የኢትዮጵያውያን ፅናትና አንድነት ማሳያ

የሕዝብ ቁጥሯ ከ120 ሚሊዮን የተሻገረው ኢትዮጵያ ከድህነትና ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ለመላቀቅ አያሌ ተግባራቶች እያከናወነች ትገኛለች። ከዚህ መካከል የዓባይ ግድብ አንዱ ነው። በተለይ የሀገሪቱ የኃይል አቅርቦት በየዓመቱ በ25 በመቶ አካባቢ እያደገ በመሆኑ ትላልቅ የኃይል ማመንጫዎችን መገንባት ካልቻለች ዕድገቷ ቀጣይነት አይኖረውም።

የዓባይ ግድብ የሀገራችንን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ከ70 በመቶ በላይ ከማሳደጉም ባሻገር ግድቡ ሲጠናቀቅ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩዩብ ውኃ የሚይዝና 1680 ኪሎ ሜትር ስኩዌር በላይ ስፋት ስለሚኖረው በዚህ ሰፊ ሰው ሠራሽ ሐይቅ ከፍተኛ የሆነ የአሳ ሀብት ማፍራት የሚያስችል ይሆናል። ጥናቶች እንዳመላከቱት በዓይነታቸው ለየት ያሉ ከዘጠኝ በላይ የአሳ ዝርያዎችን ለማርባት በጣም ምቹ እንደሚሆን እና በዓመት ከ10ሺ ቶን በላይ አሳ የማም ረት አቅም ይኖረዋል።

ግድቡ ከሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባለፈ በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል ሀገራዊ መግባባትን እንዲጎለብት አድርጓል። ግድብ የሁሉን ድጋፍ ያተረፈ ፤ ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ የፖለቲካ አመለካከት፣ የሃይማኖት ልዩነት፣ ሳይገደበው፣ የብሔር፣ የዕድሜ ወይም የጾታ ልዩነት ሳይታይበት በአንድነት ድጋፉን የቸረው ነው።

ሌላው የግድብ ጠቀሜታ በሕዝባችን ውስጥ የቁጠባ ባህልን እንዲዳብር እድል መፍጠሩ ነው። ቁጠባ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ እድገት አንዱ አመላካች ነው። የዜጎች የመቆጠብ አቅማቸው እያደገ በመጣ ቁጥር የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ምክንያት ይሆናል።

የዚህ ፕሮጀክት ሌላው ጥቅም የሥራ ዕድል ፈጠራ ነው። ግድቡ ለበርካታ ዜጎቻችን የሥራ ዕድል ይዞ የመጣ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። ከከፍተኛ ባለሙያዎች ጀምሮ እስከ ቀን ሠራተኛ ድረስ በግንባታው ሥራ በመሳተፍ በአጠቃላይ ከ13ሺ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

በቀጥታ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች ባሻገር እጅግ በርካታ ዜጎች ደግሞ ለእነዚህ ሠራተኞች የተለያዩ አገልግሎቶች በማቅረብ፤ ለአብነት በሸቀጣሸቀጥ፣ ምግብ፣ ትራንስፖርት በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል።

በተጨማሪም በዓባይ ግድብ ሳቢያ በበርካታ አካባቢዎች ህብረተሰቡ ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ እንዲነሳሳ ምክንያት ሆኗል። ህብረተሰቡ የግድቡ ዕድሜ እንዲጨምር በየአካባቢው የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን በተለይ በችግኝ ተከላና አፈር ጥበቃ ሥራዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየተረባረበ ይገኛል።

ሌላው የግድቡ ጠቀሜታ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል በተፋሰሱ ሀገራት መካከል እንዲነግስ በማድረጉ ከሀገራት ጋር አዲስ የመተማመንና የመተባበር ዲፕሎማሲን እንዲፈጠር አስችሏል። የግድቡ መጀመር ለእኛ ኢትዮጵያን ፍትሃዊ አመለካከታችንን ለዓለም ለማሳወቅ ጥሩ አጋጣሚን ፈጥሮልናል።

ኢትዮጵያ ምን ያህል ፍትሃዊ እንደሆነች የዓለም ሕዝቦች የተረዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የሀገራችንንም የመደራደር አቅም አሳድጓል። የሀገራችንን ገጽታም እጅጉን ቀይሮታል። የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተለይ ግብጻዊያንን ለውይይት እና ምክክር በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲቀመጡም አድርጓል።

