ወደ ሥራ የተመለሰው ኢንዱስትሪ ፓርክ

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረው ጦርነት ተፅዕኖ ካሳደረባቸው የምጣኔ ሀብት መስኮች መካከል አንዱ የኢንቨስትመንት ዘርፍ መሆኑ ይታወሳል። በጦርነት ቀጣና ውስጥ ከነበሩና ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ ከተፈፀመባቸው ተቋማት መካከል በርካታ የውጭ ባለሀብቶችን ሲያስተናግዱ የነበሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተጠቃሽ ናቸው።

በጦርነት ቀጣና ውስጥ ከነበሩት የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አንዱ መቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ነው። ኢንዱስትሪ ፓርኩ በሐምሌ 2009 ዓ.ም በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተመርቆ ሥራ መጀመሩ ይታወሳል። ለግንባታው ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገበትና በ238 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ፓርክ ከ20ሺ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድሎችን እንዲፈጥር ታቅዶ የተገነባ ነው።

መቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሰሜኑ የሀገሪቷ አካባቢ በነበረው ጦርነት ምክንያት ላለፉት ሦስት ዓመታት ከሥራ ውጭ ሆኖ ቆይቷል። ይሁንና ከሰሞኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረጋቸው ጥረቶች ኢንዱስትሪ ፓርኩ፣ ወደ ሥራ መመለሱ ተገልጿል። ኢንዱስትሪ ፓርኩን ወደ ሥራ ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት ያግዛሉ የተባሉ ምልከታዎችና ውይይቶች ሲደረጉ እንደነበርም ይታወሳል።

በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ገብተው ይሰሩ የነበሩ ድርጅቶች በበኩላቸው ወደ ሥራ ለመመለስ የሚያስችሏቸው ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩላቸው የሚያነሷቸው ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እንዳሉ የትግራይ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገልጾ ነበር። ባለሀብቶች ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል የሼድ ኪራይና ወለድ ስረዛ፣ የብድርና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት፣ የካሳ ክፍያ፣ የተፋጠነ የንግድና የሥራ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሁም የግብር እፎይታ ይጠቀሳሉ።

ባለሀብቶቹ ‹‹ላልተጠቀምንበትና ላልሰራንበት ሼድ ኪራይ መክፈል የለብንም፤ ለደረሰብን ጉዳትና ኪሳራ የኢትዮጵያ መንግሥት ካሣ መክፈል አለበት፤ ጥሬ እቃ ከውጭ ስለምናስገባ የውጭ ምንዛሬ ይቅረብልን፤ የሥራ ማስኬጃ ብድር ያስፈልገናል፤ ሠራተኞቻችን ተበታትነዋል፣ ስልጠና ያስፈልገናል፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ግልፅ የሆነ ጥሪ ይደረግልን…›› የሚሉ ጥያቄዎችን ማቅረባቸውን የትግራይ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል መኮንን ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ በአንድ ወቅት ገልጸው ነበር።

ለባለሀብቶች ጥሪ አድርጎ፣ አወያይቶ፣ የሚጠይቁትን ጥያቄ አድምጦና ድጋፍ አድርጎ ወደ ሥራ በማስገባት ረገድ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች ጋር በተደጋጋሚ ንግግር መደረጉንና የተሻለ ውጤት ለማግኘት ተጨማሪ ጥረቶች እንደሚያስፈልጉም አቶ ዳንኤል ተናግረው ነበር።

መቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክን ወደ ሥራ ለመመለስ በርካታ ሥራዎች ሲከናወኑ እንደቆዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃዎች ያሳያሉ። የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በሰፈነው ሰላም ምክንያት ኢንዱስትሪ ፓርኩን ወደ ሥራ ለመመለስ የዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። ኮርፖሬሽኑ ፓርኩ ወደ ሥራ እንዲመለስ ለማድረግ ካከናወናቸው ተግባራት ጎን ለጎን በፓርኩ ውስጥ በሥራ ላይ ተሰማርተው ከነበሩ ባለሀብቶች ጋር ውይይቶችን በማድረግ ወደ ፓርኩ ተመልሰው ሥራቸውን እንዲጀምሩ የጋራ መግባባት ላይ በመደረሱ ባለሀብቶቹም ወደ ሥራ ለመመለስ የሚያስችሏቸውን ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርና ከመቀሌ ከተማ አመራሮች ጋር ፓርኩን ወደ ሥራ ለመመለስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይቶችን አድርጓል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ፣ ኮርፖሬሽኑ ያከናወነው ከፍተኛ ቅንጅታዊ ሥራና የሰጠው ትኩረት ፓርኩን ወደ ሥራ ለመመለስ እንዳስቻለው ይገልፃሉ። ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንደሚሉት፣ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ያመርቱ የነበሩ ኩባንያዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ እንዲሁም አዳዲስ ኢንቨስተሮች በፓርኩ ለማምረት ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የቅድመ ኢንቨስትመንት ሥራዎቻቸውን እያጠናቀቁ ይገኛሉ። ኮርፖሬሽኑም ኩባንያዎቹ ወደ ምርት ሂደት እንዲገቡ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት ሂደት እንዲገባ፤ ውጤታማነቱ ከፍ እንዲል እንዲሁም ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅርበት ሊደግፉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና ቢዝነስ ልማት ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዘመን ጆነዲ፣ ከዚህ ቀደም ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ በሰጡት ማብራሪያ፣ ኮርፖሬሽኑ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማግስት ለረጅም ጊዜ ከሥራ ውጭ የነበረውን የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክን ወደ ሥራ ለመመለስ በርካታ ተግባራትን እንዳከናወነ ገልጸዋል።

