“የትግራይ ሕዝብ የተጀመረው የሰላም እንቅስቃሴ እንዲቀጥል በጋራ ሊሠራ ይገባል” – አቶ ጌታቸው ረዳ

አዲስ አበባ፦ የትግራይ ሕዝብ የፕሪቶሪያ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆንና የተጀመረው የሰላም እንቅስቃሴ እንዲቀጥል በጋራ ሊሠራ እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ እና የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ከተማ ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ትናንት በዓድዋ መታሰቢያ ውይይት አካሂደዋል።

በመድረኩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ እንደገለጹት፤ የፕሪቶሪያ ስምምነት በትግራይ ክልል ሰላም ለማስፈን ትልቅ መሠረት ነው። ከሰላም ስምምነቱ ወዲህም የተቋረጡ መሠረተ ልማቶችን ዳግም ወደ ሥራ ለማስገባት፣ አዳዲስ የልማት ሥራዎችን ለማጠናከርና የተፈጠረውን ሰላም የማፅናት ሥራ ተሠርቷል ብለዋል::

የትግራይ ሕዝብ ሰላምን ለማረጋገጥና ለማፅናት እርስ በርስ ከመወነጃጀል ይልቅ ሁሉም በኃላፊነት ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመው፤የውይይቱ አላማም የትግራይ ሕዝብን ሰላምና አንድነት በማጠናከር ያልተጠናቀቁ ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠልና የጋራ ሃሳቦችን ለማንሳት እንደሆነም ተናግረዋል።

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ዓላማው ችግሮች በሕገ-መንግሥታዊ አውድ እንዲፈቱ ማድረግ ቢሆንም፤ የትግራይ አመራሮች መካከል በነበረው ፖለቲካዊ አለመግባባት በስምምነቱ ተግባራዊነት ላይ ተፅእኖ የፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም የተፈናቀሉት የትግራይ ተወላጆች አጀንዳ ወደ ጎን የተተወ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም የትግራይ መሬትን ዳግም የጦርነት አውድማ ከማድረግ ውጪ ዓላማ የለውም ብለዋል።

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን በትክክል ገቢራዊ ለማድረግም ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ወደ ሰላም የሚመጣበት ሁኔታ ላይ ሕዝቡ ጫና መፍጠር እንዳለበት አስታውቀዋል።

ሕዝቡም የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግና የተጀመረውን የሰላም እንቅስቃሴ ለማስቀጠል በጋራ መሥራት እንደሚኖርበት ገልጸው፤ የራሳችንን ጥፋት በመደበቅ ሌሎችን መወንጀል የማያስፈልግ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ ትግራይ ክልል ሰላም እንጂ ዳግም ጦርነት እንዳይከሰት ኃላፊነት መወጣት እንደሚገባና ልማትን ማረጋገጥ እንደሚገባ የተጠቀሰ ሲሆን፤ መሰል ውይይቶችም በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑ ተገልጿል።

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You