ከተጀመረ 13ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የዓባይ ግድብ፣ በኢትዮጵያውያን የፋይናንስና የሞራል ድጋፍ ከተገነቡ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የመጀመሪያው ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡ በተለይም የግድቡ ግንባታ ከጅምር እስከ አሁን ውጫዊና ውስጣዊ ፈተናዎች ባሉበት ሁኔታ አልፎ በመገባደድ ላይ መሆኑም ኢትዮጵያ በፅናት እየተሻገረች ስለመሆኗ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

በተለይም በዓባይ ተፋሰስ ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ውሃውን ለብቻችን እንጠቀም የሚሉ ሀገራት ኢትዮጵያን ያላሳተፉ የቅኝ ግዛት ውሎች ዳግም ለማጽናት የዓረብ ሊግን በመጠቀም ዘመቻዎች ሲደረጉ ቢቆዩም የኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ ብርቱ የዲፕሎማሲ ጥረትና የማህበረሰብ ተሳትፎ ተደምረው ጫናዎችን በማለፍ ግድቡ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ አስችለዋል።

ኢትዮጵያ በ2003 ዓ.ም ላይ የዓባይ ግድብን መገንባት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ግብፅና ሱዳን ተቃውሞና ስጋታቸውን በተለያዩ መንገዶች ሲገልጹ እስከ ዛሬ ይደመጣሉ። ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ላለፉት አሥር ዓመታት በዓባይ ወንዝ ጉዳይ ከስምምነት ለመድረስ ሲደራደሩ የነበረ ቢሆንም፤ እስካሁን ሦስቱንም ሀገራት የሚያስማማ ሁሉን አቀፍ መግባባት ላይ መድረስ አልተቻለም።

እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጉዳይ የአንዳንድ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ሴራና ተንኮል ነው። በእኔ እምነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በተቃራኒ የሚቆሙ እነዚህ ሀገራት የዓባይ ግድብ የቅርብ ጊዜ ምክንያት ሆናቸው እንጂ በታሪክ አጋጣሚ ሁሉ የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልጉና እንደ ስጋት የሚመለከቱ ሀገራት ናቸው።

ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራራቢ የሕዝብ ብዛት ያላት ግብፅ፤ ከኢትዮጵያ 15 እጥፍ የሚያህል የኃይል ፍጆታ አላት። የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ፍጆታ 10.7 ቢሊዮን ኪሎዋት ሲሆን የግብፅ ደግሞ 159 ቢሊዮን ኪሎዋት ነው። ይህ እውነት የሚያሳየን የግብፅ አካሄድ ከመጠን ባለፈ በእራስ ወዳድነት የተሞላና የኢትዮጵያን ዕድገት እንደ ስጋት የማየት በሽታ የተጠናወታት መሆኑን ነው።

ከዓድዋ ድል በመቀጠል በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አንድነትና ትብብር የታየበት የዓባይ ግድብ ብዙዎች ፈተናዎችን አልፎ ከመገባደጀው መድረሱ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከተነሱ ሊቋቋማቸው የሚችል ምድራዊ ኃይል እንደሌለ በተግባር ምሳሌ የሆነ ነው ብል ማጋነን አይሆንም።

በአጠቃላይ የዓባይ ግድብ በሀገሪቱ እየጎለበተ ላለው ጠንካራ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት አንድ ማሳያ ከመሆኑም ባሻገር ለሀገራችን የገጽታ ግንባታ እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ይህ ፕሮጀክት በሀገራችን ሕዝቦች መካከል የይቻላል መንፈስ እንዲፈጠር ሲያደርግ ለሌሎች ታዳጊ ሀገራት ደግሞ በተፈጥሮ ሀብታቸው እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ መንገድን አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ሕዝባች ፍትሃዊነት ለዓለም ያሳወቁበት አንዱ ማሳያ ነው። የተፋሰሱ ሀገራትም የጋራ ሀብታቸውን በትብብር እና በመደጋገፍ ከመጠቀም ውጭ ሌላ አማራጭ እንደማይኖራቸው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በተጨባጭ አሳይተዋል።

የዓባይ ግድብ የትላንት አባቶቻችን የሠሩት የዓድዋ ገድል የዛሬ ትውልድ ኩራት እንደሆነው ሁሉ የዚህ ትውልድ ዓድዋ ደግሞ ከድህነት ጋር ተፋልሞ ድል በማድረግ የሚገኝ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ የራሱን ዓድዋ ለመሥራትና ለልጆቹ በጀግንነት የሚናገረው ታሪክ ለማኖር አቅሙ በፈቀደው ሁሉ መረባረብ አለበት እላለሁ። ሰላም!

ክብረአብ

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You