እንደ አቶ ዘመን ገለፃ፣ ኮርፖሬሽኑ ለሁለት ዓመታት ያህል ስለመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምንም መረጃ ሳይኖረው ቆይቷል። የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በኮርፖሬሽኑ የተዋቀረ የባለሙያዎች ቡድን ወደ መቀሌ አምርቶ ፓርኩ ስለሚገኝበት ሁኔታ ምልከታ አድርጓል። በዚህም ፓርኩ ምንም ዓይነት ዘረፋም ሆነ ውድመት እንዳልደረሰበት ታውቋል። ስለሆነም ፓርኩን በፍጥነት ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችሉ ሥራዎች ተከናውነዋል። የኮርፖሬሽኑ ዋና ትኩረት ፓርኮቹን ወደ ሥራ መመለስ በመሆኑ፣ ባለሀብቶቹና ሠራተኞቹን ወደ ሥራ መመለስ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነበር።

ኮርፖሬሽኑ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማግሥት ለረጅም ጊዜ ከሥራ ውጭ የነበረውን የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክን ወደ ሥራ ለመመለስ በርካታ ተግባራት ያከናወን ሲሆን፤ ለአብነት ያህልም ቡድን በማዋቀር በፓርኩ ምልከታ የማድረግ፣ በፓርኩ ውስጥ ከነበሩ ባለሀብቶች ጋር የመወያየት እንዲሁም የአመራር ውሳኔ ለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የመስጠት፣ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ሥራ አቁመው የቆዩ ባለሀብቶችን ከሼድ ኪራይ ነፃ በማድረግ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ለማድረግ የሚያስችሉ፣ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። በፓርኩ ውስጥ ከነበሩት ስምንት ባለሀብቶች ጋር በስልክና በኢ-ሜይል (E-Mail) መነጋገር ተችሏል፤ ወደፊትም የጋራ የውይይት መድረኮች ተዘጋጅተው ተጨማሪ ውይይቶች ይደረጋሉ።

አቶ ዘመን በዚሁ ማብራሪያቸው የኢንዱስትሪ ፓርኩን ችግሮች ለማቃለል ስለተወሰዱትና በሂደት ላይ ስላሉት የመፍትሄ አቅጣጫዎች ሲገልፁ ደግሞ፣ ‹‹በፓርኩ ውስጥ የነበሩ ባለሀብቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሚመሩት ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ ባለሀብቶችን የማግኘትና ወደ ሥራ እንዲገቡ የማሳመን ሥራ ተሰርቷል። በፓርኩ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ ሠራተኞች ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅና ባለሀብቶቹ ወደ ሥራ ሲገቡ የሠራተኛ አቅርቦት ችግር እንዳይገጥማቸው ከጊዜያዊ አስተዳደሩ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ዘርፍ ጋር ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል። ከጊዜያዊ አስተዳደሩ የትራንስፖርት ቢሮ ጋር ውይይት በማድረግ የትራንስፖርቱ ችግር የሚፈታበት ሂደትም ተመቻችቷል። የመብራትና የዳታ እንዲሁም የድምጽ መቆራረጦችን ለማስወገድ የሚያስችል ውይይት ተደርጎ ችግሩን በአጭር ጊዜ ለመቅረፍ የሚያስችሉ ሥራዎች በመሠራት ላይ ይገኛሉ። የውሃ አቅርቦትን በተመለከተ ደግሞ በአካባቢው ያለው ውሃ ከማህበረሰቡ አልፎ ለፓርኩ በትንሽ መጠን የሚደርስ በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ ከአስተዳደሩ ጋር በመነጋገርና የጉድጓድ ውሃ ለማውጣት የሚያስችል የፓምፕ ግዥ ለመፈጸም እየተሠራ ነው›› ብለዋል።

አካባቢው ጦርነት ውስጥ የቆየ እንደመሆኑ አምራቾች ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ያስተናገዱ መሆናቸው ይታመናል። በመሆኑም ልዩ የማበረታቻ ማዕቀፍ ያስፈልጋቸዋል። በዚህ ረገድ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በጦርነት ቀጣና ውስጥ የነበሩ ባለሀብቶች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ለማገዝ ለባለሀብቶቹ የተለያዩ ድጋፎችንና ማበረታቻዎችን እንደሚያደርግ አቶ ዘመን ገልጸዋል። ከመደበኛ የድጋፍና ክትትል ሥራዎች በተጨማሪ ባለሀብቶቹ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከነበረባቸው የሼድ ኪራይ ነፃ የማድረግ እና ከፓርኩ የሥራ ኃላፊዎችና ከአካባቢው አስተዳደር ጋር ተከታታይ ውይይቶችን በማድረግ ቀደም ሲል በፓርኩ የነበሩ የተለያዩ አገልገሎቶችን በፍጥነት ወደ ሥራ የመመለስ ተግባራትን እንደሚያከናውን አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ባለሀብቶችን አሳምኖ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረግ፣ በጦርነቱ ምክንያት የተበተኑ ሠራተኞችን ወደ ቀድሞ ሥራቸው መመለስ፣ የሠራተኞች ሰርቪስ የትራንስፖርት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር፣ በአንድ ማዕከል ውስጥ የሚቀርቡ አገልገሎቶች በተሟላ ሁኔታ አለመጀመር እና የውሃ አቅርቦት ችግር በጦርነት ቀጣና ውስጥ የነበሩትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ሥራ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ላይ ጫና እያሳደሩ ካሉ ተግዳሮቶች መካከል ዋናዎቹ እንደሆኑም አቶ ዘመን ጠቁመው ነበር።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከሁለት ወራት በፊት፣ ጥር 2016 ዓ.ም፣ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ለማምረት ፍላጎት ካላቸው 11 ኩባንያዎች ጋር የሠራ ስምምነቶችን መፈራረሙ ይታወሳል። ከእነዚህ ኩባንያዎች መካከል ባለፉት ሦስት ዓመታት ከሥራ ውጭ ሆኖ ወደቆየው መቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገቡ ናቸው። አቶ አክሊሉ ስምምነቶቹ በተፈረሙበት ወቅት ‹‹ኩባንያዎቹ ወደ ፓርኩ ገብተው ለመሥራት ፍላጎት ማሳየታቸውና ከኮርፖሬሽኑ ጋር ስምምነት መፈረማቸው ከሥራ ውጭ የቆየውን ፓርኩን ወደ ሥራ ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ ያግዛሉ›› ብለው ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ፓርኩ ወደ ሥራ እንዲመለስ ኮርፖሬሽኑ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሲሰራ ነበር። በጦርነቱ ምክንያት ከሠራ ውጭ የነበሩ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች ወደ ሥራ እንዲመለሱ፣ በሞራልም በፋይናንስም እንዲጠገኑና አገግመው ወደ ሥራ መንፈስ እንዲመለሱ ጥረት ተደርጓል፤ የነበረው ውዝፍ ደመወዝ እንዲከፈላቸው አድርገናል። በፓርኩ ውስጥ በምርት ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የነበሩ ባለሀብቶች ሥራ አቋርጠው ወጥተው ስለነበር ወደ ሥራ እንዲመለሱ ተደጋጋሚ ውይይቶች ተደርገዋል። ፓርኩ በጦርነቱ ጉዳት ባይደርስበትም ውስን ጥገናዎች ተደርገውለት በሙሉ ቁመና ለሥራ ዝግጁ እንዲሆን ተደርጓል። በዚህ ውጤታማ ጥረት ነባር ኢንቨስተሮችን ወደ ሥራ መመለስ ብቻ ሳይሆን፣ ከሦስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስት አዳዲስ ኢንቨስተሮች ወደ መቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመግባት የሚያስችላቸውን የሥራ ስምምነት እንዲፈርሙ ማድረግ ተችሏል›› በማለት ፓርኩን ወደ ሥራ ለመመለስ ስለተከናወኑ ተግባራት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር ለማሳካት አምራች ዘርፉ አሁን ካለው አፈፃፀም በብዙ እጥፍ እንዲጨምርና እንዲሻሻል ማድረግ ያስፈልጋል። የአምራች ዘርፉ እድገት ሊሻሻል የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ናቸው። ስለሆነም የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በመፍታትና አፈፃፀማቸውን በማሻሻል መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግሩን ማሳካት ይገባል።

ከጦርነት በኋላ የሚኖር የኢኮኖሚ ግንባታ፣ በተለይም የኢንቨስትመንት ዘርፍ አስተዳደርና አመራር፣ የተለየ አሠራር እንደሚፈልግ በርካታ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በአስረጂነት ማቅረብ ይቻላል። የምጣኔ ሀብት ጥናት ባለሙያዎችም በጦርነት ምክንያት የተጎዳ የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲነቃቃና ቀደም ሲል ከነበረው አፈፃፀምም የተሻለ ቁመና ላይ እንዲገኝ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ የድህረ ጦርነት የኢንቨስትመንት አመራርና አስተዳደር ሥርዓት መተግበር እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ። በዚህ ረገድ በኢትዮጵያም በኢፌዴሪ መንግሥት እና በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል ከተፈረመው የሰላም ስምምነት በኋላ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ መነቃቃትና ማንሰራራት ዋስትና ሊሆኑ የሚችሉ የድህረ ጦርነት የኢንቨስትመንት ማነቃቂያ ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀትና በብቃት በመተግበር የትግራይ ክልል የኢንቨስትመንት ዘርፍ ልማትንና የሀገራዊ ምጣኔ ሀብቱን ግንባታ ማፋጠን አስፈላጊ ተግባር እንደሆነ በሚገባ መገንዘብ ይገባል።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You