙበት እንደነበር ገልጿል።

ሌላው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ፈረንሳይ የሚገኘውን ታሌ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ማዕከል ጎብኝተዋል። ይህ በብዝሃ ዘርፍ የሚንቀሳቀስ የታሌ ግሩፕ የምርምር ተቋም የኩባንያው ዓለም አቀፍ የምርምር ጥረት የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ የሚያገለግል ማዕከል ሲሆን፤ በኤሮስፔስ፣ መከላከያ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መስኮች ላይ እንደሚያተኩር ጽሕፈት ቤቱ ጠቅሷል።

እነዚህ ጉብኝቶች የዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን የኢትዮጵያን የዲጂታል ሽግግር በማፋጠን ሀገራችንን የአፍሪካ የፈጠራ እና ቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ በማመቻቸት ረገድ የእውቀት ልውውጦችን አስፈላጊነት አስምረው የሚያሳዩ መሆናቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አመላክቷል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You