ኮሌራ ማለት (ቪብርዩ ኮሌራ) በተሰኘ ባክቴሪያ የሚከሰት አጣዳፊ ተቀማጥን የሚያስከትል ተላላፊ በሽታ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2019 የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ መሰረት በዓለማችን በየዓመቱ እስከ 1ነጥብ 3 እስከ 4 ሚሊዮን የሚሆን የኮሌራ ህመም የሚከሰት ሲሆን ከ21ሺ እስከ 193ሺ የሚሆነው በዓመት በኮሌራ የሚሞቱ የህዝብ ቁጥር ነው፡፡
የኮሌራ ህመም ምልክቶች
አንድ ግለሰብ በኮሌራ ህመም የተጠቃ ከሆነ እነዚህን የህመም ምልክቶች የሚያሳይ ይሆናል፡፡ በዋናነት፤ በድንገት የሚከሰት በጣም ብዛት ያለው አጣዳፊ ውሀ መሰል ተቅማጥ ይኖራቸዋል፡፡የተቅማጡም ቀለም የሩዝ ውሀ መሰል ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ማስመለስ እና ትኩሳት ወይንም ቁርጠትም ሊኖረውም ላይኖረውም ይችላል፡፡ህመሙ እየጠ ነከረ በሚመጣበት ግዜ ብዙ ፈሳሽ ከሰውነታችን በመውጣቱ ሳቢያ የሚከሰቱ ተያያዥ ምልክቶችን የሚያሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ የአይን መሰርጎድ፤ የቆዳ መሸብሸብ ፤ከፍተኛ የሆነ ድካም፤ የአፍ እና የምላስ መድረቅ ናቸው፡፡ እነዚህም ከላይ የተጠቀሱት ጠቅላላ የኮሌራ ምልክቶች በባክቴሪያው በተጠቃን ከ12 ሰዓት እስከ 5 ቀን ባለው ግዜ ውስጥ ሊከሰት ይችላል፡፡
የበሽታው መተላለፊያ መንገዶች እና ሊደረጉ የሚገቡ እርምጃዎች
• የተበከለ የውሀ ምንጭ ፤ወንዞች፤ሀይቆች እና ቧንቧ
• በእነዚህ የተበከለ የውሀ ምንጮች ለተለያዩ ነገሮች መጠቀም(ማብሰል፤ መጠጣት ማጠብ ወዘተ)
• በበሽታው በተከለከለ ውሀ አትክ ልቶችን ፍራፍሬዎችን ማጠብ
• የመፀዳጃ ቤት ፈሳሾችን በአግባቡ አለማስወገድ
• በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸውን ቁሳቁሶችን ሳያፀዱ መጠቀም እንዲሁም ከታካሚው ጋር ተገቢውን ጥንቃቄ ሳያደርጉ ንክኪ ማድረግ ምልክቶቹ በታዩ ግዜ በአፋጣኝ ወደ ጤና ማእከል በመሄድ የህክምና እርዳታ ማግኘት፤ እስከዛ ድረስ የህይወት አድን ንጥረ ነገር ወይም (ORS) በመበጥበጥ ተቅማጥ እና ትውከት በተከሰተ ሰዓት መውሰድ፡፡ ORS (ኦ.አር. ኤስ) የሌለ እንደሆነ ፈልቶ በቀዘቀዘ 1 ሊትር ውሀ 6 ሻይ ማንኪያ ስኳር እና ግማሽ ሻይ ማንኪያ ጨው በመጨመር መውሰድ የሚቻለው በተበጠበጠ በ24 ሰዓት ውስጥ ነው፡፡
በጤና ተቋማት የሚደረግ ህክምና
በጤና ተቋማት የሚደረገው ህክ ምና ታካሚውን ከሌሎች ታካሚዎች በመለየት እና በማስተኛት በደምስር የሚሰጡ ፈሳሾችን መስጠት ዋና ህክምና ነው፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ አንቲባዮቲክ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ህፃናት እንደ እድሜያቸው ከ 5 ዓመት ያነሱ ከሆነ ዚንክ የተባለውን ንጥረነገር በተጨማሪ የሚሰጣቸው ይሆናል፡፡ጡት ለሚጠቡ ህፃናት ለፈሳሽ ተጨማሪ የእናት ጡት እንዲጠቡ ይመከራል፡፡
የኮሌራ ህመም መከላከል እና ቁጥጥር
• እጅን በመመገብ ሰዓት ፤ ምግብ በማዘጋጃ ሰዓት ፤ህፃናት በመመገቢያ ሰዓት በውሃና በሳሙና መታጠብ
• አትክልቶችን እና ፍራፍሬዎችን ንፅህናው በጠበቀ ወይም በታከመ ውሃ አጥቦ ወዲያውኑ መመገብ
• ሁልጊዜ መፀዳጃ ቤቶችን በአግባቡ መጠቀም እና ፍሳሾቻቸውን በአግባቡ ማስወገድ( ቆፍሮ መቅበር)
• ምግብ በደንብ ማብሰል ሳይቀዘቅዝ መብላት
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 8/2011