
አዲስ አበባ፡- በሳውድ አረቢያ ያለ መኖሪያ ፈቃድ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ 70 ሺህ ዜጎችን በዘመቻ መልክ ለመመለስ ብሔራዊ ኮሚቴ ተዋቅሮ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ትናንት ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ ተድላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት፤ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በተለያዩ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራ እየተሰራ ነው፡፡
ሦስተኛ ምዕራፍ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የማስመለስ ስራ በቅርቡ ይጀመራል ያሉት ቃል አቀባዩ፤ መጋቢት 12 ቀን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳር ብርቱካን አያኖ የሚመራ 16 የፌዴራል ተቋማትን የያዘ ብሔራዊ ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡ ብሔራዊ ኮሚቴው በሳውድ አረቢያ ያለ መኖሪያ ፈቃድ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ 70 ሺህ ዜጎችን በዘመቻ መልክ የመመለስ ስራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዘመቻ መልክ ዜጎችን ወደ ሀገር ለመመለስ በቀን አራትና በሳምንት 12 በረራዎችን ለማካሄድ እቅድ ተይዟል ያሉት ቃል አቀባዩ፤በምዕራፍ ሶስት ዜጎችን ለማስመለስ የፌዴራልና የክልል ተቋማት በጋራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ቃል ቃባዩ፤ ወደ ሀገራቸው ከገቡ በኋላ ወደ ቀያቸው እስኪመለሱ ድረስ መጠለያ እየተዘጋጀ ነው፡፡ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም የሚጠበቅባቸውን ስራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዜጎችን ወደ ሀገር ከመመለስ ስራ ጋር በተያያዘ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጣ ልዑካን ቡድን በያዝነው ሳምንት መጨረሻ ወደ ሳውድ አረቢያ በመሄድ ከሳውዲ አረቢያ ባለስልጣናት ጋር ውይይት እንደሚያደርግም ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ ነብዩ ማብራሪያ፤ በዚህ ዓመት ከሳውድ አረቢያ በተደረጉ መደበኛ በረራዎች ስድስት ሺህ 993 ዜጎች ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል፡፡ በመደበኛ በረራ የሚደረገው የመመለስ ስራ በሳውዲ እስር ቤት ከሚገኙና ወደ እስር ቤት እየገቡ ካሉ ዜጎች ቁጥር አንጻር አናሳ በመሆኑ በቀጣይ በዘመቻ መልክ የማስመለስ ስራ እንዲሰራ ተወስኗል፡፡
ዜጎች በሕገ-ወጥ ደላሎች ተታለው ወደ ሳውዲ አረቢያ፣ መካከለኛው የባህረ ሰላጤው ሀገራት፣ ወደ ደቡብ አፍሪካና ወደ ሌሎች ሀገሮች ይሄዳሉ፡፡ በዚህ ሂደት ቁጥራቸው ቀላል የማባይል ዜጎች ለሞትና ለእስር እየተዳረጉ ነው፡፡ መንግሥት ለዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ትኩረት በመስጠት በተለያዩ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ያሉ ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት ለመመለስና መልሶ ለማቋቋም በትኩረት እየሰራ ስለመሆኑም አቶ ነብዩ ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ዘጠኝ ወራት 50 ሺህ 327 ዜጎች ወደ ሀገር እንዲመለሱ ተደርጓል ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ከሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ጅቡቲ፣ ከኬንያ፣ ዚምባቡዌ፣ ግብጽ፣ ናይጀሪያና አልጄሪያ በድምሩ 20 ሺህ 455 ዜጎቻችን ተመልሰዋል፡፡ ከመካከለኛው ምሥራቅ 29 ሺህ 872 ዜጎቻችን እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከሳውዱ አረቢያ የተመለሱት ቁጥር ከሌሎች ሀገራት ከፍ ያለ ነው፡፡
ባለፈው ዓመት በአጠቃላይ ከ139 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
በተያያዘ ዜናም በትናንትናው ዕለት የአፍሪካ የቦክሲንግ ኮንቬዴሬሽን ጽህፈት ቤቱን በአዲስ አበባ ለመክፈት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት አካሂዷል፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ለጽህፈት ቤቱ ቢሮ ለመክፈትና በቀጣይ ለሚኖሩ ተጓዳኝ ስራዎች ድጋፍ እንደሚደረግ በአምባሳደር ብርቱካን አያኖ በኩል ማረጋገጫ ስለመሰጠቱ አቶ ነብዩ ገልጸዋል፡፡
በሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም