ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የነገሮቻችን ሁሉ ወሳኝ መታጠፊያ/critical juncture/፤ የአህጉራችንን የጂኦፖለቲክስ ሚዛን ፍጹም የሚቀይር ፤ ኢኮኖሚውን ይዞ የመነሳት አቅም ያለው ፤ ሀገራዊ አንድነት ለመፍጠር የማይተካ ሚና የሚጫወት ስለሆነ ፤ እየሆነብንም ሆነ እየሆንለት ያለው ነገር ሁሉ ይገባዋል ስል ዛሬም አጽንኦት መስጠት እፈልጋለሁ።
ከአሜሪካው የካምፕ ዴቪድ ስምምነት በኋላ የግብፅና የእስራኤል ግንኙነት በመሻሻሉ ፤ የወቅቱ የግብፅ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት የፍልስጤምና የእየሩሳሌም ችግር የሚፈታ ከሆነ ከዓባይ ወንዝ 365 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ በየዓመቱ ለእስራኤል ለመስጠት ቃል ገብተው ነበር። ይህ የጂኦፖለቲካ የአሰላለፍ ለውጥ በራስጌ የተፋሰስ ሀገራት ላይ ውስብስብ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም።
ሌላዋ የግርጌ ተፋሰስና ጎረቤት ሀገር ሱዳን ግድቦችን ገንብታለች። እአአ በ1926 ሴናርን ለመስኖ ፣ በ1936 ጀበል አውሊያ ለኃይል ማመንጫና ለመስኖ ገንብታለች። በ1950 3ኛውንና 420ሺህ ሄክታር መሬት መስኖ የማልማት አቅም ያለው የሮሴሪስ ግድብን እንዲሁም ከእዚህ በተጨማሪ ሌሎች ግድቦችን ገንብታለች። በዚህም በመስኖ መልማት ከሚችለው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬቷ 1ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታሩን ማልማት ችላለች።
በግብፅና በሱዳን በመስኖ እየለማ ያለ መሬት የዓባይን 86 በመቶ ከምታበረክተው ሀገራችን ጋር ስናስተያየው እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ ሊያስቆጨን ይገባል። እንግዲህ ከፍ ብሎ እንደተመለከትነው በዓባይ የውሃ ሀብት ላይ በብቸኝነት እየተጠቀሙ ያሉት ሁለቱ የግርጌ ተፋሰስ ሀገራት በተለይ ግብፅ ናት።
በሌላ በኩል የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ የከፋ ድህነት ላይ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የግብርና ድርጅት /ፋኦ/ ይፋ ያረገው መረጃ ያመለክታል። ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርታቸው እጅግ ዝቅተኛ ከመሆኑ ባሻገር የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ እንዳልቻሉ የመንግሥታቱ ድርጅት ፋኦ ያትታል።
በተፋሰሱ ሀገራት የሚገኝ አብዛኛው ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አይደለም። አማካኝ የሀገራቱ ኤሌክትሪክ የማዳረስ ፍጥነት ከ30 በመቶ የተሻገረ አይደለም። ከዜጋዋ ከ65 በመቶ የሚልቀው ሕዝቧ ለልጆቹ ማጥኛ ፣ ለቤተሰቡ ምግብ ማብሰያና ለምሽቱ ብርሃን የሚያገኝበት የኤሌክትሪክ ኃይል የለውም። ጸሎቱ የማታ እራትና መብራት አታሳጣኝ ቢሆንም አልሰመረለትም ።
የውኃ ኃይል ማመንጫ በተለይ በራስጌ የተፋሰስ ሀገራት ለምቶ ጥቅም ላይ ባለመዋሉ በእድገታቸውና በልማታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። ይህ የኃይል እጥረት ዜጎች ፊታቸውን ወደ ከሰልና የማገዶ እንጨት እንዲያዞሩ በማድረጉ ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋን ከማስከተሉ ባሻገር የመሬት መራቆት ፣ የአየር ንብረት መዛባትንና ብክለትን እያስፋፋ ይገኛል። ለዚህ ነው በተመጣጣኝ ዋጋ ኃይል ማቅረብ የግድ የሆነው።
የራስጌ ሀገራት ግብርና በዋናነት የዝናብ ጥገኛ ቢሆንም በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአየር ፀባይ ለውጥ የተነሳ በየዓመቱ ሊባል በሚችል ሁኔታ ድርቅ ስለሚከሰት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ፈተና ከሆነ ውሎ አድሯል። ስለዚህ እንደ መስኖ ያለ አማራጭ የውሃ ሀብቶችን በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ የሕልውና ጉዳይ ነው። የናይልን የውሃ ሀብት በፍትሐዊነትና በኃላፊነት የመጠቀም ጉዳይ ከዓመት ዓመት እየገፋ ከመምጣቱ ባሻገር የተግባር እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
ታንዛኒያ ከቪክቶሪያ ሐይቅ 170 ኪሎ ሜትር በተዘረጋ ቧንቧ ውሃ በመውሰድ በሀገሪቱ በከፋ ድህነት የሚታወቀውን ካሃማ የተባለውን አካባቢ በመስኖ ለማልማት እየተንቀሳቀሰች ነው። ሌሎች የራስጌ ተፋሰስ ሀገራትም ከወንዙ ድርሻቸውን በመጠቀም የውሃ ኃይል ማመንጫና የመስኖ ግንባታዎችን በማካሄድ ርሀብንና ድህነትን ለመዋጋት ቆርጠው ተነስተዋል።
ለዓባይ ወንዝ ውሃ 86 በመቶውን የምታበረክተው ሀገራችን ኢትዮጵያ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ የምትገነባው ከከፋ ድህነት ለመውጣትና የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷን ለማረጋገጥ ነው ። የተለያዩ የጥናትና የምርምር ወረቀቶች ሀገራችን ኢትዮጵያ በመስኖ መልማት የሚችል 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ሲኖራት ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ መሬት የሚገኘው በዓባይ ተፋሰስ ነው። የሚያስቆጨው እስካሁን የለማው ከ6 በመቶ አለመብለጡ ነው።
ኢትዮጵያ እስካሁን ያለማችው ከ250ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የዓባይ ተፋሰስ ድርሻ ከ20ሺህ ሄክታር አይበልጥም። የሀገራችን ግብርና የዝናብ ጥገኛ ነው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ የውሃ ማማ በመባል ብትታወቅም በየዓመቱ ሊባል በሚችል ሁኔታ በድርቅ እየተጠቃች ነው። በየአስር ዓመቱ ይከሰት የነበረው ድርቅ በበልግና በመኸር በዓመት ሁለት ጊዜ ሲጎበኘን እየተመለከትን ነው።
ይህ ያልተስተካከለና የሚቆራረጥ ዝናብ የሚያስከትለው ድርቅ ሚሊዮኖች ለምግብ እጥረት እንዲዳረጉ ምክንያት እየሆነ ነው። በውል እንደሚታወቀው ሀገራችን ከግብፅም ሆነ ከሱዳን ጋር የዓባይን ወንዝ በጋራ መጠቀም የሚያስችል ስምምነት የለም። ሆኖም ለናይል ወንዝ 86 በመቶውን ውሃ የምታበረክተው ኢትዮጵያ በ1929ኙም ሆነ በ1959ኙ የቅኝ ገዢ ስምምነት እንደማትገዛ በየአጋጣሚው ከማሳወቅ ባሻገር እውን ሳይሆን ቢቀርም ከ1950ዎቹ ጀምሮ የኃይል ማመንጫና የመስኖ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ተደጋጋሚ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።
እ.ኤ.አ ከ1958 እስከ 1963 ድረስ አሜሪካ እንዲህ እንደ ዛሬው የግብፅ ጥቅም አስከባሪ ሳትሆን የዓባይን ወንዝ ለማልማት በሚደረጉ ጥረቶች ግንባር ቀደም ተዋናይ ነበረች። ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅ የለም እንዲሉ። የዛሬውን ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ጨምሮ 33 የመስኖና የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን አጥንታ እንዲለሙ ምክረ ሃሳብ አቅርባ ነበር። ከእነዚህ ጥናቶች ሥራ ላይ የዋለው እ.ኤ.አ በ1972 ዓ.ም የተገነባውና 128 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው የፊንጫ የውሃ ኃይል ቀዳሚ ነው ማለት ይቻላል።
ኢትዮጵያ በአንድ በኩል ድርቅ በሌላ በኩል ፈጣን የሕዝብ ቁጥር እድገት እንደ ውጋት ቀስፈው ይዘዋታል። ከዚህ ውጋት ተንፈስ ለማለት የውሃ ሀብቷን አልምታ መጠቀም አለባት። የመስኖ መሠረተ ልማትን በማስፋት እያደገ የመጣውን የምግብ ፍላጎቷን በማሟላት ሕዝቧን ከተመፅዋችነት ማላቀቅ ይጠበቅባታል። ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለምታደርገው ሽግግር እና በኩራዝ ጭስ ለሚጨናበሰው 68 ሚሊዮን ሕዝቧ የኤሌክትሪክ ኃይልና መብራት ለማቅረብ እንደ ዓባይ ያሉ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞቿን ገድባ መጠቀም የሞት ሽረት ትንቅንቅ እየሆነ መጥቷል።
ከዚህ ከፍ ሲልም ኢትዮጵያ ለተፋሰሱ ሀገራት የኃይል አማራጭ የመሆን እምቅ የተፈጥሮ ፀጋ አላት። ይሁንና እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ በድህነቷ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ብድርና ድጋፍ ለማግኘት የምታደርገው ጥረት በግብፅ የተቀናጀ ስውርና ይፋ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ የተነሳ እቅዷ ሁሉ ይጨናገፍባት ስለነበር ግዙፍ የውኃ ኃይል ማመንጫዎችንና ታላላቅ የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታዎችን ማካሄድ ስላልቻለች በከፋ ድህነት በመማቀቅ ላይ ትገኛለች።
የሚያሳዝነው ለኢትዮጵያ ሲሆን የሚታጠፈው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እጅ ለግብፅ ሲሆንግን ያለስስት ይዘረጋል። ለጋስ ይሆናል። ግብፅ ይህን በመጠቀም ኢኮኖሚዋን ማሳደግ ችላለች። የሀገር ውስጥ ጥቅል ምርቷ 235 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፤ የዜጎቿ የነፍስ ወከፍ ገቢ 2ሺህ 440 ዶላር ደርሷል። የኢትዮጵያ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሲሆን የነፍስ ወከፍ ገቢዋ ደግሞ ከ1000 ዶላር በላይ ይገመታል።
ከዚህ የድህነት አረንቋ ወጥቶ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የተፈጥሮ ሀብቷን በተለይ የውሃ ሀብቷን በአግባቡ ማልማት ይኖርባታል። ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2025 ዓ.ም ከግብፅ በላይ የሕዝብ ብዛት ይኖራታል ተብሎ ተተንብዯል። በዘወርዋራ ምግብና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያስፈልገው ሕዝብ ቁጥር አሁን ካለው ይጨምራል ማለት ነው። ከግብፅ በላይ የውሃ ሀብቷን ለመስኖና ለኃይል ማመንጫ መጠቀም ይኖርባታል ማለት ነው። በግዛቷ ስር ያለ የውሃ ሀብቷን መጠቀም ደግሞ ሉዓላዊ መብቷ ነው።
የፋይናንስ እጥረትና የቴክኖሎጂ ውስንነት ዘረፉን ለማልማት የተያዘውን እቅድ ፈታኝ ቢያደርገውም ተጨማሪ የውሃ ኃይል ማመንጫዎችንና የመስኖ አውታሮችን መገንባት ቅድሚያ የተሰጠው ተግባር ሆኖ ይቀጥላል። ቁልፉ የእድገትና የልማት ግብ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሁለንተናዊ መልኩ ድህነትን መቅረፍ ነውና።
በ2003 ዓ.ም ከሱዳን ድንበር 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ጉባ ላይ ግንባታው የተጀመረውና ለኃይል ማመንጫነት የሚውለውና 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ የሚይዘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እድገትንና ልማትን በማፋጠን ዜጎችን ከድህነት የማላቀቅ ራዕይ ሰንቋል። ግድቡ በቀን 6ሺህ ሜጋ ዋት ፣ በዓመት 15ሺህ 130 ጊጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለው። በዚህም የሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትን በማርካት ለምስራቅ አፍሪካ በተለይ ለራስጌ ተፋሰስ ሀገራትም የማቅረብ እቅድ አለው።
ግድቡ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኘውን የታዳሽ ኃይል ተደራሽነት ያሳድጋል። የዓለም ባንክ ጥናት እንደሚያመለክተው ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሪክ ሽፋን 24 በመቶ ፤ የኢትዮጵያ ከ45 በመቶ ያልበለጠ ፣ የሱዳን ከ57 በመቶ ያልበለጠ ሲሆን የግብፅ ሽፋን ግን 100 በመቶ ደርሷል። በናይል ውሃ አጠቃቀም ላይ ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶችን በመጥቀስ ብቸኛ ባለመብትና ተጠቃሚ እኔ ነኝ በማለት የያዘችው ግትር አቋም ፤ የራስጌ ሀገራት በዓለም አቀፍ ሕግ የተረጋገጠላቸውን ውሃውን በፍትሐዊነት የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት የሚጥስ ስለሆነ በንግግርና በውይይት ካልተፈታ ለግጭት ሊዳርግ ይችላል ተብሎ እየተሰጋ ይገኛል።
ይሁንና ግጭትንና አለመግባባትን ለመፍታት ሰባቱ የራስጌ የተፋሰስ ሀገራት የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ አዳዲስ ውሎች ሊተኩ እንደሚገባ የሚጠይቀውና በ2002 ዓ.ም የተፈረመውን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት Cooperation Frame Work Agreement (CFA) ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል። ስምምነቱን የተፈራረሙ ሀገራት ብሩንዲ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ ፣ ኢትዮጵያ ፣ ታንዛኒያና ሩዋንዳ ሲሆኑ የትብብር ማዕቀፉ የናይልን ወንዝ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መጠቀምን የሚያረጋግጥና ዋስትና የሚሰጥ ቋሚ ኮሚሽን እንዲቋቋም የሚጠይቅም ነው።
ዳሩ ግን ሱዳንና ግብፅ ይህን የትብብር ማዕቀፍ ለመፈረም ፈቃደኛ ባይሆኑም በ2007 ዓ.ም በግብፅ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተፈረመውን የመርሆዎች መግለጫ (Declaration of Principles) ፈርመዋል። በዚህ ስምምነት ሱዳንና ግብፅ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን የተቀበሉ ሲሆን ኢትዮጵያም ግድቡ በግርጌ ተፋሰስ ሀገራት ማለትም በግብፅና በሱዳን ሊያሳድረው የሚችል ተፅዕኖ ወይም ጉዳት ካለ ጥናት እንዲደረግ ተስማምታለች።
በዚህ ስምምነት ላይ ተከታታይ ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን ተስፋም ተጥሎባቸው ነበር። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጠናዊ ትብብር አብነት የሚሆንና የራስጌ ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ስለሆነ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል። ግብፅም በግድቡ ውሃ አሞላል ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ጀምራ ወደነበረው ድርድር ብትመለስ ሀገራቱን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል መግባባት ላይ መድረስ ይችላል።
እንደጀመርን ጨርሰነዋል !
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም