በ45ኛ የሰርቢያ ቤልግሬድ የዓለም ሀገር አቋራጭ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተሳትፎ አስር ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀው የአትሌቲክስ ልዑካን ቡድን እውቅና እና የሽልማት መርሀ ግብር ተካሂዷል።
መርሀ ግብሩ ከትናንት በስቲያ በቤልቪው ሆቴል የተከናወነ ሲሆን፤ በእለቱ በክብር እንግዶች አማካኝነት ለቡድኑ የማበረታቻና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል። አትሌቶችና አሰልጣኞችም በውድድሩ ስለነበረው ሁኔታ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
አትሌቶች በውድድሩ የነበራቸውን ቆይታ በተመለከተ ከ 20 ዓመት በታች ወጣቶች የወርቅ ሜዳሊያን ያጠለቀችው አትሌት ማርታ አለማሁና አትሌት በሪሁ አረጋዊ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል። ሁለቱም አትሌቶች ባደረጉት ንግግር በውድድሩ የገጠማቸውን ጉዳይ በማብራራት፤የተመዘገበው ውጤት ጥሩ እንደሆነና ቀጣይ በሚኖሩ ውድድሮች የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
አሰልጣኞችን በመወከል አስተያየቱን የሰጠው ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሼቦ ሲሆን፤ በአዋቂዎች ምድብ ውጤት ባይመዘገብም፣ በታዳጊ ወጣት ሴቶች የተገኘው ድል ኢትዮጵያ ተተኪ እንዳላት ያሳየ እንደሆነ ተናግሯል። በመሆኑም ከዚህ ትምህርት በመውሰድ ወደ ፊት የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል አመላካች መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ከአትሌቶቹ በተጨማሪ የቡድኑ መሪና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር ተስፋዬ አስግዶም እና የቡድኑ ቴክኒክ መሪና የፌዴሬሽኑ የተሳትፎና ውድድር ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ለልዑካን ቡድኑ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርቧል።
በሽልማት መርሀ ግብሩ የተገኙት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምክትል ፀሐፊ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ፣ ለተመዘገበው ውጤት ምስጋና በማቅረብ ለቀጣይ የ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም በቅርቡ አትሌቶችን እና ባለሙያዎችን ወደ ሆቴል የማስባት ሥራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።
በመጨረሻም የፌዴሬሽኑ ፕሬዘዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ባደረገችው ንግግር፤ በውድድሩ የተገኘው ድል አበረታች መሆኑን ገልጻለች። ቀጣይ በሚደረጉ ውድድሮች ላይ በትኩረት መሰራት እንደሚኖርበት ጠቁማለች። በተጨማሪም ለ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ከወዲሁ በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባውና ለተመዘገበው ውጤት መሳካት ከፌዴሬሽኑ ጎን ለነበሩ ባለድርሻ አካላት ምስጋናዋን አቅርባለች፡፡
ኢትዮጵያ ዘንድሮ ለ45 ጊዜ በሰርቢያ ቤልግሬድ ከተማ በተከናወነው የዓለም ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና በ14 ሴት እና በ14 ወንድ በአጠቃላይ በ28 አትሌቶች ተወክላ 10 ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ ችላለች። የአትሌቲክስ ቡድኑ ኬንያ በሰበሰበችው የወርቅ ሜዳሊያ ብልጫ የመጀመሪያ ደረጃን ይዞ ባያጠናቅቅም የተሻለ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን ችሏል። የቡድኑን ሞራል ለማነቃቃትና ለማስቀጠል እንዲሁም በቀጣይ ውድድሮች የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብም የእውቅና እና የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶለታል። መመሪያው እና አሰራሩ በሚፈቅደው መሰረት ውጤት ላመጡ አትሌቶች የማበረታቻና የገንዘብ ሽልማት እንደተበረከተላቸውም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
በዚህም መሰረት በቻምፒዮናው የወርቅ ሜዳሊያ ላስመዘገቡ አትሌቶች የ52 ሺ ብር፣ የብር ሜዳሊያ ላስመዘገቡ የ35 ሺ ብር እና የነሐስ ሜዳሊያ ላመጡ አትሌቶች የ22 ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት እንደተበረከተላቸው ተጠቁሟል፡፡
ከ51 ሀገራት የተወጣጡ 485 አትሌቶችን በ5 የውድድር ዓይነቶች አሳትፎ የተጠናቀቀው የዓለም ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና ከፍተኛ ፉክክር በማስተናገድ አራት ሀገራት ብቻ ሜዳሊያ ውስጥ ገብተው ማጠናቀቅ ችለዋል። ውድድሩ በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂዎች ወንዶችና ሴቶች፣ 8 ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶች፣ 6 ኪሎ ሜትር ወጣት ሴቶች እና በድብልቅ ሪሌይ የተካሄደ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በአዋቂ ወንዶች በአትሌት በሪሁ አረጋዊ የብር ሜዳሊያ አስመዝግባለች። በአዋቂ ሴቶች ውጤት አልተመዘገበም።
አረንጓዴው ጎርፍ የተመዘገበበት የወጣት ሴቶች 6 ኪሎ ሜትርን አትሌት ማርታ አለማሁ የወርቅ፣ አትሌት አሳየች አይቸው የብር እና ሮቤ ዲዳ የነሐስ ሜዳሊያን በማጥለቅ ታሪክ መስራት ችለዋል። ሌላው የወጣት ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር የብር ሜዳሊያ በአትሌት መዝገቡ ስሜ ማግኘት ተችላል። በድብልቅ ሪሌይ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ የብር ሜዳሊያውን መውሰዷም ይታወቃል።
ውድድሩን ኬንያ በ6 ወርቅ በ2 ብርና በ3 ነሐስ በድምሩ 11 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ቀዳሚ ሆና ስታጠናቅቅ፤ ኢትዮጵያ በ2 ወርቅ፣ 6 ብር እና 2 ነሐስ በአጠቃላይ አስር ሜዳሊያዎችን በግልና በቡድን በመሰብሰብ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች። ኡጋንዳ በ5 እና እንግሊዝ በ 1 ሜዳሊያ ቀሪውን ደረጃ በመያዝ ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም